የዲሞክራሲ ስርአትና ፈተናዎቹ

በአለም ላይ ገናና ከነበሩት ሀያላን መሀከል የሮማውያንንም ብንወስድ አውሮፓን ፣ሰሜን አፍሪካንና ከእስያም እየሩሳሌምን ጨምሮ ሰፊ ግዛትን አስተዳድረዋል ።ይሁን እንጂ የሮማውያን ስርአት ከሪፐብሊክነት ወደ ዘውዳዊ ስርአት በመቀየሩ ስለ አስተዳደር ምንም በማያውቁ ቤተመንግስት ውስጥ በተወለዱና የነገስታቱ ልጆች በመተካቱ ስርአቱ የኋላ የኋላ ፍርስርሱ ወጥቷል ። በነገራችን ላይ የዲሞክራሲ ስርአትም ቢሆን መጨረሻ ላይ ከውስጥ የሚፈታተነው ችግር ሊያጋጥመው ይችላል ። ዲሞክራሲ ደግሞ ከውስጥ የመታወክ (Degenerate) የማድረግ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።

ለምሳሌ የጥንት ግሪካውያን ስርአት የዲሞክራሲ ስርአት የነበረ ቢሆንም ዲማጎጎች ተነስተው ህዝቡን አሳመነው ስልጣን ይዘው ብዙም ሳያስቡ ጎረቤት ሲሲሊን በመውረራቸው ምክንያት የምእራቡ አለም ስልጣኔ መሰረት ተደርጎ እሚቆጠረው የግሪክ ስልጣኔ ሊንኮታኮት በቅቷል ።

የዲሞክራሲ ስርአትም አንድን ሀያል የሆነ አገር ከውድቀት አያድነውም ፣ ይሁን እንጂ መሪዎቹና ህዝቡ ከሌሎች ስርአቶች በተሻለ ሁኔታ ስርአቱ አደጋ ሲገጥመው ሊታደጉት ይችላሉ ።ማንኛውም በተቋም ደረጃ ያለ ፓርቲ ፣ መንግስት ፣ የንግድ ድርጅት ይሁን መጨረሻ ላይ የማቆልቆልና የመውደቅ አደጋ አይቀርለትም ።ለዚህም አንድ ነገር ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ መጨረሻ ላይ ለምንድነው እሚያቆለቁለው ተብሎ ቢጠየቅ በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ ። ቀድሞ እንደነበረው ፈጣን የሆነና አዲስ የሆነ ነገርንና አዲስ አቅጣጫን የሚፈጥር (Dynamic ) የሚጠቁምና አንድ የሚያደርግ መሪ ማጣት ፣ ከውስጥ የሚነሱ የከረሩ የእርስ በእርስ ውድድሮችና ሽኩቻዎች ፣ የመሪዎችየተቋሙን ወይንም ድርጅቱን ጥቅም ለራስ ወዳድነት አላማቸው ማዋል ፣ ከውጪ የሚመጣ ውድድርና ጫና ፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ለውጦችየሚሉናቸው ።ይህም በአጠቃላይ የዛ ተቋም ህልውና ቸል እየተባለ ለግላዊ ለሆነ ስልጣን ፣ሀብት ፣ዝና መሯሯጥ ሲጀምሩ የዛ ተቋም ወይም ሀገር ሀያልነት እያሽቆለቆለ ይሄዳል።  ከዚህም ሁሉ በተጨማሪ ደግሞ አገዛዙ በሀብታሞች በቀላሉ መጠለፍና ወደ በሎቢስቶች አማካይነት በድጋፍ አሰባሳቢዎች አማካይነት ወደ የብዙሀኑ ህዝብ ኪሳራ ወደ ሀብታሞች ጥቅም አስጠባቂ (ፕሉቶክራሲ) አገዛዝ ሲቀየር ደግሞ ሌላው ስጋት ነው ።

ትልቁ የዲሞክራሲ ጠላቶች ከውስጥ የሚነሱት ሀሳዊ የዲሞክራሲ ሀዋርያዎች (Demagoug) እንዲሁም በሰላ አንደበት በሚስብ ንግግር በማድረግ ማሳመን የሚችሉ ነገር ግን ክርክራችው ጥልቀት የሌለው (Sofists) ናቸው ። እነኚህ በቀላሉ በዲሞክራሲ ስርአት በህዝብ ጭምር ተመርጠው ወደ ስልጣን ሊመጡ ይችላሉ ። ምናልባት እነኚህ በጥንታዊ በግሪክ ዘመን ብቻ ያሉ ሊመስለን ይችላል ይሁንና በማንኛውም ዘመንና ጊዜ አብረው የሚኖሩ ናቸው ።

ሌላው ፖለቲከኞች ለአጭር ጊዜ ለመመረጥ ሲሉ ፣ የአጭር ጊዜ እሚያሳኩ ድርጊቶችን ሊያደርጉ ይችላሉ ። ስነ – ምግባርን ወይም ሞራልን ለጊዜያዊ ስልጣን ሲሉ መስዋእት ሊያደርጉት ይችላሉ ። ይህም በረጅም ጊዜ ሀገሮችን እንዲጎዳና መሰረታዊ መፍትሄን የሚፈልጉ ችግሮች ሳይፈቱ እየተደራረቡ አንዲቆዩና መፍትሄ ለመፈለግ አስቸጋሪ እስከሚደርሱበት ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ ።

ፕሌቶ እንደሚለው «ሰዎች የተሻሉ መሪዎቻቸውን ለመምረጥም ሆነ የተሻለውን መንገድ ለመከተል በትምህርት አማካይነት በቂ ዝግጅት ስለማያደርጉ የኋላ ኋላ የዲሞክራሲ ውድቀት ምንጭ ይሆናል »። ይህ ብቻ ሳይሆን እውቀትም ጭምር በጊዜ ውስጥ ይቀየራል ። በአንድ ወቅት ትክክልነው ተብሎ የሚታመንበት ነገር ውሎ አድሮ ሌላ ሆኖ ሊገኝ ይችላል ።

 

ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ያሉ ሀያላን ለመከላከያ የሚያወጡት ወጪ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም ። ይህንንም ደግሞ ተራው መራጭ ህዝብ ይደግፈዋል እንጂ አይቃወመውም ። ነገር ግን ምእራባውያን ከገቡበት ከፍተኛ አገራዊ እዳ አንፃር በረጅም ጊዜ ምርታማ ላልሆነው ወታደራዊ ወጪን ማውጣት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና አይረዱትም ። ምንም እንኳን ወታደራዊ ኢንዱስትሪው የስራ እድሎችን የሚፈጥር ቢሆንም ፣ ነገር ግን የሚፈጥረው የስራ እድል ምርታማ የሚባል አይነት የስራ እድልን አይደለም ። በዚህ ምክንያት ከሁለቱም ከዲሞክራቶችም ሆነ ከሪፐብሊካኖች ፓርቲ ተወካዮች ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪን የሚደግፉ ናቸው ። የአሜሪካንን ወታደራዊ ወጪን ብንወስድ ወጪዋ እየጨመረ ነው እንጂ እየቀነሰ አልሄደም ። ስለዚህ የፕሌቶ አባባል ፈላስፋዎች መሪዎች ወይም ነገስታት መሆን አለባቸው የሚለው ትክክል ሳይሆን አይቀርም ።

ይህ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ስርአትም ቢሆን ከውስጡ የሚፈጠሩ ተቋማት ፣ በውስጠ – ታዋቂ ከዋናው መንግስት በላይ የሆነ ስልጣንን ሊይዙና የዲሞክራሲ ስርአቱን ሊሸረሽሩት ይችላሉ ። ይህም በተለይም ኤድጋር ሁቨር የተባሉ ሰው የኤፍ ቢ መሪ በነበሩት ወቅት የታየ ሲሆን ተደጋጋሚ ሰሲ አይ ኤም ከዋናው የአሜሪካ የፖለቲካ መሪዎችና የኮንግሬስ አባላት እውቅና ውጪ የተንቀሳቀሱባቸው ሁኔታዎች ታይተዋል ፣በተለይም ሲአይኤ፣ኤፍ ቢአይና ፔንታጎንን የመሳሰሉ የአሜሪካ ተቋማት ከፍተኛ ስልጣንና ጉልበት ያላቸው ናቸው ። የዲሞክራሲ ስርአትም ቢሆን በስሩ ያሉትን ተቋማት በብቃት መቆጣጠር ካቃተው የዲሞክራሲስርአቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ።

ለምሳሌ በ2011 ግሪክና ጣሊያን የእዳ ቀውስ ውስጥ በገቡበት ወቅት የምጣኔ – ሀብትና የአስተዳደራዊ ባለሙያዎች (Technocrats) ወደ ስልጣን መጥተዋል ። ነገር ግን ለአጭር ጊዜም ቢሆን የፖለቲካ መሪዎች ያንን ችግር የመወጣት አቅሙና ብቃቱ በማይኖራቸው ወቅት ቴክኖክራቶች ወደ ስልጣን መምጣታቸው ፣ የዛን ሀገር ችግር ሊያቃልል ሲችል ፣ ሌላው ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ተወዳጅነታቸውን ላለማጣት ሲሉ ፣ የማይወስዷቸው እርምጃዎች እነኚህ ቴክኖክራቶች ሊወስዱ ስለሚችሉ ለጊዜውም ቢሆን ለአጭር ጊዜ ስርአቱን ለማዳን ሊያስችሉ ይችላሉ ። ነገር ግን በቀጥታ በህዝብ የተመረጡ ባለመሆናቸው የህጋዊ ውክልና (Legitimacy) ችግር ግን እንዳለባቸው መዘንጋት የለብንም ፣ በዚህም ምክንያት ስልጣን ላይ የሚቆዩበት ጊዜ በጣም አጭር ነው ።

የየትኛው ሀገር ህገ – መንግስት ቁልፉ ያለው በዳኝነት ስርአቱ ውስጥ ነው ። ይህም ህገ – መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን በተሰጠው አካል ላይ ይወሰናል ። ለምሳሌ አሜሪካንን ብንወስድ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን የአሜሪካ ፕሬዝዳነት የጎደለ ዳኛ ሲኖር መሾም ይችላል ፣የነበሩትን መሻር ግን አይችልም -በራሳቸው ወይም በጤና ችግር ምክንያት ካለቀቁ በስተቀር ፣ ። ኮንግሬሱ ወይንም ክፍላተ – ሀገሮች የሚያወጧቸው አዋጆች አጨቃጫቂ ሆነው ከተገኙ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያመራሉ ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ አሳሪና የመጨረሻ ነው ። ህገ – መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው ። በ2012 ዓ .ም. በጤና መድህን «ኦባማ-ኬር» ላይ በኦባማ አማካይነት የወጣው ህግ አጨቃጫቂ የነበረ በመሆኑ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሲያመራ አብዛኛውን የህጉን ክፍል ተቀብሎ ፣ ጥቂቱን ብቻ ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል ። ነገር ግን አንዳንድ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ህጉን አብላጫ የኮንግሩስ አባላትን በመያዝ ውድቅ እናደርገዋለን ብለው ቢዝቱም ህጉ ግን ህግ ሆኖ ሊወጣ በቅቷል ። ምንም እንኳን  ህጉን መልሰው ከተወሰኑ አመታት በኋላ በአዲስ ህግ መሸራረፍና በራሳቸው መንገድ ማውጣት ቢችሉም ለጊዜው ግን አብዛኛው የህጉ ክፍል ህግ ሆኖ ሊወጣ ችሏል ።

በሌሎች ሀገራት ግን ዳኞች በአስፈፃሚው አማካይነት በቀጥታ የሚሾሙ ሲሆን ፣ አስፈፃሚው ልክ ሌሎች የመንግስት ተሿሚዎችን በሚሽርበት መንገድ ሊሽራቸው ይችላል ። ለምሳሌ ህገ – መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሆነ ፣ ከፍርድ ቤት ይልቅ የፖለቲካ ተመራጮች ናቸው ማለት ነው ህገ – መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ያላቸው ፣ ይህም ማለት አብላጫው ወንበሮች ያሉት ፓርቲ ያመዘነ የመወሰን ሰለስልጣን ይኖረዋል ማለት ነው ።

ዲሞክራሲ ስርአትና ሜሪቶክራሲ መጀመሪያ የሚደጋገፉ ሲሆኑ ፣ ውሎ አድሮ ግን ስርአቱ ጥቂቶችን ብቻ የሚያገለግልና ብዙሀኑን የሚገፋ ይሆናል ። ለዚህም ምክንያቱ በአንድ በኩል ሀብቱ ፣ ተቋማቱና ስልጣኑ በጥቂቶች ልሂቃን ስር የመውደቅና ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ማንም ሰው ሀብት ወይም ንብረት ሊያፈራባቸው የሚችላቸው ተፈጥሯዊ የሆኑ ሀብቶች ውሱን በመሆናቸው ፣ እንደ መሬት ፣ የተፈጥሮ ሀብት የመሳሰሰሉት አንድ ጊዜ በጥቂት ሰዎች እጅ አንድ ጊዜ ከገቡ ወደ ወራሾቻቸው እየተላለፉ ይሄዳሉ እንጂ ፣ ስለዚህ ሀብት ሊፈጠርበት የሚችለው ነገር እውቀት ሲሆን ይህም ደግሞ ብዙሀኑ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ስላልሆነ ነው ። ይህም ስርአቱ ወደ ሀብታሞች አገዛዝ  ይቀየራል ።

ሲጀመር ዲሞክራሲ ባይኖር ኖሮ ሜሪቶክራሲ አብቦ እድገትንና ውጤትን ሊያመጣ አይችልም ። ሜሪቶክራሲ ችሎታና እውቀት ያላቸው ሰዎች የመስራት ነፃነትን እሚያገኙበትንና ለስራቸው ሽልማትንም፣ማበረታቻንም እሚያገኙበት ነው ። ለምሳሌ በታዳጊ አገራት ሙያና ችሎታው ያላቸው ብርካታ ዜጎች ቢኖሯቸውም ፣ ነገር ግን በአገራቸው ውስጥ ያላቸው እድል ጠባብ ስለሆነ ሀገር ጥለው መውጣትንና መሰደድን ይመርጣሉ ። በአንፃሩ ዲሞክራሲ ባለባቸው ሀገራት ስርአቱ ልሂቅ የሚባሉትን የማቀፍ ስለሚችል በራሳቸው ሙያተኞች የማደግ እድል ሲኖራቸው ፣ ነገር ግን ዲሞክራሲ በሌለባቸው ሀገራት አንድ የተወሰነ የልሂቅ ቡድን ስልጣንን ከያዘ የሌሎቹን ሊወዳደሩት ወይም የተሻለ ሊሆንየሚችሉትን እድል ይዘጋል ። በዚህም ልሂቃኑ በብዛት ለመሰደድ ይዳረጋሉ ፤በልሂቃኑ መሀከል የሚደረግ ለስልጣንና ለሀብት ለመሳሰለው የሚደረግ ውድድር ፣ ፍትሀዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ ስለማይካሄድ አሸናፊው የራሱን በሌሎች ላይ ስለሚጭን ተሸናፊዎች የሚኖራቸው እድል የጠበበ ነው የሚሆነው ስለዚህ መሰደድ ወይንም ከውድድሩ ራሳቸውን አግልለው ለመኖር ይገደዳሉ ።

ባደጉት ሀገራት ግን  እንደ ሜሪቶክራሲ ለእድገት መሰረት ሲሆን ፤ ነገር ግን ሜሪቶክራሲ እያደገ ሲሄድ የብዙሀኑን ጥቅም በማጥበብ ወደ ጥቂቶች አገዛዝ የመቀየር አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል ። ክሌፕቶክራሲ ደግሞ የጓደኛማቾችና የዘመዳማቾች አገዛዝ ሲሆን ፣ከአምባገነናዊ ስርአት ጉያ ውስጥ የሚፈጠር የአገዛዝ ስልት ነው ።

ቱርክን ብንወስድ ደግሞ የኩርድ እንቅስቃሴ ያለ ሲሆን ኩርዶች በኢራቅ በሶርያና በራሷ በቱርክ እንዲሁም በኢራን ተበትነው ያሉ ናቸው ። ይሁን እንጂ አሲሚሊሉሽን በረጅም ጊዜ ላይሰራም ሊሰራም ይችላል ። ለዚህም ውስጣዊ መብቶችን ማክበርና እውቅታና መስጠት ዘላቂ መፍትሄን ያመጣል ።

ለምሳሌ እንግሊዝንና ስኮትላንድን ብንወስድ ፣ ስኮትላንድ በሰሜናዊ የባህር ዳርቻ የሚወጣው የነዳጅ ዘይት ገቢ ወደ ስኮትላንድ ካዝና የሚገባ ሲሆን ፣ ከእንግሊዝም የበጀት ድጋፍን ታገኛለች ፤ ይህ  ብቻ ሳይሆን ስኮትላንድ ውስጥ ለዜጎቿ የምታወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው ። በዚህም ስኮትላንድን የእንግሊዝ አካል አድርጋ ማቆየት ችላለች ።

አንድ የማይካድ ነገር ፣ ምንም እንኳን የዲሞክራሲ ስርአት ያን ያህል እንደሚታሰበው ችግሮችን በአንድ ጀንበር ፈትቶ የሚያጠፋ ባይሆንም ፣ የዲሞክራሲ መብቶች በምንም ነገር እሚለወጡ አይደሉም ። የዲሞክራሲያዊ መብቶች የሰብአዊ መብትም ጭምር እንደመሆናቸው ፣ ኢኮኖሚ ቢያድግ ፣ ወይንም ያ ሀገር ሌላ ቁሳዊ የሆነ ነገርን ቢያገኝ ጭምርእንኳን የዲሞክራሲያዊ መብቶች ለአንድ አገር በሌላ በምንም ነገር እሚለወጡ አይደሉም ። በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ግን መሪዎቹ ኢኮኖሚን በማሳደግ ፣ በሌላም ጊዜያዊ ትኩረትን በሚስቡ ነገሮች የህዝቡን አትኩሮት ለጊዜውም ቢሆን በማስቀየር እውነተኛ የዲሞክራሲ መስፈንን ለማዘግየት ሙከራ ያደርጋሉ ።

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s