ህሊናዊ – ንቃት ወይንም ንቃተ – ህሊና (Consciousness)

አንደ ጉጅረየፍ አባባል ሰዎች ንቃተ – ህሊና ቢኖራቸው ኖሮ በአለም ላይ በርካታ ጦርነቶችን ማስወገድ ይችሉ ነበር ይላል ። ህሊናዊ – ንቃትን ወይም ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ በአካባቢያችን ያለውን ነገር በተሻለ ጥራት ለመገንዘብ የሚያስችለን ሲሆን ፣ ጥሩ ተመልካች በመሆን ፣ የራሳችንንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ድርጊትና ውጤት መረዳት ማለት ነው ። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ሳያውቁ ወንጀልን ሊሰሩ ይችላሉ ካደረጉት በኋላ ሊያውቁት ይችላሉ ።
ንቃተ – ህሊና ማለት አንድ ሰው እሚያደርገውን ነገር መረዳት ማለት ነው ።ለምሳሌ አንድ ሰው መጠት ከጠጣ ወይም ሀሺሽ ካጨሰ ህሊናዊ ንቃቱ ደረጃ ይወርዳል ። በዚህም የሚያደርገውን ነገር ሳይጠጣ ወይም ሀሺሽ ሳያጨስ ከነበረው ይልቅ ያነሰ ይሆናል ። የሚያደርገውንም ነገር እንደ ሰላሙ ጊዜ ጊዜ የመገንዘብ አቅሙ ስለሚቀንስ የሚያደርገውን ነገር ያልተገባ ነገርን ሊያደርግ ይችላል ። ስለዚህ በመጠጥ ሀይል ወይም በሀሺሽ ተገፋፍተው ወንጀልን ይሰራሉ ።
ሕሊናዊ ንቃት የተሞክሮና የግንዛቤ ውጤትነው ። ተሞክሮው አንድ ሰው ከልምድ የዛን ነገር ውጤት ወይም መዘዝ ፣ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ጎኖችን ለመረዳት ሲያስችለው ፤ ግንዛቤው ደግሞ ነገሮችን እሱ እንዲሆኑ እንደሚፈልገው ወይም ሊሆን ይገባዋል በሚለው ሳይሆን ፣ነገሮችን እንዳሉና እንደሆኑ አድርጎ በጠራ እይታ መረዳት ማለት ነው ።ነገሮችን በደበዘዘ ፣ ብዥ ባለ ሁኔታ ። ህሊናዊ ንቃት ማለት እውነታውንና ገሀዳዊውን አለም በትክክል መረዳት ማለት ሲሆን ፣ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው እርሱም ሆነ ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር ውጤቱን ወይንም መዘዙን የሚረዳ መሆን አለበት ።
ነገር ግን በአሁኑ ዘመን ነገሮች የፖለቲካ ትክክለኝነት እንዲኖራቸው ተደርጓል ። በዚህ ዘርፍ ብዙ ተለውጧል ማለት ይቻላል ። ለምሳሌ እንደ ቀድሞው ሰዎችን በዘራቸው ፣ በእምነታቸው ፣ በፆታቸው ወዘተ በክፉ ማንሳት ቀንሷል ፣ ሁሉም ሰውፖለቲካዊ ተቀባይነት ያላቸውን አነጋገሮችን ነው እሚናገረው ። የብዙ ሀገራትን ህግጋትን ፣ ህገ – መንግስቶችን ብንመለከት ፖለቲካዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ተደርጎ ነው እሚዘጋጀው ። በሌሎች ዘርፎች ግን የሰው ልጅ ህሊናዊ ንቃትን ለማሳደግ ብዙም አልተሰራም ማለት ይቻላል ።
ሌላው ደግሞ የንቃተ – ህሊና አለማደግን የፈጠረ ነገር የትምህርት ስርአቱ ፣ የቴሌቪዥን ፣ የሬዲዮ የጋዜጣ መረጃዎች ተመሳሳይ መረጃዎችን እሚያቀብሉ መሆናቸው አንድ አይነት አስተሳሰብ ፣ አመለካከት እንዲፈጠር ሲያደርግ ፤ በአንፃሩ ግን አሁን ያለንበት ዘመን የመረጃ ዘመን በመሆኑ በተለይም ድረ – ገፆችን ብንወስድ አንድ ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ተቃራኒ የሆኑ ፅሁፎችን ማንበብ ይችላል ። በአሁኑ ወቅት ማንም ሰው የሚፈልገውን ነገር በድረ – ገፆች ላይ መፃፍ ስለሚችል በተለየ አቅጣጫ የሚያሳዩ አመለካከቶችን የማግኘት እድል አለው ።
ነገር ግን ህሊናዊ ንቃት በእፆችና በመጠጥ ብቻ ሳይሆን በተለመደውም ሰአት ቢሆን ሁሉም ሰው አንድ አይነት ግንዛቤ ደረጃ ላይኖረው ይችላል ። ይህን መረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው ።ህሊናዊ ንቃት አንድ ሲሆን እንደ የሁኔታው ወይንም እንደ ሰውየው አስተሳሰብ የሚቀያየር ወይንም ተለዋዋጭ (Subjective) አይደለም ። ልክ በአንድ ጉዳይ ላይ እውነት አንድ እንደሆነችው ሁሉ ንቃተ – ህሊናም አንድና አለም አቀፍም ጭምር ነው ።
በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የነበሩ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ምንም እንኳን በዘመንና በመልከአ – ምድራዊ አቀማመጥ የተለያዩ ቢሆኑም ።
ሀሳብ ሊመነጭ የሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች ሲኖሩ አንዱ መመሰጥና ትኩረት ወይም አትኩሮት ማድረግ ናቸው ።መመሰጥ አንድ ሰው በተለመደው የአእምሮ አስተሳሰብ ሊደርስብት የማይችለውን በመመሰት ይደርስበታል ። ትኩረት ማድረግ ደግሞ ረቀቅ ያሉና ብዙ ማሰብን የሚጠይቁ ነገሮችን ለመረዳት የሚጠያስችል ሲሆን ትኩረት ማድረግ በቀላሉ ሀሳብ ሲበታተን ሊበታተን የሚችል ነገር ነው ። ለምሳሌ አንድ ሰው ደስ እማይል ነገርን ሲያይ ፣ ሲሳማ ፣ ሲበሳጭ ትኩረት የማድረግ አቅሙ ይቀንሳል ስለዚህ ሀሳብ ለማመንጨት ያለውም አቅም ይዳከማል ።
ብዙውን ጊዜ ሰላም በሌላቸው፣ ውጥረት በነገሳባቸው ሀገሮች ውስጥ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማድረግ ያለው እድል የሚቀንሰውም ለዚህ ሲሆን ሰላም ያለውና የተረጋጋ ሀገር ግን በርካታ ሀሳቦችንና ፈጠራዎችን የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው ።
አንድ ሰው ግንዛቤው እየጨመረ ሲሄድ ብልጥ ሲሆን ፤ እያወቀ በሄደ ቁጥርም ፈሪ እየሆነ እሚያሰላ እየሆነ ይሄዳል ። የማያውቅ ሰው ግን ሌሎች ሰዎች በብልጠት የማይደፍሩትን ነገር እሱ ግን ለመድፈር አይመለስም ።አንድ ደግ የሆነ ሰውንና አንድ ጨካኝ የሆነ ሰውን ብናነፃፅር ፣ ደግ ሰዎች በአብዛኛው ከጨካኙ የበለጠ እውቀት ያላቸውና የተሻለ ማገናዘብ ችሎታያላቸው ሲሆኑ ፣ በአብዛኛው ጨካኞች ግን በአንፃሩ ያላቸው እውቀት ውሱንነቱን ማየት እንችላልን ። ደግ እና ጥሩ መሆን የበለጠ እውቀትንና ጥረትን ሲጠይቅ ፣ በአንፃሩ አጥፊ አረመኔ መሆን ግን ብዙ ማሰብንና ራስን ማስጨነቅን አይጠይቅም ፣ ልክ አንድ ነገርን ለመስራት ጥረትንና እውቀትን እንደሚጠይቀው ሁሉ ፣ አንድ ነገርን ለማፍረስ ምንም እውቀትን አይጠይቅም በቀላሉ መናድ እና ማፍረስ ይቻላል ።
በአለም ላይ ከምናውቀው ነገር ይልቅ የማናውቀው ፣ እርግጠኛ ከምንሆንበት ነገር ይልቅ እርግጠኛ የማንሆንበት ነገር የበለጠ ነው ፤ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ራሳቸውን እንደ አዋቂ አድርገው ነው የሚቆጥሩት ።
የንቃተ – ህሊናን ግንዛቤ ለማሳደግ ፣ ሌሎች ሰዎች ያደረጉትን መጥፎ የሚባለውን ነገር ለመረዳት እዝነት (ኮምፓሽን) አስፈላጊ ሲሆን ፣ አንድ ሰው እንዲህ አይነት በጣም መጥፎ ስራን የሰራው ይህን አደርጋለሁ ብሎ ነው ወይንም ለዚህ ብሎ ነው መረዳትን ይጠይቃል ። በጣም መጥፎ የተባለው ሰው ያንን ነገር ለምን እንዳደረገው ለመረዳት አስቸጋሪ ነው ፤ ነገር ግን ህግን ብንወስድ በእዝነት ወይንም በራሮት ላይ የተመሰረተ አይደለም ፣ በአንፃሩ የህግ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን አጥፊውን በመቅጣት (በመበቀል) ፣ በማስተማርና ፣ በማስወገድ መርሆዎችን ላይ የተመሰረተ ነው ።
ማንኛውም ሀሳብ የራሱ ተቃራኒ የሆነ ተመጣጣኝ ሀሳብ ሲኖረው ፣ ሀሳቦች ትግል መቼም ቢሆን አይቆምም። ሁሉም ነገር በጊዜ ውስጥ የሚሆን ሲሆን መደሰትም ፣ ማግባትም ፣ ልጅ መውለድም ፣ መማርም ፣መዋጋትም ፣መታመም ፣ መዳንም፣ ማንኛውም ልናስበው የምንችለው ነገር በሙሉ ሊሆን የሚችለው በጊዜ ውስጥ ነው ። ለሁሉም ጊዜ አለው የሚለው የጠቢቡ ሰለሞን አባባል ።
ነገር ግን ኮንሸስነስ በመላው የሰው ልጅ ደረጃ ሲታይ ግን እያደገና እያበበ የሚሄድ ነገር ነው ። የማህበረሰብ ግንዛቤና ንቃተ – ህሊናው በማንኛውም ነገር ውስጥ እየበለፀ የሚሄድ ነገር ነው ። ስብስብ የሆነው አጠቃላዩ የሰው ልጅ ህሊናዊ ንቃት (Collective Human Consciousness) ግን እየጨመረና እያደገ እንደሚሄድ መገመት ይቻላል ። በተለይም ፖለቲካዊ ፣ አለም አቀፋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሰዎች ግንዛቤ ከአመት ወደ አመት እያደገ እና እየተሻሻለ እንደሚሄድ መገመት ይቻላል ። ለምሳሌ እንደ ዘር ማጥፋት ፣ የመብት ጥሰት የመሳሰሉት ነገሮች ቀድሞ ብዙም ግንዛቤና ትኩረት ይሰጣቸው ያልነበሩ አሁን አሁን ግን ሰፊ ትኩረትን እያገኙ መተዋል ። ይህም በቀጥታ ከእውቀትና ከልምድ ይመነጫል ፣ በዘመናት ውስጥ እውቀት እያደገ ፣ ሳይንስም ጭምር እየተስፋፋ ስለሚሄድ ነው ። ለምሳሌ አንድ አዲስ በሽታ ቢከሰት መጀመሪያ ላይ ብዙ ሰው በዛ በሽታ ተጠቂ ይሆናል ፣ ነገር ግን ውሎ አድሮ ብዙ ሰው ግንዛቤን እየጨበጠ ሲሄድ ፣ የበሽታው ስርጭት እየቀነሰና ፣ እየተገታ ይሄዳል ፣ ነገሮችም ልክ እንደዛው ናቸው ።
ብዙ ሰዎች መረጃን ፣ እውቀትን ከተለያዩ ምንጮች መሰብሰብ ይችላሉ ፣ ነገር ግን ህሊናዊ ንቃት – ግን እንደእውቀት በቀላሉ የሚሰበሰብ ሳይሆን የተሞክሮ ውጤት ሊሆን ይችላል ።ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስራአቸውን በመስራት ፣ ቤተሰባቸውን በማስተዳደር ፣ በመሳሰለው አብዛኛውን የእድሜአቸውን ዘመን የሚያሳልፉ ሲሆን ፣ ቆም ብለው ስለ ህይወት ምንነት ለማሰብ ጊዜውም ሆነ አትኩሮቱ አይኖራቸውም ፣ በዚህም ምክንያት የዚህ አይነት ንቃት ደረጃን ሳይጎናፀፉ ያልፋሉ ። ስብስብ የሆነው ንቃት ህሊና እያደገ ሲሄድ በአንፃሩ የግለሰብ ንቃተ – ህሊና ግን ሀ ብሎ ከዜሮ የሚጀምር ነገር ነው ፣ ምክንያቱም አንድ ህፃን ልጅ በተራሱ የእድሜና የልምድ ተሞክሮ እያደገና ራሱ አለምን እየተረዳና እየተገነዘበ ነው የሚሄደው ፤ ይህም እንዲሆን አንድ ልጅ በራሱ ጊዜና ሁኔታ ነገሮችን የመረዳትና የራሱን ተሞክሮ እያዳበረ ሲሄድ የራሱን ህሊናዊ ንቃት እያዳበረ ይሄዳል ።
ሌላው ደግሞ ስለራሳችን መረዳትም በራሱ ንቃተ – ህሊና ሆኖ ሊገኝ ይችላል ፤ ለዚህም አንድ ሰው እህትና ወንድሞቹን ከሚያውቅ ይልቅ ራሱን በደንብ ሊያውቅ ይገባል የሚል አስተሳሰብ አለ በጥንታዊ ቻይናውያን አባባል ፤ አንድ ሰው ስለራሱ የሚያውቀው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ራሱን ሲያገኘው ነው ፣ በጣም መጥፎ ወይንም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን ስናገኘው በተለይም ራሳችንን በሚገባ ለማወቅ እድል እናገኛለን ፣ ራሳችን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በሚገባ የማወቅ እድል ይከፍልናል።
የንቃተ – ህሊና ማደግ እውነታዎችን በተሻለ ለመረዳት ያግዛል ፤ በአለም ላይ በአሁኑ ወቅት በብርካታ መስኮች ምንም እንኳን በርካታ ባለሙያዎችና እውቀት ያላቸው ሰዎች ቢኖሩም ፣ በጥልቀት መረዳት በኩል ግን ብዙም የተለመደ ችሎታ በብዙ ሰዎች የሚታይ ነገር አይደለም ። በፖለቲካው በምጣኔ – ሀብቱ ዘርፍ ምንም እንኳን በርካታ ችግሮች ቢኖሩም እነዚህን ችግሮች አስቀድሞ ለመረዳት ግን በአለም ላይ በርካታ እጥረቶች አሉ ።
አንድ አፅናፈ – አለማዊ አእምሮ አለ ተብሎ ይታመናል ። ይህም የሰው ልጅ በአሁኑ ዘመን ከቀድመው የተሻለ ህሊናዊ እውቀት ንቃት ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሎ የሚታመንበት ዘመን ነው ። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት አንድ ሀገር አንድ ሀገርን ለድንበር ወይንም ቅኝ ግዛት ስር ለማዋል ብሎ አይወርም እንደዛ ላድርግ ቢልም ተቀባይነትን ማግኘት አይችልም ፣ እንኳን አንድ ደካማ ሀገር ቀርቶ ሀያላኑም ቢሆኑ እንደዛ ማደረግ የሚችሉበት ዘመን ላይ አይደለም ያለነው ። ይህም ልእለ – አፅናፈ አለማዊ ንቃት ደረጀ ማደጉን የሚያሳይ ሲሆን ፣ በርካታ የአለማችን ታላላቅ ሀይማኖቶችን ብንወስድ አለም ሰላምን እምታገኘው አለም አንድ ስትሆን ነው የሚል ንግርት አላቸው ። ለምሳሌ የክርስትናን ሀይማኖትን ብንወ ስድ አውሬዎች ከአንድ ኩሬ ይጠጣሉ የሚል ሲሆን ይህ ማለት የተለያዩ እርስ በእርሳቸው የማይስማሙ ሀይማኖቶች እርስ በእርሳቸው የሚስማሙበት ጊዜ ይመጣል እንደ ማለት ነው ።
ኢንተሊጀንት ዲዛይን የሚል የሚል አስተሳብ ያላቸው ሰዎች አሉ ፣መጀመሪያ ቃል ነበረ ፣ ከዚያም ምድርና ሰማይ ተፈጠሩ ፣ የሚለው ማንኛውም ነገር ከሀሳብ ነው የጀመረው የሚለውን ያጠናክራል ። ሌላው ደግሞ ግራንድ ዲዛይን የተባለው ስቴፋን ሀውኪንግስ የተባለው እንግሊዛዊ ሳይነቲስት ያመነጨው አስተሳሰብ ነው ።

በሰው ልጅ ዘንድ ሁለት አይነት ህሊናዊ ንቃቶች አሉ ተብሎ ይታመናል ። አንደኛው አእምሯዊ – ንቃተ – ህሊና (Mind Consciousness)የሚባለው ሲሆን ። ይህ ህሊናዊ ንቃት አለምን በየቀኑ የሚመራና የሚያስተዳድር ምክንያታዊ በሆነው የአእምሮ ክፍል የሚመራ ነው ። ይህም በአብዛኛው በእኔነት (Ego-Centric) ዙሪያ የሚያጠነጥንና የበላይነትን ለማስፈን ፣ አሸናፊ መሆንን ፣ ሌሎችን መብለጥን የመሳሰሉትን ሚ የሚመለከት ነው ። ይህም በአብዛኛው በዘመናዊ ትምህረት የሚሰጥና የተለያዩ ሙያዎችም ማለትም ምጣኔ – ሀብትን ፣ ፖለቲካን ፣ ስፖርት ፣ ስነ – ጥብብን ወዘተ የሚመራ ነው ። ይህም በትምህርት የሚሰጥና በአለም ዙሪያ ባሉ ሀገራት በሙሉ ትምህርት መልክ የሚሰጥ ነው ።ይህ ህሊናዊ ንቃት በስብስብ መልክ ሲገለጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል ። ለምሳሌ ብሄረተኝነት ፣ እንዲሁም ብሄራዊ ስሜትን በተመለከተ ፣ እንዲሁም ማርክስ የመደባዊ ህሊናዊ ንቃት የሚለው የሰራተኞች ህሊናዊ ንቃት መጎናፀፍ የመሳሰለው የዚህ አይነት የስብስብ ህሊናዊ ንቃቶች ሲሆኑ ወዳልተገባ አቅጣጫ ካመሩ ለራሱ ለማህበረሰቡም ሆነ ለሌሎች ህልውና አደጋን የሚፈጥሩ ናቸው ።

ሌላኛው ሁለተኛው እንዲሁም የበለጠው መንፈሳዊ ህሊናዊ ንቃት (Spiritual Consciousness) ነው ። ይህ በአብዛኛው በሀይማኖት መስራቾችና በሀይማኖት ሰዎች የሚታወቅ ነው ። አለም በአለም ላይ ታላላቅ ሀይማኖቶችን የመሰረቱ ሰዎች የዚህ ህሊናዊ ንቃት ባለቤቶች የነበሩ ናቸው ። በየትኛውም ዘመን ግን የዚህ አይንት ሰዎች ቁጥራቸው ብዙም አይደለም ። በብዙ ክፍለ – ዘመናት ውስጥ ፣ ለሰዎች ብርሀን ለመሆን አንድ ጊዜ የሚከሰቱ ክስተቶች ናቸው ። ቡድሀ ፣ ክርስቶሰስ ፣ ሙሴ፣ ባሁላን የመሳሰሉ ሰዎች የዚህ የሚጠቀሱ ናቸው ። የዚህ አይነቱ ህሊናዊ – ንቃት የንቃት ከፍተኛው ደረጃ ሲሆን የዚህ አይነት ህሊናዊ – ንቃት ላይ ለመድረስ እዝነት (Compassion) እንዲሁም አለምን እንዳለችው መቀበል መቻልን ፣ ለመለወጥ አለመታገል እንዲሁም ያለውን ነባራዊውን ሁኔታ መቀበል (ሳረንድር) ማለት ነው ። ለምሳሌ በአንድ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሰውንና አንድ የሀይማኖት ሰውን ብንጠይቅ ሁለቱ የሚሰጡት መልሶች የተለያዩ ናቸው ። በአሁኑ ወቅት የአለም የፖለቲካ መሪዎች ህሊናዊ ንቃት እንዲኖራቸው ይመከራል ። ይህም ለአለም ሰላም አስፈላጊ ጉዳይ ስለሆነ ነው።

አንዳንድ ጊዜም ይሄ «Cosmic / Jesus Consciousness » በመባልም ይጠራል ። ይህም ወይ በዘረ – መል ውርስ ወይንም በከፍተኛ ደረጃ ንቃት የሚቀዳጁት ሊሆን ሲችል በብዛት መንፈሳዊ ከሆኑ ሀገራት እንደ ህንድ እና ደቡብ ምስራቅ እስያ ባሉ ሀገራት መንፈሳውያን የሚከሰት ነው ። ይህም በሌላ አነጋገር መንፈሳዊ መገለጥ በመባል የሚጠራ ነው ። ይህም አለምን እንዳለችውና እንደሆነችው አድርጎ የመረዳት አስተውሎት ነው ። እንደውም አንዳንድ የመንፈሳውያን ሊቃውንት እንደሚመክሩት ወደፊት አለማችንን ከጥፋት ለማዳን የአለም እሚመሩት የፖለቲካ ሰዎች የዚህ አይነት ንቃተ – ህሊና እንደሚኖራቸው አስፈላጊ ነው የሚል ሀሳብ አላቸው ። ታላቁ ግሪካዊ ፈላስፋ ፈላስፋዎች ናቸው ሀገርን መምራት ያለባቸው የሚላቸው የዚህ አይነት ሰዎችን ነው ። ሄግልም መንፈስ ነው የሚመራቸው የሚላቸው መሪዎች የዚህ አይነት መሪዎች ናቸው ።

ህሊናዊ – ንቃትን በተመለከት በአለም ላይ አራት አይነት ሰዎች አሉ ።

ህሊናዊ ንቃት ያላቸው እንዲሁም ከፍተኛ ችሎታና ብቃት ያላቸው እነኚህ በአለማችንላይ በተለያዩ ከፍተኛ ሙያዎች ላይ የምናቸው በርካቶቹ የታላላቅ ሀይማኖቶች መስራቾች መንፈሳውያን ሲሆኑ ፣ እንደ ቡድሀ ፣ ሙሴ ፣ ክርስቶስ ፣ ባሀኡላን የመሳሰሉ መንፈሳዊ ፀሀዮች ናቸው ። ይህ ብዙም የተለደመ ባለመሆኑ የዚህ አይነት ሰዎች የሚከሰቱት በክፍለ ዘመናት ውስጥ ወይንም በበርካታ ትውልዶች መሀከል ነው ። የዚህ አይነት ሰዎች በጣም ብርቅ ከመሆናቸው የተነሳ በበርካታ ትውልዶች ውስጥ ተራርቀው የሚፈጠሩ ናቸው ፤ በአንድ ትውልድ ውስጥ እንኳን ሊገኙ የማይችሉ ናቸው ። ስለዚህ ያለው ትውልድ ቀድሞ በተፈጠሩ መንፈሳውያን ባስተማሯቸው ትምህርቶች በመከተል ፣ የእነሱን አስተምህሮ በመቀበልና በየቀኑ ያንን በውስጣቸው እንዲሰርፅ በማድረግ ያለው ህብረተሰብ ሲያስባቸውና ትምህርታቸው ለመከተል የሚመርጣቸው ናቸው ። ይህ መንፈሳዊ መገለጥ ተደርጎም ሊታይም ይችላል ። ይህ ከፍተኛ የመረዳት አስተውሎት ነው ።

ህሎናዊ ንቃት የሌላቸው ፣ ነገር ግን ከፍተኛ ብቃትንና ችሎታ ያላቸው ። እነኚህ አለማችንን በእውቀታቸው የሚያሽከረክሩ ናቸው ። በፖለቲካ መሪነት ፣ በንግድ መሪነት ፣ በአስተዳደር ፣ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ቀዳሚ የሚሆኑና ፣ በአጠቃላይ አለምን የሚመራው በአመክንዮ የሚመራ አእምሮ ነው ። ይህም ብቻም ሳይሆን ታላላቅ የሳይንስ ፣ የምጣኔ – ሀብት ፣ የፖለቲካ ፣ የህግ ጠቢባን ፣ የማህበረሰብ ፈላስፎች የመሳሰሉት የዚህ ዘርፍ አባል አባላት ናቸው ።

ህሊናዊ – ንቃት ያላቸው ነገር ግን ከሌሎች ጋር ተግባብተው ችሎታቸውን ተግባራዊ ማድረግ የማይችሉ ወይም «ፖለቲካዊ» ችሎታ የሌላቸው። እነኚህ ህሊናዊ ንቃቱ ቢኖራቸውም ግንዛቤያቸው ለራሳቸው በመሆኑ ማህበረሰቡ የሚጠቀምባቸው አይደሉም ። የራሳቸን ህይወት ገለል ብለው የሚኖሩ ሲሆኑ ማህበረሰቡ የሚያደርገው ብዙም ስለማይጥማቸው ወደ ማህበረሰቡ ጉዳይ እምብዛም አይገቡም ። ማህበረሱም በሚናገሯቸው ነገሮች ምንም እንኳን ትክክል ናቸው ብሎ ቢያደንቃቸውምእንደ አእምሮውን እንደ ሳተ አድርጎ ነው እሚመለከታቸው ። ከሀገራችን ገፀ – ባህርያት ብንወስድ በፍቅር እስከ መቃብር መፅሀፍ ላይ ያለው ጉዱ ካሳ ምንም እንኳም የማህበረሰቡን እንከን ከሁሉም በተሻለ መረዳት የቻለ ቢሆንም ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ግን እንደ ነካ እንደሚያርደርገው ፣ እና እሚናገረውን እንደማያውቅ ተደርጎ ነው የሚታየው ። እሱም የማህበረሰቡ ስለማይጥመው ራሱን ሲያገል ፣ ማህበረሰቡም የእርሱን ሀሳብም ሆነ መሪነትን ለመቀበል አክብሮትም ሆነ ፈቃደኝነት የለውም ።

ህሊናዊ ንቃትም ፣ ሆነ ከፍተኛ ብቃትም ሆነ ችሎታ የሌላቸው ። እነኚህም አብዛኛውን የተራውን ማህበረሰብን የሚወክል ነው ። እነኚህ በአብዛኛው ባለው ስርአት ውስጥ አሸናፊ ሆነው መኖር የሚፈል ጉና ፣ የተለደው ስርአት ተከትለው ህይወታቸውን የሚገፉና በዚያም ደስተኛ የሚሆኑ ናቸው ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s