የመሪነት ቀውስ (Leadership Crisis)

የአመራር ቀውስ እሚፈጠረው በመሪዎች ተፈጥሯዊ ባህሪና ፣ ወቅቱ በሚፈጥራቸው ችግሮች የተነሳ ነው ። ሌላው ደግሞ በመሪው መሀከልና በተከታዮቹ ወይም በሚመራው ህዝብ መሀከል መረዳዳት በማይኖርበት ጊዜ አለመግባባትና የተከታዮች ተቃውሞ እሚከተለው ። መሪዎች የህዝባቸውን ፍላጎት ወይም ላይረዱ የሚችሉበት ምክንያት ካለማወቅ ወይንም ፣ ከራስ ፍላጎት አንፃር ብቻ ከማየት ፣ ሊሆን ይችላል ። ነገር ግን የመሪነትን ቀውስ ከሚያስከትሉ ነገሮች ዋነኛው ተደርጎ ሊወስድ የሚችለው ይኀው ጉዳይ ነው ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ እንዳለ አንድን ችግር መጀመሪያ ላይ ሲፈጠር መለየት ቢያስቸግርም ችግሩ ከታወቀ ግን መፍትሄው ቀላል ነው ። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ግን አንድ ችግር ሲነሳ ካልታወቀ ውሎ አድሮ ችግሩ ቢደረስበትም መፍትሄው ግን የራቀ ነው ፣ ለመፍትሄ በዘገየበት ሰአት ነው ። በዚህ ወቅት ሁሉም ሰው ችግሩን ቢረዳውም መፍትሄውን ለማግኘት ግን ዘግይቷል ። ስለዚህ ሲጀመር ችግሮችን የመለየትና የማወቅ ለአንድ መሪ የኋላ ዘመን ስኬት ቁልፍ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ነው ።
ቀውስን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ ። አንዳንድ ጊዜ የመሪነት ቀውስ መከሰት ችግሮች ፈጠው እንዲወጡና መፍትሄን እንዲያገኙ ያደርጋል ብለው አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ ፤ በሀገርኛው አባባል ካልደፈረሰ አይጠራም እንደማለት ሲሆን ፤ ኔቼም ቀውስ ሲፈጠር ነገሮች ፈጠው ይወጡና ችግሮች መፍትሄን ያገኛሉ ተብሎ ይታመናል ። ነገር ግን ይሄ ሊሆን የሚችለው መሪው መፍትሄን መስጠት ካልቻለ ለሚመራው ተቋም እንደ አማራጭ ሊሆን ይችላል ። ይህም ቢሆንም ግን መሪው የሚሞገሰው ቀውስን መፍታት በመቻሉ ነው እንጂ በቀውሱ ተሸንፎ ከአቅሙ በላይ ሆኖ ነገሮች ሲለይላቸውና ሲፈነዱ አይደለም ፣ እንደው ማንም ሰው በሚረዳው ሁኔታ ከአቅሙ በላይ የሆነ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ።
ሌላው የመሪዎችን የመምራት ብቃትን የሚቀንስ ነገር መገለል(Isolation)ነው ። መሪነት ማለት በሰዎች መሀከል ማህበራዊ እንቅስቃሴ ባለበት ውስጥ የሚሰራ ነገር ነው ፣ እንጂ እንደ ሳይንቲስቶች በላብራቶሪ ውስጥ ለብቻቸው ሆነው እንደሚያደርጉት ምርምር የሚከናወን ነገር አይደለም ።መሪዎች በመገለል ውስጥ ካሉ ስራቸውን መስራት አይችሉም- መገለል የመሪውን የመምራት ብቃትም ሆነ አካባቢውን የመረዳትና የመቆጣጠር በንቃቱን በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርገዋል ። መሪዎች ራሳቸውን ያገለሉ ከሆነ ወይንም ከሌሎች ጋር የማይቀላቀሉ ከሆነ ፈላጊያቸው እየቀነሰና በዙሪያቸው እየሆነ ያለውን ነገር የመቆጣጠርና የመረዳት ችሎታቸውን ያዳክማል ፤ በማንኛውም መንገድ መሪዎች ይህን መከላከልና የሚደረገውን ነገር ከስር ከስሩ ማየትና መረዳት መከታተልና አስፈላጊውን ማስተካከያ እያደረጉ መቀጠል አለባቸው ። መሪዎች ስራዎቻቸውን እሚያደናቅፉባቸውን በማጋለጥ እንዲገለሉና ፣ ከመንገዳቸው ገለል እንዲሉላቸው የሚያደርጉበት ስልትም እንደመሆኑ ፣ እነሱም በሌሎች ሆነ ተብሎ የመገለል ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ራሳቸውን ነቅተው የሚጠብቁበት ስልት ነው ።
ውድድር ያለበት ወይም ውድድር እንዲኖርበት በሚፈለግ ሁኔታ ፣ አንድ መሪ ውድድሩን ካጠፋ ፣ የራሱን የሚመራውን ተቋም እድገት ያቀጭጨዋል ። ለተቋሙ ወይም ለሀገሪቱ የፖለቲካ እድገት እገዛን ሊያደርግ ይችል የነበረውን ፣ እንዲሁም ለወደፊቱ ሽግግር ወቅት ሲመጣ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችለውን ተቋማዊና ፣ እውቀትና የሰው ሀይል እድገት እንዲጫጭ ነው እሚያደርገው ። የጤናማ ውድድር መኖር ለተቋማትም ሆነ ለመንግስታት እድገትና ጥንካሬ አስፈላጊ ነው ። ለምሳሌ መሪው የሚመራው የንግድ ድርጅት ቢሆን እንኳን ተወዳዳሪ ድርጅቶችን በሙሉ ከገበያ ቢያስወጣና ብቻውን ገበያውን ቢቆጣጠር ራሱን በራሱ መልሶ መብላትና ፣ ብቸኛ የገበያው አቅራቢ ወይም ሻጭ መሆን ሲሆን ይህም በማህበረሰብ ደረጃ ሲታይ ከሚያስገኘው ትርፍ ይልቅ የሚያመጣው ጉዳት ሲያይል ነው ።
ያም ብቻ ሳይሆን በታሪክ በርካታ ግዙፍ በብቸኝነት ገበያውን የተቆጣጠሩ ሞኖፖሊዎች የተፈጠሩ ሲሆን ሞኖፖሊዎች ውድድር ስለሌለ ራሳቸውን በራሳቸው ወደ ማጥፋት እንደሚያመሩ ሲረጋገጥ ሞኖፖሊ የነበሩ ኩባንያዎችም በጊዜ ሂደት ህልውናቸውን እያጡ ወይም እየተዳከሙ በመሄድ በሌሎች በአዳዲስ ተተክዋል ሄደዋል ። ሞኖፖሊዎች ሌላም አደጋ አለባቸው ይኀውም የገበያው ሁኔታ በራሱ የሚቀየርበትና ሞኖፖሊ ኩባንያዎች ሳያስቡት የገበያ ድርሻቸው በሌሎች የሚወሰድበትና መወዳደር የሚያቅታቸው ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል ።
አንድ መታወቅ ያለበት ለአንድ ሀገር ፖለቲካው ከምጣኔ – ሀብቱ እድገት በላይ ሲሆን ፣ ልዩነቶችን እሚያስተናግድ የፖለቲካ ስርአት ከጊዜያዊ የምጣኔ – ሀብት እድገት በረጅም ጊዜ ለአንድ ሀገር የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረዋል ። ይህ ብቻ ሳይሆን ልዩነችን ማስተናገድና የተለዩ ሀሳቦች እሚገለፁበት መንገድና እድል መኖር ከማፈን ልዩነቶችን ማስተናገድና የተለያዩ ሀሳቦች እሚገለፁበት መንገድና እድል መኖር ከማፈን ይልቅ የተሻለ ነው ።
በመሪነት ውስጥ በጣም የሚፈራው ጉዳይ የስርአት አልበኝነት (Anarcy) መፈጠር ነው ። ሌላው ደግሞ መሪው ለምሳሌ ተቃውሞ ቢነሳበት ወይንም ስርአት አልበኝነት ቢፈጠርበት ሀይልን በመጠቀም የተወሰኑ ሰዎችን መስዋእት (Scape goat) በማድረግ ያንን ተቃውሞ ለጊዜው ሊገታ ይችላል ፤ ነገር ግን ዋናው የነገሩ መነሻ ጉዳይን አውቆ ካላከመ በስተቀረ ከበሽታው ይልቅ ምልክቱን ማከም ይሆንበታል ፤ ነገር ግን ነገሩን ከስሩ ከፈታው ያ ችግር ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ሊያደርግ ሲችል ፣ ምልክቱን ብቻ ማለትም ስርአት አልበኝነቱን ብቻ ሊያስቆም ቢችል እንኳን ያ ነገር በጊዜ ሂደት ውስጥ ተመልሶ አለመምጣቱን ማረጋገጥ አለበት ። ሌላው ለአንድ መሪ እንቅፋት የሚሆነው መልካም ስሙን መጠበቅ ካልቻለ ነው ። አለማችን በታሪክ ስማቸውን ባለመጠበቃቸው ለውድቀት የተዳረጉ በርካታ መሪዎችን አስተናግዳለች ።
አንድ መሪ ችግሮች ገና ብቅ ሲሉ መለየት ካልቻለ ፣ የመሪነት ብቃት እንደሚጎድለው ሊገመት ይችላል ። ነገር ግን ይህ ክህሎት በብዙ መሪዎች ዘንድ ጎድሎ የሚገኝ ብቃት ነው ። አንድ ችግር ገና ሲፈጠር አውቆ ችግሩን ማስተካከል ቀላል ሲሆን ፣ በአንፃሩ መለየቱ ግን ከበድ ይላል ። ነገር ግን ያ ችግር አድጎ እና ጎልምሶ በቀላሉ በማንም ሰው ሊታይ የሚችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ፣ ማስተካከል አዳጋች ይሆናል ። ልክ አንድ በሽታን ሀኪም ሲጀምር ህመምተኛውም ሆነ ሀኪሙ በቀላሉ ለመለየት እንደ ሚያስቸግራቸው ነገር ግን በሽታው ቢታወቅ ግን ማከም ቀላል እንደሆው ሁሉ ፣ በሽታው ከተንሰራፋና ከተስፋፋ በኋላ ግን ሀኪሙና ህመምተኛው ብቻ ሳይሆኑ ማንም ሰው በቀላሉ የሚያየው ይሆናል ፣ለማዳን ግን ጊዜው ረፍዷል -የማይድንበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ልዩነቶችንም መጠበቅ እንዲሁ አስፈላጊ ሲሆን ፣ ለምሳሌ በእንግሊዝ ሀገር የሌበር ፓርቲው ምንም እንኳን ግራ ዘመም ቢሆንም ፣ ነገር ግን የወሰዳቸው እርምጃዎች ለምሳሌለንደንን የፋይናንስ ማእከል ማድረጉና ፣ በርካታ የወግ አጥባቂዎቹንም ርእዮተ – አለም በመውሰድ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ በሁለቱ ፓርቲዎች መሀከል ያለውን ልዩነትን አጥቧል ። ሌላውም እንዲሁ በአሜሪካን አገር ምንም እንኳን ሁለቱም ፓርቲዎች ዲሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካኖች አንዱ ስልጣን ሲይዝ አንዱ ሲቃወም የተለየ መስሎ ለመራጩ ቢታይም በተግባር ግን አዲሶቹ መሪዎች ከቀድሞው ፖሊሲ አለመከተላቸው መሪ የተለየ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል ። ጉልህ የሆነ ልዩነት በሁለቱ መሀከል የሚታየው በግብርን መጨመርና አለመጨመር ጉዳይ ላይ ሲሆን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ግን የሚጠበቀው ልዩነት በተግባር አይታይም ። ቀድሞ ቡሽ አሸባሪዎችን በጓንታናሞ ቤይ ሲያስሩ ፣ የቡሽን ድርጊቶች ነቅፈው ወደ ስልጣን የመጡት ኦባማ ደግሞ በስልጣን ዘመናቸው ፣አሻባሪዎች ናቸው የሚሏቸውን በሰው አልባ አውሮፕላኖች መግደልን አማራጭ አድርገው ወስደውት ቆይተዋል ። ስለዚህ ሁለቱም አስተዳደሮች በቅርፅ ጦርነት ውስጥ ይበልጥ እየተዘፈቁ መጡ እንጂ ከጦርነት ራስን የማውጣትና ሌላ አቅጣጫን የመያዝ አዝማሚያ አላሳዩም ። ይህም በሁለቱ ፓርቲዎች መሀከል በዚህ ዘርፍ ልዩነት የሚል አስተሳሰብን በመራጩ ህዝብ ዘንድ እንዲያድርና ሁለቱንም አንድ አድርጎ እንዲያያቸው ያደርጋል ለመራጩ ህዝብም አማራጭን ያሳጣል ።
ይህ ብቻ ሳይሆን ለድርድር ክፍት የሆኑ ስርአቶች በአጭር ጊዜ በድርድሩ የተወሰነ ስልጣናቸው ሊቀነስ ቢችልም እና የፖሊሲ ለውጥን ወይም ማሻሻያን እንዲያደርጉ ቢገደዱም ፣ ውሎ አድሮ ግን በድርድር ያጣውን መልሶ ለማግኘት ይችላል ። ለድርድር ክፍት ያልሆኑ ስርአቶች ግን ምንም እንኳን ለድርድር (Compromising) ፈቃደኛ ስለማይሆኑ ለወቅቱ ምንም ስልጣናቸው ባይቀነስና የፖሊሲ ማሻሻያን ወይም ለጊዜው ለውጥን ባያደርጉም ፣ ውሎ አድሮ ግን ነባር ችግሮችና ልዩነቶች ጉልበት ጨምረው ይመጡባቸዋል ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሽግግር የሚደረግበት ሁኔታ ከተፈጠረ ፣ቀድሞ ነገሮች በተወሰነ ደረጃ የለዘቡ ስለሚሆን ሽግግሩን ቀላል ሲያደርግ እንደ አብዮት የመሳሰሉ ስር ነቅል የስርአት ለውጦችን ከማድረግ ያድናል ።
አንድ መሪ የሚያደርገውን ነገር የሚያስከትለውንም ሆነ ያሚያደርገውን ነገር መዘዙንም ሆነ ጠንቁን ክፉንናደጉን በሚገባ የሚረዳ ነው መሆን አለበት ። ይህም ንቃተ – ህሊናው (Consciousness) ሊኖረው ሲገባ ነው ። ንቃተ – ህሊና ማለት አሁን እሚደረግ ነገር በወደፊቱ ላይ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ያለውን አንድምታ በበጎም ይሁን መጥፎ ከሌሎችበተሻለ መረዳት መቻል እንዲሁም ፣ በሌላ አነጋገር ንቃተ – ህሊና ማለት ሌሎችንም ሆነ ራስን በሚገባ ማወቅ (Self – Consciousness) ማለት ነው ።አንድ ሰው ራሱ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ መረዳት ፣ እንዲሁም ሌሎች በሱ ላይ የሚኖራቸውን ተፅእኖ በአግባቡ መረዳት ራስን ለማወቅ በእጅጉ ይረዳል ። ራስን ማወቅ ማለት በተዘዋዋሪ መንገድ ሌሎችን ጠንቅቆ መረዳት ማለት በመሆኑ ፣ ራሳቸውን ሆነ ሌሎችን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሪዎች የተሻሉ ውጤታማ መሪዎች መሆናቸው በአስተዳደር ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የታረጋገጠ ነገር ነው ።
በሰው ልጅ ዘንድ ሁለት አይነት ህሊናዊ ንቃቶች አሉ ተብሎ ይታመናል ። አንደኛው አእምሯዊ – ንቃተ – ህሊና (Mind Consciousness) የሚባለው ሲሆን ። ይህ ህሊናዊ ንቃት አለምን በየቀኑ የሚመራና የሚያስተዳድር ምክንያታዊ በሆነው የአእምሮ ክፍል የሚመራ ነው ። ይህም በአብዛኛው በዘመናዊ ትምህረት የሚሰጥና የተለያዩ ሙያዎችም ማለትም ምጣኔ – ሀብትን ፣ ፖለቲካን ፣ ሳይንስን ፣ስፖርት ፣ ስነ – ጥብብን ወዘተ የሚመራ ነው ። ይህም በትምህርት ስርአቱ ውስጥ የሚሰጥና በአለም ዙሪያ ባሉ ሀገራት በሙሉ ትምህርት መልክ የሚሰጥ ነው ።
ሌላኛው ሁለተኛው እንዲሁም የበለጠው መንፈሳዊ ህሊናዊ ንቃት (Spritual Consciousness) ነው ። ይህ በአብዛኛው በሀይማኖት መስራቾችና በሀይማኖት ሰዎች የሚታወቅ ነው ። መንፈሳዊ መገለጥ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል ። በአለም ላይ ታላላቅ ሀይማኖቶችን የመሰረቱ ሰዎች የዚህ ህሊናዊ ንቃት ባለቤቶች የነበሩ ናቸው ።እነኚህ መንፈሳውያን «ሚስቲክ» የሚባሉ ናቸው ። በየትኛውም ዘመን ግን የዚህ አይንት ሰዎች ቁጥራቸው ብዙም አይደለም ። በብዙ ክፍለ – ዘመናት ውስጥ ፣ ለሰዎች ብርሀን ለመሆን አንድ ጊዜ የሚከሰቱ ክስተቶች ናቸው ። ቡድሀ ፣ ክርስቶስ ፣ ሙሴ፣ ባሁላን የመሳሰሉ ሰዎች የዚህ የሚጠቀሱ ናቸው ። የዚህ አይነቱ ህሊናዊ – ንቃት የንቃት ከፍተኛው ደረጃ ሲሆን የዚህ አይነት ህሊናዊ – ንቃት ላይ ለመድረስ እዝነት (Compassion) እንዲሁም አለምን እንዳለችው መቀበል መቻልን ፣ ለመለወጥ አለመታገል እንዲሁም ያለውን ነባራዊውን ሁኔታ መቀበል (Surrender) ማለት ነው ። ይህም በምክንያት የተሞላው አእመሯዊ ከሆነው ህሊናዊ ንቃት በእጅጉ የተለየ ነው ። ለምሳሌ በአንድ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሰውንና አንድ የሀይማኖት ሰውን ብንጠይቅ ሁለቱ የሚሰጡት መልሶች የተለያዩ ናቸው ። በአሁኑ ወቅት የአለም የፖለቲካ መሪዎች ህሊናዊ ንቃት እንዲኖራቸው ይመከራል ። ይህም ለአለም ሰላም አስፈላጊ ጉዳይ ስለሆነና
ለምሳሌ መሪው በሚመራው ክፍል ውስጥ አንድ ችግር ቢፈጠር ለምሳሌ አንዱን ምንም ስህተት መስራት የለበትም ቢባል ፣ ወይንም አንዱ የሰራውን ስህተት አንደኛው አጉልቶ ቢያይበት ሰውየው ካደረገው በላይ እንዲቀጣ ቢፈልግ የፖለቲካ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው ። ይህም እስከ ፍርድ ቤት ድረስ መካሰስ ደረጃ የሚያዳርስ ሲሆን ፣ ይህም የፖለቲካ ወይም የህግ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው ፣ ይህም ጠለቅ ያለ የመረዳት ችሎታን ይጠይቃል ። ይህም ማለት ጉዳዩ በፖለቲካ ወይንም በህግ መታየት ያለበትና በዛ መንገድ ብቻ መፍትሄን የሚፈልግ ነውማለት ነው ።
ሌላው መሪነትን ቀውስ እሚያስከትል ነገር መሪው በስሩ የሚመራአቸው ተቋማት ከእርሱ ስልጣንና ቁጥጥር ወሰን ውጪ መሆን የሌለባቸው ሲሆን ፣ የአንዱ ተቋም ስልጣን ወሰን ከሌላኛው በግልፅ የተለየ መሆን አለበት። በአሜሪካ ለምሳሌ ሲአይ ኤንና ኤፍ ቢ አይን የስልጣን ወሰን በመለየት አሻሚ እንዳይሆን ማድረግ ችለዋል ። የዚህ አይነት ግልፅ የሆነ የስልጣን ወሰን ከሌለ አንድ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት የሚጠየቅ ስለማይኖር አንዱ በአንዱ ላይ ጣቱን እንዲጠቁም እና በአንድ ተቋም (መንግስት) ውስጥ ለአንድ አላማ የሚሰሩ ተቋማት መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር ያደርጋል ፣ሌላው ደግሞ መሪው በስሩ በአግባቡ ሊመራቸው ይገቡ የነበሩትን ሰዎችን ወይንም ተቋማትን በአግባቡ መምራት ካልቻለ ስርአት አልበኝነት ወይንም (Anarchy) ይፈጠራል ። ስርአት አልበኝነት በዘርፉ ባለሙያዎች በጣም የሚፈራ እና እንዳይከሰት በጥብቅ ጥረት የሚደረግበት ሲሆን መሪም ይህንን ሊፈጠር የሚችል ስርአት አልበኝነት አጥብቆ መከላከል አለበት ። ባሀኡላ እንደሚለው « እውቀቱ ለሌለው ሰው ነፃነትን ከመስጠት በላይ የበለጠ አደገኛ ነገር የለም» ።
ይህ አባባል በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ እየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ለማስተማር ከተናገረው በመዋስ ፣ የተከፋፈለ ቤት አይቆምም እንዲል መፅሀፉ ፤ ይህንን አባባል አብረሀም ሊንከን በአሜሪካን አገር ሰሜኑ ከባርነት ነፃ በሆነበትና ደቡቡ የአሜሪካ ክፍል ከባርነት ነፃ በነበረበት ወቅት ማለትም በአንድ ሀገር ላይ ሁለት ስርአትና ህግ በነበረበት ወቅት ይህን አባባል ተጠቅሞበታል ።እየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች መታዘዝ አይችልም ሲል አንድ ሰው ለሁለት አለቆች በአንድ ጊዜ ሊያገለግል አይችልም ማለት ነው ። አንድ መሪ ከሁለት አለቆች ትእዛዝን እሚቀበልበት ሁኔታ ሲፈጠር ቦታውን እልቀበልም ቢል ይመረጣል የሚል አስተሳሰብ አለ ።
ሌላው ደግሞ መሪዎች ነገሮችን መቆጣጠር ሲያቅታቸው ፣ ወይንም በአግባቡ መምራት ሲያስቸግራቸው ወይንም አመፅ ሲያጋጥማቸው በሽብር (Terror) ለመምራት ሊሞክሩ ይችላሉ ።ነገር ግን ይህ ስልት ለአጭር ጊዜ ሊሰራ ቢችልም በረጅም ጊዜ ግን ስኬታማነቱ እየቀነሰ ስለሚሄድ አዋጪ ስልት አይደለም ፣ውሎ አድሮ በመሪው ላይ ተቃራኒ ውጤትን ማስከተሉም አይቀሬ ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን ጎጂናበረጅም ጊዜ በቀላሉ የማይስተካከል ከባድ ዋጋንና ጥፋትን የሚያስከትል ሆኖ ሊገኝ ይችላል ። እንዲሁም የመሪዎቹን በታሪክ ትተውት በሚያልፉት አሻራ ላይ ጥቁር ነጥብን ጥሎ ያልፋል ።
በመሪነት ውስጥ የመሪነትን ቀውስን ከሚያስከትሉ ነገሮች አንዱ የበላይ አመራር እርስ በእርስ መከፋፈል ነው ። ሌላው ደግሞ የአመራር መፈረካከስ ነው ። አንድ አመራር በራሱ ውስጣዊ ችግር ምክንያት ሊፈረካከስ ይችላል ። ለምሳሌ እርስ በእርሱ ከተከፋፈለና ያንን ልዩነቱን በውይይት መፍታት ካልቻለ ፣ እንዲሁም ለምሳሌ መሪው ቢታመምና መምራት ቢያቅተውና አግባብ ባለው መንገድ አዲስ አመራርን መተካት ካልቻለ ፣ እንዲሁም የመሪው ማርጀት ፣መጃጀትና እንዲሁም በአዲስ ለመተካት ፈቃደኛ በማይሆንበት ወቅት የአመራር መፈረካከስ ሲፈጠር እንዲሁም ይህ በበኩሉ የአመራር እና የስልጣን ክፍተትን ይፈጥራል ። ይህ የስልጣን ክፍተትን የስልጣን ሽኩቻንና የአመራር አቅጣጫ መሳትንና መዋለልን ያስከትላል ።
ሌላው ለመሪነት ቀውስ አስተዋፅኦ የሚያደርገው ነገር ፣ መሪው የሚመራበት ዘመን ራሱ ይወስነዋል ። ለምሳሌ የሰላም ዘመን መሪ ፣ ለጦርነት ጊዜ ላይሆን ይችላል ። የጦርነት ጊዜ መሪ ደግሞ የሰላም ዘመን መሪ ላይሆን ይችላል ።ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሆኑት ዊኒስተን ቸርችል ሲሆኑ እንግሊዝን ከናዚ መንጋጋ ማዳን ቢችሉም በሰላሙ ጊዜ ግን በምርጫ ተሸንፈዋል ። በእርግጥ መራጩን ህዝብ ውለታ ቢስ ስለሆነ ሳይሆን በጦርነት ጊዜ አንድ መሪ የተከተለው ስረትራቴጂና በሰላም ወይም ትልቅ ችግር በሌለበት ሰአት የሚኖረው የአመራር ስልት የተለያየ ስለሆነና መሪው ራሱን ለሁኔታዎች ጋር ካለማዛመድና ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ።
እንዲሁም ፈረንሳይን ከናዚዎች በጀግንነት ተዋግተው ነፃ ያወጡት ቻርልስ ደጎልም ፈረንሳይን ነፃ ካወጡ በኋላ በፊት በጦርነቱ ሰአት እንደነበራቸው ተወዳጅነታቸውን ጠብቀው አልዘለቁም ፤ ብዙም ተወዳጅ አልነበሩም ።ደጎልም እንደ ቸርችል ሀሉ በምርጫ ተሸንፈዋል ።
በመሪነት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የህልውና ጉዳይን ለመረዳት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ሩዝቬልት እንዲሁም ቸርችል የእንግሊዝ መሪዎች ባይሆኑ ኖሮ አሜሪካ በኮሚኒስቶች ወይንም በፋሺስቶች እጅ ውስጥ መግባቷ አይቀርም ነበረ ፣ አውሮፓም የናዚ ጀርመን መፈንጫ ልትሆን ትችል ነበረ ፣ በእንደዛ ሁኔታም ናዚዎችን ከአለም ላይ ማጥፋት አይቻልም ነበረ ማለት ይቻላል የሚሉ የታሪክ ሰዎች አሉ ፤ ይህም መሪዎች ምንያህል የታሪክን አቅጣጫ በበጎም ይሁን በመጥፎ ሊቀይሩ እንደሚችሉ የሚያመለክት ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን በአብዮት ጊዜና በሰላም ጊዜም የመሪዎች ስራ ይለያያል ። የአብዮት ጊዜ መሪዎች የሰላም ጊዜ መሪዎች ሆነው ላይገኙ ይችላሉ ።
ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት የሰው ልጅ አእምሮ ጥሩ ጥሩውን ነው እንጂ አሉታዊ ወይም ክፉ የሆነውን ነገር ወደ ውስጥ አያስገባውም ያወጣዋል የሚል ግኝት አግኝተዋል ። ማለትም አንድ ሰው ጥሩ ጥሩውን ብቻ ነው እንጂ ክፉውን ወይም አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን መስማት ወይም ማየት ወይም ቢያየውና ቢሰማውም፣ እንዳለ አድርጎ ግን እውቅና መስጠትን አይፈልግም ። ይህም የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው ፣ ሁሉንም ነገሮች መጥፎ አድርጎ መመልከት ለሰዎች በጣም አሰልቺና የማይፈለግ ስለሆነ ነው ። መሪም ይህን መረዳት እውነታዊውና ነባራዊ የሆኑ ነገሮችን ለመረዳት ሊጋርደው የሚችለውን ነገር ለመረዳት ሊያግዘው ይችላል ።
ሌላው አንድ መሪ ራሱን ተፈላጊ ማድረግ በረጅም ጊዜ አንዱን ሀላፊነት ከጨረሰ በኋላ ሌሎች የበላለጡ እድሎች እንዲከፈቱለት ያደርጋል ይህም የሚሆነው መልካም ስሙንና ተአማኒነቱን የጠበቀ መሪ ከሆነ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ተፈላጊ ያደርገዋል ።መልካም ስም ውስጥ ክተተው ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s