ስልጣኔና ምጣኔ ሀብት

ስልጣኔዎች የሚፈጠሩት ሰዎች ከጥረት ፣ ከእልህ ፣ ራሳቸውን ጠላት ከሆነ ወገን ለመከላከል ወይንም የሆነ ደረጃ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ነው ።በአጭሩ ስልጣኔ የሚፈጠረው ከችግርና ከመከራ ነው ። ለምሳሌ ከግሪክ ስልጣኔ በኋላ አውሮፓውያን ቀድመው እየሰለጠኑ የመጡበት ምክንያት አገራቸው በበረዶ የተሸፈነ ስለሆነ የሚመገቡትን ምግብ ለማምረት ፣ የሚኖሩበትን ቤት ለመስራት ብዙ ማሰብና አእምሯቸውን ማሰራት ነበረባቸው የሚል ንድፈ – ሀሳብ አለ ። በአንፃሩ ግን የምድር ወገብ አካባቢን ብንመለከት አካባቢው በደን የተሸፈነ ሲሆን ፣ አንድ ሰው ቢርበው እንኳን በቀላሉ ወደ ደን ሄዶ አድኖ ወይም ፍራፍሬ ልቅ ለቅሞ መብላት ይችላል ፣ ፀሀይ ከአመት እስከአመት ድረስ ትወጣለች ፣ አፈሩ ለም ነው የተሰጠውን ያበቅላል ፣ ውሀ እንደልብ ነው ስለዚህ ምንም ችግር የለም ። ለመኖር እንደ በረዷማ አካባቢዎች ብዙ መከራና ችግር የለም ።
የስልጣኔዎች ውድቀት መነሾው ምንድነው ቢባል ፣ከስኬት መደራረብ ውድቀት ሊመጣ እንደሚችል መርሳት፣ ቀላል ድሎች ይመጣሉ በሚል ወደ አደገኛ መንገድ ውስጥ መግባት ፣ ነገሮች በፍጥነት እንደሚቀያየሩ አለመረዳት እና ውሎ አድሮ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አለማገናዘብ እና ችግሮች እየተደራረቡ ሲመጡ ቁልጭ ያለ መፍትሄውን ባለማስቀመጥ ወደ ተሳሰሰተው አቅጣጫ ለብዙ ጊዜ የቆየ ጉዞን ማድረግ ነው ። በየትኛውም ዘመን ያሉ ሀያላን ሲያቆለቁሉ ማየት የተለመደ ሲሆን ሀያላኑ የሚገቡበትን ችግርና ተመልሰው መውጣት ሲያቅታቸው በማየት በቀላሉ መረዳት ይቻላል ።
ስለዚህ ኑሮው ስላልፈተናቸው ነው ወደ ኋላ የቀሩት ፣ ወደሚል ድምዳሜ ያመራል ፣ ምንም እንኳን በተፈጥሮ ሀብት የምድር ወገብ አካባቢ የታደለ ቢሆንም ነገር ግን ለአውሮፓውያን መሰልጠንና ለተቀረው አለም ለስልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት ግን አመርቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም ። ምክንያቱም ከግሪክ ስልጣኔ በሺ አመታት እሚቀድሙ ስልጣኔዎች በአፍሪካም፣ በእስያም ነበሩ ። ነገር ግን በአጠቃላይ ሲታይምንም እንኳን ግሪካውያን በኋላ ላይ ቢወድቁም ፣ አውሮፓውያን ለስልጣኔ መሰረትን እየጣሉና እየተጠናከሩ ሲሄዱ የተቀረው አለም ግን ከአውሮፓውያን አንፃር ከማደግ ይልቅ እንደውም በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች የስልጣኔዎች ማቆልቆልና ወሎ አድሮ ለአውሮፓውያን የበላይነት ስር ሊሆን ችሏል።
ይሁን እንጂ ከአውሮፓውያኑ የግሪካውያንና የሮማውያን ስልጣኔ በፊትም በስተደቡብ በአፍሪካና በእስያ በምድር ወገብ አካባቢ በርካታ ከአውሮፓውያን የቀደሙ ስልጣኔዎች ነበሩ ። እነኚህ ስልጣኔዎች እየከሰሙ ሲመጡ በኋላ ላይ ግን አውሮፓውያን ገነው ሊወጡ ችለዋል ። ለዚህም በአውሮፓ እየበዛ ያለው ህዝብ ያለው ሀብትና መሬት ሊበቃቸው ስላልቻለ መሬት ፍለጋና በዘመኑ ዋነው ንግድ የቅመማ ቅመመን ንግድ ሲሆን ወደ ህንድ ያመራ የነበረውን የንግድ መስመሩን ለማግኘት በነበራቸው ፍላጎት ከበርካታ ሙከራ በኋላ የአሜሪካ አህጉርን ለማግኘት በቅተዋል ።
የግሪካውያንን ስልጣኔ ብንወስድ አንድ ሰው ደስታውን ምኞቱንና መሻቱን እሚፈልገው የከተማ መንግስት (City State) ውስጥ ሆኖ ነው ውስጥ ነው የሚል መስመር የተቃኘ የጥንታዊ ግሪኮች ፍልስፍና ነው። በተለይም የአቴን የከተማ መንግስት አስደናቂ የስልጣኔ ሀሳቦች የፈለቁበትና በርካታ ፈላስፋዎችንና በርካታ የሙያ ዘርፍ አሁንም ድረስ ጠቃሚ አስተዋፅኦን ያደርጉ ሰዎች የነበሩበት ከተማ ነበረች ። በነገራችን ላይ መንግስት የአንድ ሰው የደስታውንም የኑሮውም የሁሉም ነገር ማእከሉ መንግስት ነው ማል ለት ሰፊ አንድምታ ነው ያለው ። በኋላ ላይ ለነበሩት ለበርካታ አመታት አውሮፓውያን ለስልጣኔያቸው የረዳቸው አሰተሳሰብ ነው ።
ይህም ከእነሱ በኋላ የመጡት ሮማውያንም ግዛተ – መንግስታትን (Empire) በማቋቋም ይህንኑ የመንግስትን ቦታና አቅም አስፋፍተውታል ። ታላቁ አሌክሳንደር እስከ ፐርሽያ ድረስ በመንቀሳቀስ በአጭሩ ከተቀጩት ዘመቻዎች ውጪ ፣ የጥንቶቹ ግሪኮች እንደ ሮማውያን ሰፊ መሬትን ፣ ግዛትን ለመያዝ አልተንቀሳቀሱም ይሁን እንጂ በአስተሳሰብ ግን የምእራቡ አለም ፈር ቀዳጆች ሲሆኑ ሮማውያን ግዛትንና ስልጣንን ሲይዙ በርካታ የግሪኮችን አስተሳሰብና ፍልስፍና ተጠቅመዋል ።
በታሪክ ውስጥ እንደሚታወቀው ሮማውያን በፍልስፍና ፣በቲያትር ፣በስነ ጥበብ፣ በንግድ በመሳሰሉት በርካታ ጥበቦች ግሪኮችን ባያክሉም ዘመናዊ አስተዳደርን ለአለም በማስተዋወቅ ፣ በኪነ -ህንፃና ፣ በጦርነት ጥበብና በስትራቴጂ የበኩላቸውን የታሪክ አሻራ በአለም ላይ አሳርፈው አልፈዋል ። ነገር ግን በዛን ዘመን የነበሩ በርካታ የሮማውያን ፣ ከግሪካውያን ባሮች በርካታ እውቀቶችን ወስደዋል ተብለው ይታማሉ ። የግሪኮች ስልጣኔ ሲፈራርስና በሮማውያን አገዛዝ ስር ሲወድቁ በርካታ የግሪክ ፈላስፎች፣ የቁም ፅህፈት ባለሙያዎች ፣ የስነ – ጥበብ ባለሙያዎች ፣ ሀኪሞች ፣ የመሳሰሉት ባለሙያዎች በሮማውያን የባርነት አገዛዝ ስር ወድቀዋል ። ነገር ግን ከተራው ባሪያ ይልቅ የተሻለ አያያዝ የነበራቸው ይሁኑ እንጂ የጥበብ ስራቸው ግን ስራቸው ግን በአብዛኛው በሮማውያን ተወስዷል ።ሮማውያን ራሳቸውን የእነኛ ግሪካውያን ስራዎች ባለቤት አድርገው አቅርበዋል ፣ ብዙዎቹ የሮማውያን ፈላስፎችም የግሪኮችን ስራ በመስረቅ ይታማሉ ። በዚህም ሮማውያን የግሪካውያንን ስራ በመስረቅ (Plagarism) ይታማሉ ።
ነገር ግን ትልቁ የግሪካውያን ስለ ፍልስፍና መሰረት የጣሉት ስለ መንግስት በተለይም ዲሞክራሲያዊ ስለሆነ መንግስት ፣ በአጠቃላይ መንግስት ምን መምሰል እንዳለበት በሰፊው በነበሯቸው ታላላቅ ፈላስፋዎች አማካኝነት አትተዋል ። በተለይም ፕሌቶ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳረፈ ሲሆን ከእርሱ በመቀጠል አሪስቶትል ከፍተኛ ሀሳቦችን አበርክቷል ፤ ከዚህም በሂሳብ ፣ በጂኦሜትሪ እንደ ኢክሊድ፣ ፓይታጎራስና አርኪሜዲስን የመሳሰሉ ታላላቅ የሳይንስና የሂሳብ ሊቃውንትንም አፍርተዋል ። መንግስትን ማእከል ማድረጋቸው ትልቁ የምእራቡ ስልጣኔ የአስተሳሰብ መሰረት ነው – በተለይም በዘመኑ በነበሩት የከተማ – መንግስታት (City State) አንፃር። ጥንትም ሆነ አሁን እንደ መንግስት ያለ ተቋም ባይኖር ኖሮ በአለም ላይ ስለየትኛውም ስልጣኔም ሆነ እድገት ማሰብ አይቻልም ነበረ ፣ ትልቁ ጥንታዊ ግሪኮች ያደረጉት አስተዋፅኦ ስለ መንግስት ያፈለቋቸው ሀሳቦችና በተግባርም ሲሰሩባቸው የቆዩ ሀሳቦች ነው ።
የአቴናውያን ስልጣኔ ብቻ ነው ወዲያው በአንድ ጊዜ ቦግ ያለው ፣ የተቀረው አለም ስልጣኔ ግን በበርካታ መቶዎችና ሺዎች አመታት ውስጥ እያበበ የሄደ ነው ። ለዚህም የሚጠቀሰው የጥንቷ ኢትዮጲያ ማለትም የኩሽ ስልጣኔ እና በፈርኦኖች ይመሩ የነበሩት የግብፅ ስልጣኔዎች ይጠቀሳሉ ። በአንፃሩ ከዚያ በኋላ ያበበውና በግሪካውያን በተለይም በአቴናውያንየሚወከለው የምእራባውያን ስልጣኔ ግን በአንድ ወቅት ቦግ ብሎ የታየ ነው ።
ይህ ብቻ ሳይሆን አውሮፓውያን የግሪክን ስልጣኔ ከፈጠሩ በኋላ ፣ ምንም እንኳን የግሪክ ስልጣኔ ኋላ ላይ ቢፈራርስም ፣ ይበልጥ ጠንካራና ሰፊ ግዛትን ያስተዳድር በነበረው የሮማውያን አፄ – ግዛት (Empire) ተተክቷል ። የሮማውያንም ስርአት ሲደክም እንዲሁ በቤዛንታይን ተተክተቷል ። በሌላው አለም የነበሩት ስልጣኔዎች ግን የመተካካት አቅማቸው አነስተኛ ሆኖ ነው የቆየው ። በዛ መንገድ ምእራባውያን ቀዝቀዝ ቢልም መጀመሪያ በመካከለኛው ዘመን ፣ ከዚያም በህዳሴው ፣ እውቀትን በማስፋፋት በንቃት ወይም አብርሆት (The Age of Enlightenment) ዘመን እንዲሁም በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን እየተቀባበሉ ባልተቋረጠ የእድገት ጎዳና ላይ መጓዝ ችለዋል። አውሮፓውያን ያልተቋረጠ በሚባል ሁኔታ ባላቸው ላይ እየጨመሩ ሲሄዱ ፣ በአንፃሩ የተቀረው አለም በባሪያ ንግድ ፣በቅኝመገዛት ፣ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ፣ በእርስ በርስ ሽኩቻበመሳሰለው እድገቱ የኋልዮሽ ሆኖ ቆይቷል ።
በአጭሩ ሲገለፅ መንግስት ማለት ህግ ነው ። ዋናው ትልቁ የመንግስት ስራ በየትኛውም የዜጎች እንቅስቃሴ ውስጥ ህግና ስርአትን ማስፈን በመሆኑ ነው ። ነገር ግን ያ መንግስት በምን አይነት መንገድ ስልጣኑን እንደሚጠቀምበት የዛን መንግስት ባህሪና አፈጣጠር ያሳያል ።ምጣኔ – ሀብቱንም በተመለከተም የመንግስት ሚና መቆጣርና ማበረታቻዎችን በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው ። ለምሳሌ አንደ ባለሀብት አንድ ፖሊስ የሚሰራውን ስራ አይሰራም ። ነገር ግን ልክ አንድ መንግስት ሲቀየር በውስጠ ታዋቂ የህጎች መለወጥ እንዳለም እንረዳለን ።አውሮፓውያን ከ11ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲጣጣሩበት የቆዩት የስልጣኔ ጉዳይ ከሶስትና አራት መቶ አመታት በኋላ ውጤት ማሳየትን በመጀመሩ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ግን የአውሮፓ ህዳሴ ተጀምሮ ውጤትን መስጠት የጀመረው ። በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በማህበራዊ ሳይንስ ፣ በፖለቲካ ሳይንስ ፣ በህክምና ፣ በሳይንስ ፣ በስነ – ክዋክብት ፣ በኢንጂነሪንግ ፣ በመሳሰለው ሀይማኖታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ውጪ ባሉ ዘርፎች አዳዲስ ውጤቶች ማስመዝገብ የጀመሩት ።
በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ አዲስመልክና ቅርፅን በመያዝ ላይ የሚገኝ የአለም የገናናነት አሰላለፍ አለ ። ይህም ከአስርና አስራ አምስት አመታት በኋላ በግልፅ ወቶ የሚታይ ሲሆን አሁን ግን ገና ቅርፅ በመያዝ ላይ ነው የሚገኘው ። ይኀውም በግርድፉ ሲገለፅ ለ500 አመታት የዘለቀው የምእራባውያን የበላይነት እየቀነሰ እስያውያን የምጣኔ – ሀብት ገናናነቱን ስፍራ በመረከብ ላይ መገኘት ነው።የምጣኔ – ሀብቱ ሚዛን ወደ እስያውያን እየተሸጋሸገ (Shift) ሲሆን ፣ እንዲሁም ቀድሞ ጨለማው አህጉር በመባል ይታወቅ የነበረው አፍሪካ ሳይቀር የእድገትና የስልጣኔ ጮራን በማየት ፣ በአለም መድረኮችም ላይ ሁነኛ ተፅእኖን ማሳረፍ እየጀመረ ነው ።
ለምሳሌ በአውሮፓ በ2011 አ.ም ግሪክ፣ ጣሊያንና ስፔን ያሉት ሀገራት በእዳ ውስጥ ስትያዝ የአውሮፓ ሀገራት ብቻቸውን መወጣት ባቃታቸው ወቅት ፣ ፊታቸውን ወደ አሜሪካ ሳይሆን ወደ ቻይና ነበረ ያዞሩት ። ሳይውሉ ሳያድሩም ወደ ቻይና የልኡካን ቡድናቸውን ልከዋል ፤ ይህንንም አንዳንድ ተመልካቾች የአሜሪካ ስልጣኔ የበላይነት ማቆልቆሉንና በቻይና መተካቱን አመላካች ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰተዋል ። ነገር ግን በምጣኔ – ሀብት ማደግ ወይም ከፍተኛ የአገራዊ ምርት ባለቤት መሆን ብቻውን ከፍተኛ የስልጣኔ ደረጃ ላይ መድረስ ነው ወይ የሚለው አከራካሪ ሊሆን ይችላል ። ምክንያቱም ምንም እንኳን ቻይና በጥቂት አመታት ውስጥ አከለም ግዙፉ ምጣኔ- ሀብት ባለቤት እንደምትሆን በርካታ የምጣኔ- ሀብት ባለሙያዎች እየተነበዩ ቢሆንም ፣ ቻይና በዲሞክራሲ ረገድ እንኳን ከአሜሪካ ፣ ከአፍሪካ አገራት ጋር እንኳን የማይወዳደር በአንድ ብቸኛ የኮሚኒስት ፓርቲ የምትገዛ ሀገር መሆኗ ይታወቃል ። በአንድ በኩል ምእራባውያንን ስጋት ውስጥ እየጨመራቸው ያለውም ይሄው ሲሆን ፣ በአለም የግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆነች ሀገር ዲሞክራሲ ከሌላት ፣ ከባድ የውስጥ ችግር ቢያጋጥማት ወይም ብትወድቅ ፣ የሷ ችግር ለአለም የሚተርፍ የከፋ መዘዝን ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው ።
ቀደምት የሆኑ ስልጣኔዎች ብዙውን በወንዝ ዙሪያ አካባቢ ነው የሚመሰረቱት። ለምሳሌ የግብፆችን ስልጣኔ ብንወስድ በአባይ ወንዝ ዳርና ዳር ላይ ለም የሆነውን ግብርናና ለመኖሪያ አመቺ በሆነው አካባቢ ነው ተቋቋመው ። ግብፅ የአስዋንን ግድብ በሚሰሩበት ወቅት ዳርና ዳር የነበሩትን ቅርሶች ለማንሳት ተገደው የነበረ ሲሆን ቅርሶቹ እየተቆረጡ እንዲነሱ ተደርገዋል ።በአሁኑ ወቅት ግን በመሰራቱ አግባብ አልነበረም የሚል እምነት አላቸው። በመካከለኛውም ምስራቅ ብንወስድ የሜሶፖታሚያና የባቢሎን ስልጣኔዎች ተመሰረቱት በኤፍራጥስና በጤግሮስ ወንዝ ዙሪያ ነው ።
ብዙውን ግዜ ጥንታዊ ስልጣኔዎች የተፈጥሮ ሀብት ባለበት አካባቢ ነው የሚመሰረቱት ፣ ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው ለምሳሌ የጥንታዊቷ የኩሽ ወይንም የኢትዮጲያን ስልጣኔ ብንወስድ የኢትዮጲያ ምድር ደጋማ መሆኑና የበርካታ ወንዞችና ለም መሬት የነበረው እንደመሆኑ ለምጣኔ – ሀብት እንቅስቃሴ ምቹ ሲያደርጋት ከዚህም ሌላ ለአለም አቀፍ ንግድ ያላት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ለመካከለኛው ምስራቅ ያላት ቅርበት ጋር ለሚደረግ ንገድ መተላለፊያነት አመቺ ያደርጋት ስለነበረ በዚህም ለምጣኔ – ሀብቷና ለንግዷ ማበብ አስተዋፅኦን አድርጎላታል ። የጥንቷ ኢትዮጲያ ለጥንታዊ ነጋዴዎች ስጋ የምታበላበት ለጥ ያለ የተራራ ሜዳ እንደነበራትም ተጠቅሷል ።
አንዳንድ ጊዜ በቀደምት ስልጣኔዎች የተሰሩ ነገሮች በአሁኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እማይሰሩ ናቸው ። ለምሳሌ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተፈለፈለው የአክሱም ሀውልት እንዴት እንደቆመ ብናይ ቀጥ ብሎ ለመቆም ለሺ አመታት ዘጠና ዲግሪውን ጠብቀው ማቆማቸው የጂኦሜትሪ ህግጋትን ያውቁ እንደነበረ ሲያመለክት የጥንት ግብፃውያንም እንዲሁ ፒራሚዶቹን የሰሩበት ሁኔታ 90 ዲግሪውን ጠብቀው አራት ማእዘኑን መጠበቃቸው የነበራቸውን (Geometry) እውቀት ያሳያል። ከዚያ በኋላ ግን ኢክሊድ የተባለ የጥንታዊ ግሪክ የሂሳብና የጂኦሜትሪ አዋቂ በርካታ የጂኦሜትሪ ህግጋትን በፅሁፍ አድርጎ ያወጣቸው።ግብፃውያኑም ሆኑ አክሱማውያን ግን ከኢክሊድ በፊት እነኚህን የጂኦሜትሪ ህግጋትን ጠንቅቀው ያውቋቸው ነበረ ።
የጥንት አክሱማውያን ግን ከዚያ በፊት ያወቁት እንደነበረ ከሰሯቸው ቋሚ ሀውልቶች መረዳት ይቻላል ። እነኚህን ስልጣኔዎች ለመስራት የሚያስፈልገውን ሀብትና እውቀትም ባለቤቶች እንደነበሩ መገመት ይቻላል ። ይህ ብቻ ሳይሆን ጥንቃዊ ግብፃውያንም ስለ ትርያንግል(Triangle) ወይም ሶስት ማእዘን በነበራቸው እውቀት ነው እነኛን ታላላቅ ፒራሚዶችን የገነቡት ። ለምሳሌ የሶስት ማእዘንን ህግ አገኘ የሚባለው ፓይታጎራስ ቢሆንም እሱ ከመወለዱ በፊት 2 ሺ አመት በፊት ግን ጥንታዊ ግብፆች ታላላቆቹን ስልጣኔዎች በእነኛ ህግጋት ላይ ተመስርተአው የሰሯቸው ነበሩ ። በላቲን አሜሪካም እንዲሁ ከፍተኛ የስልጣኔ እርከን ደረጃ ላይ ደርሰው የነበሩት ማያውያንም «Mayas» እንዲሁ የሰሯቸው ፒራሚዶች ደርሰውበት የነበረውን የጂኦሜትሪና የስነ – ህንማፃ ጥበብን ያመለክታል ። እንዲሁም የነበራቸው የቀን አቆጣጠርም ከአለም እጅግ ረቃቂቅ ከሆኑ አንዱ እንደነበረም ይታወቃል ።
ሌላው ስለ አክሱም ገናናነት ስናነሳ ለአክሱምስልጣኔ መክሰም እንደ አንድ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ነገር ለንግድ ቁልፍ የነበሩትን የቀይ ባህር ዳርቻዎችን አክሱማውያን መቆጣጠር እያቃታቸው መምጣት ሲሆን በዚህም ምክንያት ዋናው የንግድ መስመር የነበረውንና የሸቀጦች መተላለፊያ የነበረውክልል ከቁጥጥራቸው ስር እየወጣ በአረቦችና በፋርሶች ቁጥጥር ስር እየዋለ መምጣት ነው ። የቀይ ባህር ዳርቻዎችን ብንመለከት በአለም ላይ ካሉ ቁልፍ የንግድ መስመሮች አንዱና ዋነኛው ሲሆን በዛን ዘመን ከነበሩ ታላላቅ ጥንታዊ ስልጣኔዎች በነበሩት በግሪክ ፣ በሮም ፣ በፋርስ ፣ በህንድና በቻይና መሀከል ለሚካሄድየባህርም ሆነ የየብስ ንግድ ዋነኛ የመተላለፊያ መስመር የነበረ ነው ።
ይህ ለአለም አቀፍ ንግድ እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የባህር ክልልና ጠረፍ አክሱማውያን ለረጅም ጊዜ በቁጥጥራቸው ስር በማድረጋቸው እንዲሁም ቀይ ባህርን ተሻግረው አረቢያንን ይገዙ በነበረት ወቅት ይቆጣጠሩት የነበረ እጅግ ጠቃሚ የንግድ መስመር ነው ፣ ለሀያልነታቸውንና በንግድ ለመበልፀጋቸው አስፈላጊ ነበረ ። ይሁን እንጂ በስተመጨረሻ ላይ በገጠማቸው ውስጣዊና ውጫዊ ግፊቶች ምክንያት አካባቢው ከአክሱማዉያን ቁጥጥር ስር መውጣቱ ውሎ አድሮ ለአክሱም ስልጣኔ መዳከምና መክሰም አስተዋፅኦን አድርጓል ። ፐርሽያዎችና አረቦች አቅማቸውን አጠንክረው የአክሱማውያን ግዛት የነበረውን የአረቢያን ክልል በመውረራቸው ምክንያት ከአክሱም ቁጥጥር ውጪ ሊወጡ ችለዋል ። ከዚያም ትኩረታቸውን ለደህንነት አስጊ እየሆነ ከመጣው ከባህር ጠረፉማው አካባቢ ይልቅ ብዙ ተቀናቃኝ ወደ ማይበዛበት ወደ ደጋውና መሀል አገር አድርገዋል ።
የአክሱም ስልጣኔ ከተዳከመ በኋላ በርካታ የታሪክ ፀሀፊዎች በተደጋጋሚ እንደገለፁት ኢትዮጲያ ለሺዎች አመታት የዘለቀ አለምም ረስቷት ፣ እሷም አለምን ረስታ ፤ከተቀረው አለም የመገለል እጣ ገጥሟታል ። ነገር ግን ይህ መገለል በአብዛኛው በምጣኔ – ሀብትና በሳይንስ ካደገው አውሮፓውያን ጋር በተለይ የጎላ ነበረ ። በአካባቢው ግን በተለይም አቅራቢያዋ ካሉ ሀገራት እንደ ግብፅና የመን ካሉት ሀገራት ግን የሞቀ ግንኙነት እንደነበራት አንዳንድ የታሪክ ፀሀፊዎች ይገልፃሉ ። ለምሳሌ ግብፅን ብንወስድ እስከ 1950ዎቹ ድረስ የኢትዮጲያ ፓትርያርክ ከግብፅ ተሹሞ ይመጣ እንደነበረ ይታወቃል ፣ከየመንም ጋር ካላት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ቅርበት የተነሳ የንግድ ግንኙነት ነበራት ።
ይህም አልፎ አልፎ የተወሰኑ ማንሰራራቶች የነበሩ ቢሆንም የአክሱምን ያክል ገናናነት ፣ ሀብትና ሀያልነትን ግን ዳግመኛ አልተጎናፀፈችም ። በተለይም ከውጪ ሀገራት ጋር የነበረው ንግድ ጨርሶ ተቋርጧል ባይባልም ከቀድሞው ጋር ግን ፈፅሞ እሚወዳደር አልነበረም ። ይህ መገለል አገሪቱን በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ መጉዳቱ በግልፅ የሚታይ ነው ።በኢትዮጲያ ሁኔታ የውስጥ ግጭቶች ያደረሱት ጉዳት ከውጭ ወረራ እና ጥቃት የበለጠ ሲሆን ፣ በአንፃሩ የውጪ ወረራ ህዝቡ በአንድነት ሆ ብሎ የሚመክተው ሲሆንበተደጋጋሚም በአስተማማኝ ሁኔታ ተገትቷል ፣ የመገታት እድሉም ሰፊ ነው ። ለዚህም ነው አገሪቱ በቅኝ አገዛዝ ስር ወድቃ የማታውቀው ፣ በአንፃሩ ግን ከውስጥ የሚነሱ ግጭቶችና የእርስ በእርስ ጦርነቶች ግን ውጤታቸው አስከፊ ሆኖ በተደጋጋሚ በታሪክ ተመዝግቧል ። ራቅ ያለውን የአክሱምን ዘመን ብናይ እንኳን ለውድቀቱ ዋና አስተዋፅኦን ያደገረው የውስጥ መበጣበጥና የእርስ በእርስ ጦርነት ሆኖ እናገኘዋለን ። ከዛ ወዲህ ቀረብ ያሉትን የግራኝ አህመድ ጋር የተደረገው ጦርነትና ፣ ዘመነ – መሳፍንትን መጥቀስ ይቻላል ።

Advertisements

One thought on “ስልጣኔና ምጣኔ ሀብት

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s