ሶሻሊዝም ወይም ህብረተሰብአዊነት

ሶሻሊዝም በዘመኑ በርካታ ምሁራኖችንና አሳብያኖችን ያፈራና ያስከተለ ማህበረ – ፖለቲካዊና- ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና ሲሆን አሁን ግን የድሮውን ዝናውንና ስሙን ደብዝዟል ማለት ይቻላል ። በ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አሁንም ድረስ የሶሻሊዝምን ስም የያዙ ፓርቲዎች ያሉ ቢሆኑም ስር – ነቀል (Radical) ከሆነው ማርክሲዝም ግን በእጅጉ የተለዩ ናቸዉ ። ከርሱ በፊት በርካታ የሶሻሊዝም ምሁራኖችና በተግባርም ሞካሪዎች የነበሩ ቢሆንም ሶሻሊዝምን (Socialism) በተቀናጀና ስልታዊ በሆነ መልኩ የተነተኑት ካርል ማርክስና ፍሬደሪክ ኤንግልስ ሲሆኑ ማርክስ አብዛኞቹን ሀሳቦች ከዴቪድ ሪካርዶና ከአዳም ስሚዝ ወስዷል ።ሶሻሊዝምን በተግባር ከመሩ ሰዎች አንዱ ጆሴፍ ስታሊን አንዱ የነበሩ ሲሆን አወዛጋቢ ስብእናም ጭምር ነው ። በአንድ በኩል ሶሻሊዝምን ያጠናከረና ከምእራቡ አለም እኩል ተወዳዳሪ ማድረግ የቻለ ተብሎ ሲሞገስ በዚህ ምክንያት ምእራባዉያን ለሱ ከፍታኛ ጥላቻ ቢኖራቸዉ አስገራሚ አይሆንም ። በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊዝምን ወደ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ስርአት በመቀየሩ ፣እንዲሁም በዙሪያውየተክለ – ሰውነት ግለሰባዊ የሆነ አምልኮን (Cult) በማበረታታቱ ፣ ለሶቭየት ህብረት ስጋትን ደቅኖ ለነበረው ለናዚዎች የወረራ ስጋት ምንም ዝግጅት አለማድረጉ ፣ በሀሰት በተቀነባበሩ ውንጀላዎች ቀደምት የሆኑ በርካታ የራሱን ፓርቲ አባላትን ማስወገዱ ፣ የጀርመንን ግንብ በመገንባት አውሮፓን ለሁለት እንድትከፈል ማድረጉ፣ በርካታ የራሱን ዜጎች በመጨፍጨፉና ወደ ሳይቤሪያና የጉልበት ስራ ወደ ሚሰራባቸው ካምፖች (Labor Camps) በማጋዙ ሲወቀስ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም ሶቭየት ህብረትን ወደ ኢንዱስትሪ ሀገር ደረጃ በማሳደጉ እንዲሁም የናዚዎችን ወረራ በተሳካ ሁኔታ በመመከቱ በታሪክ እንደ ጥንካሬ ይታይለታል ።

በርካታ አይሁዳውያን የሶሻሊዝምን ፅንሰ – ሀሳብ በማሰራጨትና ወደ ተግባር ለመለወጥም በመታገል ይታወቃሉ ፣አንዳንዶች ሶሻሊዝምን የአይሁዳዉያን ሴራ አድርገዉ የሚወስዱ ሰዎች አሉ ። ለምሳሌ ናዚዎች የቦልሽቪክ አብዮትን የአይሁዳውያን አለም አቀፋዊ ሴራ አድርገው ነው የቆጠሩት ። በዛንወቅት አይሁዳውያን ሀገር ስላልነበራቸው በሶሻሊዝም አለም – አቀፋዊነት ባህሪ መሳባቸው የጣወቀ ነው ። በነገራችን ላይ አይሁዳውያን በሶሻሊዝም ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፋዊ ካፒታሊዝምም ጭምር ስማቸው አብሮ ተያይዞ የሚነሳ ነው ። ሶሻሊዝም በውስጡ ብዙ አይነት ውላጆችን የያዘ ነው ፣ ከአናርኪስቶች ጀምሮ በአውሮፓ ስልጣን እሚይዙት ሶሻል ዲሞክራቶችን ብንወስድ ከሶሻሊዝም አብራክ የተፈጠሩ ናቸው ። ንሂሊስቶችም (Nihilists) ከዚሁ የሚመደቡ ናቸው ። ተምኔታዊ ሶሻሊዝም የሚባሉትም የዚሁ ዘውግ አባል ናቸው ።

ከእርሱ በኋላ አንዳንድ ሶሻሊስቶች የስታሊንን ምሳሌ በመከተል በአለም ዙሪያ በርካታ መንግስታትን መስርተዋል ይሁን እንጂ አሁን እየወጡ ያሉ የምርመራ ዉጤቶች እንደሚያሳዩት አንጎሉን በመመርመር የተወሰዱ ምስሎች እንደሚያሳዩት ስታሊን አእምሮዉ ጤነኛ እንዳልነበረ የሚጠቁሙ ሆነዉ ተገኝተዋል። የቀድሞዋሶቭየት ህብረትን እሚያክል ሀያል ሀገር በእንደዛ አይነት ሰውትመራ የነበረች መሆኗ ሳይንቲስቶችን በእጅጉ አስገርሟል። ይሁን እንጂ ሁሉንም እሚያስማማው የስታሊን አምባገነናዊ ስርአት ሶሻሊዝም እንዴት በአምባገነን ግለሰቦች ሊቀለበስ እንደሚችልና የራሱን ፍልስፍናውን ለህዝቦችና ለሀገራት የሚያስገኘውን ጥቅም ጥያቄ ውስጥ እስከማስገባት ደረጃ አድርሷል ።

በስታሊን ላይ ሁለት አይነት ክርክሮች የነሳሉ በአንድ በኩል ከነበረው የምእራባውያን ጥንካሬና ውድድር አንፃር ሶሻሊዝምን ያጠናከረው እሱ ነው የሚሉ አሉ በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊዝምን ወደ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ስርአት የቀየረውና አለም አቀፋዊ ገፅታውን ያሳጣው እሱ ነው ስለዚህ ለሶሻሊዝም ውድቀት ተጠያቂ የሚሆነው እሱ ነው እሚሉ አሉ ። ስታሊናዊ አምባገነናዊ ስርአት ብዙዎችን ህይወት በመብላቱ እንዲሁም አለም አቀፍ ሲሶሻሊስቶች የሱ ፖሊሲዎች የሶሻሊዝምን ውድቀት ጉድጓድ የቆፈሩ ናቸዉ በሚል ሶሻሊዝምን ስርአት እንደቀለበሰ ይቆጥሩታል ።

ከእርሱ በኋላ የመጡምመሪዎች የሱን መንገድ በመከተላቸው ስርአቱ ለአስርት አመታት ምንም አይነት ማሻሻያዎችን ባለማድረጉ ምክንያት መጨረሻ ላይ ሊንኮታኮት በቅቷል ።

አንዱ የካፒታሊዝም ስርአት ጥንካሬው ራሱን ከሁኔታዎችና ከጊዜው ጋር ማስማማት መቻሉ (Adapt) ማድረጉ ሲሆን በአንፃሩ ግን የኮሚኒዝም ስርአት ይህንን ለማድረግ የሚያስችል መዋቅራዊም ሆነ ስልታዊ አካሄድ የለዉም።የካፒታሊዝም ወይንም የነፃ ዲሞክራሲ ስርአት (Liberal Democracy) ነጻ ምርጫዎችን ስለሚያካሂድና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትን ስለሚፈቅድ በዛዉ ስርአት ውስጥ ማሻሻያዎችንና ለውጦችን እያደረገ ሲቀጥል በአንፃሩ የኮሚኒዝም ስርአት ግን ለዚህ የታደለ አይደለም። ቻይናን ራሱ ብንወስድ ምንም እንኳን ቻይና መሪዎቿን በየአስር አመቱ እርስ በእርስ በመመራረጥ የምትተካ ቢሆንም በተግባር ግን መሪዎቹ አዲስ ለውጥን በማካሄድ የፖለቲካ ስጋት እንዲፈጠር አይፈልጉም ፤ ከዚያ ይልቅ የነበረውን ስርአት ባለው መንገድ እንዲቀጥል የማድረግ ስራን ነው የሚሰ ሩት ። ይህም ውሎ አድሮ የህዝብ ተስፋ መቁረጥንና ችግሮችም መፍትሄ ሳያገኙ እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው ።

ስልጣኑን በግለሰብ ወይንም በጥቂት ግለሰብ ቡድኖች እጅ ስለሚገባና ስልጣናቸውን ማጣት ወይንም መቀነስ ስለማይፈልጉ ማሻሻያዎችን ሳያደርጉ ለብዙ አመታት ስለሚቆዩ መጨረሻ ላይ ነገሮች ከቁጥጥር ዉጪ የሚሆኑበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ። በአስገራሚ ሁኔታ ግን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ይህንን አደጋ የተረዳ ይመስላል ፣ለዚህም በተደጋጋሚ ጥገናዊ ለውጦችንና ማሻሻያዎችን በማድረጉ በአለም ላይ ከታዩ የኮሚኒስት ስርአቶች ሁሉ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት ችሏል።  ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ የዲሞክራሲ ስርአቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታት ህልውናቸውን አስጠብቀው አሁንም ድረስ መቀጠል ሲችሉ በአንፃሩዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ የኮሚኒስትና ፣ ምርጫን የማያካሂዱ አምባገነናዊ የሆኑ ስርአቶች ግን መጨረሻ ላይ በሚወገዱበት ወቅት ከሚፈጥሩት ቀውስ በተጨማሪ ፤እድሜአቸው ከጥቂት አስርት አመታቶች በላይ ሊዘል አልቻለም ።

ከሶሻሊስቶች ከማርክስና ከኤንግልስ ቀጥሎ ሌኒን የጠቀሳል ። ምንም እንኳን ሌኒን የካርል ማርክስን ያህል የሶሻሊዝም ርእዮተ – አለም ዋነው ፈጣሪው ባይሆንም፣ ምሁር የነበረና በርካታ ፅሁፎችን ያበረከተ እንዲሁም በርካታ ቋንቋዎችን ጀርመንኛንና ሌሎች የአውሮፓውያንን ቋንቋ የሚያውቅ እና አቀላጥፎ የሚፅፍና የሚናገር ሲሆን በተለይም ማርክስ በንድፈ – ሀሳብ ደረጃ ያስቀመጣቸውንና ያን ግዜ ካፒታሊዝምና ባላደገባትና ፊውዳል በነበረችው ሩሲያ የማርክስን የሶሻሊዝም ንድፈ ሀሳብ ወደ ሶሻሊዝም በተግባር እንዲቀየር በርካታ ሀሳቦችን ያመነጨ ሰው ነዉ ።

ማርክስ በአብዛኛው ያቀረባቸው ሀሳቦች ካፒታሊዝም ከፍተኛ ደረጃ ለደረሰባቸው በኢንዱስትሪ ለዳበሩትና ብዛት ያለው የኢንዱስትሪ ሰራተኛ ላላቸው እንደ ፈረንሳይ ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ለመሳሰሉት የአውሮፓ ሀገራት እንጂ በፊውዳል ስርአት ለነበሩና በኢንዱስትሪ ላልዳበሩ እንደ ሩስያ ላሉ ሀገራት እልነበረም ።

ምእራባውያን ግን በአንድ ወቅት በሜሊኒየሙ መጨረሻ የወጣ ያታይም መፅሄት ሌኒንን ዘመናዊ የጭቆና መሳሪያዎችን የፈለሰፈ ወይንም የፈጠረ በማለት ይገልፀዋል። ሌኒን በርካታ የጭቆና መሳሪያዎችን ይፈልስፍ እንጂ ፣ ረጅም ስልጣን ዘመን የነበረው በመሆኑ በተግባር ላይ ያዋላቸው ስታሊን ነው ። ሌላው የሶሻሊዝምን ስርአት ድክመት የነበረው የሰው ልጅ በተፈጥሮው ግላዊ (Individualistic) ሲሆን ሶሻሊዝም ያንን ግላዊ የሆነ ባህሪውን በማጥፋት ወደ ጋራ የሚቀይር በመሆኑ መጀመሪያ ላይ አማላይ ሆኖ በተቀበሉት ሀገራት ሳይቀር የኋላ የኋላ ተቀባይነትን እያጣ እንዲመጣ አስተዋፅኦ አድርጓል ።

ማርክስ የሶሻሊዝምን ሀሳብ ሲያመነጭ የምርት ሀይሎች  (Factors of Production) ያላቸው ጉልበትን፣መሬትንና ካፒታልን ሲሆን በዛን ወቅት ነበረው የማርክስም ሆነ የሌሎች የብሉይ ዘመን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች  (Classical Economists)ስራ -ፈጠራን ወይም ኢንተርፐርነርሽፕን ከፍ ያለ ግምት ውስጥ አልሰጡትም ። ይሁን እንጂ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሹምፔተር ግን የስራ ፈጠራ ጥበብን (Entrepreneurship)የምርት ሀይል አካልነት አስረግጦ ማስረዳት ችሏል ። ስለዚህ አንድ ካፒታሊስት ሀብቱን የሚያካብተው ሰራተኞቹን በዝብዞ ነው የሚለው አስተሳሰብ ነገሮችን በጣም አቅልሎና አድበስብሶ ማየት ሊሆን ይችላል ።

የሰራተኞቹን ጉልበት መጠቀሙ እንዳለ ሆኖ ፣ አብዛኛውን ሀብቱን ስራን በመፍጠር ፣ የነበረውን በማሻሻል ፣ወይንም አዲስና ያልነበረ ነገርን በመፍጠር ሊያገኝ ይችላል። ሶሻሊስቶች እንደሚሉትና በርካታ ተከታዩቹም ያምኑ እንደነበረው ከፍተኛው ዲሞክራሲ የሚሰፍነው በሶሻሊዝም ስርአት ነው ። ይህ ሀሳብ ይሁን እንጂ ሀሳባዊ (Ideal) እና ተምኔታዊ (ዩቶፒያን) ነው እንጂ በተግባር የሶሻሊዝም ተከታዮች ነን በሚሉት አገራት አልታየም ፣ ምክንያቱም ከሰው ልጅ መሰረታዊ ከሆነው ራስ ወዳድ ከሆነው ባህሪ በመነሳት ሶሻሊዝም በተለይም ማርክሲዝም ያለው የዲሞክራሲ አይነት አልታየም ። እንደውም ከሊበራል ዲሞክራሲ በባሰ ሁኔታ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተፈጠሩት አምባገነኖች ከናዚዎችና ፋሺስቶች እሚገዳደሩ አምባገነናዊ ስርአቶች በማርክሲስቶች ተፈጥረዋል ። ይኀውም የሰው ልጅ ማንኛውንም ነገር እሚያደርገው ከራሱ ባህሪ በመነሳት ነው ።

በአሜሪካን በኮምፒውተር ሳይንስና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በርካታ አዳዲስ ኩባንያዎችን ያቋቋሙትና አሜሪካን በዚህ ዘርፍ አለምን እንድትመራ ያደረጉት የግል ኢንተርፐርነሮች ወይንም ስራ ፈጠራ ጥበበኞች ናቸው  ። እንደ ጎግል፣አፕል ፣ ማይክሮሶፍት  ፣ ያሆ  ፣ ዴል እና ፌስቡክ የመሳሰሉት በዚህ መንገድ የተቋቋሙ ሲሆን እነኚህም በርካቶቹ የኮሌጅ ትምህርታቸውን አቋርጠው የወጡ ወጣቶች ሲሆኑ በቤታቸው ውስጥ ባደረጓቸው ሙከራዎችና ምርምሮች አለምን የለወጡ ግኝቶችንና ፈጠራዎችንለማግኘት ችለዋል።እነኚህ ኢንተርፐርነሮች (Enterperuners) በርካታ ሀብት ማጋበሳቸው አሌ ባይባልም ለማህበረሰቡ ፣ለሀገራቸውና ለአለም የፈጠሩትን ተጨማሪ እሴት ግን ማንም ሊክደው አይችልም ።

አንዳንዶቹ ሀብታቸውን ለበጎ አድራጎት እንዲውል ያደረጉ ሲሆን የማይክሮሶፍቱ መስራችና ባለቤት ቢል ጌትስ ከእነዚህ አንዱ ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀብት ያላቸው ሰዎች ከመንግስት ብቻ ከመጠበቅ ተላቀው ሀብታቸውንም ስራ ላይ አውለው ለሌሎች ሰዎች የስራ እድልን እንዲፈጥርና እንዲንቀሳሰቀስ ማድረጋቸው ፣ እንዲሁም ብዙ ማሰብንና ጥረትንና ፣ ጭንቀትን ተቋቁመው ስራ መስራታቸውና ሀብት መፍጠራቸው በአጭር ጊዜ ሰዎቹ ራሳቸው እሚጠቀሙ ቢመስልም ፣ ውሎ አድሮ ግን ሀገርንና ወገንን እንዲሁም መጪውን ትውልድ እሚጠቅም ነው ።

ይሁን እንጂ ኒዎ – ማርክሲስቶች ይህንን ክርክር እንደማይቀበሉት እንደማይቀበሉት የታወቀ ሲሆን ፤ የለብለብ ወይም የጥራዝ – ነጠቅ ኢኮኖሚስቶች (Vulgar Economists) ክርክር ነው ይሉታል ። እንደ እነሱ አባባል የቡርዧ ኢኮኖሚስቶች ትርፍን ትክክለኛ ወይም ፍትሀዊ ለማድረግ በርካታ ሀሳቦችን አመንጭተዋል ይላሉ እነኚህም ካፒታሊስቱ ከእለት ፍጆታው ቆጥቦ ባስቀመጠው ገንዘብ እናአደጋን ተጋፍጦ እና«ሪስክን» ወስዶ ነው እነኚህን ድርጅቶች ያቋቋመው ስለዚህ መጀመሪያ ሲያቋቁም አደጋን ስለተጋፈጠና ቢከስርም ኖሮ ከስሮ ይቀር ነበረ እንጂ እሚያገኘው ትርፍ ነገር የአልነበረም ስለዚህ ትርፉ አደጋን የተጋፈጠበት በገንዘቡ ፣ በጊዜውና በማንኛውንም ነገር ፣ የሚለውን የካፒታሊስት ኢኮኖሚስቶችን የመከራከሪያ ሀሳብ ቢያጣጥሉትም ፤ እንደ ማርክሲስቶች አባባል ግን የሶሾሊዝም ስርአት የሚመሰረተው ግን የካፒታሊዝም ስርአት በፈጠረው የሀብትና የእውቀት ክምችት ላይ መሆኑ ግን የሀብት ክምችትን (Capital Accumulation) ቅድመ – አስፈላጊነት ማርክሲስቶችም እንደሚረዱት መገመት ይቻላል ።

ይሁን አንጂ ባለሀብቶች እሚከፍሉት ግብርና ሰራተኞች እሚከፍሉት ግብር ላይ ክርክሮች አሉ ። ለምሳሌ አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ከሰራተኞች ጋር ሲነጻጸር ሀብታሞች የሚከፍሉት የግብር ምጣኔ አነስተኛ ነው ብለዋል ። ይሁን እንጂ ባለሀብቶች የሚከፍሉት ግብር (Capital Gains) ግብር ሲሆን ሰራተኞች ደግሞ የደሞዝ ገቢ ግብር ነው ። በእርግጥ ባለሀብቱ ከዚህ በላይ ክፈል ቢባል ወይም ግብር ቢጨመርበት ገንዘቡን ይዞ ወደ ሌላ አነስተኛ ግብር ወደሚከፈልበት አገር ሊሄድ ይችላል ፣ ስለዚህ ግብር ሊጨመርነት አይገባም የሚል ሀሳብ አለ ። ነገር ግን የግብር ምጣኔው ነው እንጂ በአጠቃላይ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ ሲታይ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ሰዎች የሚከፍሉት ግብር የተቀረው ከሚከፍለው የግብር መጠን የበለጠ ነው ።

በዚህ ምክንያት አለአግባብ ከፍ ያለ ግብር ባለሀብቶችንና ስራ ፈጣሪዎችን እንዲሸሽና እንደሚያሰንፍ ይታወቃል ። በነገራችን ላይ ይሄ ጉዳይ በአሜሪካን አገር ሰፊ ክርክርን የፈጠረና በምርጫ ዘመቻ ወቅት ዋነኛ ጉዳይ ሲሆን ሪፐብሊካኖች ግብር እንዳይጨመር ከተቻለም እንዲቀነስ ፣ ዲሞክራቶች ደግሞ በበኩላቸው ግብር እንዳይቀነስ ፣ ሲሆን ሲሆን እንዲጨመር ነው ክርክራቸው ። ሁለቱን ፓርቲዎች በሀገር ውስጥ ጉዳይ የሚለያያቸው ዋናው ጉዳይ ከሆነም ውሎ አድሯል ።ምጣኔ – ሀብታዊ ከሆኑ ጉዳዮችጋር ብቻ ሳይሆን ፣ የግብር መጨመርና አለመጨመር ጉዳይ ከመንግስት ወጪ እና ካለበትእዳ አንፃርም ጭምር የሚታይ ነው ። ይህም ብቻ ሳይሆን ጉዳይ ምጣኔ – ሀብታዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ጉዳዮችን ሊያካትት ይችላል ።

በካፒታሊዝም ስርአት የፖለቲካ ምጣኔ – ሀብት (Political Economy) ውስጥ ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ በካፒታል (በገንዘብ) ባለቤትነት እና በጉልበት ባለቤትነት መሀከል ማስታረቅ አለመቻል ነው ። ካርል ማርክስ በሁለቱ መሀከል ሊታረቁ ስለማይችሉና የካፒታሊዝም ስርአት በውስጡ ውስጣዊ ቅራኔዎች ተቃርኖዎች የተሞላ ነው ። ስለዚህ የዚህም ለማስታረቅ ስለማይቻል የካፒታሊዝምን ስርአት በአመፃ ማስወገድ ነው የሚል ድምዳሜን  አቅርቧል ።በነገራችን ላይ ይህ ተቃርኖ ለምሳሌ ምን ያህል ግብር ማን ይክፈል በሚባልበት ወቅት በሌላ መንገድ የሚንፀባረቅ ነው ።

ነገር ግን የሊበራል ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት የሚታይ ሌላም ችግር አለ ፣ ይኀውም የፖለቲካ መሪዎች በኮርፖሬሽኖች ተፅእኖ ስር መሆናቸውና የትላልቅ ግዙፍ ባንኮችንና የትላልቅ ኩባንያዎችን ጥቅም በዋናነት ለማስከበር መነሳሳታቸው የዚህ ስርአት ዋነኛ ችግር ነው ። የዚህን አስተሳሰብ በሚያንፀባርቁ ሰዎች እንደሚሉት የመንግስት ቁጥጥር ከላላላቸው የንግድ ኩባንያዎች እና ኮርፖሬሽኖች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው የበለጠ ትርፍንና የስራ እድልን ይፈጥራሉ የሚል ሲሆን ፣ ይህንን አስተሳሰብ በመደገፍ በተለይም የአሜሪካ የሁለቱም ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ይህን ሀሳብ በስልጣን ዘመናቸው አስፈፅመዋል ። ነገር ግን ይህ ፖሊሲ በአንደ በኩል የኑሮና የገቢ ልዩነትን በዜጎቻቸው መሀል ሲፈጥር በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ ቁጥጥር ወደ ማይደረግበት የአገራቸውንም ሆነ አለምን ኢኮኖሚ ጤንነት በቀጥታ የህዝብ ተጠያቂነት በሌለባቸውና ለራሳቸው ትርፍ በዋናነት በሚንቀሳቀሱ በግል ኩባንያዎች መዳፍ ስር እንዲወድቅ አድርጎታል ።

ጥንታዊው ታላቁ የግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ አንዳስቀመጠው ፈላስፋው ንጉስ መሆን አለበት ሲል ፣  ማህበረሰብን በሶስት ሲከፍል ፈላስፋው ንጉስ፣ ነጋዴው ፣ እና የወታደር ክፍሎች ሲሆኑ እንደሱ አባባል ነጋዴው (ካፒታሊስቱ) ለትርፍ ስግብግብ ስለሆነ ከዛ ጥቅሙ ውጪ ሌላ ነገርን ስለማያስብ በፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም የሚል አቋም ነበረው ። ወታደሩም ሀገርን መጠበቅ ነው እንጂ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም ይላል ። አርቲስቶችንም ዝቅ ያለ ቦታ የሚሰጣቸው ሲሆን ፕሌቶ ለአርቲስቶችም ቢሆን ብዙም ቦታ አይሰጣቸውም ነበረ ። ነገር ግን ፈላስፎች ግን ለአመራር ቦታ መታጨት አለባቸው ብሎ ያምን ነበረ ።

በአሁኑ አለም ባሉ የዲሞክራሲ ስርአቶች ፕሌቶ ከሚለው በእጅጉ የተለየ ሲሆን ፣ ወደ  መንግስት ስልጣን መምጣት የለባቸውም የሚላቸው ነጋዴዎች በእጅ አዙር ፖለቲካውን መዘውር  የሚቆጣጠሩ ናቸው ። ውስጥ ግን የንግድ ኮርፖሬሽኖች ፖለቲከኞችን ድጋፍ በመስጠትና መንሳት ወደ ስልጣን ማምጣት ብቻ ሳይሆን እንደ አሜሪካን አገር ባሉ ሀገራት ፣ የመገናኛ ብዙሀኖቹ ፣ ጋዜጦች ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎችም ጭምር በግል ኩባንያዎች የተያዙ በመሆኑ የነሱን ድጋፍ ያላገኘ የፖለቲካ ሰው ወደ ስልጣን ሊመጣ አይችልም ። ይህም እ.ኤ.አ. በ2012 በተደረገው በታላላቅ የምእራብ ሀገራት በተደረጉ ሰልፎች ይኀው ተንፀባርቋል ።

ሀብታሞቹ የተለያዩ ኩባንያዎችን በመቆጣጠር እርስ በእርስ የሚደጋገፉ ሲሆን ፣ የተቀረው ብዙሀኑ ህዝብ ግን ጉልበቱን ሸጦ እና ያለማቋረጥ ሁለትናሶስት ስራዎችን ሰርቶ እሚያድር እንዲሆን ፣ ገንዘቡ በጥቂት ካፒታሊስቶች እጅ መከማቸት ሰርአቱ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጥቂቶችን ብቻ ወደሚያገለግል ተቋምነት እንዲቀየርና የተቀረው ወደ ባይተዋርነት እንዲቀየር ሊያደርግ የሚችል ነው ።

በአሁኑ ወቅት በርካታ አንተርፐርነሮች ኢኮኖሚያቸው እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ እየወጡ ይገኛሉ ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌዋ ቻይና ስትሆን እያደገ ባለው ግዙፍ ኢኮኖሚዋ በርካታ አንተርፐርነሮች እየወጡ ይገኛሉ ። ስራ ፈጣሪዎች እያገደ ባለ ምጣኔ – ሀብት ውስጥ በቀላሉ ድልን የማግኘት እድል ሲኖራቸው ፣ እድገታቸውን በጨረሱና እድገታቸው እየተጓተተ ባሉ የምእራብ ሀገራት ግን አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች ወደ የነበረውን  ገበያ ደርሻ ነው እሚቀራመቱት ፣ ምክንያቱም ምጣኔ – ሀብቱ እያደገ ባለመሆኑ አዳዲስም ሆነ ነባር ኩባንያዎች በነበረው የገበያ ድርሻ ላይ በመወዳደር ፣ የተካረረ የገበያ ውድድር በማድረግ አንዱ አንዱን ከገበያ የማስወጣት ደረጃ የደረሰ የገበያ ውድድር ያደርጋሉ ።

ማርክስ የሰው ልጆችን በተለይም የሰራተኛውን የህብረተሰብ ክፍል በወቅቱ ከነበረው አስከፊ ብዝበዛና ከጭቆና ነፃ ለማውጣት ፣ ቀና ከሆነ አቅጣጫ የነደፈው ንድፈ – ሀሳብ ነው ። የማርክስ ሀሳብ ከዘመኑ የቀደመ ሀሳብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ፣ ለዚህም አንዱ ምክንያት እርሱ ያቀረባቸው ሀሳቦች ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ወቅት በአለም ሀገራት ላይ መታየት የጀመሩ ናቸው ፣ ለምሳሌ የካፒታል መከማቸት ፣ የስራ አጥቁጥር መጨመር የመሳሰሉት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየታየ ያለ ሲሆን የካፒታሊስት ሀገራት ማሻሻያዎችን ካላደረጉ ይበልጥ የካፒታሊዝምን ስርአት ተቀባይነትን የሚያሳጡ ጉዳዮች ይበልጥ ጎልተው እየታዩ እንደሚሄዱ ዛሬ ላይ ሆኖ መገመት ከባድ አይ ሆንም ።

እጅግ በርካታ መስዋእትነት የተከፈለ ሲሆን በሁሉም ታላላቅ አህጉራት በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካማርክሲዝም ነው ትክክለኛው ፍልስፍና ብለው ያመኑ እጅግ በርካታ ሰዎች ለተግባራዊነቱ ይህ ነው እማይባል ከባድ መስዋእትነትን ከፍለዋል ። በኮሚኒስት ወይም በማርክሲስት ስርአቶች ዲሞክራሲ ማለት ድርጅታዊ ዲሞክራሲን ይወክላል ። ከድርጅቱም በማእከላዊ ወይም ዋና ውሳኔ ሰጪ የሆን አካል ውሰጠ – ዲሞክራሲ ማለት ሲሆን ፤ ከዛም ውስጥ ደግሞ ፣ ስልጣኑ ከኮሚቴው አልፎ በቡድን ወይም በአንድ ጠንካራ መሪ ስር ይወድቃል ።

የዲሞክራሲ አተረጓጎሙም ሆነ አሰራሩ ከምእራቡ አለም የሊበራል ዲሞክራሲ አንፃር በእጅጉ የተለየ ሲያደርገው ፣ በታሪክም በተደጋጋሚ እንደታየው ፣ በቀላሉ ወደ አምባገነናዊ ወይም ቡድናዊ ፈላጭ ቆራጭ ወደ ሆነ ስርአት የመቀየር እድሉ ሰፊ ነው ። ይህም የኮሚኒዝም ስርአቶችመሰረታዊ የሆነ ውስጣዊ ድክመት ሲሆን የማርክሲስት ስርአቶች ውስጣዊ ዲሞክራሲ ስላልነበራቸው አብዛኞቹ ፈራርሰዋል ። የተራረፉትም ቢሆኑ ብዙ ማሻሻያዎችን አድርገውና ፣ በተለይም በምጣኔ – ሀብት አስተዳደሩ በኩል እንደ ቻይና ፣ ቬትናም ያሉት በርካታ የነፃ ገበያ ሀሳቦችን ወስደው ነው ። ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልገው ለዘብተኝነትና ፣ አማራጭ ፖሊሲዎችን መሞከርም ሆነ መቀበል በኮሚኒዝም ስርአት ውስጥ አይታወቁም ። ይሄም ለብዙዎቹ ስርአቶች መፈራረስ ምክንያት ሆኗል ።

ማርክስ የካፒታሊዝምን ስርአት ያለምህረት የተቸ ሰው ሲሆን ፣ የካፒታሊዝምን ስርአት ውስጠ – አሰራሩን በተመለከተ ከፍተኛ እውቀት እንዳለው እና ተመስክሮለታል ፣ ምሁራዊ ሀቀኝነቱም እንዲሁ የተመሰከረለት ነው ። ማርክሲዝም ንድፈ – ሀሳባዊ ይዘቱበአብዛኛው ትክክል ቢሆንም ድምዳሜው ግን ማለትም የካፒታሊዝም ስርአትን በአመፃ ጥሎ የወዛደሩን አምባገነናዊ ስርአት ይመሰርታል እሚለው ግን በአያሌው አወዛግቧል ፣ ይህ አስተሳሰብ ችግሮቹ አንዱ ቀዳሚውን ስርአት በአመፃ መጣል የሚለው ሲሆን ቀጥሎም የወዛደሩን አምባገነናዊ ስርአት ይተካል የሚል ነው ።

የቦስራት ንድፈ – ሀሳብ ከማልተስ ሀሳብ ተቃራኒ ቢሆንም ማርክስና ኤንግልስ ግን የማልተስን  ሀሳብ ያጣጥሉታል ። እንደውም ማርክስ የማልተስን ሀሳብ የተማሪ ስራ ነው በማለት ያጣጥለዋል ። ለማርክስ ህዝብ ብዛት ማልተስ እንዳለው በሞራል ጉድለት የሚመጣ ሳይሆን የካፒታሊዝም ስርአት የፈጠረው ነው ።

ይህም እሚሆነው የካፒታሊዝም በፈጠረው ወይም ባከማቸው ካፒታልና ፣እውቀት ላይ ሲሆን የካፒታል መከማቸትም ቀጣዩን የሶሻሊዝም ስርአትን ለመገንባት የሚያስችለውን መደላድል ይፈጥራል ። በእርግጥ እዚህ ጋ ሶሻሊዝም ስርአት የሚገነባውው የካፒታሊዝም ስርአት ባከማቸው ሀብትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ነው መባሉ ፣ በሶሻሊዝም ስርአት ፍትሀዊነት ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል ። ነገር ግን እዚህ ጋ  ማርክስ የኮሚኒዝምን ስርአት ከገነባባቸው ፅንሰ -ሀሳቦች አንዱ የዝግመተ – ለውጥ (Evolution)አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ ነው ። ስለዚህ እንደ ማርክሲስቶች አባባል ካፒታሊዝም ስርአት የፊውዳሉን ስርአት እንደተካው ፣ ፊውዳሊዝምም የባርያ አሳዳሪውን ስርአት እንደተካው ሁሉ ፣ ቀደምት ስርአተ – ማህበራትም በአዝጋሚ ለውጥ እየተተካኩ እንደመጡት ሁሉ ሶሻሊዝም የካፒታሊዝም ስርአትን ይተካዋል የሚል ነው ፤የማርክሲዝምን ስርአት አወዛጋቢና ስር ነቀል (Radical) ከሚያደርጉት ጉዳዮችም አንዱ ይሄ ነው ።

በእርግጥ ቀደም ያሉት በረጅም ጊዜ አዝጋሚ – ለውጥ ከባርያ አሳዳሪው ወደ ፊውዳሊዝም ፤ ሲሸጋገር ቀስ በቀስ በብዙ አስርት እና መቶ አመታት አዝጋሚ ለውጥ ነው እንጂ ማርክሲስቶች እንደሚሉት ቅፅበታዊ ወይም ግብታዊ በሆነ አብዮት አይደለም ። ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ስርአትም የተሸጋገረው የምርት ዋነኛ የምርት ግብአት ማለትም መሬት መሆኑ ቀርቶ ኢንዱስትሪ እየሆነ ሲመጣ ባለኢንዱስትሪዎች ፣ ባለገንዘቦችና የባንክ ባለቤቶች ከመሬት ከበርቴው ወይም ከባላባቱ የበለጠ የኢኮኖሚ ውሎ አድሮም የፖለቲካ ሚዛን እየደፉ ስለመጡ በርካታ አመታትን በፈጀ አዝጋሚ – ለውጥ ወደ ቡርዧ ወይም ወደ ከበርቴ ስርአት ተሸጋግሯል ።

በነገራችን ላይ የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና የስነ – ህይወት ተመራማሪዎች ደርሰውበት ነገር ግን ሶሻሊስቶች በዛን ወቅት ሰራተኞች የካፒታሊዝምን ስርአት አፍረስው ኮሚኒዝምን ይገነባሉ ተብሎ ይታመን ስለነበረ ዝግመተ – ለውጥን ይፋ ለማድረግመጀመሪያ ላይ ራሱ ቻርልስ ዳርዊንም ሆነ ሌሎቹ የእንግሊዝ የገዢው መደብ አባላት ግኝቱ ይፋ እንዲሆን አልፈለጉም ነበረ ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ማርክስ ሶሻሊዝም ካፒታሊዝምን ይተካዋል ያለው ፤ ካፒታሊዝም ካደገ በኋላ በሶሻሊዝም ስርአት ይተካል ማለቱ ነው ። ስለዚህ ለሶሻሊዝም ስርአት መፈጠር ያደገ የካፒታሊዝም ስርአት ቅድመ -ሁኔታ ነው ማለቱ ነው ። ይህ ማለት ያደገ የካፒታሊዝም ስርአት ያላቸው እንደ ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ ለመሳሰሉት አገሮች ነው ። ይሁን እንጂ ማርክሲዝም ተግባራዊ የተደረገባቸው እንደ ሩስያ ፣ ቻይና የመሳሰሉት ሀገሮች ግን ማርክሲዝም ስራ ላይ ሲውልባቸው የፊውዳል ስርአት ያላቸው ሀገራት ነበሩ እንጂ በኢንዱስትሪ የበለፀጉና ብዛት ያለው የፋብሪካ ሰራተኛ ያላቸው አልነበሩም ። ይህን ችግር የተረዳው ሌኒንም የሩስያን የቦልሺቪክን አብዮት ሲመራ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ፍልስፍናን በመፍጠር አብዮታዊ በሆነ ሁኔታ የካፒታሊዝም ስርአት ባይዳብርም ከፊውዳሊዝም ወደ ሶሻሊዝም  ይደረግባቸዋል ያላቸውን ሀሳቦችን አፍልቋል ፤ ይህም በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረትና በመጀመሪያ አካባቢ ቻይናና በሌሎች አገራት ተግባራዊ ተደርጓል ።

ምንም እንኳን ሶሻሊዝም በንድፈ – ሀሳብ ደረጃ ከካፒታሊዝም ስርአት በበለጠ ማራኪ ሆኖቢቀርብም ፣ በተግባር ሲታይ ከካፒታሊዝም በበለጠ በተግባር ለማዋል አስቸጋሪና ውስብስብ ስርአት ነው ። በተለይም ዲሞክራሲን የማስተናገድ አቅሙ ከካለፒታሊዝም ስርአት በእጅጉን ያነሰ ነው ።

ይህም ማርክስ የሽረት ሽረት ህግ በማለት ገለፀው ሲሆን ፣ አንድን ስርአተ – ማህበር የሻረና የተካ እሱም በተራው በሌላ ስርአት  ይሻራል ወይም ይተካል እንደማለት ነው  ። ይህ ህግ ማቆሚያና መጨረሻ በሌላው ሁኔታ የሚሰራ ሲሆን አዲሱ አሮጌውን እየተካና እየሻረ ይቀጥላል። አንድ መንግስት ስልጣን ላይ በቆየ ቁጥር የሚፈጥራቸው የፖሊሲ ስህተቶችም ይሁን በሌላ ምክንያት ቅራኔዎች ይፈጠሩና ህጋዊ ተቀባዩነቱን ከእለት ወደ እለት እየሸረሸሩት ይመጡና  የሚፈጠሩት ቅራኔዎች ለሚቀጥለው ስርአት ምቹ መደላድልን መፍጠር  ይጀምራሉ ። ይህም ለበርካታ አምባገነኖች መፈጠር ሰበብ ሆኗል ። ወታደራዊ አምባገነኖች ሳይቀሩ በአለም ዙሪያ መንግስት ገልብጠው የኮሚኒስት ስርአትን መስርተናል እያሉ አምባገነናዊ ስርአቶች ተፈጥረው ቆይተዋል ። ነገር ግን ይህ ወደ ተግባር ሲመነዘር የመጣ ነው እንጂ ከንድፈ – ሀሳቡ እሚመነጭ አይደለም ። ነገር ግን ማርክስ ወዛደራዊ አምባገነንነት የሚለው ትክክለኛ ንቃትና ብቃት ያለው አመራር ብቻ ነው በአምባገነንነት ሊንቀሳቀስ የሚችለው እንጂ ወታደራዊ መሪዎችም በሶሻሊዝም ስም መንግስትን ገልብጠው አምባገነኖች ቢሆኑ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ። ማርክስ ግን መሪው ሙሉ ብቃት አለው ከሚል ግንዛቤ በመነሳት ነው ሰራተኛው አምባገነነት መምራት አለበት የሚለው ። ይህም አስተሳሰቡ ከሄግል መሪውን መንፈስ ይመራዋል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ሄግልም ቢሆን ይህንን ሀሳብ ሲያቀርብ መሪው ሙሉ ግንዛቤ አለው ፣ ለመምራት አስፈላጊው ክህሎትና ችሎታ አለው ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው እንጂ እንደው ዝም ብሎ መሪ ስለሆነ ብቻ አምባገነን መሆን ይችላል ማለቱ አልነበረም ። ይሁን እንጂ ሶሻሊዝም ራሳቸው ተከታዮቹ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱትና እንዲተረጎሙት ካደረጉት  አደናጋሪ የሶሻሊዝም ፅንሰ – ሀሴቦች ይኀው የሰራተኛው አምባገነንነት የሚለው ነው ።

ሶሻሊስቶች ማርክስን ሄግልን ሀሳባዊ «idealist»  ነው በማለት ያጣጣሉት ሲሆን ፣  ምንም እንኳን ማርክስ የሄግልን ዲያሌክትቲክ የአመክንዮ ትንተናን ቢወስድም በቁስ አካላዊ ፍልስፍና ለሚያምነው ማርክስ የሄግልን ሀሳባዊነት ውድቅ እንዳደረገው የታወቀ ነው ። የማርክስ ሀሳቦች ግን የካፒታሊዝምን ስርአት ማሻሻያዎችን ለማድረግ ረድተዋል ። ለምሳሌ የካፒታሊዝም ስርአት ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥርም እንደሚፈጥር ማርክስ ተገንዝቦታል ፤ ምክንያቱም አሰሪዎች ልክ እስከሚፈልጉት ድረስ ብቻ ሲሆን ሰራተኞችን የሚቀጥሩት ከዛም በላይ ወጪን ለመቀነስ በቴክኖሎጂና በማሽኖች ሰራተኞችን ቁጥር ቀዝቅ ሊያደርግ እንደሚችሉም ግልፅ ነው ። ማህበራዊ ዋስትና ስርአት የተጀመረው የማርክስን ትችቶች መሰረት በማድረግ ሲሆን ፣ ቀደም ባለው ጊዜያት ሰራተኞች ስራ ካጡ ወይን ከስራ ከተቀነሱ ምንም ገቢ እማይኖራቸው ሲሆን በዚህም ምክንያት በርካታ የሰራተኞች አመፅንና ይፈጥር ነበረ ። ሌላው ደግሞ የሰራተኞች የመደራጀት መብትም እንዲሁ ቀደም ባለው ጊዜያት የማይፈቀድ የነበረ ሲሆን ውሎ አድሮ ግን ሰራተኞች ተደራጅተው መብታቸውን ማስከበራቸው ያለውን ጥቅም በመረዳት በብዙ የአለም ሀገራት መደራጀት የተፈቀደ ሆኗል ። በዚህም ሰራተኞች መደራጀት መቻላቸው እና ህጉን ተከትለው መብታቸውን ማስከበራቸው፣ ችግሮች ውስጥ ውስጡን የማይብላሉ ከመሆኑም በላይ ሰራተኞች አለአግባብ መብታቸውን እንዳይነካ ስለሚያደርግ መኖሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ።

በአውሮፓም በርካታ የሶሻሊስት ፓርቲዎች ሲኖሩ በምርጫ የሚወዳደሩና ባለው ስርአት ውስጥ እሚንቀሳቀሱ ናቸው ። የአሜሪካኖችን ስርአት ስናይ ግን ሙሉ ለሙሉ በንፁህ የፈጠጠ የካፒታሊዝም ስርአት መሆኑ ግልፅ ነው ። የአውሮፓውያን ስርአት ለዘብ ያለ እና ሶሻሊዝምን በተወሰነ ደረጃ እሚያስተናግድ ሲሆን ፣ እንደ ጀርመን ፈረንሳይ ባሉት በብዙ የአውሮፓ ሀገራትም ሶሻል ዲሞክራቶች አሉ  የአሜሪካኖቹ ግን የፈጠጠ የካፒታሊስት ስርአት ነው ተብሎ ይተቻል ። የሰሜን አውሮፓ ሀገራት የማህበራዊ ደህንነት ዋስትና ያላቸው ሲሆኑ (Welfare States) በመባልም ይታወቃሉ ።

ይሁን እንጂ ይህ ፍልስፍና በርካታ ደጋፊዎች በተለይም በወጣት ተማሪዎችና ምሁራን ዘንድእ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ በአለም ዙሪያ የጋለ ድጋፍን ቢያገኝም ወደ ተግባር ሲመጣ ግን በቀላሉ በስልጣን ጥመኞች ሊጠለፍና ሊቀለበስ የሚችል በመሆኑ ምክንያትና ለመሪዎቹ ግላዊ ጥቅም ሲባል አብዛኛውን አቅጣጫውን በመሳት ፣ በብዙ ሀገራት ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነትና አስከፊ የሆኑ አምባገነናዊ ስርአቶች እንዲፈጠሩ ስላስቻለ ደጋፊዎቹ እየተመናመኑ ሄዱ ፣ በውጪ ከመጣበት ጫና ይልቅ በራሱ ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት በበርካታ ሀገራት ሊፈረካከስ በቅቷል ። በአሁኑ ወቅትም ንድፈ- ሀሳባዊ ክርክሮች በትምህርት ተቋማት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በተግባር እንደ ቀድሞው በአለም ላይ በተግባር የሚለውልበት እድል እየጠበበ ሄዷል ።

በ2011 የወጡ ጥናቶች እንደጠቆሙት የአለምን 90 በመቶ ሀብት የሚቆጣጠሩት 10 በመቶ የሚሆኑት የአለማችን ሀብታሞች ከ20 አመታት በፊት የነበራቸው ሀብት ፤ አሁን ካላቸው ሀብት ጋር ሲነፃፀር በ500 ፐርሰንት ጨምሮ ሲገኝ ፤ በአንፃሩ ከአለማችን ሀብት 10 በመቶ ብቻ የሚሆነውን የሚጠቀሙት 90 በመቶ የሚሆኑት የአለማችን ህዝቦች ያላቸው ሀብት ከ20 አመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር አሁን ያላቸው ሀብት በአያሌው ቀንሶ ተገኝቷል ። ይህም በአለማችን ያለው የሀብት ክፍፍሉና ፤ ሰፋ ባለ ሁኔታ እየተዛባ እንደሄደናየመካከለኛው መደብ የህብረሰብ ክፍል በቁጥርም ሆነ በኑሮ ደርጃው እየተዳከመ እንደሄደ ሲያሳይ የደሀው የህብረተሰብ ክፍል ግን ወደ ባሰ ድህነት ሊወርድ እንደሚችል መገመት ይቻላል ።

Advertisements

የአለም የንግድ ስርአት ፍትሀዊ አለመሆን

ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ይሄንን የአለም የንግድ ስርአት ሚዛኑን የጠበቀ አለመሆኑን በ20ኛው ክ.ዘመን መባቻ ላይ ታገንዝበውታል ። ይሁን እንጂ ይህ የጥገኝነት ንድፈ – ሀሳብ (Depenedency Theory) በተባለው በአብዛኛው በላቲን አሜሪካን ሀገር የምጣኔ – ሀብት ባለሙያዎች በ1950ዎቹ የተደረሰበት ነው ። በእርግጥ በአንዳንዶች ይህ ንድፈ – ሀሳብ ሶሻሊዝም ቀመስ ነው ተብሎ ይገመታል ፣ ኒኦ – ማርክሲዝምን ይወክላል  በሚል ።

የራኡል ፕሬቢሽና የሲንገር ንድፈ – ሀሳብ «Prebish – Singer Theses» ላይ በሚገባ የተቀመጠ ሲሆን ፣ እነሱም ከ1930ዎቹ በኋላ በተከሰተው ታላቁ የምጣኔ – ሀብት መቀዛቀዝን ተከትሎ በተፈጠረው የአለም የምጣኔ – ሀብት ችግር በመነሳት የተለያዩ መረጃዎችን በመጠቀም አስልተው የደረሱበትና በቁጥርም መረጃዎች የተረጋገጠ እውነታ ነው ። ይሁን እንጂ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ይህንን ንድፈ – ሀሳብ በዚያን ዘመን አስቀድመው መረዳት ችለዋል ። ይህንን ንድፈ – ሀሳብንም በመከተል በርካታ የላቲን ሀገራት ወደ የሀገር ውስጥ ገበያቸውን መከላከልንና ከውጪ ለሚገቡ ምርቶች ታሪፍን በመጣል የኢንዱስትሪ እድገታቸውን ለማጠናከር ሞክረዋል ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ከተወሰኑ አመታት ኋላ የተደረጉ ምርምሮች እንዳሳዩት ግን ሀገራት ለኢንዱስትሪዎቻቸው ከለላ እሚያደርጉ ከሆነ በሀገር ደረጃና በሸማቾች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ታይቷል ።

    ይህም ሀብታም ሀገራት የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን በውድ ዋጋ ለአለም ገበያ ሲያቀርቡ ፣ ደሀ ሀገራት ግን የግብርና ምርታቸውን ለአለም ገበያ ያቀርባሉ ። ይህም ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ በተደረጉ ጥናቶች የግብርና ምርቶች ዋጋ ከኢንዱስትሪ ምርቶች ጋር ሲወዳደር በአንፃራዊነት እየቀነሰ ነው የመጣው ። ይህ እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ ይታይ የነበረ ክስተት ነው ።

ነገር ግን የእስያውያን በምጣኔ – ሀብት እያየሉ መውጣት በጀመሩበት ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ ገቢ ማግኘት መጀመራቸው አሌ የማይባል ሀቅ ነው ። በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ የግብርና ምርቶች ፣ የማእድናት ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት የዚህ ሀብት ባለቤት የሆኑ ሀገራት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው ። ነገር ግን ይሄ የተፈጥሮ ሀብት ላይ የተንጠለጠለ ምጣኔ – ሀብት ግን የራሱን ችግሮችንም ይዞ ብቅ ማለቱ የሚታወቅ ነው ። በአንድ በኩል የነዳጅ ፣ የአልማዝ ፣ የወርቅ የመሳሰለው ሀብት ባለቤት የሆኑ ሀገራት ውስጥ ምጣኔ ሀብታቸው በአንድ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ካልተመሰረቱ ሀገራት በአንፃሩ ሙስና መስፋፋቱ ፣ የተዛባ የሀብት ክፍፍልም በእነዚህ ሀገራት በስፋት የሚታይ ሀቅ ነው ።

    በርካቶቹ ታላላቅ የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ደሀ ሀገራት የገንዘባቸውን ምንዛሬ ዝቅ እንዲያደርጉ ሲመክሩ በአንፃሩ ግን በየፋብሪካ ምርቶቿን ለአለም የምታቀርበውን ቻይናን ገንዘቧን ዝቅ በማድረግ የአለምን ገበያ እየተቆጣጠረች ነው የሚል ትችት ይሰነዝራሉ ። ይህም እነሱን ሊወዳደር የሚችልን ላለማበረታታት ፣ እነሱን ሊጠቅም የሚችልን ደግሞ ለማነቃቃት ሲሉ የሚያደርጉት ነው ።

በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ በታየው የዋጋ ግሽበት ምክንያት የግብርና ምርቶች ዋጋ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋቸው እየጨመረ መጥቷል ።የማእድናት ዋጋም እንዲሁ ዋጋቸው እየጨመረ በመምጣቱ ማእድን ላኪ የሆኑ የአለምን ሀገራት ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ። እ.ኤ.አ በ2050 የአለም ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መቶ ወደ 9.5 ቢሊየን ይጠጋል ተብሎ የሚገመት ሲሆንበህዝብ ቁጥር መጨመርና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለግብርና አመቺ የሆነው ለም መሬት ከአመት አመት እያነሰ በመምጣቱ እስያውያንና አረቦችም ጭምር በአፍሪካ ውስጥ መሬትን እየተኮናተሩ የግብርና ስራ የጀመሩ ሲሆን የግብርና ምርቶች በአለም ገበያ የተሻለ ዋጋን ሊያወጡ የሚችሉበት እድል አለ ።

በ2011 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ብራዚል እንግሊዝን በአጠቃላይ ምርት በመተካቷ ሲነገር መሰረታዊ ምርት የሚያመርቱ ሀገራት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራትን መተካታቸውንማሳያ ሆኗል ። ለዚህ ምክንያቱ ብራዚል ካላት ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የተነሳ ያላትን ሀብት እየተጠቀመች በሄደች ቁጥር ሀብቷና አገራዊ ምርቷ እያደገ ነው የሄደው ። በአንፃሩ ግን እንግሊዝ ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ያላት ስላልሆነ እድገቷ ከተወሰነ ደረጃ በኋላ ግን የቀነሰ የመሄድ አዝማሚያ ስለሚኖረው ግዙፍና ሰፊ የሆነችውን ከኢትዮጲያ አራት ጊዜ እጥፍ ስፋት ያላትን ብራዚልን ልትበልጥ አልቻለችም ።

በአሁኑ ወቅት ግን በአንፃራዊነት ለታዳጊ አገራት የተሻለ ሁኔታ ተፈጥሯል ። ከዚህ ቀደም አሜሪካና አውሮፓና ያደጉት ሀገራት ሲስማሙ ሌላው ታዳጊ አለም ያለምንም ጥያቄ ተሰብስቦ ይፈርም የነበረ ሲሆን ፣ አሁን ግን ታዳጊዎቹ ሀገራት በተናጠል ከሀብታሞቹ ሀገራት ጋር መደራደር እንደማይችሉ ሲረዱ ፣ ሰብሰብ ብለው ጥቅማቸውን የማስከበር ስራን እና ጠለቅ ያለ ጥቅማቸውን እሚያስከብር ክርክርንና ድርድርን ማድረግ ችለዋል ። በሌላ በኩል ደግሞ ታዳጊዎቹ አገራት የገንዘብ ምንጭን በሚፈልጉበት ወቅት ወደ ቻይናና ህንድና ብራዚል ማማተር ጀምረዋል ። ቀድሞ ግን ወደ «IMF» እና «World Bank» ብቻ እንጂ ሌላ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ አልነበረም ። በተለይም «BRICS» የተባሉት አገራት ማለትም ብራዚል ፣ ሩስና ፣ ህንድና ቻይና የገበያና የገንዘብ ምንጮችን ከእነሱ ላነሰ ደረጃ ላሉ አገራት አማራጭ እድሎችን ከፍተዋል ።

 

የወደፊቱ የአለማችን ፈተናዎች

እስካሁን የሰውን ልጅ ከተፈታተኑ ችግሮች መሀከል የአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ እጅግ አስከፊው ነው ማለት ይቻላል ። ተፈጥሮ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ አመታት በዝግመተ – ለውጥ አቀነባብሮና አዘጋጅቶ ያቆየውን ስነ – ምህዳር የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ፣ በመኪኖች እተፈጠረ ያለውየተበከለ አየር እየበከለው ይገኛል ። ህይወት ላላቸው እንሰሳት ህልውና እጅግ አስፈላጊውን አየር ማለትን ኦክስጅንን የሚያመነጩትና ፣ ዝርያቸው በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ህይወት ያላቸውን ፍጥረታት በውስጣቸው አቅፈው የያዙ ውቅያኖሶች ፣ ባህሮችና ሀይቆችም እንዲሁ ከምድር በሚለቀቁ መርዛማ ኬሚካሎች እየተበከሉ ይገኛሉ ። 

ድንጋይ ከሰል ርካሹ የሀይል ምንጭ ስለሆነ በብዙ ሀገራት በስፋት ስራ ላይ እየዋለ ሲገኝ ፣  አለምን በመበከልና የአለምን ሙቀት በመጨመር በኩልም ከድንጋይ ከሰል የሚለቀቀው ጭስ ትልቅ አስተዋፅኦን እንደሚያደርግ ሳይንቶስቶች ይናገራሉ ። በነገራችን ላይ ታዳጊ ሀገራትም ቀድሞ የበለፀጉት በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙ ሀገራት አካባቢን ስለበከሉ አሁን የኛ ተራ ነው ብለው አለምን ለመበከል ትክክል የማያደርገው ሲሆን ፣ በአንፃሩ ያደጉት ሀገራት በውስጣዊ ምጣኔ ሀብት ችግሮች እየተጠመዱ ስለሆነ የአካባቢን ጉዳይ ለመቀነስ ያስችል የነበረው አቅማቸው ደከም ማለቱ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ።

ከዚህ ቀደም አለምን ሊያጠፉ ደርሰው የነበሩ እንደ የኒውክሊየር ጦርነት ስጋቶች የነበሩ ቢሆንም ለምሳሌ የኩባውን የሚሳይል ቀውስ ብንወስድ በእ.ኤ.አ. በ1963 ተከስቶ የነበረው ጉዳዩ ለአለም የሚያሰጋ የነበረ ቢሆንምየተፈራው ሳይሆን ቀርቶ ነገሩ ሊፈታና ሊቋጭ ችሏል ።

ለምሳሌ የአርክቲክ በረዶ በከፍተኛ ሁኔታ ፍጥነት እየቀለጠ ሲገኝ በጥቂት አመታት ውስጥም ሙሉ ለሙሉ ቀልጦ እንደሚያልቅ በሳይንቲስቶች ተተበንብዮአል ። በረዶው በመቅለጡ አዲስ የመርከቦች የጉዞ መንገድ የተከፈተ ሲሆን በሰሜን አውሮፓ ፣ በሳይቤሪያ ወደ ጃፓንና ሩቅ ምስራቅ እስያ እስከ ታይላንድ ድረስ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያስተናግድ ሲሆን ከሳይቤሪያ የነዳጅና ሌሎች ማእድናትን ለሚያጓጉዙ ግዙፍ የመርከብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ቀድሞ የነበረውን መስመር በእጅጉ ሊያሳጥረው ችሏል፣ አዲስ የንግድ መስመር ለመከፈትም በቅቷል ።

አስገራሚው ነገር አንዳንድ አካባቢዎች በአየር ንብረት ለውጡ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉ አሉ ። በዚህም የመርከብ ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅቶች የተደሰቱ ሲሆን በአንፃሩ ግን የበረዶው መቅለጥ በርካታ የባህር ጠረፎችን ፣ ዳርቻዎችንና ትናንሽ ደሴቶችን በውሀ እንዲዋጡ ያደርጋል ። ይህ ብቻ ሳይሆን በበረዷማ አካባቢው ይኖሩ የነበሩ ፣በሌላ ቦታ እማይገኙ በርካታ እንሰሳትና አእዋፋትም አካባቢው ለኑሯቸው አመቺ ስለማይሆንላቸው አካባቢውን ለቀው ሊሰደዱ ወይም ሊጠፉ ይችላሉ ። በአለም ዙሪያ በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ላይ የባህሮችና የውቅያኖሶች የባህር ከፍታ በአንድ ሜትር ከፍ ይላል ተብሎ ይገመታል ።

በሰሜናዊው ንፍቀ – ክበብ የሚገኙት ሀገራትም እንደ ሩስያ ፣ ካናዳና አሜሪካ ጭምር ያሉት በበረዶው መቅለጥ ምክንያት የሰሜናዊው ንፍቀ – ክበብ በውስጡ ያለውን የማእድን ሀብት ለማውጣትና ፣ ለንግድ ዝውውር አዲስ የንግድ መስመር ይከፍታል ። እንዲሁም በአርክቲክ አካባቢ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የአለማችን የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ፣ በርካታ ማእድናት በዚሁ አካባቢ እንደሚገኙ በፍለጋና አሰሳዎች ተረጋግጧል ።

በአለም ላይ የፖለቲካና የምጣኔ – ሀብት ፍልስፍና እንዲሁም የአስተሳሰብ ልዩነቶች አሉ ። እነኚህ የአስተሳሰብ ልዩነቶች በአጠቃላይ ለአለም ሰላምና ደህንነት ኣሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ እንዳይደረስ እንቅፋት ሆነዋል – ለምሳሌ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ ።

የአለማችን የአየር ንብረት ከለውጥን ሳይንቲስቶችና የንግድ ሰዎች ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ  ቢያዩት አስገራሚ አይሆንም ። ለንግድ ሰዎች ከኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ አዲስ የንግድ መስመርን ይከፍታል በዚህም የንግድ መስመሩን ያሳጥራል ፣ ማእድናት ይገኙበታል ከሳይንቲስቶች እይታ አንፃር ደግሞ  ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ግን የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ ። እስካሁን ድረስም ወደ ከባቢ አየር በተለቀቀው በካይ ጋዝና ጭስ ብቻ ለሚቀጥሉት አንድ ሺ አመታት በአለም ዙሪያ የባህሮችንና የውቅያኖሶችን ከፍታ እንዲጨምር እንደሚያደርገው ሳይንቲስቶች ያምናሉ ።

አንዳንድ ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ ስለጠፈር ለመመራመር ካለው ጉጉት ይልቅ ስለውቅያኖሶች ጉጉት ቢያሳድር ጥሩ ነበር የሚሉ አሉ ። እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ጥልቀት ያለው የውቅያኖስ ወለል በውስጡ በርካታ የስነ – ህይወት ሚስጥሮችን የያዘ ነው ። የአለም ወደ 70በመቶ የሚሆነው ኦክስጅን የሚመነጨው ውቅያኖስ ውስጥ ከሚኖሩ ተክሎችና ፣አልጌዎች ሲሆን ከዛ ውስጥም ከምንተነፍሰው 20 በመቶ የሚሆነውን ኦክስጅን የሚመጣው ከአንድ አይነት የባህር ባክቴርያ የሚያመነጨው ነው ። ስለዚህ የባህር የህይወት ሰንሰለት ቢዛነፍ ሰውም ሆነለእንሰሳት ህይወት እጅግ አስፈላጊ የሆነው የኦክስጅን አቅርቦት አደጋ ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን ውቅያኖሶች ከመሬት ፋብሪካዎች በሚለቀቁ መርዛማ ነገሮች ያለማቋረጥ እየተበከሉ ሲሆን በውቅያኖስ ውስጥ ያሉትም ህይወት ያላቸው ፍጡራን ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እየወደቀ ነው ።

ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ሞንጎሊያ ባሉ ሀገራት የኦዞን መቀደዱን ሳይንቲስቶች ያረጋገጡ ሲሆን ሰዎችን ለአይን ሞራ ግርዶሽ ፣ እና ለቆዳ ካንሰር ሊያጋልጥ እንደሚችል ሳይንቲስቶች አስገንዝበዋል።ይህ ብቻ ሳይሆን ከሳተላይት የተነሱ ፎቶግራፎች እንደሚያመለክቱት አለማችን መሬቷና የውሀ አካላቷ አሲዳማ እየሆነ እንደሄደ ነው ። ለዚህም ምክንያቱ የማዳበሪያዎች እና የኬሚካሎች በብዛት ጥቅም  መዋል ፤ የድንጋይ ከሰል ስራ ላይ መዋል ፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የመሳሰሉት ምድርን ወደ አሲዳማነት እየቀየራት ይገኛል ። ይህም የአሲድ ዝናቦችም እንዲሁ በተለያየ የአለማችን ክፍሎች እንደሚጥሉም በሳይንቲስቶች በተደጋጋሚ የተገለፀ ጉዳይ ነው ።

በተለይም የአለማችን ችግሮች እየበዙ ባለበት በዚህ ዘመን በአጠቃላይ በአለም ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ (Status Quo) አስጠብቆ መቆየት ይበልጥ አስቸጋሪ ሲሆን ፣ የነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መውጣት ግን በቀላሉ ሊከሰትና ለአለም በርካታ ችግሮችን ሊፈጥር ይችላል ። በአሁኑ ወቅት የምንኖርባት አለማችን ይበልጥ አደገኛ እየሆነች በመሄድ ላይ ትገኛለች ።

ሀብትን መፍጠር

ሀብትን መፍጠር የሚችለው የሰው ልጅ ብቻ ነው ። የማሰብ ችሎታ ያለው ብቸኛው ፍጡር የሰው ልጅ እንደመሆኑ በማሰብ ችሎታው ሀብትን ይፈጥራል ። እንሰሳትን ብንወስድ ደመ – ነፍሳዊ በሆነ መንገድ ምግባቸውን ለችግር ጊዜ ያከማቻሉ ፣ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ያዘጋጃሉ ፣ ወይም መርጣሉ ። ለምሳሌ ንቦች ፣ ጉንዳኖችና ሌሎችም ነፍሳት ለችግር ጊዜ ምግብን ቢያከማቹና ታታሪ ሰራተኞች ቢሆኑም ስራቸው ግን እንደ ሰው ልጅ አውቀውና ተረድተው እሚሰሩት ሳይሆን ፍፁም ደመ – ነፍሳዊ ነው።

በአንፃሩ የሰው ልጅ በደግ ጊዜ ያመረተውን በጎተራ አከማችቶ ፣ የሚመገበውን አዘጋጅቶ ፣ የሚኖርበትን ቤት ሰርቶ ይኖራል ። ከዚያም አልፎ የስራ ክፍፍልን በመፍጠር ሁሉም የሰው ልጅ በአንድ ዘርፍ ተሰማራ እንዳይሆን በማድረጉና በየራሱ ሙያ የላቀን ችሎታ በመፍጠሩ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ምርታማ እንዲሆን አድርጓል ። የስራ ክፍፍል ባይኖር ኖሮ የዚህን ያክል ምርታማነትና ሀብት አይፈጠርም ነበረ ።አዳም ስሚዝ ይህንን የስራ ክፍፍል በመረዳት ለምጣኔ ሀብት የትምህርት ዘርፍ አንዱ መሰረታዊ እሳቤ ለመሆን በቅቷል ።

ሀብትን መፍጠር ለአንድ ማህበረሰብ የተደላደለ ህይወት እንዲኖርና የማህበረሰቡ ህይወት እንደዲቀጥል አስፈላጊ ነው ። ይሁን እንጂ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሀብትን መፍጠር የሚችሉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ የተቀረው የህብረተሰቡ ክፍል ከነሱ ጋር አብሮ በመስራት ኑሮው የተደላደለ ያደርጋል ።ባደጉት ሀገሮች ሳይቀር ሀብትን መፍጠር የሚችሉት ዜጎች ቁጥር ብዙ አይደለም ። ብዙዎቹም ስራ ፈጣሪዎች ኢንተርፐርነሮች ሲሆኑ የተቀሩትም ሳይንቲስቶች ፣ አርቲስቶች ፣ባለሀብቶች ፣ የፖለቲካ መሪቀዎች ፣አንዲሁም አንዳንድ የላቀ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ናቸዉ።

አዳም ስሚዝ የሀገሮች ሀብት በተሰኘው ምጣኔ – ሀብት እንደሙያ መስክ መወለድ አስተዋፅኦን አድርጓል ተብሎ በሚታመነው ፈር – ቀዳጅ መፅሀፉ ይህንን የሀገሮችን ሀብት ምንነትና ምንጭ በመረዳት መተንተን በመቻሉ የምጣኔ ሀብት የትምህርት ዘርፍ ተወለደ ።አንዳንዶች የአዳም ስሚዝን መፅሀፍ የካፒታሊዝም መፅሀፍ ቅዱስ በማለት ይገልፁታል ። በአብዛኛው የፈረንሳይ ፈላስፋዎችን መሰረት በማድረግ መፅሀፉን እንደፃፈው ይታመናል ። ምጣኔ – ሀብትን ፈጠሩ እሚባሉት ፈረንሳውያን ፈላስፋዎች ሲሆኑ በተደራጀና ደርዝ ባለው መልክ ግን ያቀረበው አዳም ስሚዝ ነው ። አዳም ስሚዝ የእንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰቦች አስተማሪ ስለነበረ ከንጉሳውያኑ ጋራ በአውሮፓ በተለይም ጉብኝቶችን ያደርግ በመሆኑ ከአውሮፓ ፈላስፎች ጋር የመወያየትና በርካታ ሀሳቦችን የመለዋወጥ እድል ነበረው ።ይሁን እንጂ በርካቹን ዋናዎቹን ቀደምት ሀሳብ አፍላቂዎችን ባለመጥቀሱ በጥቂቱም ቢሆን መወቀሱ አልቀረም ።

ከሱ ቀደም የምጣኔ ሀብት አንደ የስነ – ምግባር (ethics) የትምህርት ዘርፍ አካል ተደርጎ ይቆጠር ነበረ ።ማንኛውም የማህበረሰብ እሴት በግለሰቦች አስተዋፅኦ (contribution) እየዳበረ የሚሄድ ነገር ነው ።  

       ሀብት በሁለት መንገዶች ይፈጠራል ። አንዱ ምርታማነትን በመጨመር ሲሆን ሌላው ደግሞ አንዲት ሀገር ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመሸጥ ወይም በማከራየት ነው ። ምርታማነትን ለመጨመር አንዲት ሀገር አዳዲስ ቴክኖሎጂን በመፍጠር ፣ በስራ ፈጠራን (Enterperunrship) አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችንና አሰራሮችንበማስፋፋት ፣ ዘመናዊ ማሽኖችንና ፋብሪካዎችን በመትከል ሲሆን የተፈጥሮ ሀብቷን ነዳጇን በመሸጥ ወይም መሬቷን በማከራየት ልክ የአፍሪካ ሀገራት እንዳደረጉት ወይም ያላቸውን ነዳጅም ይሁን ወርቅ አልማዝ ፣ ለገበያ በማቅረብና በመሸጥሊሆን ይችላል ። እንደ አንዳንዶች ግምት አሁን ታዳጊ ሀገራት እያገኙ ያሉት ፈጣን የምጣኔ – ሀብት እድገት የተፈጥሮ አካባቢ ላይ በደረሰ ጉዳት አማካይነት የመጣ እንዳይሆን ስጋት ያላቸው አሉ ።

ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ሀብትን ስለመፍጠር መንግስትና ህዝብ አስተዳደር በተሰኘ መፅሀፋቸው እንዲህ ይላሉ ፣ ሀብት ማለት የተከማቸ ስራ ነው ፣ ይላሉ ያ ማለት አንድ ሰው ብዙ እውቀት ባለቤት በሆነ ቁጥር በርካታ ስራን ማከማቸት ይችላል ስለዚህ በቀላሉ ሀብትን መፍጠር ይችላል ። ለምሳሌ አንድ በጃፓን ውንም በጀርመን ያለ ፋብሪካ በሰአታት ውስጥ በርካታ ሀብትን መፍጠር ይችላል ። ወይንም አንድ ሀኪም በአንድ ሰአት ውስጥ የሚያገኘው አንድ የቀን ሰራተኛ በቀን ውስጥ ተቀጥሮ ከሚያገኘው ይበልጣል ምክንያቱም ሀኪሙ በአመታት ውስጥ በርካታ እውቀትን ስለሰበሰበ በአጭር ጊዜ ውስት ያንን እውቀቱን ወደ ተከማቸ ስራ ማለትም ወደ ሀብት መቀየር ይችላል ማለት ነው ።

የተከማቸ ስራ የሚፈጠረው ከተከማቸ እውቀትና የአካላዊ ስራና እንቅስቃሴ ሲሆን ፣ የዴቪድ ሪካርዶ ፍቺ ጋራ ተመሳሳይ ነው ። እሴት ማለት በእሴት ውስጥ ያለ ጉልበት ነው የሚል ፍቺ ነው ። እዚህ ጋ ምንድነው ጊዜን እማንጨምረው ቢባል ጊዜ ደሞዝን ወይም ምንዳን ወይም ኪራይን ለማስላት ነው የሚጠቅመው ። በእርግጥ አንድን እሴት ለመፍጠር ጊዜ የሚያስፈልግ መሆኑ ይታወቃል ፤ የጊዜ ስሌት ደግሞ ምንዳን ወይም ደሞዝን ለማስላት ነው የሚጠቅመው ።

የተፈጥሮ ሀብቶችን ብንወስድ ምንም እንኳን ውድ ማእድናት ነዳጅም ይሁን ወርቅ ወይም አልማዝ እነዚህን ማእድናት መጀመሪያ ለመፈለግ ፣ ለማግኘት ብሎም ለማውጣት ስራ መስራትን ይጠይቃል ። ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብትም ቢሆን እሴቱ ወይም ዋጋው እሚተመነው በወጣበት ጉልበትና እውቀት ልክ ነው ። ለምሳሌ አልማዝን ወይም ወርቅን ለማግኘት በጣም አድካሚ ሲሆን ከአፈርና ድንጋይ አላቆ ፈልፍሎ ለማውጣትም እንደዛው ብዙ ድካምን ይጠይቃል ስለዚህ ዋጋው በጣም ውድ ይሆናል ።

ስለዚህ ማንኛውም የሰው ልጅ ሀብት እሚለው ነገር የተፈጠረው በጉልበት እና በእውቀት ነው ። ለምሳሌ በመሬት ላይ ያደገ ዛፍን እንኳን ብንወስድ ለመትከልና ለማሳደግ ጉልበት ሲያስፈልግ በራሱ በተፈጥሮ ያደገ ነው ብንል እንኳን ለመቁረጥ ጉልበት ያስፈልጋል ፣ እሚተካ ዛፍ ካልተተከለበት ደግሞ የነበረውን ወሰድነው እንጂ አዲስ ሀብትን አልፈጠርንም ፣ ወደ ፊት ሌላ እንጨትን አይሰጥም ።

ሀብት የሚፈጠረው ከጉልበት ነው እሚመነጨው ። ይህን ዴቪድ ሪካርዶ የጠቀሰው ሲሆን ፤ ካርል ማርክስም የጉልበት እሴት ንድፈ – ሀሳብ ከሪካርዶ አስተሳሰበች የተቃኙ መሆናቸው ይታወቃል ። በነገራችን ላይ ካርል ማርክስ የኮሚኒዝምን ንድፈ- ሀሳብ የገነባው ዴቪድ ሪካርዶ ባስቀመጠው መሰረተው ጉልበት የእሴት ዋጋ ንድፈ – ሀሳብ በላይ በመመስረት ነው ። በምጣኔ – ሀብት ውስጥ የጉልበት ዋጋ እሴቱም ሆነ አንድምታው በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው ። 

አሁን ካለው የቀደሙትን የሰው ልጆች አኗኗራቸውን ብናይ በብዙ መልኩ ከአሁኑ ያነሰ ሲሆን ፣ የነበራቸው ሳይንሳዊ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ መጓጓዣ፣ ወዘተ ከአሁኑ በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ምክንያት የሀብት ደረጃቸውም ከአሁኑ አነስተኛ ሆኖ ኖሯል።

በሀገርም ደረጃ ተመሳሳይ ነው ። ብዙ እውቀትንና ክህሎትን የሰበሰበ ሀገር ፣ ከፍተኛ ሀብትን ያገኛል ። ከመላው አሉ የተባሉ በአሜሪካን ሀገር መሰባሰባቸው ለአሜሪካ ትልቅ እሴትንና ሀብት ን ፈጥሯል ። ለምሳሌ አሜሪካንን ብንወስድ ሆሊወድንና ብንወስድ ከፍተኛ እውቀትና ሙያ ባላቸው ሰዎች የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሲሆን ፣ በካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኘው ፣ ሲልከን ቫሊ በመባል የሚታወቀው የኮምፒውተር ፣ የመገናኛና የሞባይል ቴክኖሎጂን እሚያንቀሳቅስ ኩባንያዎች እሚገኙት በዚሁ አካባቢ ሲሆን አሜሪካ ባላት በተከማቸ እውቀቷ በመጠቀም ከአለም ግዙፍ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን መመስረት ችላለች ፣ ምንም እንኳን ትችት ቢቀርብባቸውም የፋይናንስ ተቋማቷም እንዲሁ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚያደርጉ ናቸው ። ይህም ብቻ ሳይሆን በታላላቅ ኩባንያዎቿ አማካይነት ባላት የባለቤትነት መብት ለምሳሌ እንደ ኮካ ኮላ ፣ ፔፕሲ እና በሌሎችም ከፍተኛ ሀብትን ያገኛሉ ያንቀሳቅሳሉ ።

በአለም ደረጃም ስናየው አሁን ያለው የአለም ህዝብ ሀብት እያደገና እየተመነደገ ይሄዳል ። ቀድሞ የሰው ልጅ ከነበረበት የሀብት ደረጃ ሲታይ ፣ አነስተኛ ሀብት የነበረው ምክንያቱ ዋናው በዛን ዘመን የነበረውም እውቀት አነስተኛ ስለሆነ የሀብት ደረጃም አነስተኛ ነበረ ። ከዚህ በኋላም የሚመጡት ትውልዶች ከፍተኛ የእውቀት ደረጃ ላይ ስለሚደርሱ ፣ የሚያፈሩት ሀብትም እንደዛው እያደገ ይሄዳል ። የእውቀት ደረጃቸው እየጨመረ ስለሚሄድ የኑሮ ፣ የጤና ፣ በአጠቃላይ አኗኗራቸው ሁሉ አሁን ካለው የላቀ እየሆነ ይሄዳል ።

ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2050 አለማችን ምን ትመስላለች ፣ ወይም ምን አይነት ልትመስል ትችላለች ተብሎ ሲታሰብ ለምሳሌ የአሜሪካን ምጣኔ – ሀብት አሁን ካለበት 15.5 ትሪሊየን ዶላር አካባቢው አመታዊ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) ወደ 27 ትሪሊየን ሲደርስ ፣ የቻይና የህንድም ምጣኔ – ሀብትም እንደዛው ከፍ ይላል ። በአጠቃላይ የአለም ምጣኔ – ሀብት ከእጥፍ በላይ እንደሚያድግም ይጠበቃል ። ይሁን እንጂ በአካባቢ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን ግን ከወዲሁመገመት አያስቸግርም ።   

የተፈጥሮ ሀብት መሟጠጥንም እንደዛው እየተባባሰ የሚሄድ ሲሆን ለምሳሌ ነዳጅን ብንወስድ የአለም የነዳጅ ዘይት ሀብት መሟጠጡና ብሎም ማለቁ አይቀርም ፣ ነዳጅንም ፍለጋ በጣም ሩቅ የሆኑና የሰው ልጅ በቀላሉ የማይደርስባቸው አካባቢዎች ጭምር የፍለጋ ማእከል ሲሆኑ ፣ በሰሜንና በደቡብ ዋልታዎች ያሉ አካባቢዎች እንዲሁም የውቅያኖስ ወለሎችም ነዳጅንም ሆነ ሌሎች ማእድናትን ፍለጋ የሚታሰሱ ይሆናሉ ። የነዳጅ ዘይት በስፋት ስራ ላይ መዋል የጀመረው ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ሲሆን ፣ ከዚያ በፊት የኢንዱስትሪው አብዮት ሲጀመር የድንጋይ ከሰል፣ የእንፋሎት የሀይል ሳይቀር ምንጭ ሆኖ አገልግሏል ። ስለዚህ ነዳጅ ዘይትም ሆነ ድንጋይ ከሰል ቢያልቅ ሌላ የሀይል አማራጭ መፈለጉ አይቀርም ። ይህም ከአሁኑ ታዳሽ የሆኑትን የፀሀይ ብርሀንን ፣ የንፋስ ሀይልን ፣ የባህር ማእበል ሞገድ ግፊትን በመጠቀም ሀይል ማመንጨት የተጀመረ ሲሆን ፤ ወንዞችንም ለሀይል ማመንጪያነት ስራ መዋላቸው ይታወቃል ። ከዚህም ሌላ የኒውክሊየር ሀይል ምንም እንኳን አካባቢ ላይ አደጋን ሊፈጥር ቢችልም፣ ማመንጫ ራሱ ለኤሌክትሪክ ማመንጪያነት በበርካታ ሀገሮች ስራ ላይ እንደዋለም ይተወቃል።

ይሁን እንጂ ነዳጅ ከአለማችን ላይ ቢጠፋ የአለም ምጣኔ – ሀብት አይቆምም ፣ ከዛ ይልቅ በሌላ ቴክኖሎጂ መተካቱ የማይቀር ሲሆን ፣እንደውም በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትም ሊቀንሰው ይችላል ተብሎ ይገመታል ፣ በመጪዎቹ ክፍለ ዘመን በአለም ላይ ያለው የነዳጅ ዘይት በሙሉ ተሟጦ ያልቃል ተብሎ በሳይንቲስቶች ይገመታል። አሁን እንኳን ነዳጅን በኤሌክትሪክ መኪኖች የመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ፣ ታዳሽ የሀይል ምንጮችንም ለማሳደግ ሀገራት ተግተው እየሰሩ ነው ። ያም ብቻ ሳይሆን ወደፊት ከነዳጅ ዘይት ይልቅ የተፈጥሮ ጋዝ የበለጠ ተፈላጊ እንደሚሆን ይገመታል ፣ ዋጋው ርካሽ ከመሆኑና ፣ አካባቢን እንደ ነዳጅ  ዘይት የማይበክል እንደመሆኑ ከድንጋይ ከሰልም ሆነ ከነዳጅ ዘይት ተፈላጊ እንደሚሆን ይጠበቃል ።

የወደፊቱ ትውልዶች በእውቀታቸውም ሆነ በሀብታቸው ከፍተኛ ደረጃላይ ስለሚደርሱ ምናልባትም በጨረቃ ላይ ከተማ ሊሰሩና ፣ ኑሯቸውን በጨረቃ ወይም በሌላ ፕላኔት ላይ ሊያደርጉ ይችላሉ ። እነኚህ ሁሉ የሚሆኑት የተከማቸ እውቀት ስለሚጨምር ፣የአለም ሀብትም ቴክኖሎጂም ከፍ ከዛ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ይወዳደራል ።

ሌላው ደግሞ ከመንግስታት ይልቅ ግለሰቦች ሀብት በመፍጠር የተሻለ ብቃትና ስሉጥነት (Efficiency) ያላቸው ሲሆኑ ፣ መንግስታትም ሀብትን የሚፈጥሩ ቢሆንም አዳዲስ ፈጠራን በመፍጠርና አዲስ መንገድን በመቀየስ ግለሰቦች የበለጠ አቅምና ብቃት አላቸው ። መንግስት ይበልጥ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያተኩር ፣ ህግና ስርአትን ማስፈንና የተደላደለ የውድድር ሜዳን ማዘጋጀት ነው ። ለምሳሌ ሀብትን መፍጠር ምጣኔ – ሀብትንና ሳይንስን ፣ ቴክኖሎጂን ፣ አስተዳደርን ሲመለከት ፣ ያንን የተፈጠረውን ሀብትን ማከፋፈል ግን ፖለቲካ ነው።

ስለሀብት መፈጠር ካነሳን ስለ ሀብት ክፍፍልም ማንሳት በተገቢ ይሆናል ። የአፍሪካ ሀገራት ምጣኔ – ሀብታቸው ቢያድግም በሀብት ክፍፍሉ በኩል ግን ይቀራቸዋል ። በእርግጥ ገና እያደገ ባለ ምጣኔ – ሀብት በቂ ሀብት ሳይፈጠር ስለ ሀብት ክፍፍል ማውራት ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ማስቀደም ሊሆን ይችላል ። ጥቅሉ ምጣኔ – ሀብት (Macroeconomy) በውጪ ባለሀብቶች ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎት እያደገ ሲሄድ እያደገ ይሄዳል ። ነገር ግን ከአንድ አማካይ የኑሮ ደረጃ ባለው ዜጋ ቦታ ላይ ሆነን ስናየው የአንድ ሀገር ምጣኔ – ሀብት በዚህ መቶኛ በአመት አደገ ሲባል ለሱ ምን ትርጉምን ነው እሚሰጠው ? የዛ እድገትስ ወደሱ ኑሮ እንዴት ነው ሊመነዘር የሚችለው ?እነኚህ በፖለቲካ መሪዎች ተስማሚ በሆነ መንገድ ሊደረጉ የሚችሉ ናቸው ።

በደሀ ሀገራትም የሀብት ክፍፍል ማድረግ አብንገብጋቢ ጉዳይ ሊሆን ይችላል ። ይህም ሊሆን የሚችለው ያቺ ሀገር ያላት የተፈጥሮ ሀብት ወይም መሬት በጥቂቶች እጅ ውስጥ ከገባና የተቀረው ህዝብ መፈናነፈኛ ካጣ የሀብት ክፍፍል ማድረግ ግድ የሚልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ።በሀገራችን በ1966 ዓ.ም. የተካሄደው አብዮት ዋነኛው ምክንያት ሰፊው መሬት በጥቂት የመሬት ከበርቴዎች እጅ መውደቁና ብዙሀኑ ህዝብ ጭሰኛ የሆነበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነበረ ። በወቅቱ በሀገራችን ላይየተዛባ የሀብት ክፍፍል እንደነበረ መገመት ይቻላል ። ዋና የሀብት ምንጭ የሆነው መሬት በጥቂቶች መያዙ ለተዛባ የሀብት ክፍፍል መንስኤ የነበረ ሲሆን ፣ ወደፊትም ይኀው የመሬት ጉዳይ ለሀብት መዛባት መነሾ ሊሆን ይችላል ።

አንድ እማይካድ ነገር በአለም ዙሪያ በግርድፉ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሀብት ከ10 በመቶ ባልበለጡ ሰዎች እጅ ነው እሚገኘው ። ይህም የሀብት ክፍፍል በአሁኑ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ባለበት ዘመን በተለይም እየሰፋ ነው የመጣው ። ስራ – ፈጣሪዎች ሊያገኙ የሚችሉት ሀብት አንድ ሰራተኛ ከሚያገኘው እጅግ የበዛ ነው ። ዋናው ነገር ግን ለማንም ክፍት የሆነና ማንም ሰው ችሎታውና ትጋቱ እስካለው ድረስ ያለ ሌላ አድልኦ ማለትም በዘሩ ፣ በፆታው ፣ በመሳሰሉት መድልኦ ሳይደረግበት ማደግ የሚችልበትን ፍትሀዊ ስርአት መዘርጋቱን ማረጋገጥ ነው ፣ ሀብትን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ በማከፋፈል ዘላቂ መፍትሄን ማምጣቱ አጠራጣሪ ነው ።

የፖለቲካ ስርአታቸው በማይፈቅድባቸው ሀገራት ውስጥ ፣ ግብርን በመጠቀም ቋሚ የሆነ ሰፊ መሰረት ያለውን የሀብት ክፍፍልን ማድረግ አይቻልም ፤ በአንፃሩ በአንዳንድ ሀገራት ለምሳሌ በስካንድኔቪያ ሀገራት ከፍ ያለ ግብርን በመጣል ተቀራራቢ የኑሮ ደረጃን መፍጠር ችለዋል ። በአንፃሩ በአሜሪካን አገር አንደኛው ፓርቲ ግብር ይጨመር ሲል አንደኛው ይቀነስ ስለሚል አንዱ የጨመረውን ግብር ሌላው ሲመጣ ይሽረዋል ።በዚህ ምክንያት የመካከለኛውና የደሀው ህብረተሰብ ክፍል ገቢ መንግስትም ቢሆን በግብር ያን ያህል ሊያቀራርበው  አይችልም ። ከልክ በላይ ግብርን ልጨመር ቢል ባለሀብቶቹም ግብር ወደ ማይከፈልበት ፣ ግብር አነስተኛ ወደ ሆነበት አካባቢ ስለሚሄዱ፣ እና ሀብታቸውን ስለሚያሸሹ ይህንን ስለሚፈራ ነው ። ስለዚህ ነገሩ በጣም ውስብስብና የፖለቲካ መግባባት እና ስምምነት የሌለበት እንደሆነ መገመት ይቻላል ።

ፖለቲከኞች ተሰብስበው ምን ያህል የግብር ምጣኔ መጣል እንዳለበት ፣ ማን ምን ያህል መክፈል እንዳለበት የሚወስኑት እነሱው ሲሆኑ እንደሚመሩበት ፍልስፍናና ርእዮተ – አለም የተለያየ አቋም ሊኖራቸው ይችላሉ።ባደጉትና በበፀጉት ሀገራት የግብር ጭማሬና ቅናሽ ጉዳይ ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ሲሆን ፣ በፓርቲዎቹም መሀከል ጉልህ ልዩነት እሚንፀባረቅበት ነው ። በእነሱ ምጣኔ – ሀብት 1በመቶ እንኳን ግብር ቢጨምር ወይም ቢቀንስ በምጣኔ – ሀብቱ ከላይ ጉልህ ተፅእኖ ይኖረዋል ። ገና ታዳጊ በሆነ  ሀገር ግን እዛ ደረጃ አልተደረሰም ።

ሌላው ደግሞ አንድ ማህበረሰብ ሀብቱ በጥቂቶች እጅ ተጠቃሎ ሲገባ ፣ እንዲሁም መሀከለኛው መደብ ማህበረተሰብ እየደኀየና ፣ ወቶ ወርዶ ተወዳድሮ አዲስ ሀብትን መፍጠር እያቃተው ሲሄድ፣ የዛ ህብረተሰብ ልሂቃኑ ተጨማሪ ሀብትን ከመፍጠር ይልቅ ያለውን ሀብት ላይ ግመታናአየር ባየር ስራ (Speculation) እንዲሁም በኪራይ ሰብሳቢነት (Rent Seeking) ውስጥ በመሰማራት ፣ ከአዲስ ሀብት ፈጠራ ይልቅ ስለሀብት ክፍፍል ትኩረትን ማድረግ ይጀምራል ። ይሄ አሁን በምእራቡ አለም በመታየት ላይ ያለ ክስተት ሲሆን ፣ በአንፃሩ በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉት (Emerging Markets) በሚባሉት ደግሞ ፈጣን የሆነ የአዲስ ሀብት ፈጠራ ስራ እየተከናወነ ነው ።

የምጣኔ ሀብት አስተዳደር

የምጣኔ ሀብት አስተዳደር ከፖለቲካ አስተዳደር የተለየ ሲሆን ማንኛውም የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረታዊ የሆነውን ህግ ማለትም የአቅርቦትንና የፍላጎትን ህግ መፃረር የሌለበት ሲሆን የሚወጡ አዋጆችና ደንቦችም ከዚህ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም። ለአንድ ሰሞን ተብለው የሚወሰዱ በጥናት ያልተደገፉ ከሆነ ገበያውን በማዛባት ከዚያ በኋላ ወደ ነበረበት ለማስተካከል ረጅም ጊዜን ይፈጃሉ። የምጣኔ – ሀብት አስተዳደር በትእዛዝ የሚመራ ነገር አይደለም ፣ መሰታዊ የሆኑ የምጣኔ – ሀብትበህ ህግጋትን መጠበቅ ነው እንጂ ያለበት ።
በሀገራችን የግብይት ስርአቱ ለረጅም ጊዜ ችግር የነበረበት ሲሆን እየጨመረ ከመጣው ዋጋና ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር በህዝቡ ኑሮ ላይ አሉታዊ ተፅእኖው እየጎላ ስለመጣ የመንግስትን ትኩረት እሚስብበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል ፤ ለዚህ የግብይት ስርአት ችግር በርካታ ምክንያቶች አሉት ። በተለያየ ወቅት በባለሙያዎች የተጠኑ ጥናቶች በርካታ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል ።
ማንኛውም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይሄንን መርሆ የሚጥስ ከሆነ ለረጅም ጊዜ መስራት መቻሉ ያጠራጥራል ። መሰረታዊ የሆኑ የምጣኔ ሀብት ህግጋት በተለይም የአቅርቦትና የፍላጎት ህግ እንደ ተፈጥሮ ህግ ተደርጎ የሚወሰዱ ናቸው ። ለምሳሌ የዋጋ ቁጥጥርን ብንወስድ በረጅም ጊዜ መስራቱ ከጥያቄ ውስጥ እሚገባ ነው እሚሆነው ። እንደ ኢትዮጲያ ባለ የነፃ ገበያ በደንብ ባልተደራጀባት ሀገር ጥቂት ሻጮች ወይም አቅራቢዎች(Monopoly) ብቻ መኖርችግሮችን እንደሚፈጥር የታወቀ ሲሆን ለዚህም ገበያው በነጻ ውድድር ላይ እንዲመሰረትና በርካታ ሻጮችና አቅራቢዎችን ወደ ገበያ ውድድሩ ማምጣት ያስፈልጋል ።
ሌላው የባንክ የወለድ ምጣኔ (Interest Rate) ከዋጋ ግሽበት ምጣኔው ማነስ የሌለበት ሲሆን እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ገንዘብ ባንክ ከመቀመጥ ይልቅ ወጪ አድርጎ የሆነ ነገር መግዛት የተሻለ ስለሚሆን ይበልጥ ዋጋ ግሽበቱን የማባባስ ውጤት ሊኖረው ይኖረዋል ። የዋጋ ግሽበቱ አራት ዋና ዋና መነሾ ይኖሩታል አንዱ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ የሚዘዋወረው የገንዘብ ህትመት ሲጨመር ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ዝውውሩ ፍጥነት (Velocity) ኢኮኖሚው ከሚችለው በላይ ሲጨምር ወይም ፣ በሀገር ውስጥ የሸቀጦች አቅርቦት ሲቀንስ ወይም ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች እንደ ነዳጅ ዘይት የመሳሰሉት አቅርቦታቸው ሲቀንስ እና ዋጋቸው ሲጨምር ነው ።
የኋላ ኋላ ቻይናና ህንድም ለዚህ አሳሳቢ ለሆነ ዋጋ ግሽበት ምላሽ ሰጥተዋል ። ይህንንም ያደረጉት እድገታቸውን በመቀነስ ወይም በማቀዝቀዝ ሲሆን ለምሳሌም እ.ኤአ. በ 2012 የቻይና መሪዎች አመታዊ የምጣኔ – ሀብት እድገታቸውን ወደ 7.5 በመቶ ዝቅ በማድረግ የዋጋ ግሽበቱን ወደ 4 በመቶ ለማውረድ እንደሚሰሩ ሲገልፁ ይህም በሁለት አሀዝ ሲያድግ ለቆየው የቻይና ምጣኔ ሀብት ከስምንት አመታት ወዲህ አነስተኛው የምጣኔ ሀብት እድገት መሆኑ ነው ። በተመሳሳይም ህንድም እንዲሁ እድገቷን ዝቅ በማድረግ የዋጋ ግሽበትን ዝቅ ለማድረግ እንደምትሰራ ገልፃለች ።
ይህም የአለም ምጣኔ – ሀብት ትስስር መኖሩ ምንም እንኳን ብሪክስ የተባሉት ሀገራት አለምን ከምጣኔ – ሀብት ቀውስ ያወጣሉ ቢባልም ፣ ራሳቸውም ቢሆኑ የአለም ኢኮኖሚ አካል እንደመሆናቸው በምእራቡ አለም የተፈጠረ የኢኮኖሚ ቀውስ እነሱንም ውሎ አድሮም ቢሆን እንደማይምር ያሳየ ነው ።
በነገራችን ላይ የነፃ ገበያ ውድድር አለመኖር ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን በፊትም በኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ላይ ቀድሞም ቢሆን በጉልህ ይታይ የነበረ ችግር ነው ። አንዳንዴ ሲታሰብ ሀገራችን ነጋዴዎች የተጋነነ (Excessive) ትርፍን የሚያገኙ ይመስላል ይህን የበዛ ትርፍ በመቀነስሸማቹ እንዳይጎዳ ማድረግ የሚቻለው በገበያ ውስጥ ተጨማሪ የገበያ ውድድር እንዲኖር በማድረግ ብቻ ነው ።
ሌላው ደግሞ የንግድ ልውውጡን ዋጋ (Transaction Cost) እንዲቀነስ በማድረግ ነው ። ይኀውም አንድ ሸቀጥ ከተመረተበት ቦታ ተነስቶ ለተጠቃሚው እስከሚደርስ ድረስ ለግብይት የሚፈጀው ጊዜ ፣ ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ለሸቀጦች ዋጋ መወደድ አንዱ ምክንያት ነው ። ሌላው ለግብይት ዋና መናር ምክንያት ደግሞ በተለይ ከውጪ ለሚገቡ ሸቀጦች በአንድ ጊዜ በብዛት አለመገዛት አንዱ ምክንያት መሆኑ በባለሙያዎች ተደርሶበታል ። ገንዘቡ በኢኮኖሚው ውስጥ እሚሽከረከርበት ፍጥነትም የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ። ፈጣን የገንዘብ መሽከርከር በሌለበት ገንዘብ ቢታተምም ግሽበትን አያመጣም ተብሎ ሊታሰብ ይችላል ።
ሌላው ደግሞ ህገወጥነት ሲሆን በንግድ ስርአቱ ላይ ህገ – ወጥነት በሰፊው የሚታይ ነው ። መጠናቸውን ባልጠበቁ በተሳሳቱ ሚዛኖች መመዘን ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ቀናቸውን ቀይሮ እንደ አዲስ መሸጥ፣ ከጥራታቸው በታች የሆኑ ሸቀጦችን ያለምንም ሀፍረት ወደ ገበያ ማቅረብ፣ለምግብነት እሚቀርቡ ሸቀጦችን ለጤና ጎጂ ከሆኑ ነገሮች ጋር መቀላቀል እና የመሳሰሉትእነኚህ ሁሉ ለአንድ ሰሞን ዘመቻ ይደረግባቸውና ከዚያም ተመልሰው ይረሳሉ ።
ሌላው ደግሞ እሴትን የሚጨምሩ (Value Add) ፋብሪካዎችና ማቀናበሪያዎች በሀገራችን በብዛት አለመኖር ሲሆን የዛ አይነት ተቋማት ቢኖሩ ከሀገር ውስጥ ግብአቶችን ወይንም ከውጪ ጥሬ እቃን በማስገባት በቀላሉ እዚህ እሴትን በመጨመር የመጨረሻ ምርት አድርጎ በማውጣት ከውጪ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን የስራ እድሎችንም መፍጠር ያስችላል ። በኢንዱስትሪ ያደጉት ሀገራት ብዙም በጥሬው እንዳለ እሚልኩት ነገር የለም ማለት ይቻላል ፣ በርካታ ግብርና ምርቶችን አምራቾች ቢሆኑም አብዛኛውን እንዳለ ወደ ውጪ አይልኩትም ፣ ለእርዳታ ከሚልኩት ከስንዴ ፣ ከበቆሎ ከመሳሰለው በስተቀር ፣ የተቀረውን በሙሉ እዛው በሀገራቸው ውስጥ አቀናብረው ፣ እሴት ጨምረው ነው ወደ ውጪ እሚልኩት ።
ቡናን ብንወስድ ከታዳጊ ሀገራት ወስደው በሀገራቸው ማቀናበሪያዎች ነው እሚያቀናብሩት ፣ እንጂ የቀዝቀዝ ያለ የአየር ንብረት ባለቤት የሆኑት ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ሀገራት ቡና አምራቾች አይደሉም ።
እዚህ ላይ ስለ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማንሳት ይቻላል ። የምጣኔ ሀብት አቅማቸው በግብርና፣ በማእድን ወይንም በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሀገሮች የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው የሚሆነው ወይንም ከፍተኛም ቢሆን እንኳን የነዳጅ ላኪ ሀገራት እንደሆኑት ቀጣይነቱ ያጠራጥራል ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሰፊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሚዛኑን የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ ፣አንዱ ዘርፍ ላይ የሚደርስ ኪሳራ ወይም በአለም ገበያ የዋጋ መዋዠቅ ቢያጋጥም የዛ ሀገር ገቢ ክፉኛ ይጎዳል ፣ ለምሳሌ ነዳጅ ላኪ የሆኑ በርካታ ሀገራት ዋናው ገቢያቸው ከነዳጅ ከመሆኑና ነዳጅ ዘይት ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆናቸው ፣ ባጀታቸውን በነዳጅ ዋጋ ላይ ተመስርተው እንደሚመድቡ ይታወቃል። በሌሎች ዘርፎች ላይ ምጣኔ – ሀብታቸውን እያሰባጠሩ ካልሄዱ እነሱም ቢሆኑ ውለው አድረው ነዳጅ በሌላ የሀይል ምንጭ ሊሰጥ በሚችል ነገር ቢተካና ዋጋው ቢወድቅ ወይም ያላቸው የነዳጅ ሀብት ጨርሶ ተሟጦ ቢያልቅ አማራጭ የገቢ ምንጮች ከሌሏቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት እድል ሊፈጠር ይችላል ። ብዙዎቹ ደሀ ሀገሮች የምግብ ፍላጎታቸውን ከውጪ ነው የሚያስገቡት ።
የኢንዱስትሪ እሴት የመጨመር አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ የተቀረው አለም ከሚያደርገው እሴት ጭማሪ እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የአፍሪካ ሀገራት ጭማሬ 1% ብቻ መሆኑ ነው ። በምጣኔ ሀብት አስተዳደር ውስጥ በመሬቱ ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታና ሁነት እንደሌለ አድርጎ መውሰድ ጎጂ ነው ።
አንድ ፖሊሲ እማይሰራ ከሆነና አለመስራቱ በግልፅ የሚታይ ከሆነ ይሰራል ብሎ በዛ ነገር መግፋት ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አያመጣም ። ዋጋዎችን ብንወስድ ትልቁ ማበረታቻ ዋጋ ሲሆን የዋጋ ማበረታቻን የማያቀርብ ፖሊሲ ግን ውጤትን አያመጣም ። ለምሳሌ የቀድሞው የእርሻ ሰብል ድርጅት ከገበያ ዋጋ ባነሰ አነስተኛ ዋጋ ከገበሬው ወስዶ በርካሽ ዋጋ ለከተማ ነዋሪ ይሸጥ ስነበረ የእየቆየ ሲሄድ የአርሶ አደሩን ለማምረት የሚያነሳሳውን ማበረታቻ አጠፋው ፣በዚህ ብቻ ሳይገታ በአርሶ አደሩ ለመንግስት የነበረውን ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዲቀንስም አድርጓል ። በእርግጥ ይህ ፖሊሲ ለከተማ ነዋሪው የምግብ ሰብል በርካሽ እንዲያገኝ አስችሏል ቢባልም ፤ ከሀገሪቱ ህዝብ አብዛኛው በሆነው እስከ 80 በመቶ ይደርስ ከነበረው ከአርሶ አደሩ ዘንድ ግን ድጋፍን እንዲያጣ ካደረጉት የፖሊሲ ግድፈቶች እንደ ዋናው ተደርጎ በበርካታ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የተገለፀ ነው ።
ራሳቸው ትልቅ አቅም ያላቸው ምእራባውያን ሳይቀሩ የማይሆነውን ነገር ይሆናል ብለው ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን አያባክኑም ። የሚሰራውንና ሊሆን የሚችለውን ብቻ ነው እሚከተሉትም ስራ ላይ እሚያውሉትም ።
ሌላው ፖሊሲ አውጪዎችን ሊፈታተን የሚችለው ነገር ገንዘብ ማተም ሲሆን ገንዘብ ማተም በምጣኔ – ሀብት ላይ በቀላሉ የማይስተካከል የዋጋ ግሽበትን ይፈጥራል ። በተለይም አብዛኛው ግብይቱ በገንዘብ ላይ የተመሰረተ (Monitised) አይደለም ፣ መደበኛ ያልሆነ የምጣኔ – ሀብቱ ዘርፍ ሰፊ ነውተብሎ በሚገመት ምጣኔ – ሀብት ውስጥ ገንዘብ ቢታተም ያን ያህል የዋጋ ግሽበትን አይፈጥርም ተብሎ ስለሚታሰብ ፖሊሲ አውጪዎች ገንዘብ ማተም ያን ያህል የገንዘብ ግሽበትን አያስከትልም ሊሉ ይችላሉ። ይሁን ውጤቱ ያልተጠበቀ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።
አንድ ሀገር እድገቷን ለማፋጠን የገንዘብ ምንጭን በምታስብበት ወቅት ሌላው የሚመጣው አማራጭ ብድር መበደር ነው ። ሀብታሞቹ ሀገራትም ጭምር ሳይቀሩ ብድርን የሚበደሩ ሲሆን የትኛውም ሀገር ብድር የሚበደር በመሆኑ አስገራሚ አይሆንም ፣ ነገር ግን ይኀው ከፍተኛ ብድር ውስጥ መዘፈቅ ከተከተለ ደግሞ ፣ ለአንድ ሀገር ለመወጣት አስቸጋሪ የሆነ የእዳ ማጥ ውስጥ መዘፈቅን ያስከትላል ። ይኀውም ለሀብታሞቹ ሀገገራትም ጭምር የብድር መብዛት ለመውጣት የሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ሲዘፍቅ በተደጋጋሚ ታይቷል ።
በተለይም የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው ሀገራት ፈጣን እድገትን ለማስመዝገብ ከሚሰማቸው ጉጉት የተነሳ በአንድ በኩል የዋጋ ንረት ውስጥ መዘፈቅ ወይንም በእዳ ውስጥ የመዘፈቅ አደጋ ውሰጥ ሊገቡ ይችላሉ ። በአፍሪካ እንደ አንደ አንጎላ ያሉት ሀገራት በአንድ አመት እስከ 35በመቶ የምጣኔ – ሀብት እድገትን በአንድ አመት ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን ፣ የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው ሀገራት ግን ለፈጣን እድገት የሚያስፈልገውን የገንዘብ ምንጭ ለማፈላለግ ብድርን አንዱ አማራጭ አድርገው ሊወስዱት ሲወስዱት ይታያሉ ።
በምእራቡ አለም አንድ ምጣኔ – ሀብት ውስጥ ምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት ማእከላዊ ባንኮች ገንዘብ ሊያትሙ ፣ ወይም ተጨማሪ ገንዘብን በተለያየ መንገድ ወደ ምጣኔ – ሀብቱ ሊለቁ ይችላሉ ፣ ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (Monetery Easing) በመባል የሚታወቀው ሲሆን ። ይሁን እንጂ ልክ ምጣኔ ሀብቱ መነቃቃት ሲጀምር በተፈጠረው የፍላጎት ማደግ ምክንያት ከዛ ገንዘቡ ተመልሶ መሰብሰብ (Contract) አለበት ። ያን ለማድረግም የሚያስችል ጠንካራ የገንዘብ ፣የአክስዮን፣ እና የካፒታል ገበያዎች (Capital Market) በአጠቃላይ የዳበረ የካፒታሊስት የገበያ ስርአት ስላላቸው በተወሰነ ደረጃ ማስተካከል ቢችሉም ፣ ለነሱም ቢሆን ግን ገንዘብ ማተም የሚያስከትለው ችግር ማስከተሉ አይቀሬ ነው ።
በነገራችን ላይ የኬነዢያን ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች (Kenysian Economists) ምጣኔ ሀብቱ ችግር ውስጥ በሚገባበት ወቅት የመንግስትን ወጪ መጨመርን ወይም በተወሰነ መልኩ ገንዘብ ማተምን ያበረታታሉ ። በእርግጥ መጀመሪያ አካከባቢ አንድ ገንዘብ ሲታተም ፍላጎትን ያነቃቃል ይሁን እንጂ የታተመውን ገንዘብ የሚያክል ምርትና አገልግሎት በኢኮኖሚው ውስጥ አለመኖሩ ጉልህ ሆኖ መታየት ሲጀምር ግን የዋጋ ወይንም የገንዘብ ግሽበት መታየት ይጀምራል ። ስለዚህ የዋጋ ወይንም የገንዘብ ግሽበት መታየት ይጀምራል ። ስለዚህ ወዲያው ወደ ኢኮኖሚው የተለቀቀው ገንዘብ ተመልሶ መሰብሰብ አለበት ። ግን ይሄም ፖሊሲ እሚሰራው የዳበረ የነፃ ገበያ ስርአት ወይም የካፒታሊስት ስርአት ሲኖር ሲሆን የወድ ምጣኔው ፣ የብድር አቅርቦቱና የአክስዮንና የካፒታል ገበያ የመሳሰሉትም ለዚህ ምላሽን የሚሰጡ መሆን አለባቸው ።
በኋላ ላይ የተነሱት የኬነስ ተከታዮች በኋላ የተነሱት ሞኒተርስቶች (Moniteristts) የተባሉት (Neo – Classical) የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማሳየት እንደቻሉት ደግሞ (Inflation is a Monetary Phenomenon) የገንዘብ ማተም ክስተት ከመሆኑን ማስረዳት ችለዋል ። ስለዚህ የኬኒዢያኖቹ ሀሳብ በምእራቡ አለም አገራት በ1970ዎቹ የገንዘብ ግሽበትን ማስከተል ሲጀምር ደግሞ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው መርጨትን ማቆም ጀምረዋል ። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ ሊስተካከል የማይችልና ከቁጥጥር ውጪ የወጣ የዋጋ ግሸበት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በምጣኔ – ሀብቱ ላይ ያለውን አመኔታ ይሸረሽራል ፣ ብሎም ኢንቨስትመንትን በማዳከም ወደ አጠቃላይ ምጣኔ – ሀብታዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ያመራል ። ስራ አጥነትን ለመቀነስ ሲሉ መንግስታት ተጨማሪ ገንዘብን ወደ ምጣኔ – ሀብቱ ስለሚለቁ የዋጋ ግሽበትን ይፈጥራል ፣ ስለዚህ የዋጋ ግሽበት በፖሊሲ አቅጣጫ መሳት እሚፈጠር ነገር ነው እንጂ እንደ ስራ አጥነት በራሱ እሚፈጠር አይደለም ። የገንዘብ ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት ያንን እንዲሁለማስተካከል በሚወሰዱ እርምጃዎች የዋጋ ግሽበትን ይፈጥራል ።
የተረጋጋ የዋጋ ምጣኔ (ስቴብል ኢንፍሌሸን) የተሻለ ነው ። በሀምሌ 2012 በወጡ መረጃዎች መሰረት ቻይና የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን ፣ በአንፃሩ ግን የአውሮፓውያን በእዳ ሰበብ ምንክንያት ኢኮኖሚያቸው ችግር ውስጥ መግባት የወጪ ንግዷን በመጎተቱ የዋጋ ባለበት መቆም ብሎም መቀነስ (ዲፍሌሸሽን) በቻይና መከሰት ጀምሯል ። የዋጋ ግሽበቷም በ2.5 በመቶ ደረጃ ማውረድ ችላለች ። በተለይም የምግብ ዋጋ መቀነሱ ጥሩ ዜና ቢሆንም በአንፃሩ ግን አጠቃላይ ምጣኔ – ሀብተ ግን ወደ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቷል ። ከ2008 በኋላ የተደረገውም ለቀቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲም በቀጥታ ገንዘብ አትሞ በምጣኔ – ሀብቱ ውስጥ መልቀቅ የዋጋ ንረትን እንደሚያመጣ ግን አጠራጣሪ አይደለም ።

ወደብና የምጣኔ ሀብት እድገት

አንዱ ምጣኔ ሀብት እድገት አስፈላጊ ሆኖ የሚጠቀስ ነገር የባህር በር ወይም ወደብ መኖር ነው ። ነገር ግን የባህር በር ሳይኖሯቸው እጅግ ሀብታም የሆኑ ሀገራት አሉ ። ለምሳሌ ከአውሮፓ ስዊዘርላንድንና ኦስትርያን ብንወስድ የባህር በር ባይኖራቸውም በአለም ላይ ካሉ እጅግ ሀብታም ሀገራት የሚመደቡ ሲሆን፣ የህዝባቸው የኑሮ ደረጃም በአለም ላይ ካሉት በግንባር ቀደምትነት እሚጠቀስ ነው ። በጣም ትናንሽ የሆኑትን የአውሮፓ ሀገራትን ላግዘምበርግን ብንወስድ እንደዛው የባህር በር የሌላትና በጣም ትንሽ ሀገር ብትሆንም ሀብታምና ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላት ስትሆን ፣ከራሷ አልፋም ለአሜሪካ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ብድር ማበደር የቻለች ሀገር ነች ።

ስዊዘርላንድ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ የዲፕሎማቲክ ማእከል ከመሆኗም በተጨማሪ ፣ የበርካታ ኤግዚቢሽኖች የመኪኖች ትርኢትን ጨምሮ ፣ ስብሰባዎች የሚካሄድባት ፣ እንዲሁም በአውሮፓ ካሉ ዋና የቱሪስት መናሪያም ጭምር ነች ።

በአለም ላይ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው ከተሞች በርካቶቹ የወደብ ከተሞች መሆናቸው ይታወቃል ። ለምሳሌ ኒውዮርክ፣ ሆንግ ኮንግ ፣ ሻንግሀይ ፣ የመሳሰሉት ነገር ግን ሁሉም ደግሞ የወደብ ከተሞችም አይደሉም ። ለምሳሌ የጀርመን ብሎም የአውሮፓ የገንዘብ ዘርፍ ማእከል የሆነችውን ፍራንክፈርትን ብንወስድ የወደብ ከተማ አይደለችም ፣ ከዚህም በላይ በአለም ላይ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ አላቸው በሚል በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት የኦስትሪያዋ ቪየናና ፣ የስዊዘርላንዷ ዙሪክ ከፍተኛ ለኑሮ አመቺ ናቸው በሚል የሚጠቀሱ ሲሆን እነኚህም የወደብ ከተሞች አይደሉም ።

የወደብ ጉዳይ አንዱ የአንድን ሀገር ምጣኔ – ሀብት ለመረዳት ጠቃሚ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነው ። ወደብ አለመኖርም ብቻ ሳይሆን ሀገራቱ ቅርባቸው ከሆነው ወደብ ያላቸው ርቀት ፣ የባለወደብ የሆኑት ጎረቤቶቻቸው የሆኑት ሀገራት የመሰረተ ልማት አገልግሎት፣ መንገዶች ፣ መኖር ሲሆን ወደብ የሌላቸው በየብስ የተከበቡ (Land Locked) ሀገራት ለምጣኔ ሀብታቸው አወቃቀር ለራሳቸው ይበልጥ ተስማሚ ከመሆን ይልቅ ለጎረቤት ሀገራት በሚስማማ መልኩ የመቀረፅ እድሉም ሰፊ ነው ። ይህም ያቺ ሀገር ለራሷ የሚያዋጣትን ነገር ከማምረት ይልቅ ለጎረቤት ሀገሮች ይበልጥ አዋጪ በሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እንድትገባም ያደርጋታል ፣ ለምሳሌ ከወደብ በጣም ሩቅ የሆነች ሀገር ካዛኪስታን ስትሆን ከ3000 ሺ . ኪ. ሜትሮች በላይ ትርቃለች ።

በተለይም ሀገራቱ ሰፋ ያለ መሬትና የራሳቸው የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው ከሆኑም ችግራቸው የባሰ ነው የሚሆነው ። የቆዳ ስፋታቸው በጣም ጠባብ የሆኑ ሀገራትም ቢሆኑ እንዲሁ ወደብ ከሌላቸው ፣ ነገር ግን ሰፋ ያለ መሬት ካላቸው ሀገራት የባሰ የሀብት ውሱንነት ሊያጋጥማቸው ይችላል ። በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚገኙ ትናንሽ ደሴቶችም ለኑሯቸው ፣ ግብር የሌለባቸው ወይም የማይከፈልባቸው የፋይናንስ ዘርፎችን በመስጠትና በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ነው ምጣኔ – ሀብታቸው ። 

ወደ አፍሪካም ስንመጣ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የባህር በር ስለሌላቸውብቻ ደሀ ሆነው እንደማይቀሩ መገመት አያዳግትም ። ለምሳሌ ቦትስዋናን ብንወስድ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲህ በመልካም ሁኔታ እየተዳደረችና እያደገች የሄደች ሀገር ስትሆን፣እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራትመፈንቅለ መንግስታትን ፣ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን ያስተናገደች ሀገር አይደለችም ። ዋና ገቢዋ በአልማዝ ፣ በቱሪዝምና በስጋ ላይ የተመሰረተውይህቺው ሀገርትክክለኛ የእድገት መስመርን የተከተለች ነች ። ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያጋጠማቸው የእርስ በእርስ ጦርነትና ፣ መፈንቅለ መንግስታት ስላላጋጠማት እና በሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና በዲሞክራሲ ጎዳና በመጓዟ በተሻለ የእድገት ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ዙምባብዌንም ብንስድ እርሷም ወደብ የሌላት ሲሆን ፣ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ በወጣችበት ወቅት በግብርና ፣ በማምረት ጥሩ ደረጃ ላይ ከነበሩ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት የምትመደብ ሀገር ነበረች ፤ በእርግጥ በኋላ ላይ በሙጋቤ አመራር ኢኮኖሚዋ እያሽቆቆለና በአለም ከፍተኛውን የስራ አጥ ቁጥርና ፣ ከፍተኛ የተባለ የዋጋ ንረት የተመዘገበባት ሀገር ለመሆን ብትበቃም ።

አፍሪካዊቷ ኡጋንዳን ከወደብ ራቅ ያለች ሀገር ነች ፣ በዚህች ሀገር አንድ እቃ ከወደብ ተነስቶው እስከሚደርስ ድረስ 53 ቀናት ይፈጃል ። ሀገራችን ምንም እንኳን ወደብ ባይኖራትም ፣ እንደ እድል ሆኖ ግን ከወደብ ግን የራቀች ሀገር ግን አይደለችም ። ይህ ብቻ ሳይሆን ባለወደብ የሆኑትም ጎረቤቶቿ ምጣኔ ሀብታቸው ያነሱ ሀገራት ስለሆኑ ኢትዮጲያ በእነሱ ላይ ጥገኛ ከሚሆኑ ይልቅ እነሱ ይበልጥ በኢኮኖሚ ጥገኛ ይሆናሉ ። በተጨማሪም በአለም ከፍተኛው የንግድ ዝውውር ከሚካሄድበት ከቀይ ባህር የንግድ መስመርና ከዋናው ከነዳጅ ዘይት ምንጭ ማለትም ከመካከለኛው ምስራቅ የራቀች ባለመሆኗእንደ አንድ የተሻለ እድል ተደርጎ ሊቆጠርላት ይችላል ።

በእርግጥ የወደብ መኖር ለንግድ እንቅስቃሴ አስፈላጊ መሆኑ አሌ አይባልም ። ወደብ ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ዘርፍ በመሆኑ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሲሆን ፣ ለወደብ ኪራይ ይከፍሉት የነበረውን ገንዘብ ከማዳናቸውም በላይ ለጎረቤቶቻቸውም የወደብ አገልግሎትን በመስጠት ከፍተኛ የገቢ ምንጫቸው ሊሆን ይችላል ። ያደጉትን ሀገራት ራሱ ብንወስድ በየእለቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበት ዘርፍ ይኀው ከወደቦቻቸው የሚያገኙት ገቢ ዘርፍ ነው ። ቢያንስ አሁን ያለው ትውልድ እንኳን በትክክል ባይጠቀምበት እንኳን መጪው ትውልድ በአግባቡ ሊጠቀምበት ስለሚችል የወደብ ባለቤት የሆኑ ሀገራት ሰፊ የምጣኔ – ሀብትና የስታራቴጂ ጥቅም እንደሚኖራቸው መገመት አያዳግትም ።

የባህር ባህርን እና ክፍት የመርከቦች መተላለፊያን ለማግኘት በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ለንግድ እንቅስቃሴ ቁልፍ ከሆኑ ስልታዊ መሰረተ – ልማት አውታሮች አንዱ ነው። ይህንን በመረዳት እንግሊዞችና ፈረንሳዮች የስዊዝ ካናልን በማስቆፈር ቀይ ባህርን ሜዲተራኒያን ባህርን ሲያገናኙ በአለም  ላይ በጣም ስራ የሚበዛበትንና ቁልፍ የሆነ የንግድ መስመርን መፍጠር ችለዋል ፤ እንዲሁም አሜሪካኖች  የፓናማ ቦይን በመቆፈር እንዱሁ ደቡባዊ አሜሪካንና ሰሜናዊ አሜሪካን አጭር በሆነ የመርከብ መስመር ለማገናኘት ችለዋል ፣ ሚጠይቀው መዋእለ ንዋይ ከፍተኛነት ካላገደ በስተቀር ። በአፍሪካ ቀንድም በዚህ አይነት መንገድ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮችን በቦይ በመቆፈር የወደብ ችግርን ማቃለል ይቻላል ።

ነገር ግን አፍሪካ ውስጥ እንደሌላው ዘርፍ ሁሉ የወደብ አገልግሎቱም በሚገባ ያላደገና ባለወደብ የሆኑ ሀገራትም ያላቸውን እምቅ አቅም በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም ማለት ይቻላል ። ለምሳሌ የኬንያው ሞምባሳ ወደብ ለማስተናገድ አንድ አመት የሚፈጅበትን የሲንጋፖር ወደብ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ማንቀሳቀስ ይችላል ። ይህም በአፍሪካ ዘርፉ ገና እንዳላደገና ገና ብዙ ማደግ እንዳለበት ያመለክታል ። 

ስልጣኔ የትና መቼ ተጀመረ ?

ስልጣኔ የት ተጀመረ የሚለው ጥያቄ አወዛጋቢ ነው ። አውሮፓውያን የስልጣኔ መጀመሪያ እነሱ እንደሆኑ በተደጋጋሚ በበርካታ ፅሁፎቻቸውንና ፣ ጥናታዊ ፅሁፎችን አውጥተዋል ። ለምሳሌ ከ40 ሺ አመት በፊት የሆሞሳፒያንስ የተባለው ሰው አውሮፓ ከደረሰ በኋላ ስልጣኔ አቆጠቆጠ የሚል አስተሳሰብ ለረጅም ገዜ ትክክለኛ ነው ተብሎ ሲታመንበት ቆይቷል ። የሰው ልጅ ማሰብ የጀመረው መቼ ነው የሚለው ፣ በተዘዋዋሪ መንገድ ስልጣኔ መቼና የት ጀመረ ብሎ እንደመጠየቅ ሲሆን ቀደም ባሉ የአውሮፓውያን ጥናቶች መሰረት የሰው ልጅ ማሰብ የጀመረበትና ፣ ልሳንን ወይም ቋንቋን የጀመረው ወደ አውሮፓ ከዘለቀ በኋላ ነው የሚል እምነት የነበረ ሲሆን ለዚህም የነበረው ማስረጃ አውሮፓ በዋሻ ውስጥ በተገኙ ጥንታዊ ስእሎች ሲሆኑ በቅርቡ የተገኙት ግንቀደምቱ የሰው ዘር ወደ አውሮፓ ከመዝለቁም በፊት በአፍሪካ እያለ ቋንቋ እንደነበረውና ልሳኑንም ይጠቀም እንደነበረ ታውቋል ። እነኚህም እስከ 77 ሺ አመት በፊት በአፍሪካ የነበረው ጥንታዊ ሰው በርካታ የእጅ መሳሪያዎች እንደበሩት ፣ ልሳን ወይም ቋንቋ እንደነበረው ማረጋገጥ ተችሏል ።

ቀደምቱ ሰው ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ከመዝለቁ በፊት ኒያንደርታል የሚባለው ከሰው ልጅ ጋር በጣም ተቀራራቢ የሆነ ዝርያ በአውሮፓ ይኖር የነበረ ሲሆን ።ይህም ዝርያ ጥንታዊው ሰው ከአፍሪካተነስቶ አውሮፓ እንደደረሰ ብዙም ስቆይ ዝርያው ከምድረ ገፅ ጠፍቷል ። ቀድሞ በነበረው አስተሳሰብ ይሄ ዝርያ ከሆሞ ሳፒያንስ ጋር መወዳደር ስላቃተው ከእነኚህ የሰው ዘሮች ጋር ባደረገው ጦርነት ነው የጠፋው የሚል የነበረ ሲሆን ፣ ከሆሞ ሳፒያንስ ጋር በተደረገውም ጦርነት ሆሞ ሳፒያንስ በድንጋይ ናዳ ነው ያጠፋው የሚሉ መላ ምቶችም ተሰንዝረዋል ። በጣም ኋላ ቀር ስለነበረ ፣ የአእምሮው እድገት አነስተኛ የነበረ በመሆኑ ነው የሚል ነው ።

ሌሎች የስነ – ምድር የቁፋሮ መረጃዎችም እንዳመለከቱት እንዲሁ በእንግሊዝ ሀገር ከ45 ሺ አመት በፊት ኒያንደርታሎችና ሆሞ ሳፒያኖች ጎን ለጎን አብረው ይኖሩ እንደነበረ ኒያንደርታል ዝርያ ይኖርባቸው በነበሩ ዋሻዎች ውስጥ ከተገኙ የእጅ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች አመልክተዋል ። 

ይህም ጥናት ኒያንደርታል ዝርያ (Neandertal) ቋንቋ ወይም ልሳን እንዳልነበረውና ፣ የእጅ መሳሪያዎችንም እንደማይጠቀም ነው ፣ ከዚያ በኋላ በተደረጉ ጥናቶች ይህም ዝርያ የራሱ የሆኑ የእጅ መሳሪያዎች እንደነበሩትና ልሳንም እንደነበረው ለመናገር የሚያስችለው የጉሮሮ አጥንቶች እንደነበሩት እስራኤል ውስጥ በተደረገ ምርምር መረጋገጥ ተችሏል ።

ስለዚህ ያን ያህል ይታሰብ እንደነበረው ከሆሞ ሳፒያንስ ያን ያህል ኋላ ቀር እንዳልነበረና የጠፋትም ምክንያት ወይ ሆሞ ሳፒያንስ (Homo Spians) አውሮፓ ከደረሰ በኋላ በተላላፊ በሽታ ወይም ባልተጠበቀ ክስተት ሊሆን እንደሚችልና ዝርያው ቢቀጥል ኖሮ በዘመናዊው አለም እንዴት አሁን ካለው የሰው ዘር እንዴት አብሮ ሊቀጥል ይችል እንደነበረ እንቆቅልሽ ነው አሁን ላይ ቆሞ መገመት ይቻላል ።

      ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ማሰብ የጀመረው መቼ ነው የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ ፣ የሰው ልጅ መቼ ማሰብ እንደጀመረ ማወቅ ከተቻለ ሰልጣኔም መቼና የት እንደተጀመረ ማወቅ ይቻላል ። በአውሮፓውያን በቀድሞው አስተሳሰብ መሰረት ስልጣኔ የተጀመረው አውሮፓ ውስጥ ነው የሚል ነው ። ይህም የሰው ልጅ አፍሪካን ትቶ ከወጣ በኋላ አውሮፓ ውስጥ ነው ማሰብ የጀመረው፣ ልሳንንም የፈጠረው እዛ ነው የሚል ነው ። እንደዛ ቢሆን ኖሮ ቀደምትና ጥንታዊ የሆኑ ስልጣኔዎች አውሮፓ ውስጥ መገኘት ነበረባቸው ። ነገር ግን በአለም ላይ በጣም ቀደምት የሆኑት ስልጣኔዎች ማለትም የግብፅ ፒራሚዶች ፣ የአክሱም ስልጣኔ ፣ የሜሶፔታሚያና የባቢሎን እንዲሁም የቻይናና የህንድ ሰልጣኔዎች የአውሮፓውያንን ስልጣኔ መጀመሪያ ተብሎ የሚወሰደውን ግሪክን ስልጣኔ በሺዎች በሚቆጠሩ አመታት ይቀድሙታል ።

ስለዚህ ይህ የተገኘው የዝግመተ – ለውጥ (Evolution) ግኝት ስልጣኔ ከኛ ነው የጀመረውን የሚለውን ቀደምቱን የምእራባውያንን አስተሳሰብ ይቃረነዋል ።ይህም ራሳቸው ባደረጓቸው ተደጋጋሚ ጥናቶች እየተረዱ የመጡት ሀቅ ሆኗል ። ይሁን እንጂ አውሮፓውያን በበርካታ ነገሮች ያላቸው ጠንካራ ዲሲፕሊን ፣ በስራም ይሁን በየትኛውም በሚይዙት ነገር ፣ እንዲሁም ጠንካራና ታታሪ ሰራተኝነታቸው ፣ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሳይንስ ፣ በቴክኖሎጂ ያለማቋረጥ ሲመራምሩ በርካታ ውጤቶችን አግኝተው ነው እዚህ የደረሱት ።

ሌላው ደግሞ አውሮፓውያንን ሀያልነት እድልም ረድቷቸዋል፣ ሊባል የሚችለው ነገር የአሜሪካ አህጉር በኮሎምቦስ አማካኝነት መገኘቱ ነው ።አዳም ስሚዝ ይህንን ነገር  ገልፆታል ። ከአሜሪካ አህጉር መገኘት በፊት የአለም የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድ የነበረው በአውሮፓ ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በቻይናና፣ በህንድ አማካይነት የነበረ ሲሆን ቬኒስ የተባለች የጣሊያን ከተማም ይህ ንግድ ይንቀሳቀስባት የነበረች ከተማ ነበረች። ነገር ግን የአሜሪካን አህጉር ከተገኘች በኋላ ግን የንግድ እንቅስቃሴው በዋናው የአውሮፓ አህጉርና ፣በእንግሊዝ ፣ በአሜሪካና በጃፓን መሀከል በሚሆንበት ወቅት ግን እነኚህ የምስራቅ ከተሞችና ሀገራት መቀዝቀዝና መዳከም ታይቶባቸዋል ። በነገራችን ላይ አዳም ስሚዝ ይህንን ጉዳይ የሀገሮች ሀብት በተሰኘ መፅሀፉ ላይ የጠቀሰው ጉዳይ ነው ።

አሜሪካ ባላት ሰፊ  መሬት የእርሻ ምርቶችን በባሪያ ጉልበት አማካይነት ስታመርት ፣ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አውሮፓውያን ደግሞ ከአሜሪካ አህጉር በሚመጣው የግብርና ምርት ፣ እንደ ጥጥ ፣ የሸንኮራ አገዳ በመሳሰሉት የአውሮፓ ኢንዱስትሪዎችን ጥሬ እቃ ፍላጎታቸውን ያሟሉ ነበር ።በታሪክ ባለሶስትዮሽ ንግድ እሚባለው ፣ ማለትም የአፍሪካ ባሪያ ጉልበት ወደ አሜሪካ ሄዶ በትላልቅ ሁዳዶች ገንዘብ የሚያመጡ (Cash Crops) ተመርተው ወደ አውሮፓ ኢንዱስተሪዎች ተልከውየግብርናን ስራ ሰርቶ ያም አውሮፓ ሄዶ ሲሸጥ ፣ ከአውሮፓም እንዲሁ የኢንዱስትሪ ምርቶች ተመልሰው ወደ አሜሪካ ለገበያ የሚቀርቡበት የንግድ ግንኙነት ነው።

ያን ግዜ አሜሪካ ገና በኢንዱስትሪ አልበለፀገችም የነበረ ሲሆን የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የነበሩት ምእራብ አውሮፓውያን ነበሩ።በአሜሪካ ውስጥ በዛን ጊዜ ሁለት ስርአት መኖሩ ማለትም ደቡቡ የባርያ አሳዳሪ መሆኑ ፣ ሰሜኑ ደግሞ በኢንዱስትሪ እያደገ መሆኑ የኋላ ኋላ የማይታረቅ ችግርን መፍጠሩ አልቀረም ። ይሁን እንጂ የሰሜኑ ባለኢንዱስትሪዎች በደቡቡ የነበረውን ርካሽ ጉልበት ለመጠቀም ያስችላቸው ዘንድ ከአሜሪካ የባርያ አሳዳሪው ስርአት መወገድ እንዳለበት ከኢኮኖሚም ከፖለቲካም አንፃር አስልተውታል ።አሜሪካ በፍጥነት ያደገችው በደቡባዊ ክፍሏ የነበረውን የባርያ አሳዳሪ ስርአት በአብረሀም ሊንክን መሪነት ካስወገደች በኋላ ሰሜናዊው አሜሪካ በተለይም በኢንዱስትሪ በፍጥነት በማደጉን ተከትሎ ነው ፣የአንደኛው የአለም ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት ከአለም ቀዳሚ ሀብታሟ ሀገር ለመሆን በቅታለች ።

በእርግጥ ከማንኛውም ሀብት በስተጀርባ አንድ ወንጀል አለ የሚባለው አባባል አንዳንዴ ሳይሰራ አይቀርም ።አውሮፓውያን በባሪያ ንግድ ፣ ከዚያም በቅኝ ግዛት ፣ በቅኝ ግዛትነት የያዟቸውን ሀገራት ህዝቦች ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት በመበዝበዝ ፣ በኢንዱስተሪ ላመረቷቸው ምርቶች ያለተቀናቃኝ ብቸኛ መሸጫ ገበያቸው በማድረግ ከአለም ዙሪያ እጅግ ብዙ ሀብት አጋብሰዋል ። ለምሳሌ ህንድን የራሳቸውን እቃ ማራገፊያ በማድረግ ፣ ግብፅንና ህንድን የኢንዱስትሪ እድገታቸውን በማቀጨጭ ፣ ግብፅን ለእንግሊዝ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ አቅራቢ ለማድረግ ለራሷ ስትል የመስኖ እርሻን አስፋፍታ ቆይታለች።በእርግጥ በወንጀል የተገኘ ሀብት ውሎ አድሮ ወደ ዋናው ባለቤቶቹ መመለሱ አይቀርም ፣ የማይቀር ሲሆን ትክክለኛው መንገድ ግን ዘላቂ ሀብት ሆናል ።

ነገር  ግን አሁን በቅርቡ በተለይም የህንድና የቻይና መልሶ ማንሰራራት በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲሁም በጃፓንምጭምርተይዞ የቆየው የኢኮኖሚ የበላይነት ዳግም በእነኚህ ሀገራት ተመልሶ መያዝ ጀምሯል ።

ቀደምባለው ዘመን የነበሩ የኢትዮጲያ ምሁራን ኢትዮጲያ የጃፓንን ምሳሌ በመከተል ልታድግ ትችላለች የሚል ሀሳብ አቅርበው የነበረ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለውን መመሳሰል በተለይም ሁለቱም የራሳቸውን ባህል መጠበቃቸውን፣ በቅኝ ግዛት አለመገዛታቸውንና ፣ ሁለቱም የዘውዳዊ ስርአትን የሚከተሉ መሆናቸውን መሰረት በማድረግ ነበረ ። ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገራት ከላይ ሲታይ ተመሳሳይ ቢመስሉም መሰረታዊ የሆነ ግን ልዩነቶች ነበሯቸው ። ለምሳሌ በጃፓን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የጃፓን ንጉስ በፖለቲካው ውስጥ ያለው ቦታ እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ምንም አይነት የፖለቲካ ተፅእኖ ያልነበረው ሲሆን ፣ፖለቲካውንም ይመራ የነበረው በህዝብ በተመረጡ ፖለቲከኞች ነበረ ። ይህ በኢትዮጲያ ከነበረው ፊውዳላዊና ፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ በአያሌው የተለየ ነው ።ከዚህም ሌላ የጃፓን መንግስት ኢንዱስትሪዎችን ይደጉምና ያበረታታ የነበረ ሲሆን ከምርምር ጀምሮ ኢንዱስትሪዎች እንዲበረታቱ ያልተቋረጠ ጥረትን በማድረጉ መጨረሻ ላይ ጃፓን በኢንዱትሪ ራሷን የቻለች ሀገር ልትሆን በቅታለች ፣ ይህም በኢትዮጲያ ከነበረው የጭሰኛ ስርአት በእጅጉ የተለየ ነው በታሪክ እንደሚታወቀው ሁሉ የጃፓን ባለመሬቶች ቀደም ብለው መሬታቸውን ለህዝቡ እንዳከፋፈሉም ይታወቃል ። ይህ ብቻም ሳይሆን መመሳሰሎች እንዳሉ ሆነው የጎሉ ልዩነቶች ግን ነበሩ ፣ ስለዚህ የጃፓን ተምሳሌትነት (Role Model) ብዙም ሊሰራ አልቻለም ።

 

ፍቅርና ፍርሀት

ብዙ ሰዎች ከአለም ጋር ትስስር በመፍጠር ስቃይንም ይቀበላሉ ። በተለይም አንድ ሰው በእውቀት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ከነገሮች ጋር ያለው ትስስር እየጨመረ ይሄዳል ። የማያውቅ ወይም ብዙም በእውቀት ያልዳበረ ሰው እንደውም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አስተሳሰብ ሊኖረው ይችላል ።ህይወት ከእውቀት ይልቅ በጥበብ የምትኖር ስትሆን ፣ ብዙዎች ለእውቀት ነው እንጂ ለጥበብ ብዙም ቦታን አይሰጡም ።

ሰዎች ከቁሳዊ ሀብታቸው ጋር ፣ ከስራቸው ጋር ፣ ከቤተሰባቸው ጋር ፣ ከገንዘባቸው ጋር ፣ ከስልጣናቸው ጋር ወዘተ ትስስርን እና ቁርኝትን ይፈጥራሉ ። ይህም ቁርኝት ውሎ አድሮ በዛነ ነገር ም ክንያት የሚመጣውን መከራንና ስቃይን ለመቀበል ሲገደዱ ፣ ይህም ለጤና ማጣት ፣ ለህመም ለብስጭት ለስቃይ ይዳርጋቸዋል ። አንድ የቡድሂዝም ሀይማኖት ከተመሰረተባቸው አስተምህሮቶች አንዱ የስቃይ መፈጠር ምክንያቱ ፣ ሰዎች ከአንድ ነገር ጋር ቁርኝትን ሲፈጥሩ ነው ይላል ። ነገር ግን በአንድ በኩል ቁጥ ርኝት ሰው የመኖር ህልውናውን የሚያረጋግጥበትና በማህበተሰቡ ውስጥ ከለላን እና ደህንትን የሚያ ገኝበት ነገር መሆኑን ሳንረሳ ሲሆን ፣ ነገር ግን ከልኩ ሲያልፍ ግን ለዛ ሰው መጥፊያው ነው እንጂ መልሚ ያው ሊሆን አይችልም ።

ቁርኝትን የምንፈጥረው በስሜቶቻችን አማካይነት ነው ። ዌለሽ እንደሚለው ሁለቱ ዋና ዋና የሰው ልጅ ስሜቶች የሚባሉት ፍቅርና ፍርሀት ናቸው ። ይኀውም ለአንድ ነገር የሚኖረን ስሜት ፍቅር ሲሆን ለዛ ነገር ያለንን መውደድ ያሳያል ። ፍቅር ለዛ ነገር ከፍተኛ መስዋእትነትን እንድንከፍል የሚያደርገን ነው ። ፍርሀት ደግሞ የምንወደውን ነገር ላለማጣት ማድረግ የምንችለውን ማንኛውምን ነገር እንድናደርግ የሚያደርገን ነው ። ይኀም ወንጀል ወይንም ጥፋት የሚባል ነገርንም ጭምር እንድንፈፅም ሊያደርገን ይችላል ። ሰዎች የያዙትን ላለማጣት ወይንም እናጣለን በሚል ስጋት ማንኛውምን ነገር ያደርጋሉ ።

የሰው ልጅ ተፈጥሮ / ባህሪ

የሰው ልጅ ባህሪ ቀላል ፣ አሰቸጋሪና አንዳንዴም ውስብስብ ነው ። ቀላል የሚያደርገው ሁሉንም ሰው አንድ አይነት ነገሮችን ይወዳል ፣ በአንድ አይነት ነገሮች ይሸነፋል ፣ አስቸጋሪ የሚያደርገው ለጥቅምና ለአስተሳሰብ ልዩቶች መሀከል የሚደረግ ሽኩቻ ሲሆን ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ የሰው ልጅ አንዳንድ ጊዜ እርስ በእርሱ የሚጋጩ ፍላጎቶችን ያናራምዳል ።

ዴቪድ ሂዩም የተባለው እንግሊዛዊ ፈላስፋ እንደሚለው የሰዎች ባህሪ ይበልጥ ስሜታዊ ነው ። «Treatise on Huaman Nature» በተሰኘ ሀቲት ፅሁፉ ስፒኖዛ በበኩሉ ኤቲክስ በተሰኘው ፅሁፉ እንደሚለው ከጥሩ ጥሩ ሰዎች ይልቅ የመጥፎ ሰዎች ቁጥር ያይላል ። እየሱስ ክርስቶስ «የተቀደሰውን ለውሾች አትስጥ » ካለው ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም ። ድንጋይን ፈልጎ ማግኘት ቀላል ሲሆን በአንፃሩ ግን አንዲት ግራምን ወርቅ ለማግኘት እጅግ ብዙ በርካታ መኪና ድንጋይንና አፈርን ማንሳትን ይጠይቃል ። ልክ እንደዛው ሁሉ ጥሩ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት እጅግ የከበደና ፣ መለየቱም አስቸጋሪ ነው ፤ ምክንያቱም መጀመሪያ ፈልጎ ማግኘቱ የበለጠ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው ።  

በነገራችን ላይ አይሁዳውያን በዚህ ዘርፍ ያደረጉት ብሉይ ኪዳንን ብንወስድ በርካታ የስነ – ምግባር መርሆዎች የታጨቀ ነው ። ኦስካር ዋይልዴ ስለ ሰው ባህሪ መርምረን ፣ መርምረን መጨረሻ ላይ እምንደርሰው በጣም አስፈሪ ወደ ሆነው ማለትም ወደ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ወይም ባህሪ «Human Nature» ይሆናል ይለናል ።

ይሄውም የሰው ልጅ ባህሪ ዝቅተኛና ተራው ያሰ የሰው ልጅ ባህሪያት የሚባሉት ምቀኝነት ፣ ጨካኝነት ፣ ዋሾነት ፣ አስመሳይነት ፣ ለራስም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ደንታ ቢስ መሆን ፣ ወዘተ ሲሆኑ በአንፃሩ ከፍተኛ የሚባሉትና የዚህ ተቃራኒ የሆኑ የሰው ልጅ ባህሪያት ደግሞ መንፈሳዊነት ፣ እዝነት ወይም ርህራሄ ፣ ታማኝነት የመሳሰሉት ታላላቅ የስነ – ምግባር መርሆዎች ናቸው ።

የሰው ልጅ ባህሪ ሁለት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል ። አንደኛው ሰዎች ጥሩዎች አይደሉም ከሚል አስተሳሰብ የሚነሳው ሲሆን ፣ ሌላው ደግሞ እዝነትን ወይም ርህራሄን የሚመለከተው ነው ። ይህም የበርካታ ታላላቅ እምነቶች መሰረታዊ ፍልስፍና ነው ። በርካታ የአለማችንን ታላላቅ ሀይማኖቶችን የመሰረቱ የሰው ልጅን ባህሪ ውስጠ ሚስጥሩን አብጠርጥረው ያወቁ ሰዎች ናቸው ። በዚህም ድክመቱንና ጥንካሬውን የተረዱና ለዛም መንፈሳዊ ድህነትን ያመጡ ናቸው ። ቡድሀ የመሳሰሉት ለሰዎች ጥፋትንም ቢሆን በእዝነት «Compassionate» በሆነ እይታ የሚያዩ እንደሆኑ ታሪክ ይመሰክርላቸዋል ።

በርካታ ማህረበራዊ ሳይንስን የሚመከለቱ ፍልስፍናዎች የሰው ልጅ ባህሪን በመረዳት ላይ የተመሰረቱ ናቸው ። ፖለቲካን ፣ ህግን ብንወስድ «ሰዎች እኩያን ናቸው» ከሚል አስተምህሮ የሚመነጩ ናቸው ። ማክያቬሊን ብንወስድ መስፍኑ በሚለው መፅሀፉ ይህንን አስተሳሰብ  በሰፊው ያንፀባረቀ መሆኑ ይነገርለታል ። ይህም አስተሳሰሰቡ በእጅጉ በታሪክ በመጡ ደራስያን እጅግ የተወገዘ ቢሆንም ፣ የፖለቲካ ሳይንስ መሰረት ሊሆን የበቃ ነው ። ህግንም ብንወስድ ህግ ሌሎችን ለማስፈራራት ፣ ለማስጠንቀቅ እንዲሁም ለመቅጣትና ለመበቀልም ጭምር የሚዘጋጅና ስራ ላይም የሚውል እንደሆነ ይታወቃል ።

በአብዛኛው የአለማችን ሀይማኖቶች ስለ እራሮትና እዝነት የሚያስተምሩበት አብዛኛው ምክንያት ፣ ይኀው ነው ። ብዙ ሰዎች የጭካኔ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ፣ የቅናት ስሜታቸውን እንዳለዝቡ ፣ አዛኝ እንዲሆኑ ፣ በየቀኑ እየደጋገሙ የሚያስተምሩበትም ምክንያት ይኀው ነው – እነኚህ አሉታዊ ስሜቶች የሰው ልጅ በህሊናው ዳኝነትና ፣ በፈሪሀ እግዝአብሄርነትና በግንዛቤው ካልተቆጣጠራቸው በስተቀር ፣ ልክ እንደማንኛውም እንሰሳ በሰው ልጅ ላይም አመዝነው የሚታዩ ስለሆኑ ነው ። በአንፃሩ ህግን ብንወስድ በእዝነት ወይንም በራሮት ላይ የተመሰረተ አይደለም ፣ የህግ አላማው መቅጣት ፣ መበቀልና ማስተማር ፣ ብሎም ከማህበረሰቡ ማስወገድ ነው ። እዝነት ወይንም እራሮት የተሰኘው ፅንሰ – ሀሳብ ከሀይማኖት አንፃር ሲሆን የሰዎችን ድርጊት ለመረዳት ፣ ለምን መጥፎ ነገሮችን እንደሚያደርጉት ለመረዳት የሚነሳ ፅንሰ – ሀሳብ ነው ።

የሰው ልጅ ለራሱ ደህንነት ደንታ የሌለው ፣ የማያገናዝብ እንዲሁም ጨካኝ ሲሆን ይህ ባህሪ መሞረድና ለራሱም ሆነ ለሌላውም ሆነ ለማህበረሰቡ ጠቃሚ ወደ ሆነ ባህሪ መለወጥ አለበት ። ፕሌቶ ያልተሞረደው የሰው ልጅ ባህሪ በትምህርት ሊስተካከል ይችላል ብሎ ያምናል ። ነገር ግን የሰው ልጅ ባህሪ ትምህርት ሊያስተካክለው ይችላል ። «የሰው ልጅ ባህሪ በትምህርት ሲሞረድ ኖብል ’ቅዱስ’ ይሆናል ይላል» ።

ሌላው ከሰው ልጅ ባህሪ አስገራሚው ነገር ሁሉም ሰዎች አንድ አይነት የሕይወት ግብም ሆነ አላማ የላቸውም ። የከፍተኛ ትምህርት በሚለው መፅሀፍ ላይ አንዱ ፖለቲካንና ስልጣንን ሲወድ ፣ አንዱ ገንዘብን ይወዳል መፅሀፉን ተመልከተው ። የአለማችንን ታላላቅ ሀይማኖቶች ቅዱሳን መፅሀፍት ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ድረስ ስለ ሰው ልጅ ባህሪና ተፈጥሮ የሚያወሱ ናቸው ። የሀይማኖት በሳይንስ ላይ ያለው ጠንካራ ጎኑም ይሄው ሊሆን ይችላል ። ሳይንስ የሰውን ልጅ ውስጣዊ ማንንነት ለመረዳት ምንም ጥረትን የማያደርግ ሲሆን በአንፃሩ ግን ሀይማኖት አብዛኛውን ጥረት የሚያደርገው ስለ ሰው ለጅ ምንነት ለመመርመርና ለመረዳት ነው ። ስልጣንን ብንወስድ ሰልጣን የተመሰረተው የሰውን ልጅ ባህሪና ምንነት በመረዳት ላይ ነው ። ምድራዊ ገዢዎችም ሆኑ መንፈሳዊ ገዢዎች ስልጣናቸው የተመሰረተው የሰውን ልጅ ባህሪ በመረዳት መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁታል ። መቼም ቢሆን ስህተት በማይሆኑ የሰው ልጅ ባጅሪ ባህሪያትን መረዳት ነው ።

ይሁን እንጂ ስለ ሰው ልጅ ባህሪ ለውጥ ብዙ አይነት ንድፈ ሀሳቦች ሲኖሩ የሰው ልጅ ባህሪ ይለወጣል ፣ አይለወጥም የሚለው ነገር አከራካሪ ሲሆን አንዳንዶቹ የሰው ልጅ ባህሪ በዝግመተ – ለውጥ ይለወጣል ሲሉ ፣ ሌሎች ደግሞ የለም የሰው ልጅ ባህሪ በማህበራዊ ኑሮ ይለወጣል የሚል ነው ።

ኒቼ እንደሚለው «ልእለ – ሰብ» አንድ ሰው ከፍተኛው ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚገልፀው ነው ። ነገር ግን ይህም ሰው እዚህ ደረጃ ላይ ቢደርስም ህግን ፣ ሀይማኖትን ፣ ባህልን ወዘተ ማክበር ግዴታው ነው ። እነኚህን ካላደረገ ግን በማህበረሰቡ ውስጥ በሰላም የመኖር እድሉን ያጣል ። ነፃነት ሲባል ውስጣዊ የሆነው ሲሆን በአንፃሩ ግን ከውጪ የሚታየውን ግን ማክበር አለበት ።

የሰው ልጅ ባህሪው በዚህ ምድር ላይ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያመለክት ነው ። ለምሳሌ የከፍተኛ ትምህርት በኢትዮጲያ መፅሀፍ ላይ አንደኛው ለስልጣንና ለፖለቲካና ለስልጣን ሲል  ማንኛውንም ነገርን የሚያደርጉ ጤናውን ጭምር የሚጎዳ ፣ ገንዘብን የሚወዱ ወዘተ እያለ ይከፋፍላቸዋል ፣ ሌላኛው ለገንዘብ ሲል ምንም ነገርን ከማድረግ የማይመለስ ፣ ሌላው ለዝና ፣ ሌላው ደግሞ ለእውቀት እስከ አለም መጨረሻ የሚደርስ እያለ ይከፋፍለዋል ። በከበደ የስልጣኔ አየር ሚካኤል መፅሀፍ ላይ ደግሞ ጂኒየስ ፣ ጄኔ ፣ ቀጥሎ ያሉ እያሉ ይከፋፍሏቸዋል ።የከበደ ሚካኤልን የስልጣኔ አየር በሚለው መፅሀፋቸው ላይ ጂኒየስ እንደ ናፖሌዎን ያሉ ፣ የአስተዳደር ሰዎች ፣ የንግድ ሰዎች ወዘተ በማለት ይከፋፍሏቸዋል ።

ማንኛውም አይነት ስልጣን የሰው ልጅ ባህሪን መረዳት ላይ የተመሰረተ ነው ። «ምድራዊ ገዢዎችም» ይሁኑ «መንፈሳዊ ገዢዎች» ስልጣናቸው ትክክልኛ በሆነ የሰው ልጅ መረዳት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አንድ የሀይማኖት መስራች በኒቼ አባባል መቼም ቢሆን በማይሳሳት «ኢንፎለብል» የሆነ የሰዎች ስነ – ልቦና የመረዳት ችሎታ ሊኖረው ይገባል ይላል ።

ይሁን እንጂ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሰው ባህሪ ፣ የሰው ልጅ ያለውን ስልጣን ከሌሎች ጋር መጋራት አይፈልግም ፣ በጣም ጥሩ የሚባሉ ሰዎች እንኳን ስልጣናቸውን ወይንም ያ ስልጣን የሚያስገኝላቸውን ክብር ፣ ጥቅም ወዘተ ለመከላከል የማይጠበቁ ነገሮችን ሊያደርጉ ይችላሉ ።ስልጣን በራሱ እሚሰባበርና እሚከፋፈል ነገር አይደለም ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ያን ስልጣን ሊጋራቸው የሚችልን እንዲሁም ከዛ ስልጣን ላይ እኩል ይገባኛል ሊል የሚችልን ሰው ከአጠገባቸው ያርቃሉ ለምሳሌ ሁለት ወንድማማቾች አንዱ አንዱን አጠገቡ አይፈልግም ፣ ለአንድ ነገርም እኩል ይገባኛል የሚሉ ሰዎችም ብዙውን ጊዜ አንዱ አንዱን አይፈልግም ።

መሪ የሚወርሰውና ትቶት ስለሚሄደው አሻራ (Legacy)

ማንኛውም መሪ ሰው እንደመሆኑ መጠን ፣ እድሜውን ጨርሶ ወይንም የሀላፊነት ዘመኑን ጨርሶ መልቀቁ አይቀርም ። ስለዚህ ትቶት ስለሚያልፈው አሻራ ማሰብ አለበት ። አንድ መሪ የፈለገ ተፈላጊ ቢሆንና ችሎታ ቢኖረው ወይንም ከፍተኛ ድጋፍ ቢኖረው በመጨረሻ የሚመራውን ተቋም መልቀቁ አይቀርም ። ብዙውን ግዜ ብቃትና ችሎታ እንዲሁም ተክለ – ሰውነት ያላቸው መሪዎች ከተቋማቱ ጋር ሳይነጣጠሉ ተያይዘው የሚታዩበት ጊዜ አለ ። ለምሳሌ ስቲቭ ጆብስ ከአፕል ኩባንያ ጋር ፣ ቢል ጌትስ ከማይክሮሶፍት ጋር አብረው የሚታዩበት ፣ አንዳንድ የሀገር መሪዎችም ከዚያች ሀገር ጋር ተያይዘው የሚታዩበት ጊዜ አለ ። ነገር ግን መሪዎች ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን በጨረሻ ከያዙት ቦታ መልቀቅ ወይንም መሰናበት እጣ አይቀሬ ነው ። ነገር ግን በአንፃሩ ተቋማትና ሀገራት ግን ከሰዎች በላይ የረዘመ እድሜ እንዳላቸው ይታወቃል ።

አንድ መሪ ከቀደምት መሪዎች የወረሰው አሻራ ይኖራል ። አሻራ ወይም ቅሪት ወደፊት የሚያስተላልፈው ብቻ ሳይሆን እርሱ ከቀደምት መሪዎች የወረሰውም ጭምር ነው ።መሪው ያለፈውን አሻራ ሊወደውም ሊጠላውም ሲችል ፣ ነገር ግን ካለፉት የወረሰው በጎን ይሁን መጥፎ የታሪክ ቅሪት እንደሚኖር ግን መገመት አለበት ።

ካለፈው ከወረሰው ብንጀምር ጥሩም ፣ መጥፎም እንዲሁም ጠንካራም ደካማ ጎኖችም የሚወረሱ ሲሆን የስልጣን ምንጭም ሆኖ ያገለግላል ።ሌጂቲሜሲ የስልጣን መንጭ ሲሆን ፣ ጠንካራ የነበሩ የቀድሞዎቹ መሪዎች ለምሳሌ መሪው የቀድሞው መሪዎች ያደረጉትን ሁሉ አድርጌ እነሱ ያመጡትን ድል አመጣለሁ ቢል ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል ። መሪው በራሱ መንገድ ራሱ በቀደደው ጎዳና መሄድ ሲኖርበት ፣ የቀድሞዎቹ ገናና መሪዎች ያደረጉትን ሁሉ በመከተል የነሱን ስኬት ማስመዝገብ አይችልም ።

ለምሳሌ በቀድሞ ዘመን ከነገስታቱ የዘር ሀረግ መመዘዝ ለአንድ ንጉስ ለመንገስ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነበረ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከነገስታቱ የዘር ሀረግ ያልሆነ መንገስ እንደማይችልና ህዝቡ እንደማይቀበለው የታወቀ ነው ። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በታሪካችን ዘመነ – መሳፍንት በመባል በሚታወቀው ዘመን በጦር አሸናፊ የነበሩ መኳንንትና መሳፍንት ምንም እንኳን አሸናፊ ቢሆኑና መንገስ ቢችሉም ነገር ግን በቀጥታ ከነገስታቱ የዘር ሀረግ የሚመዘዙ ባለመሆናቸው ፣ የህዝብ ተቀባይነትን እንደማያገኙ ስለሚያውቁ ከነጋሲ ዘሮች እየመረጡ እያነገሱ በቤተመንግስቱ ለይስሙላ ያስቀምጡ ነበረ ። ይህም ህዝቡ የነገሰው የነጋሲ ዘር ነው ብሎ እንዲያምንና የህጋዊ ተቀባይነት ጥያቄን እንዳያስነሳባቸው ለማድረግ ሲባል ያደርጉት የነበረ ሲሆን ፣ ቀላል ለማይባሉ ዘመናት ሀገሪቱ በዚህ መንገድ መተዳደሯ በታሪክ ሰፍሮ የሚገኝ ነው ።

ወደ ሀገርኛው አባባል ስንመልሰው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለች በቅሎ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው ። ይሄ ነገር የግብፁ ፈርኦን በቀን በሺ የሚቆጠሩ በቅሎዎች ፣ በጎችና ፍየሎች የሚቀርቡለት የነበረ ቢሆንም ከእኔ በኋላ ግንብፅን የአባይ ውሀ ይብላት ይል እንደነበረ ይነገራል ።
ይህ ብቻ ሳይሆን መሪው እርሱን እሚገልፁት የራሱ ነገሮችም ሊኖሩት ይገባል ። የቀድሞው መሪ በጣም የታወቀ ፣ የተወደደ እንዲሁም ግዙፍ ስብእና ያለው ቢሆንና አንድ መሪ እንደዚህ አይነቱን ባለ ግዙፍ ተክለ – ሰውነት ባለቤት ቦታ ቢተካ ፣ እንዳለ የቀድሞውን ሰው ግዙፍ ስብእናውንና አካሄዱን ለመውረስና ለመከተል ቢሞክር ያንን ግዙፍ ቦታ ሙሉ በሙሉ መሸፈን ሳይችል ይቀራል ። ስለዚህ ቀስ በቀስ የራሱን መንገድ በቀስ ከግዙፉ ጥላ ከመጋረድ መውጣት አለበት ።

በብዛት በምእራቡ አለም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ከተሸነፈ ብዙውን ጊዜ የፓርቲው መሪዎች ይቀየራሉ ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የቀድሞዎቹ መሪዎች ፓርቲው እንዲሸነፍ ያደረገውን ምክንያት አዲሶቹ መሪዎች በመቀየር ፓርቲውን ወደ ድል እንዲያመጡት ሲባል ነው ።የቀድሞዎቹ መሪዎች እንዳለ ቢቀጥሉ ፓርቲው የፖሊሲም ሆነ የአደረጃጀት ለውጥ የማምጣት እድሉ ጠባብ ነው እሚሆነው ፤ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግም ካስፈለገ አዲሶቹ መሪዎች ያንን የፖሊሲ ለውጥ ከቀድሞው አመራር በተሻለ ለውጥ የማድረግ እድል ስለሚኖራቸው ነው ። ይህንን ስለሚረዱ ከቀድሞዎቹ መሪዎች አሉታዊ ሊሆን ከሚችል ጥላ እንዲወጣ ያስችለው ዘንድ አመራሮቹን በመቀየር ፓርቲው ወደ ቀድሞው ህዝባዊ ተቀባይነቱ ለማምጣት ያለውን እድል ያሰፋዋል።ነገር ግን የግድ የአመራር ለውጥ ማምጣት ፣ አንድ ፓርቲ በሌላ ምክንያትም ሊሸነፍ ይችላል ። በዛው አመራርም ከተወሰኑ አመታት በኋላ ወደ ድል ሊመጣም ይችላል።

ሌላው ደግሞ በተለይም በቀደመው የአመራር ዘመን በጣም ሰኬታማ የሆነ ፣ የጎላ ተክለ – ሰውነት የነበረውን መሪ መተካት ይበልጥ አስቸጋሪ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ አዲሱም መሪ የቀድሞውን ስኬታማና ከፍተኛ ተፅእኖ ያለውን መሪ ስለተካ ተከታዮቹም አዲሱ መሪ ያንን ተከትሎ እንዲሄድ ስለሚጠብቁ ሲሆን ፤ ይህም ብቻ ሳይሆንየቀድሞው መሪ የነበረው የገዘፈ ተክለ – ሰውነት እና ስብእና (Charisma) የአዲሱን መሪ ይጋርደዋል ፣ ሰዎች በአዲሱን መሪ ውስጥ የቀድሞውን መሪ ነው እሚያዩት ። ስለዚህ ከቀድሞው መሪ ጥላ መውጣትና በራሱ መንገድ ወይም ጎዳና መጓዝ አለበት ። በቀድሞው መሪ ጥላ ከተጋረደና ከዛ ጥላ መውጣት ካልቻለ የራሱን ገፅታ ወይም ምስልመፍጠርም ሆነ በራሱ መንገድ ሊያደርግ እሚፈልገውን ማድረግ አይችልም ።

ይህን አንድ መሪ ስኬታማ እንዲሆን ፣ የራሱን መንገድ መከተል አለበት ፤ አንዳንድ ሰዎች የቀድሞዎች ሰዎች ያደረጉትን በማድረግ ስኬታማ እንደሆናለን ብለው የሚያስቡ አሉ ፤ ነገር ግን አንድ መሪ ምንም እንኳን ሌሎች ያደረጉትን ማወቅና ከዚያም ትምህርትን መውሰድ የሚጠቅመው ቢሆንም የራሱ ባልሆነና ሙሉ ለሙሉ በሌሎች ሰዎች በሆነ እውቀት መተማመን የለበትም ፤ ከዚያ ይልቅ በተለይ በጣም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የራሱን መስመር መከተል ይበልጥ ይጠቅመዋል ። ሌላው ደግሞ መሪው የቀድሞዎቹ መሪዎች ያደረጉትን መንገድ ብቻ ተከትሎ የሚሄድ ከሆነ በራሱ ትቶት የሚሄደው አሻራወይም ኗሪ ታሪክ ፣ ወይም ቅርስ (Legacy) አይኖረውም ። ከቀድሞው መሪ ራሱን የሚለይበትና የራሱ የሆነ ትቶት ሄደ የሚባለው አሻራ አይኖረውም ። ለምሳሌ የቀድሞው መሪ በአንድ ጉዳይ ላይ በማተኮር ስኬትን አግኝቶ ከሆነ ፣ እርሱ ደግሞ ሌላ አቅጣጫን በመከተል በዚያ መስመር የራሱን ስኬት መፍጠር የራሱን አሻራ ማሳረፍ መቻል አለበት ።

ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የነበሩት ሁኔታዎችና አሁን ያሉት ሁኔታዎች በጣም ስለሚለያዩ ነው ። ቀድሞ የነበሩ መሪዎች ያገኙት እድል ፣ የገጠማቸው ፈተና እንዲሁም አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታዎች ቀላል በማይባል ሁኔታ ይቀያየራሉ ። ስለዚህ አዲሱ መሪ በድሮው የቀድሞዎቹ መሪዎች ባገደረጉት ዝም ብሎ ቢጓዝ ወደ ስኬት ለማምራት ያለውን እድል ያጠባል ። ስለዚህ ከወቅቱ ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው ። ልክከጦጣይቱ ተማሪው ደብተሩ ላይ ፅሁፉም ፅፎ ሲጨርስ ሲጨርስ ሲሄድ ልክ እሱ ያደረገውን አይታ መፅሀፉን እላዩ ላይ እየቸከቸከች ስታስቸግረው ፣ ተማሪው ለብልሀቱ ቢላዋ አምጥቶ በስለት በሌለው በደነዘው በኩል አንገቱን አስነክቶ ሲያስቀምጥ ትመለከታለች ፣ ከዚያም ቢላዋውን አስቀምጦ ሲሄድ እንደለመደችው ልክ እሱ እንዳደረገው አደርጋለሁ ብላ ቢላዋውን በስለቱ በኩል አንገቷ ላይ ብታውለው አንገቷን ቆርጦ እንደጣላት ሁሉ ፣ በአመራር ውስጥም አንዱን መሪ ለድል ያበቃውን አድርጌ ሌላ መሪ ያደረገውን እኔም አድርጌ እንደ እሱ ስኬታማ እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ለመሪው የራሱን ውድቀት እንደ እንደ ማምጣት ያስቆጥርበታል ።

የሰው ሁሉ እድሜው የተወሰነ ነው እንደሚለው መፅሀፉ ፣ መሪም ስለወደፊቱ ማሰብ አለበት ፣ በእርግጥ መሪው እሱ የማይኖርበትን ዘመን በአካል ተገኝቶ ቅርፅ ሊያሲይዝና ሊመራ ባይችልም ፣ አሁንላይ ሆኖ የሚያደርገው ነገር ግን ወደፊቱ ለሚመጣው የራሱ የሆነ በጎም ይሁን አሉታዊ ተፅእኖ ኖረዋል ።መሪው ካወቀውና ከተረዳው አሁን ካላይ ሆኖ እሚያደርገው ማንኛውም ነገር እሱ በማይኖርበት በወደፊቱ ላይ የተወሰነ የራሱን አሻራና ተፅእኖን ሊያሳርፍ ይችላል ።

ልክ ዘንድ አርቲስት ስራው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆንለት እንደሚፈልገው ሁሉ ፤ አንድ መሪም ጥሎት ስለሚሄደውም አሻራ ማሰብ ሲገባው ፤ ከሱ በኋላ ስለሚመጣውና መጪው ትውልድ በጥሩ እንዲያስታውሰው ጥሩ ስራን ትቶ ለማለፍ መጣር አለበት ።ለምሳሌ የሀይለስላሴን ስርአት ብንወስድ ከቀዳሚዎቻቸው የኢትዮጲያ ነገስታት የበለጠ ተወዳጅነት የላቸውም ።

ለዚህም ምክንያቱ በጣም ቀላል ነው ። ማንም ሰው ከተወሰነለት እድሜ በላይ አይኖርም ስለሆነም ያ ሰው ያስተማራቸው ትምህርቶች ፣ የወጠናቸው ሀሳቦች በእርሱ እድሜ ተሳክተው እማያልቁ ስለሆነ እና በርካታ አመታትንና ትውልዶችን ሊጠይቅ ይችላል ። ስለሆነም የትውልድ መተካካት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል ። መሪም ሰው እንደመሆኑ እንደሰው ይታመማል ብሎም ያልፋል ። ይሁን የምንወዳቸውም ይሁን የማንወዳቸው የኛም ሀገር ይሁን የውጪ ሀገራት መሪዎች እንደ ሰው ሲያልፉ ታሪካቸው በታሪክ መፅሀፍት ውስጥ ነው እሚገኘው ፣ ስለዚህ ጥሩ ለሰሩ እስከመቼውም ድረስ ሲመሰገኑ ይኖራሉ ፤ መጥፎ ከሰሩም እንደዛው እንደተቀሱና እንደተኮነኑ ይኖራሉ።

ለቀጣዩ የሀገር ወይንም የአንድ ድርጅት ቀጣይ ህልውና ሰላማዊና ፣ እንዲሁም አዲሱ መሪ ህጋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ሲባል በአንድ ድርጅት ውስጥ መተካካት ሲካሄድ ወይንም አንድ መንግስት በአንድ መንግስት ሲተካ መተካካትን ሲባል ህግንና ስርአቱን ተከትሎ መሄድ አለበት ። ይህም እጅግ በጣ ም አስፈላጊ ነው ። ህገ – ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ስልጣን የመጡ መሪዎች ያንን ያለፈ ታሪካቸውን መሸፈን የማያደርጉት ነገር የለም ። በሀገር ደረጃን ስናስበው ለምሳሌ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በ1980ዎቹና እስከ 90ዎቹ ድረስ መፈንቅለ – መንግስታት ይካሄዱ ነበር ነገር ግን ፣ አንደኛ ውጤቱ አጠራጣሪ ከመሆኑም በላይ ደም አፋሻሽም ጭምር በመሆኑ ፣ ሌላው ደግሞ ቢሳካም ባይሳካም ደም አፋሳሽ ከመሆኑ በተጨማሪ ፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ስልጣን የመጡ ሀይላት በተደጋጋሚ ወደ ስልጣን መ ጣን የሚሉት የቀድሞው መሪ አጠፋ የሚሉትን ሰበብ አድርገው ቢሆንም ፣ እነሱም በተራቸው መሪዎች በሚሆኑበት ወቅት የገቡትን ቃል ማክበራቸው በእጅጉ አጠራጣሪ ነው ። አፍሪካ ውስጥ በዚህ አይነት መንገድ ስልጣንን ያስረከቡ መሪዎች ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ነው ። ምክንያቱም ስልጣኑን እንዲይዙ ያደረጋቸው በራሳቸው ሀይልና ጉልበት ነው እንጂ በህዝብ ፈቃደኝነት ባለመሆኑ ለህዝብ ፍላጎት ጠብቀው መሄዳቸው አጠራጣሪ ነው ።

በዚህም በርካቶች ወደ ስልጣን መጥተው እነሱም ከእነሱ ቀድሞ ከነበረው ብሰው ቁጭ ያሉ ወይንም የማይሻልን ስርአትን የፈጠሩ መሪዎች በአለም ዙሪያ ተከስተዋል ። እነሱን ለማስወገድና በአዲሱ ስርአት ለመረዳት እንደገና ሰላምን ማጣትን ያስከትላል ። በእርግጥ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በህዝብ በተመረጠ መንግስት እንዲተካ ያደረጉና የተሳካላቸው በጣም ጥቂት መሪዎች አሉ ፣ ነገር ግን በአብዛኛው የዚህ አይነቱ መንገድ አጥፊ የሆነው ጎኑ ይብሳል ። በእርግጥ ዲሞክራሲ ባለበት ሀገር የመተካካት ስርአቱ ግልፅ ያለ በመሆኑ አሻሚ የሆኑ ሁኔታዎች አይፈጠሩም ። በመሆኑም አንድ መሪ ከእርሱ በኋላ የመተካካት ስርአት የሌለው ከሆነ ራሱ በስልጣን ላይ እያለ ፅኑና የማያሻማ የመተካካት ስርአትን ማቆም መቻል አለበት ። ልክ አንድ አባት ልጆቹ እርስ በእርሳቸው በንብረት እንዳይጣሉ ግልፅ ያለ ኑዛዜን አስቀምጦ እንደሚሄደው ሁሉ መሪም እንደዛው ማድረግ ፣ ስርአቱ ከሌለ ስርአቱ እንዲኖር ማድረግ በተጣለበት ሀላፊነቶች ዋነኛውና ትልቁ ነው ።

ሰላማዊ የመተካካት ስርአት እንዲኖር ሀገራት ጉዳዩን ግልፅና በማያሻማ ሁኔታ መሪዎች እንዴት እንደሚተኩ የሚገልፅ ህገ – መንግስትም ይሁን ሌላ የህግ ስርአት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ግልፅ ካልሆነ ግን በቀሩት መሪዎች መሀከል የስልጣን ሽኩቻና ትግል ፣ እንዲሁም አዲሱ መሪ ስልጣኑን አስረግጦ እስከሚያፀና ድረስ ትርምስና ውዥንብር እና ሌሎችም ጥፋቶቸ ሊከሰቱ ይችሉ ። ስለሆነም የመተካካት ስርአት ማስፈን ቁልፍና አስፈላጊ ከሆኑት የመሪነት ተግባራት ዋናው ነው ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት መሪዎች ወጣቶችን የማያቀርቡና ወደ ስልጣን የማያስጠጉ የነበሩ በመሆናቸው ያረጁት መሪዎች እርስ በእርስ እየተተካኩ አንድ በአንድ ሞተው ሲያልቁ ከእነሱ ቀጥሎ የሚረከብ ወጣት ትውልድን አላዘጋጁም ማለት ይቻላል ። ከብሬዥኔቭ ጀምሮ በተከታታይ ሶቭየት ህብረትን የመሩት ያረጁት መሪዎች እዛው እርስ በእርስ እየተተካኩ ሲቀጥሉ እነሱም ብዙም ሳይቆዩ በሞት ሲለዩ ፣ የሚተካቸው ወጣት ትውልድ አልነበረም ፣ሁሉም ሞተው ሲያልቁ ስርአቱን ሊያስቀጥል የሚችል ወጣት ትውልድን ግን አላዘጋጁም ነበረ ። በአንፃሩ ቻይናውያንን ብንወስድ የዚህም የመሪነትን ክፍተት በሚገባ ተረድተውት ነበረ ማለት ይቻላል ።

ከማኦ ዜዱንግ ሞት በኋላ የመጡት የቻይና መሪዎች በተለይም ዴንግ ዚያዎፔንግ ለወጣቶች በማስረከብ ለስልጣኑ ወንበር ገለል ሲሉ በኋላም በሞት ሲለዩ የተተኩትም መሪዎች ያንኑ መስመር በመከተል ፣ ተተኪ ወጣቶችን በመመልመል የቻይና የኮሚኒስት ስርአት አገዛዝን ማስቀጠል ችሏል ። በእርግጥ ምርጫው በራሱ በኮሚኒስቶት ፓርቲው ውስጥ እርስ በእርስ የሚከናወንና በዲሞክራሲያዊ መንገድበህዝብ የተመረጡ አይደሉም የሚል ትችት ሊቀርብበት ቢችልም በአንፃሩ ግን ስርአታቸውን ማዳንና ማስቀጠል ችለዋል ። በተመሳሳይም የሳኡዲ አረቢያ መሪዎችም የዚህ አይነቱ ሁኔታ ዋና ዋናዎቹ ልኡላንና አልጋ ወራሾች በሞት ሲያልፉ የሚተካ የቅርብ ወጣት የሌላቸው ከመሆኑ የተነሳ አዲሱን ትውልድ አቅርበው ወደ ስልጣን ባለማስጠጋታቸው የተነሳ እንደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ውስጥ የተፈጠረው አይነት የስልጣን ክፍተት ሊፈጠርባቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል ።
ብዙውን ግዜ በምእራባውያን ሀገራት በተደረጉ ጥናቶች በተደጋጋሚ እንደታየው አንድ ሁነኛ ስራ በአራት ትውልድ ውስጥ ፍርስርሱ እንደሚወጣ መረዳት ተችሏል ። የመጀመሪያው ትውልድ ያንን ነገር ጥሮና ተጣጥሮ ያንን ነገር የገነባና የፈጠረ ሲሆን ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ የመጀመሪያው ትውልድ የገነባውን ያሳደገና ያደራጀ ሲሆን ሶስተኛው ትውልድ ግን ብዙም እድገትን ሳያመጣ ነገር ግን ባለበት እንዲቀጥል ያደርገዋል ፣ በአራተኛው ትውልድ ዘመን ግን በግዴለሽነትና ባለማወቅ ፣ በስንፍና አራተኛው ትውልድ ሁሉንም ነገር ያፈራርሰዋል የሚል ሀሳብ አለ ። በእርግጥ ሁሉም አራተኛ ትውልዶች ያንን ነገር ያፈራርሱታል ማለት አይደለም ከተረከቡት አስበልጠው ማሳደግና መምራት የሚችሉ በርካታ አራተኛ ትውልዶች እንዳሉም ይታወቃል ። በእርግጥ ይሄ ሀሳብ ማጠቃለያ አይደለም ።

በመሆኑም ምንም እንኳን አንድ መሪ መተካት ቢኖርበትምና ፣ እርሱን ለመተካት አስፈላጊው ምክንያት ከበቂ በላይ ቢኖርም የሚተካበት መንገድ ህጋዊ መሆን መቻል አለበት ። ይህም ለቀጣዩ ስርአት ለወደፊት ህጋዊ ተቀባይነትና የህዝብ ይሁኝታ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ።
መሪው ትቶት የሚያልፈው አሻራ የሚመራው ድርጅት ፣ ወይም ሀገር እንዳለበት ሁኔታና ፣ ችግር ውስጥ ካለም እንዳለበት ችግር ይወሰናል ። ስለዚህ ያንን ተቋም ችግር በመፍታት ችሎታውና ብቃቱ ነው (legacy) የሚወሰነው ።

የመሪነት እሴቱ ትቶት የሚሄደው አሻራ (Legacy) ሲሆን ፣ አንድ መሪ ስልጣን የሚቆይበት ዘመን የትየለሌ ከሆነውና መጨረሻ ከሌለው ጊዜ አንፃር ስናየው በጣም አጭር ሲሆን ፣ እንኳን አንድ መሪ ስልጣን ላይ የሚቆይበት ቀርቶ የሰው ልጅ እድሜም የተገደበ ነው ። የእርሱ በሀላፊኔት መቆየት በተወሰኑ አመታት የተገደበ እንደመሆኑ ፣ለሚቀጥለው ትውልድ ትቶት የሚሄደው እሴት ይኋውነ አሻራው ነው ።የየትኛውም መሪ አቅም በጊዜ ውሱንነት በተገደበ ነው ። የመሪው እድሜ ስናስበው ለረጅም ጊዜ ፀንቶ የሚቆይን ስራ መስራት መሪው ከአንድ ሰው ህይወት በላይ የዘለቀ እንዲሆን ያደርገዋል። መጽሀፉ «የሰው ሁሉ እድሜ የተወሰነ ነው» እንደሚለው መሪም ሰው እንደመሆኑ እድሜውም ሆነ የስራ ዘመኑ በጊዜ ውስጥ የተወሰነና የተገደበ ነው ። ስኬታማ የሆኑና በብዙ ትውልዶች ተወዳጅ የሆኑ መሪዎች ይህንን ቀላል የሆነ ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች ትልቅ ስልጣንንና ዝናን ሲቀዳጁ በቀላሉ የሚዘነጉት ሀቅ ነው ።

የውጪ ምእራባውያን ጋዜጠኖች አንድ ተለቅ ያለ መሪን ቃለ – መጠይቅ ሲጠይቁ ብዙ ጊዜ የሚጠይቁት ጥያቄ ውስጥ ምን አይነት አሻራን ወይም ቅርስን ትተህ ማለፍ ትፈልጋለህ ? በታሪክ ውስጥ እንዴት ለመታወስ ወይም ምን አይነት ቦታ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ ? የሚል ነው ። ይሄም ውሎ አድሮ መሪው የሚሰራው ስራ ወደ ሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ ስለሆነ የወደፊቱ መጪው ትውልድ በምን አይነት እንዲያስታውሰውና ፣ ለመጪው ትውልድም ባለው ትልቅ ቦታና ተሰሚነት ምንን ትቶ ወይም አውርሶ ማለፍን እንደሚፈልግ ለማወቅ የሚደረግ ጥያቄ ነው ። በተዘዋዋሪም አሁን እየሰራው ያለው ስራ ለወደፊቱ የሚኖረውን በጎም ይሁን አሉታዊ ተፅእኖን ራሱ መሪው እንዴት እንደሚረዳው ለማወቅ የሚደረግ ነው ።
የአገር መሪ ከሆነ ፣ መሪው ትቶት የሚሄደው ቅርስ ወይም አሻራ ከሀገሪቷ ካለችባቸው መሰረታዊ ችግር ይመነጫል ።

ለምሳሌ አሜሪካን በኢራቅና በአፍረጋኒስታን ጦርነቶች ውስጥ በተዘፈቀችበት ወቅት ተመርጦ ለሚመጣው መሪና ለሀገሪቷም አንገብጋቢ የሆነው ጦርነቶቹን ማስቆምና ፣ ሀገሪቷን ከእነኚህ ጦርነቶች ውስጥ ማውጣት ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ችግርም ካለ የወጣት ስራ አጥ ቁጥሩ ከፍተኛ ከሆነ የስራ እድሎችን መፍጠር ፣ እና ሌሎችንም ችግር መፍታት ነው ። በአሁን አለማችን ብዙም የተለመደ ባይሆንም አንድ ሀገር የውጪ ወረራ ካጋጠማት ወረራውን መመከትና የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበርም ሊሆን ይችላል ። እነኚህ ሁሉ የመሪውን ትቶት የሚያልፈውን የታሪክ አሻራ አይነት ይወስናሉ ። ትቶት ስለሚሄደው አሻራ እሚወስነው ራሱ መሪው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ለአጭር ግዜ ግብ ወይም ለአጭር ጊዜ የፓርቲ ጥቅምን እሚያስገኙ ሆነው ፣ነገር ግን በረጅም ጊዜ የመሪውን አሻራ እሚጎዱ ፣ መልካም ስሙን ጥላሸት የሚቀቡ ነገሮች ይከሰታሉ ። ለምሳሌ ፕሬዝዳንት ቡሽ ትንሹ አሸባሪዎችን በጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ውስጥ ያለ ፍርድ ሲያጉሩና ፣ በእስረኞች ላይ ስቃይ እንዲፈፀም ሲፈቅዱ ፣ አንዳንድ የራሳቸው ባለስልጣኖች ሳይቀሩ የፕሬዝዳንቱን በታሪክ የሚኖራቸው ቦታን (Legacy) ይጎዳል ብለው ተከራክረዋል ። በእርግጥ በዚህ መንገድ አሜሪካ በርካታ ጠቃሚ መረጃዎችን ፣

ቢንላደንን ለማግኘት ያስቻላትን መረጃ ጭምር በዚህ መንገድ ለማግኘት ብትበቃም የአሜሪካንን አለም አቀፋዊ ገፅታ ግን ክፉኛ ጎድቷል ። አንድ መሪ ትቶት የሚያልፈው አሻራ መሪው ካለፈም በኋላ ቢሆን ፣ የታሪክሰዎችን ሊያወዛግብ ይችላል ። ለምሳሌ ለሚመራው ህዝብ እንደ ጀግና የሚታይ ሲሆን ፣ ለጠላቶቹ ግን የተጠላ ሊሆን ይችላል ። ለምሳሌ የዘመናዊቷ ቱርክ መስራች አባት በመባል የሚታወቁት ከማል አታ ቱርክ ለቱርካውያን እንደ ብሄራዊ ጀግናና እንደ ሀገሪቱ አባት ተደርገው የሚታዩ ቢሆንም ለአርመናውያን ግን በርካታ አርመናውያን በመጨፍጨፋቸው እንደ ወንጀለኛ ነው የሚታዩት ፣ይህ ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ቱርክ በአታቱርክ ዘመን የተፈፀመውን የአርመናውያንን የዘር ማጥፋት አምና ይቅርታ እንድትጠይቅ ከአውሮፓውያን ግፊት እየተደረገባትና ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ማለትም ያንን የዘር ማጥፋት አድርገው ከተቀበሉ ሀገራት ከአውሮፓውያን ጋር ያላትን ግንኙነት እያበላሸባት እና የአውሮፓ ህብረት አባል የመሆን እድሏን እየተፈታተነባት ይገኛል ።

ይህ በታሪክ የሚተወው አሻራ በተከታታይ በሚመጡ ትውልዶች በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም ይችላል ። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የቀድሞው የፕሩስያ ወይንም የጀርመን መሪ የነበረው ኦቶ ቮን ቢስማርክ ሲሆን ፣ እርሱ የገነባው የጀርመንን ብሄረተኝነት ስሜት እንዲያንሰራራ በማድረግ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ የረዳና በአውሮፓ የተከበረች የተዋሀደች ሀገር እንድትሆን ለማድረግ ያስቻለ ቢሆንም ፣ ከእርሱ ህልፈት ከብዙ አስርት አመታት በኋላ የመጡት ናዚዎች እርሱ የገነባውየጀርመንን የብሄረተኝነት ስሜትን የጀርመንን ህዝብ ለመቀስቀስእና ወደ ስልጣን ለመምጣት ተጠቅመውበታል ። አንዳንድ የታሪክ ፀሀፊዎች ለናዚዎች መፈጠር ቢስማርክ ትቶት የሄደው አሻራ አስተዋፅኦ አድርጎ እንደሆነ ብለው ይጠይቃሉ ።

አዲሱ ትውልድ መሪው ትቶት የሚሄደውን አሻራ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ነው የሚተረጉመው ። መሪው የሰራውን ፍርስርፈሱን ሊያወጣው ይችላል ወይንም የተሻለ አድርጎ ሊያሳድገው ይችላል ። ለምሳሌ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መሪ የነበሩት ብሮንዝ ቲቶ ምንም እንኳን በዘመናቸው የሶሻሊስት ሀገራት በተለይ ሁኔታ ሀገራቸውን ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ በተሻለ የኢኮኖሚ አቅም መምራት ቢችሉም፣ የቀድሞዋን ዩጎዝላቪያን በአለም የተከበረች እና ከቀዝቃዛው ጦርነት ገለልተኛ አድርገው አገራቸው እንዳትጎዳ አድርገው ቢመሩም ፣ እርሳቸው ህልፈት ህይወት በኋላ ግን የእርስ በእርስ ጦርነት ተካሂዶ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ምድር ታይቶ የማይታወቅ ጦርነትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የተፈፀሙባትና የተበታተነች ሀገር ልትሆን በቅታለች ። ይህም የሚያሳየው ምንም እንኳን መሪዎች በትክክለኛ መንገድ እየመራን ነው ከኛ በኋላም እኛ የጀመርነው ይቀጥላል ብለው ሊያስቡ ቢችሉም እነሱ እንደሚያስቡት ላይሆን እንደሚችልና ፣ ከባሰም ተቃራኒ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ነው ።

በታሪክ ፀሀዩ ንጉስ በመባል የሞታወቀው የፈረንሳዩ ንጉስ ሊዊስ 14ኛ ከሀምሳ አመት በላይ የዘለቀ የስልጣን ዘመኑ ፈረንሳይን ወደ አውሮፓ ሃያል ሀገርነት የለወጠና ፣ በአውሮፓም ሀብታሟ ሀገር አድርጎ ማብቃት የቻለ ቢሆንም ፣ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ የእርሱን መንገድ በመከተል ማለትም ጨቋኝ የነበረውን ስርአት ምንም ባለማሻሻልና ፣ አንዳንዴም ባስ ባለ ጨቋኝ በሆነ መንገድ መምራታቸውን በመቀጠላቸው በምእራቡ አለም የመጀመሪያው የሆነው የፈረንሳይ አብዮት ሊካሄድና የዘውዳዊ ስርአቱ ከመሰረቱ ሊናድ በቅቷል ። መሪው ራሱ በዚያ ዘመን ቢኖር እንኳን እንደዛ ይደረግ ላይል የሚችለውን ነገር ተተኪዎቹ በቀድሞው መሪ በእርሱ ዘመን ስለተሳካ በዛ መንገድ መሄድ የለባቸውም ፣ ራሱ መሪው እንኳን በዛ ዘመን ቢገኝ እንደዛ ይደረግ ላይል ይችላል ።

መሪው የስልጣን መተካካትን ሲያደርግ በትክክለኛው መንገድ መተካካቱን ማድረግ አለበት ። በአብዛኛው ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት ውስጥ ህዝቡ አዳዲሶቹን መሪዎችን ስለሚመርጥ መሪዎች እከሌ ይተካኝ ማለት አይችሉም ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ መሪዎች የሚተካቸውን ሊመርጡ ይችላሉ ነገር ግን ተተኪው ህጋዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ መከናወን አለበት ። ሰዎች የግል ንብረታቸውን ፣ ሀብታቸውን ንብረታቸውን ለልጆቻቸው ማውረስ ሲችሉ ፣ መንግስት ስልጣንን ግን ማውረስ አይችሉም – ነገስታት ካልሆኑ በስተቀር ። በ 2012 የተነሳውን የአረብ አመፅ ብንወስድ ፣ አንዱ አመፁ የተነሳበት ምክንያት በምእራባውያን ድጋፍ መሪዎቹ ራሳቸው ለአስርት አመታት ስልጣን ላይ መቆየታቸው ሳያንስ ፣ ልጆቻቸውን ለመተካት ማሰብ መጀመራቸው ተስፋ የቆረጠው ህዝብ አማራጭ በማጣት ወደ መመለሻ ወደ ሌለው አመፅ በማምራት ጨርሶ የመንግስታቱን መወገድ አስከትሏል ።

ይህም መሪዎች የሚገነቡት መሰረት በትክክለኛ መሰረት ላይ መጣሉን ማረጋገጥ አለባቸው ፣ በትክክለኛ መሰረት ላይ ያልተጣለ ከሆነ ፣ ወይንም ለጊዜው በይድረስ ይድረስ ድረስ የተገነባ ከሆነ ጠንካራ መሰረት የሌለው ነገር በቀላሉ እንደሚፈርሰው ሁሉ የመሪው ስራም እርሱ በማይኖርበት ወቅት በቀላሉ ይናዳል ። ብዙውን ጊዜ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ያላቸው ሀገራት በጊዜ ሂደት ስርአታቸው እየተጠናከረ ሲሄድ ፣ ዲሞክራሲያዊ የልሆኑ ስርአቶች በአንፃሩ ግን እድሜአቸው ረጅም አይደለም ። መሰረታቸው ጠንካራ የሆኑ ስርአቶች በጊዜ ሂደት እንደውም እየተጠናከሩና እየዳበሩ ይሄዳሉ ፣ ለምሳሌ የአሜሪካንን የዲሞክራሲ ስርአትን ብንወስድ በጊዜ ሂደት ውስጥ ይበልጥ እየተጠናከረ መሄዱ የሚታይ ሀቅ ነው ፣ ለዚህም አንዱ ማሳያ የሚሆነው ቀድሞ በስርአቱ ውስጥ መመረጥም ሆነ መምረጥ የማይችሉ የነበሩ ጥቁሮችና ሌሎችም ዘሮች መብታቸው መከበሩና የስርአቱ አካላት መሆን መቻላቸው ነው ።

ዲሞክራሲ ባልተጠናከረባት ሀገር ውስጥ አንድ መሪ የዲሞክራሲ እድገቱን ቸል ብዬ ምጣኔ – ሀብቱን ብቻ አሳድጋለሁ ቢል ፣ አግባብ መሆኑ አጠያያቂ ነው ። ለዛች ሀገር በጣም አንገብጋቢው ጉዳይ የዲሞክራሲ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ምጣኔ – ሀብቱን ካሳደኩ የዲሞክራሲውን ጉዳይ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ጎን ማድረግ እችላለሁ ብሎ ቢል ትቶት በሚሄደው አሻራ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ያሳርፋል ። ይህ ማለት የምጣኔ – ሀብቱ እድገት አያስፈልግም ማለት ሳይሆን እድገቱ እንዳለ ሆኖ ይበልጥ ግን ትኩረት ማድረግ ያለበት በዲሞክራሲው እድገት ላይ መሆን አለበት ። በምጣኔ – ሀብት ማሳደጉ ሊሳካለት ቢችል እንኳን ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ በማተኮሩ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ግን ምሉዕ የሆነ በጎ አሻራውን ማሳረፍ ሳይችል ይቀራል ።

መሪው ትቶት የሚያልፈው አሻራ የሚመራው ድርጅት ፣ ወይም ሀገር እንዳለበት ሁኔታና ፣ ችግር ውስጥ ካለም እንሳዳለበት ችግር ይወሰናል ። ስለዚህ ያንን ተቋም ችግር በመፍታት ችሎታውና ብቃቱ ነው በታሪክ ትቶት እሚያልፈውን ቦታ (Legacy) የሚወሰነው ። ያም ሆኖ ግን የቀድሞ መሪዎች በጅምር ትተዋቸው ሳይቋጯቸው ያለፏቸው ጉዳዮችም ይኖራሉ ፣ እነኚህ ጅምር ስራዎችንም በአግባቡ የመቋጨትና የመጨረስ ጉዳይም የአዳዲስ መሪዎች ተግባር ነው ።

መሪው ትቶት የሚያልፈው አሻራ እጅግ ትልቅ ተፅእኖ ያለው ነው ። ለምሳሌ ታላላቅ ሀይማኖቶችን ብንወስድ ለሺዎች አመታት መቆየት የቻሉት ዋናዎቹ መስራቾች መሪዎች ትተውት ባለፉት አሻራ ነው ። እነኚህ ሰዎች እጅግ ሀያል ከመሆናቸው የተነሳ መንፈሳቸው ለሺህ አመታት በሰዎች ልብ ውስጥ እድሮ ሰዎችን ይገዛል ። ለምሳሌ ብንወስድ እየሱስ ክርስቶስ ፣ ሙሴ ፣ ቡድሀ ፣ ጋንዲ እንዲሁም ከቅርባችን ከደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላን ብንወስድ የዚህ አይነት መሪዎች ተፅእኗቸው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የብዙዎችን ልብ በተስፋ የሚያሞቁ ናቸው ። ከአገራት መሪዎችም እንዲሁ እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን ያሉት የተውት አሻራ ነው የዛሬይቱን ታላቋን አሜሪካንን የፈጠረው ፣ አሜሪካኖች እንደ ቅዱስ መፅሀፍ የሚቆጥሩት ህገ – መንግስታቸውም የተረቀቀው በነ ጆርጅ ዋሽንንግተን መሆኑ ይታወቃል ።

አንድ መሪ መቼ ስልጣኑን መልቀቅ እንዳለበት ማወቅ አለበት ። በትክክለኛው ወቅት ስልጣና ቸውን የለቀቁ ፣ መሪዎች መቼም ቢሆን ሲደነቁ ይኖራሉ ።አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ምንም እንኳን በርካታ ጥሩ ነገርን ያበረከቱ ቢሆንም ፣ ነገር ግን ብዙ ከመቆየት መልካም ስራቸው ሁሉ ተቃሎ ይታይባቸዋል ። ነገር ግን በትክክለኛው ወቅት ከዛ ቦታ ራሳቸው ገለል ማለት ይበልጥ ከዚያ በኋላ እንዲደነቁና እንዲከበሩ ያደርጋቸዋል ።

ለውጥ ከሁለት አቅጣጫ የሚመጣ ሲሆን ፤ ከላይ ወደታች (Top Down) እና (Bottom Up) ወይም ከላይ ወደታች ነው ። ከላይ ወደ ታች እሚመጣው የለውጥ አይነት በመሪዎች የራስ ተነሳሽነት የህዝቡ ግፊት ቢኖርም ባይኖርም ራሳቸው መሪዎቹ አምነውበት የሚገፉት የለውጥ አይነት ሲሆን ፣ ሁለተኛው አይነት ለውጥ ደግሞ ከራሱ ከህዝቡ በራሱ ግፊት የሚመጣና ሀገሩ የምትሄድበትን አቅጣጫ ራሱ እሚመራበትና እሚጠቁምበት ነው ። ብዙ ጊዜ ከታች የሚመጣን የለውጥ ግፊት ከላይ ያሉ መሪዎች የማይቀበሉ ወይም ለማዘግየት የሚሞክሩ ከሆነ ከብዙ ትእግስት በኋላ የለውጥ እንንቅስቃሴዎች ብሎም አብዮቶች ሁሉ ሊካሄዱ ይችላሉ ።

ስለዚህ ምንግዜም ቢሆን መሪው የለውጡን አቅጣጫና አካሄድ አስቀድሞ መገመትና መጠበቅ መቻል ሲኖርበት ፣ በአንድ በኩል የለውጡን ጥቅም ማየት ከቻለ ምንም እንኳን የራሱን ግላዊ ስልጣን እሚቀንስና እሚያሳጣ ሆኖ ቢገኝ ነገር ግን በታሪክ የሚኖረውን ስፍራውን በመልካም ለማስፈርና አይቀሬም ከሆነም ያንን ለውጥ ለማገዝ መደገፍ አንድ አማራጭ ሲሆን ፣ ነገር ግን የለውጡ ፍላጎት የብዙዎች ሆኖ እሱ ብቻውን ለማስቆምና ለመግታት ከሞኮረ ግን በታሪክ የሚኖረውን ቦታ ማበላሸት ብቻ ም ሳይሆን መሪነቱን ፍፃም ጥላሸት ሊቀናባው ፣ እና ቀድሞ የሰራቸውን ጥሩ ስራዎች ሊጋርድበትና ይችላል ። በእርግጥ ሀገራት ወደ ጥሩ ብቻ ሳይሆም ወደ መጥፎም አቅጣጫ ሊያመሩ ይችላሉ ፣ መሪው መጥፎው አቅጣጫ ማስቀየር እና ከመጥፎው ጎዳና መመለስ አንዱ ሀላፊነቱ እንደመሆኑ የለውጡን ምንነት ከሌሎች በተሻለ ሊረዳ የሚችልበት ቦታ ላይም እንደመሆኑ ተቋሙን ከመጥፎም መንገድ መጠብ ቅ አንዱ ሀላፊነቱ ነው ።

ሌላው ደግሞ አንድ መሪ ውድድሩን ካጠፋ ፣ የራሱን የሚመራውን ተቋም እድገት ያቀጭጨዋል ። ለተቋሙ ወይም ለሀገሪቱ የፖለቲካ እድገት እገዛን ሊያደርግ ይችል የነበረውን ፣ እንዲሁም ለወደፊቱ ሽግግር ወቅት ሲመጣ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችለውን ተቋማዊና ፣ እውቀትና የሰው ሀይል እድገት እንዲቀጭጭ ነው እሚያደርገው ። የጤናማ ውድድር መኖር ለተቋማትም ሆነ ለመንግስታት እድገት አስፈላጊ ነው ። በውድድር ባለበት አለም ውስጥ የመጨረሻ አሸናፊና ተሸናፊ እሚባል ነገር የሌለ ሲሆን በየትኛውም ውድድር ምንግዜም ጊዜያዊ ተሸናፊና ጊዜያዊ አሸናፊ ናቸው ያሉት ።

የውድድር አለመኖር ሊተካ የሚችልን ተቋማት አለመኖርን ያስከትላል ። ልዩነቶች መጠበቅና መኖር ሲኖርባቸው ። ልዩነቶችን ማጥፋት ወይም እንደሌሉ መቁጠር አማራጭ ሀሳብ እንዳይኖር ያደርጋል ። ለምሳሌ አንድ ሀሳብ መስራት ቢያቅተው እሱን የሚተካነ ወይም ያ ያልሰራውን ነገር ፣ በሌላ ሀሳብ እንዲቀጥል የሚያደርገው ሀሳብ ሊመጣ የሚችለው የተለየ ሀሳብ ካለው ተቋም ነው የሚሆነው ፣ ስለዚህ ልዩነቶች ምንግዜም መኖር ሲኖርባቸው ፣። ለምሳሌ በምእራቡ ኦመ አለም ብንወስድ በተለያየ ጊዜ የተለያየ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው ስልጣን የሚይዙት ፣ ሌላው ቀርቶ በአንድ መንግስት ውስጥ እንኳን ህግ አውጪው ወይም ፓርላማው በሌላ ፓርቲ ሊያዝ ይችላል ፤ ስለዚህ በመደራደርና ሰጥቶ በመቀበል ይመራሉ ።

ስፖርትን እንኳን ብንወስድ አንድ ቡድን በአንድ ውድድር ቢያሸንፍ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ሌላው ያልተጠበቀው ቡድን ያሸንፋል ፣ስፖርትን በውድድሩ ወቅት ካለው ትእይንት በተጨማሪ አጓጊ የሚያደርገው ይሄው ያልተጠበቀው ማሸነፍና መሸመፍ ናቸው ። በመሪነት ውስጥም ያልተጠበቀው ፓርቲ ተመርጦ ወደ ስልጣን ሊመጣ ሲችል ፣ የተጠበቀው ፓርቲ ደግሞ ሊሸነፍ ይችላል ። ስለዚህ ሽንፈትን እንደ መጨረሻ መወሰድ የሌለበት ሲሆን ማሸነፍም እንዲሁ ዘላለማዊ አይደለም ። አሁን ያሸነፈ ፓርቲ ከጥቂት አመታት በኋላ ተሸናፊ ሆኖ እሚገኘው እሱ ይሆናል ፤ ተሸናፊውም በሚቀጥለው ጊዜ ድሉ የእርሱ ይሆናል ።

ለምሳሌ በምእራባውያን ሀገራት በእንግሊዝ ሀገር ሌበር ፓርቲ ወደ ስልጣን ሲመጣ ለንደንን የአለም አቀፍ የፋይረናንስ ማእከል ሲያደርግ ወደ ግራ ዘመም የሆነው ይሄው ፓርቲ የወሰደው አቋም ፣ ወግ አጥባቂዎቹ ወደ ስልጣን ቢመጡ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሲሆን ይህም በሁለቱ ፓርቲዎች መሀከል ልዩነትን ሲያጠብ ለመራጩ ህዝብም አማራጩን ይዘጋበታል ። ምክንያቱም በሁለቱ መሀከል ስልጣን ሲይዙ ልዩነታቸውን ማወቅና አማራጭ ፖሊሲ አይኖርም ።

በአሜሪካን አገርም እንዲሁ በሁለቱ መሀከል ያለው ልዩነት ግብርን በመጨመር ፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ ላይ ሲሆን ከዚያ ውጪ ግን በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ልዩነታቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ሲሆን ፤ አንዱ የጀመረውን ጦርነት ስልጣን ከመያዙ በፊት ሌላኛው ቢያወግዘውም እርሱም በተራው ስልጣን ሲይዝ ግን ጦርነቱነን አባብሶ ይቀጥለዋል ። ይህም በቀድሞው ፕሬዝደንት ቡሽ የተጀመረውን ጦርነት ስልጣን የተረከቡት ዲሞክራቶች ከማስቆም ይልቅ ይበልጥ በተለያየ መንገድ እየተዘፈቁበት ስለመጡ አንዱ የህዝብ ደስተኛ አለመሆንና መራጩ ህዝብ ሊኖረው የሚችለውን አማራጭ ከማጥበቡም በላይ ፅንፈኛ ቡድኖች ተሰሚነታቸው እየጨመረ ስለሚመጣ ለፖለቲካ ስርአቱ ጤናማነት አደጋን ይደቅናል ።

ሌላው አንድ መሪ የሚመራበትም ዘመንም ራሱ ይወስነዋል ። ለምሳሌ የሰላም ዘመን መሪ ፣ ለጦርነት ጊዜ ላይሆን ይችላል ። የጦርነት ጊዜ መሪ ደግሞ የሰላም ዘመን መሪ ላይሆን ይችላል ። የችግር ጊዜ መሪዎች በአብዛኛው ሀይለኛና ፣ሌሎችን የሚጫኑ ሊሆኑ ይችላሉ ። በጦርነት ወይም በእግር ሰአት በእርግጥ የዛ አይነት አመራር ሊያስፈልግ ይችላል ። ይሁን እንጂ የዚህ አይነት መሪዎች ችግሩ ካለፈ ፣ በኋላ ግን በቀድሞው የአመራር ዘያቸው መቀጠል አይችሉም ። ሁኔታዎች ስለተቀያየሩ ፣ የአመራራቸውም መንገድ መቀየር ሲኖርበት በቀድሞው በችግሩ ሰአት ይሰጡት የነበረውን የአመራር መንገድ ከተከተሉ ግን እንደ ቀድሞው ውጤታማ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው ።

ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሆኑት ዊኒስተን ቸርችል ሲሆኑ እንግሊዝን ከናዚ መንጋጋ ማዳን ቢችሉም በሰላሙ ጊዜ ግን በምርጫ ተሸንፈዋል ። በእርግጥ ቸርቺል ድጋሚ ያልተመረጡት መራጩን ህዝብ ውለታ ቢስ ስለሆነ ሳይሆን በጦርነት ጊዜ አንድ መሪ የተከተለው ስረትራቴጂና በሰላም ወይም ትልቅ ችግር በሌለበት ሰአት የሚኖረው የአመራር ስልት የተለያየ ስለሆነና መሪው ራሱን ለሁኔታዎች ጋር ካለማዛመድና ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ። ጥሩ የአብዮት ወቅት መሪም ብቃት ያለው የሰላም ጊዜ መሪ ላይሆን ይችላል ፤ ብዙ መሪዎችን አብዮትን በመምራት የተዋጣላቸው አብዮቱን ካሳኩ በኋላ ግን በሰላሙ ጊዜ ግን እንደ ቀድሞው ስኬታማ መሆን ሲያቅታቸው በታሪክ በተደጋጋሚ ተስተውሏል ።

አንዳንዶቹ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ትተውት ወይንም ጥለውት ስለሚሄዱት አሻራ (legacy) ወይም የታሪክ ቅሪት ብዙም አይጨነቁም ። ከዚያ ይልቅ የሚያስጨንቃቸው ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት ነው ። አፍሪካ ውስጥ በርካታ መሪዎች ከ30 አልፎ አልፎም አንዳንዶቹም ከ40 አመት በላይ ስልጣን ላይ መቆየት የቻሉ እንዳሉ የታወቀ ነው ። ይሁን እንጂ ለአንድ ፓርቲ የበለጠ በታሪክ ቦታ የሚያሰጠው ነገር ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየቱ ሳይሆን ለዛ ሀገር ምን ዘላቂ ነገር ትቶ ሄደ የሚለው ነው ። ይሄም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲ ባላደገባቸውና ገና በጅምር ደረጃ ባለባቸው ሀገራት ውስጥ ስልጣን አንድ ግዜ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ከገባ ከሌላው አማራጭ ዘግተው ለረጅም ግዜ ስልጣን ላይ ይቆያሉ ፣ አንድ ግዜ ስልጣናቸውን ካጡ የሚደርስባቸውን ግለሰባዊ የሆነ ኪሳራ ስለሚረዱ በተቻለ መጠን ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት ጥረት ያደርጋሉ ።

ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካን መሪዎች ብንወስድ አንዳንዶቹ በትጥቅ ትግል ስልጣን የያዙ ሲሆኑ ከሌላው የአፍሪካ ሀገራት ደካማ የዲሞክራሲ ሂደት የሚታየውም በዚሁ አካባቢ ነው ። በአንድ በኩል ክልሉ ከአፍሪካ በጣም አደገኛው እንዲሁም አለምን የሚያሳስቡ ተደጋጋሚ ድርቅና ረሀብ ፣ የሰብአዊ ድቀት የሚታይበት ክልል መሆኑ አይካድም ።

በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙ አለማቀፋዊ ውግዘትንና በመፍራትና ወታደሮችም ስለሆኑ አገር ለመምራት የሚያስችለው ህዝባዊ ይሁንታና ውክልና (legitimacy) ስለማይኖራቸው ፣ የአገር ውስጥ ተቀባይነትን በማጣት ስልጣንን ሲያስረክቡ ብዙውን ጊዜ በትጥቅ ትግል ስልጣን የያዙ ግን በምርጫ ቢሸነፉ እንኳን በቀላሉ ስልጣን አያስረክቡም ። በእርግጥ የአሁኖቹ የአፍሪካ መሪዎች ከቀደምቶቹ አንፃር የልማትን አስፈላጊነት የተገነዘቡ ናቸው ይሁን እንጂ የዲሞክራሲውም ጉዳይ መዘንጋት የለበትም ።

የአንድ መሪ ስራ ለበርካታ ዘመን ዘላቂ ሊሆን የሚችለው የእሱ የጀመረውን ነገር ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ካስቻለ ብቻ ነው ። ለምሳሌ የታላላቅ ሀይማኖት መስራቾች ብንወስድ እነሱ ካለፉ በኋላ እነኛ ሀይማኖቶች ዘላቂ ሆነው ለሺ ዘመናት ሊዘልቁ የቻሉበት አንዱ ምክንያት በአንድ ሰው ግርማ ሞገስና ሀያል ከሆነ ከተፈጥሮ ልእልና በላይ ከሆነ ካገኘው ሀይል በተጨማሪ ውጪ በሰዎች ዘንድ ያ ነገር ተቋማዊ መሆን በመቻሉ ነው ። እና ተቋማዊ በሆነ መንገድ አስተምህሮቶቹ ፣ አስተሳሰቡና አደረጃጀቱ በተቋም መልክ ሊተላለፍ በመቻሉ ነው ።
ለምሳሌ የሀያሏን ሀገር አሜሪካንን ብንወስድ ፕሬዝዳንቶቿ ስልጣን ላይ እሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ሲሆን ቢበዛ ከስምንት አመት አይበልጥም ። ይሁን እንጂ በአለም ላይ ሀያል እንደመሆኗና በብዙ ነገር ላይ መሪዎቹ አሻራቸውን አሳልፈው ስለሚሄዱ ትተውት የሚሄዱት አሻራ ግን ለረጅም ጊዜ ይቆያል ።

አንዳንድ ጊዜ ለአጭር ጊዜ ግብ ወይም ለጊዜው አማላይ መስለው ለሚታዩ ነገሮች ተብለው እሚደረጉ ነገሮች በረጅም ጊዜ የመሪውን የታሪክ አሻራ ወይም ትቶት ሊሄድ የሚችለውን መልካም ስምና ዝና የሚያበላሹ ሊሆኑ ይችላሉ ። በመጀመሪያ የዚህ አይነት ነገሮችን መሪው በሚገባ መረዳት አለበት ። ከፍተኛ ጥንቃቄንና ብስለትንም የሚጠይቅ ሁኔታን ይፈጥራል ። ለምሳሌ መሪው ጊዜያዊ ዝናን የሚያስገኝለትን ፣ ወይም ስልጣኔን ያስጠብቅልኛል በሚል ወደፊት ስሙን በመልካም እንዲነሳ የማያደርጉትን ነገሮች ሊፈፅም ይችላል ።

ትቶት ስለሚሄደው አሻራ እሚወስነው ራሱ መሪው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ለአጭር ግዜ ግብ ወይም ለአጭር ጊዜ የፓርቲ ጥቅምን እሚያስገኙ ነገር ግን በረጅም ጊዜ የመሪውን አሻራ እሚጎዱ ነገሮች ይከሰታሉ ። ለምሳሌ ፕሬዝዳንት ቡሽ አሸባሪዎችን በጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ውስጥ ያለ ፍርድ ሲያጉሩና ፣ በእስረኞች ላይ ስቃይ እንዲፈፀም ሲፈቅዱ ፣ አንዳንድ የራሳቸው ባለስልጣኖች ሳይቀሩ የፕሬዝዳንቱን በታሪክ የሚኖራቸውን ቦታወይም የታሪክ አሻራቸውን (legacy) ይጎዳል ብለው ተከራክረዋል ። በእርግጥ በዚህ መንገድ አሜሪካ በርካታ ጠቃሚ መረጃዎችን ፣ ቢንላደንን ለማግኘት ያስቻላትን መረጃ ጭምር በዚህ መንገድ ለማግኘት ብትበቃም የአሜሪካንን አለም አቀፋዊ ገፅታ ግን ክፉኛ ጎድቷል ።

የዚህ አይነቱን አሻራ የሚወርስ መሪ ለወራሹ መሪ መልካም አይደለም ። ኦባማን የወረሱት የቡሽን ውርስ ሲሆን ለማስተካከል 4 አመት ስላልበቃ መራጩ ህዝብ ጨምሮላቸዋል።በአራት አመት ውስጥ ከችግሩ ጥልቀት የተነሳ ማስተካከል አለመቻሉን የተረዳው ህዝብ ። መሪዎች ስማቸው ተያይዞ እንዲነሳ የማይፈልጉትን የታሪክ ውርስ በሚወርሱበት ወቅት ከዛ ከወረሱት መልካም ካልሆነ ነገር ጋር ለመላቀቅ ጥረትን ማድረግ ይገባቸዋል ። ሌላው ከጆን ኤፍ ኬኔዲ በኋላ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት የነበሩት ሊንደን ቢ ጆንሰን ምንም እንኳን በአሜሪካ ታሪክ የሁለተኛውን የአለም ጦርነትን አሜሪካንን መርተው በድል የተወጡትን እንዲሁም አለምን ከናዚዎችና ከፋሽስቶች መንጋጋ ነፃ ያዉ ካወጡት ከፍራንክሊን ሩዝቬልት ቀጥሎ በ20ኛው ክፍል ዘመን በርካታ ቁም ነገሮችን ለሀገራቸው ያከናወኑ ናቸው ። ነገር ግን ምንም እንኳን ጆንሰን በወቅቱ አሜሪካንን አብጠው የነበሩትን ችግሮችን ማለትም የአፍሪካ አሜሪካውያንን መብትን የሚያስከብሩ በርካታ ህጎች የወጡበትና ስራ ላይ የዋሉበት ሲቪል መብቶችን ፣ ሲሆን ነገር ግን ምንም እንኳን የቬትናም ጦርነት ቀድሞ በነበሩት በኬኔዲ አማካይነት የተጀመረ ቢሆንም ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው ግን በእርሳቸው ዘመን በመሆኑ አሜሪካ በዚህ ጦርነት ከባድ ዋጋንና ብሎም ሽንፈትን ልትከናነብ ብቅታለች ። በዚህም በመላው አሜሪካን የተማሪዎችና የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ የተጥለቀለች ሲሆን አንዳንዶቹም ለወታደርነት ምልመላን በመስጋት ወደ ካናዳና ስዊድን ወደ መሳሳሉ አገራት ለመሰደድ በቅተዋል ። በዚህም ጆንሰን በድጋሚ ላለመወዳደር ወስነው ራሳቸውን ከፖለቲካው አግልለዋል ። በታሪካቸውም ምንም እንኳን በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ያከናወኑ ቢሆንም ይህ ጦርነት በሀገራቸው ላይ ያስከተለው ጠባሳ ግን በታሪካ ያላቸውን አሻራ ሊያደበዝዘው በቅቷል ።

መሪው ራሱ በረጅም ጊዜ ሊተወው ስለሚችለው የታሪክ አሻራ ላይም ማሰብ አለበት ። በዚህም ምክንያት ብዘዉን ጊዜ መሪዎች የተደበላለቀና እርስ በእርሱ የሚጋጭ (Mixed Legacy) ትተው ሊያልፉ ይችላሉ ። ይኀውም ለአጭር ጊዜ ጥቅም ወይም ግብ ሲሉ በሚፈፅሟቸው ድርጊቶች የተነሳ ነው ። ነገር ግን አንድ መሪ ዘመን አይሽሬ በሆነ ሁኔታ በበጎ መነሳት ከፈለገ ቀላሉ መንገድ መሰረታዊ ለሆኑ መርሆዎች ራሱን ማስገዛት ነው ። ይህም ከመርህ ያፈነገጡ ፣ እንዲሁም ጉዳትን ሊያደርሱ የሚችሉ ድርጊቶችን ከመፈፀም ይጠብቀዋል ። በታሪክ ጥፋትን ያስከተሉ ድርጊቶች ፣ ከመርህ እጅግ ያፈነገጡ ፣ ድርጊቶች ናቸው ። ለምሳሌ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች በአውሮፓ አህጉር የፈፀሙት ወንጀል ፣ አውሮፓ ከምታምንበት ከክርስትና ሀይማኖትም ሆነ ከደግነት ወይንም ከሰብአዊነት (Humanism) ፍልስፍና በእጅጉ ያፈነገጠ ድርጊትን በመፈፀማቸው ታሪክ የማይረሳውን አሰቃቂ ወንጀልን በመፈፀም በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ ጨለማ የሆነ የታሪክ ቅርስን ትተው አልፈዋል ።

የሀገር መሪ ከሆነ ሀገራት ካላቸው በሺዎች አመታት ከሚቆጠረው ዘመናት ውስጥ ፣ አንድ መሪ በስልጣን ላይ የሚቆይበት ዘመን እጅግ በጣም አጭር ነው ። እድሜ ጠገብ ከሆኑት ሀገራት አንፃር እንደ ቅፅበት የሚቆጠር ነው ፣ ለዚህም ነው መሪው ትቶት የሚያልፈውን አሻራ መጠንቀቅና ማሰብ የሚኖርበት ።

መሪው የሚተወው አሻራ የራሱ ህሊናዊ ንቃት ደረጃ ይወስነዋል ። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለሺዎች ዘመናት የቆየ የታሪክ አሻራን ትትው ያለፉ ሰዎች ከፍተኛ ህሊናዊ ንቃት ያላቸው ሰዎች ናቸው ። እነኚህም ሙሴ ፣ ቡድሀ ፣ ክርስቶስ፣ ባሀኡላ የመሳሰሉት ረቂቅ መንፈሳውያን (mystics) የነበራቸው ንቃተ – ህሊና ከፍተኛ በመሆኑ ትተውት ያለፉት መንፈሳቸው ለሺዎች አመታት የዘለቀ ነው ። በእርግጥ መሪዎች የዚህን ያህል ንቃትና ግንዛቤ ይኑራቸው ባይባልም በተወሰነ ደረጃ ህሊናዊ ንቃት ቢኖረው ግን በተሻለ ሁኔታ ሊመራና ፣ መልካም የታሪክ ቅርስን ትቶ እንዲያልፍ ያስችለዋል ።

አንድ መሪ የሚመራበትም ዘመን ራሱ ይወስነዋል ። ለምሳሌ የሰላም ዘመን መሪ ፣ ለጦርነት ጊዜ ላይሆን ይችላል ። የጦርነት ጊዜ መሪ ደግሞ የሰላም ዘመን መሪ ላይሆን ይችላል ። የችግር ጊዜ መሪዎች በአብዛኛው ሀይለኛና ፣ሌሎችን የሚጫኑ ሊሆኑ ይችላሉ ። በጦርነት ወይም በእግር ሰአት በእርግጥ የዛ አይነት አመራር ሊያስፈልግ ይችላል ። ይሁን እንጂ የዚህ አይነት መሪዎች ችግሩ ካለፈ ፣ በኋላ ግን በቀድሞው የአመራር ዘዬአቸው መቀጠል አይችሉም ። ሁኔታዎች ስለተቀያየሩ ፣ የአመራራቸውም መንገድ መቀየር ሲኖርበት በቀድሞው በችግሩ ሰአት ይሰጡት የነበረውን የአመራር መንገድ ከተከተሉ ግን እንደ ቀድሞው ውጤታማ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው ።

ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሆኑት ዊኒስተን ቸርችል ሲሆኑ እንግሊዝን ከናዚ መንጋጋ ማዳን ቢችሉም ሰላም ከመጣ በኋላ ግን በምርጫ ተሸንፈዋል ። ቸርቺል ድጋሚ ያልተመረጡት መራጩን ህዝብ ውለታ ቢስ ስለሆነ ሳይሆን በጦርነት ጊዜ አንድ መሪ የተከተለው ስትራቴጂና በሰላም ወይም ትልቅ ችግር በሌለበት ሰአት የሚኖረው የአመራር ስልት የተለያየ ስለሆነና መሪው ራሱን ለሁኔታዎች ጋር ካለማዛመድና ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ። ጥሩ የአብዮት ወቅት መሪ ብቃት ያለው የሰላም ጊዜ መሪ ላይሆን ይችላል ፤ ብዙ መሪዎችን አብዮትን በመምራት የተዋጣላቸው አብዮቱን ካሳኩ በኋላ ግን በሰላሙ ጊዜ ግን እንደ ቀድሞው ስኬታማ መሆን ሲያቅታቸው በታሪክ በተደጋጋሚ ተስተውሏል ። የፈረንሳይ ፕሬዝደንት የነበሩትም ደጎልም እንዲሁ ሀገራቸውን ከወራሪዎቹ ናዚዎች ነፃ ማውጣት ቢችሉም እንዲሁ በህዝብ ምርጫ ከውድድሩ ሜዳ ተወግደዋል ።

መሪዎች የመምራት ህጋዊ ተቀባይነታቸውንና ውክልናቸውን የሚያጡት በርካታ ስህተቶችን ከሰሩና የሚመሩትን ሀገር ወይም ድርጅት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ በመምራት ብዙ ዋጋን ካስከፈሉ በኋላ ሲሆን ከብዙ ትእግስት በኋላ ፣ ህዝቡ በሚነሳባቸው ወቅት የመምራት ፣ ህጋዊ ተቀባይነታቸውንና ውክልናቸውን (Legitimacy) ለማጣት ይገደዳሉ ። ይህ ብቻ ሳይሆን እየቆዩ በሄዱ ቁጥር ስህተታቸውና አጓጉል ስራም ከሰሩ የስራቸው ውጤት ቁልጭ ብሎ መታየት ስለሚጀምር የተቃውሞ ድምፆች እየበረታባቸው ይሄዳል ። በተለይ ለአንድ መሪ አነሳስ በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው ። ሲጀመር ስህተቶችን የሰራ መሪ ከዛ በኋላ ለማስተካከል በጣም ይቸገራል ።

ልክ ሯጮች አነሳስ ላይ እንደሚጠነቀቁት ፣ አነሳሳቸው ከተሳሳተ ከውድድር ወጪ እስከመሆን ወይም በሌላው ሊደርሱበት በማይችሉበት ሁኔታ መቀደም ደረጃ ድረስ ይደርሳሉ ። በተለይም ከሰው ልጅ ስነ – ልቦና ጋር የተያያዙ ነገሮች አጀማመራቸው በጣም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ።ምክንያቱም ከአንድ አዲስ ሰው ፣ወይም ህዝብ ጋር ስንተዋወቅ ትውውቃችን በጥሩ መንገድ ከተጀመረ ከዛ በኋላ በጥሩ የመቀጠል እድሉ ሰፊ ነው ፣ ስህተቶች በኋላ ላይ ቢሰሩም መጀመሪያ ላይ ከሚሰሩት የበለጠ ትኩረት አይደረግባቸውም ።

በነገራችን ላይ የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች ልክ ተመርጠው እንደመጡ ፣ የህዝብ ድጋፍ ሳይቀዘቅዝ አወዛጋቢ ሊሆኑ የሚችሉ ህጎቹን ኮንግሬሱ እንዲያሳልፍ እሚያደርጉት ። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ መሪዎች አወዛጋቢ የሆኑ ውሳኔዎቻቸውን በእለተ – አርብ ይፋ ማድረግም የተለመደ ነው – ቅዳሜና እሁድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስለሚዘጉ ወዲያውኑ የከረረ ተቃውሞ እንዳይገጥማቸው በመፍራት ።እየቆዩ ሲሄዱ የህዝብ ድጋፍ እየተዳከመ ስለሚሄድ መጀመሪያ የነበራቸው ድጋፍ ስለሚቀንስ ፣ ቆየት ብለው ከሚያደርጉት ይልቅ ወዲያው እንደተመረጡ ብዙም ሳይቆዩ እነዛን በኋላ ላይ ቢሆን አጨቃጫቂ ፣ አወዛጋቢ ሊሆኑ የሚችሉ አዋጆችን እሚያሳልፉት ፣ ይሄ በሎችም ዘርፎች በደንብ የሚሰራ ነው ።

አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ከተነሱበት አላማ የመዘናጋት ፣ ብሎም የመውጣት አዝማሚያዎች ሊፈታተኗቸው ይችላሉ ፤ ብዙውን ጊዜ ለማሳካት ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለባቸው ስኬቶች ዘላቂ የሆነ አላማቸውን አሻራን ጥለው ማለፍ አለባቸው ። በመሰረታዊነት የተነሱበትን ግብ መቼም ቢሆን መሳት የለባቸውም። ብዙ ሰዎች ያን ያህል መስዋእትነት እሚከፍሉት የዛን ሀሳብ ዘላቂነትና ዘመን ተሻጋሪነት በመረዳት ነው እንጂ ትልቅ አላማ ለሌለው መጀመሪያም ቢሆን ብዙ ደጋፊዎችንና መስዋእትነትን እሚከፍሉ ሰዎች አያገኝም ፤ በእንደዚህ አይነት መስዋእትነት የተገኙ ድሎች እንደ ታሰበላቸው አላማ ዘመን ተሻግረው መሄድ አለባቸው ። ስለዚህ የዚህ አይነት ድሎች መሰረታዊ አላማቸውን እንዳይስቱ ጥረት መደረግ አለበት ። ይሄ መሪው እሱም ሆነ ሌሎች ከተነሱበት አላማና ግብ ላለመውጣት ከሀዲዱ ላለመውጣት መሪ አቅጣጫ ይሆነዋል ።

አንድ መሪ ለሚፈጠሩ ችግሮች ወይንም ለፈተጠሩ ችግሮች ምንም እንኳን ፣ አመርቂ ምክንያት ንና ትንታኔን መስጠት የሚችል ቢሆንምና ፣ ትንታኔ ቢሰጥም ፣ ነገር ግን ውሎ አድሮ ግን እውነተኛ መፍትሄን መስጠት መቻል አለበት ። እንጂ ችግሩ በተደጋጋሚ ሲቀርብለት ምክንያትን ቢደረድርም ፣ ነገር ግን በተግባርም ምላሽን እና መፍትሄን ማግኘት መቻል አለበት ።ይህም ብቻ ሳይሆን ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄን ያልሰጠ መሪ ፣ ምንም እንኳን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እርሱ የተስማማው ቢሆንም ፣ ወቅታዊ የሆነው ነባራዊ ሁኔታ (Stasus Quo) ግን ዘላቂ አይሆንም ።ምላሽን መስጠት ካልቻለ ግን የመ ሪነት ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ሌል ሎች የጠቃውሞ ድምፆች ተሰሚነት እያገኙ እንዲሄዱና በአመራር ብቃቱ ላይ ጥርጣሬን እንዲያጭር ያደርጋል ።

ስለሰዎች ባህሪ የተለያዩ አስተሳሰቦች ያሉ ሲሆን ፣ hይማኖቶችን ብንወስድ ሰዎች በመሰረቱ ጥሩዎች ናቸው ነገር ግን ከእነሱ ፍላጎት ውጫዊ ሀይል ወይም የሚገፋፋቸው ነገር ሰይጣን ያሳስታቸዋል የሚል ነው ። ሌላው ደግሞ ሰዎች ላያውቁ ይችላሉ (Unconscious) ሊሆኑ ስለሚችሉ ለሚያደርጉት ነገር ትልቅ ሀላፊነት ሊጣልባቸው አይችልም ፣ ስለዚህ በትክክለኛው መንገድ አቅጣጫ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው ፣ ሌላው ደግሞ ከቅንነት ልቦና ውጪ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ስለዚህ መሪው ይህንን እውነታ በመረዳት ፣ ያንን ሊያስቀር የሚችል አካሄድን መከተል አለበት የሚል አሰተሳሰብ አላቸው የሚሉም አሉ ።