መሪ የሚወርሰውና ትቶት ስለሚሄደው አሻራ (Legacy)

ማንኛውም መሪ ሰው እንደመሆኑ መጠን ፣ እድሜውን ጨርሶ ወይንም የሀላፊነት ዘመኑን ጨርሶ መልቀቁ አይቀርም ። ስለዚህ ትቶት ስለሚያልፈው አሻራ ማሰብ አለበት ። አንድ መሪ የፈለገ ተፈላጊ ቢሆንና ችሎታ ቢኖረው ወይንም ከፍተኛ ድጋፍ ቢኖረው በመጨረሻ የሚመራውን ተቋም መልቀቁ አይቀርም ። ብዙውን ግዜ ብቃትና ችሎታ እንዲሁም ተክለ – ሰውነት ያላቸው መሪዎች ከተቋማቱ ጋር ሳይነጣጠሉ ተያይዘው የሚታዩበት ጊዜ አለ ። ለምሳሌ ስቲቭ ጆብስ ከአፕል ኩባንያ ጋር ፣ ቢል ጌትስ ከማይክሮሶፍት ጋር አብረው የሚታዩበት ፣ አንዳንድ የሀገር መሪዎችም ከዚያች ሀገር ጋር ተያይዘው የሚታዩበት ጊዜ አለ ። ነገር ግን መሪዎች ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን በጨረሻ ከያዙት ቦታ መልቀቅ ወይንም መሰናበት እጣ አይቀሬ ነው ። ነገር ግን በአንፃሩ ተቋማትና ሀገራት ግን ከሰዎች በላይ የረዘመ እድሜ እንዳላቸው ይታወቃል ።

አንድ መሪ ከቀደምት መሪዎች የወረሰው አሻራ ይኖራል ። አሻራ ወይም ቅሪት ወደፊት የሚያስተላልፈው ብቻ ሳይሆን እርሱ ከቀደምት መሪዎች የወረሰውም ጭምር ነው ።መሪው ያለፈውን አሻራ ሊወደውም ሊጠላውም ሲችል ፣ ነገር ግን ካለፉት የወረሰው በጎን ይሁን መጥፎ የታሪክ ቅሪት እንደሚኖር ግን መገመት አለበት ።

ካለፈው ከወረሰው ብንጀምር ጥሩም ፣ መጥፎም እንዲሁም ጠንካራም ደካማ ጎኖችም የሚወረሱ ሲሆን የስልጣን ምንጭም ሆኖ ያገለግላል ።ሌጂቲሜሲ የስልጣን መንጭ ሲሆን ፣ ጠንካራ የነበሩ የቀድሞዎቹ መሪዎች ለምሳሌ መሪው የቀድሞው መሪዎች ያደረጉትን ሁሉ አድርጌ እነሱ ያመጡትን ድል አመጣለሁ ቢል ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል ። መሪው በራሱ መንገድ ራሱ በቀደደው ጎዳና መሄድ ሲኖርበት ፣ የቀድሞዎቹ ገናና መሪዎች ያደረጉትን ሁሉ በመከተል የነሱን ስኬት ማስመዝገብ አይችልም ።

ለምሳሌ በቀድሞ ዘመን ከነገስታቱ የዘር ሀረግ መመዘዝ ለአንድ ንጉስ ለመንገስ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነበረ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከነገስታቱ የዘር ሀረግ ያልሆነ መንገስ እንደማይችልና ህዝቡ እንደማይቀበለው የታወቀ ነው ። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በታሪካችን ዘመነ – መሳፍንት በመባል በሚታወቀው ዘመን በጦር አሸናፊ የነበሩ መኳንንትና መሳፍንት ምንም እንኳን አሸናፊ ቢሆኑና መንገስ ቢችሉም ነገር ግን በቀጥታ ከነገስታቱ የዘር ሀረግ የሚመዘዙ ባለመሆናቸው ፣ የህዝብ ተቀባይነትን እንደማያገኙ ስለሚያውቁ ከነጋሲ ዘሮች እየመረጡ እያነገሱ በቤተመንግስቱ ለይስሙላ ያስቀምጡ ነበረ ። ይህም ህዝቡ የነገሰው የነጋሲ ዘር ነው ብሎ እንዲያምንና የህጋዊ ተቀባይነት ጥያቄን እንዳያስነሳባቸው ለማድረግ ሲባል ያደርጉት የነበረ ሲሆን ፣ ቀላል ለማይባሉ ዘመናት ሀገሪቱ በዚህ መንገድ መተዳደሯ በታሪክ ሰፍሮ የሚገኝ ነው ።

ወደ ሀገርኛው አባባል ስንመልሰው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለች በቅሎ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው ። ይሄ ነገር የግብፁ ፈርኦን በቀን በሺ የሚቆጠሩ በቅሎዎች ፣ በጎችና ፍየሎች የሚቀርቡለት የነበረ ቢሆንም ከእኔ በኋላ ግንብፅን የአባይ ውሀ ይብላት ይል እንደነበረ ይነገራል ።
ይህ ብቻ ሳይሆን መሪው እርሱን እሚገልፁት የራሱ ነገሮችም ሊኖሩት ይገባል ። የቀድሞው መሪ በጣም የታወቀ ፣ የተወደደ እንዲሁም ግዙፍ ስብእና ያለው ቢሆንና አንድ መሪ እንደዚህ አይነቱን ባለ ግዙፍ ተክለ – ሰውነት ባለቤት ቦታ ቢተካ ፣ እንዳለ የቀድሞውን ሰው ግዙፍ ስብእናውንና አካሄዱን ለመውረስና ለመከተል ቢሞክር ያንን ግዙፍ ቦታ ሙሉ በሙሉ መሸፈን ሳይችል ይቀራል ። ስለዚህ ቀስ በቀስ የራሱን መንገድ በቀስ ከግዙፉ ጥላ ከመጋረድ መውጣት አለበት ።

በብዛት በምእራቡ አለም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ከተሸነፈ ብዙውን ጊዜ የፓርቲው መሪዎች ይቀየራሉ ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የቀድሞዎቹ መሪዎች ፓርቲው እንዲሸነፍ ያደረገውን ምክንያት አዲሶቹ መሪዎች በመቀየር ፓርቲውን ወደ ድል እንዲያመጡት ሲባል ነው ።የቀድሞዎቹ መሪዎች እንዳለ ቢቀጥሉ ፓርቲው የፖሊሲም ሆነ የአደረጃጀት ለውጥ የማምጣት እድሉ ጠባብ ነው እሚሆነው ፤ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግም ካስፈለገ አዲሶቹ መሪዎች ያንን የፖሊሲ ለውጥ ከቀድሞው አመራር በተሻለ ለውጥ የማድረግ እድል ስለሚኖራቸው ነው ። ይህንን ስለሚረዱ ከቀድሞዎቹ መሪዎች አሉታዊ ሊሆን ከሚችል ጥላ እንዲወጣ ያስችለው ዘንድ አመራሮቹን በመቀየር ፓርቲው ወደ ቀድሞው ህዝባዊ ተቀባይነቱ ለማምጣት ያለውን እድል ያሰፋዋል።ነገር ግን የግድ የአመራር ለውጥ ማምጣት ፣ አንድ ፓርቲ በሌላ ምክንያትም ሊሸነፍ ይችላል ። በዛው አመራርም ከተወሰኑ አመታት በኋላ ወደ ድል ሊመጣም ይችላል።

ሌላው ደግሞ በተለይም በቀደመው የአመራር ዘመን በጣም ሰኬታማ የሆነ ፣ የጎላ ተክለ – ሰውነት የነበረውን መሪ መተካት ይበልጥ አስቸጋሪ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ አዲሱም መሪ የቀድሞውን ስኬታማና ከፍተኛ ተፅእኖ ያለውን መሪ ስለተካ ተከታዮቹም አዲሱ መሪ ያንን ተከትሎ እንዲሄድ ስለሚጠብቁ ሲሆን ፤ ይህም ብቻ ሳይሆንየቀድሞው መሪ የነበረው የገዘፈ ተክለ – ሰውነት እና ስብእና (Charisma) የአዲሱን መሪ ይጋርደዋል ፣ ሰዎች በአዲሱን መሪ ውስጥ የቀድሞውን መሪ ነው እሚያዩት ። ስለዚህ ከቀድሞው መሪ ጥላ መውጣትና በራሱ መንገድ ወይም ጎዳና መጓዝ አለበት ። በቀድሞው መሪ ጥላ ከተጋረደና ከዛ ጥላ መውጣት ካልቻለ የራሱን ገፅታ ወይም ምስልመፍጠርም ሆነ በራሱ መንገድ ሊያደርግ እሚፈልገውን ማድረግ አይችልም ።

ይህን አንድ መሪ ስኬታማ እንዲሆን ፣ የራሱን መንገድ መከተል አለበት ፤ አንዳንድ ሰዎች የቀድሞዎች ሰዎች ያደረጉትን በማድረግ ስኬታማ እንደሆናለን ብለው የሚያስቡ አሉ ፤ ነገር ግን አንድ መሪ ምንም እንኳን ሌሎች ያደረጉትን ማወቅና ከዚያም ትምህርትን መውሰድ የሚጠቅመው ቢሆንም የራሱ ባልሆነና ሙሉ ለሙሉ በሌሎች ሰዎች በሆነ እውቀት መተማመን የለበትም ፤ ከዚያ ይልቅ በተለይ በጣም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የራሱን መስመር መከተል ይበልጥ ይጠቅመዋል ። ሌላው ደግሞ መሪው የቀድሞዎቹ መሪዎች ያደረጉትን መንገድ ብቻ ተከትሎ የሚሄድ ከሆነ በራሱ ትቶት የሚሄደው አሻራወይም ኗሪ ታሪክ ፣ ወይም ቅርስ (Legacy) አይኖረውም ። ከቀድሞው መሪ ራሱን የሚለይበትና የራሱ የሆነ ትቶት ሄደ የሚባለው አሻራ አይኖረውም ። ለምሳሌ የቀድሞው መሪ በአንድ ጉዳይ ላይ በማተኮር ስኬትን አግኝቶ ከሆነ ፣ እርሱ ደግሞ ሌላ አቅጣጫን በመከተል በዚያ መስመር የራሱን ስኬት መፍጠር የራሱን አሻራ ማሳረፍ መቻል አለበት ።

ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የነበሩት ሁኔታዎችና አሁን ያሉት ሁኔታዎች በጣም ስለሚለያዩ ነው ። ቀድሞ የነበሩ መሪዎች ያገኙት እድል ፣ የገጠማቸው ፈተና እንዲሁም አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታዎች ቀላል በማይባል ሁኔታ ይቀያየራሉ ። ስለዚህ አዲሱ መሪ በድሮው የቀድሞዎቹ መሪዎች ባገደረጉት ዝም ብሎ ቢጓዝ ወደ ስኬት ለማምራት ያለውን እድል ያጠባል ። ስለዚህ ከወቅቱ ጋር መሄድ አስፈላጊ ነው ። ልክከጦጣይቱ ተማሪው ደብተሩ ላይ ፅሁፉም ፅፎ ሲጨርስ ሲጨርስ ሲሄድ ልክ እሱ ያደረገውን አይታ መፅሀፉን እላዩ ላይ እየቸከቸከች ስታስቸግረው ፣ ተማሪው ለብልሀቱ ቢላዋ አምጥቶ በስለት በሌለው በደነዘው በኩል አንገቱን አስነክቶ ሲያስቀምጥ ትመለከታለች ፣ ከዚያም ቢላዋውን አስቀምጦ ሲሄድ እንደለመደችው ልክ እሱ እንዳደረገው አደርጋለሁ ብላ ቢላዋውን በስለቱ በኩል አንገቷ ላይ ብታውለው አንገቷን ቆርጦ እንደጣላት ሁሉ ፣ በአመራር ውስጥም አንዱን መሪ ለድል ያበቃውን አድርጌ ሌላ መሪ ያደረገውን እኔም አድርጌ እንደ እሱ ስኬታማ እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ለመሪው የራሱን ውድቀት እንደ እንደ ማምጣት ያስቆጥርበታል ።

የሰው ሁሉ እድሜው የተወሰነ ነው እንደሚለው መፅሀፉ ፣ መሪም ስለወደፊቱ ማሰብ አለበት ፣ በእርግጥ መሪው እሱ የማይኖርበትን ዘመን በአካል ተገኝቶ ቅርፅ ሊያሲይዝና ሊመራ ባይችልም ፣ አሁንላይ ሆኖ የሚያደርገው ነገር ግን ወደፊቱ ለሚመጣው የራሱ የሆነ በጎም ይሁን አሉታዊ ተፅእኖ ኖረዋል ።መሪው ካወቀውና ከተረዳው አሁን ካላይ ሆኖ እሚያደርገው ማንኛውም ነገር እሱ በማይኖርበት በወደፊቱ ላይ የተወሰነ የራሱን አሻራና ተፅእኖን ሊያሳርፍ ይችላል ።

ልክ ዘንድ አርቲስት ስራው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆንለት እንደሚፈልገው ሁሉ ፤ አንድ መሪም ጥሎት ስለሚሄደውም አሻራ ማሰብ ሲገባው ፤ ከሱ በኋላ ስለሚመጣውና መጪው ትውልድ በጥሩ እንዲያስታውሰው ጥሩ ስራን ትቶ ለማለፍ መጣር አለበት ።ለምሳሌ የሀይለስላሴን ስርአት ብንወስድ ከቀዳሚዎቻቸው የኢትዮጲያ ነገስታት የበለጠ ተወዳጅነት የላቸውም ።

ለዚህም ምክንያቱ በጣም ቀላል ነው ። ማንም ሰው ከተወሰነለት እድሜ በላይ አይኖርም ስለሆነም ያ ሰው ያስተማራቸው ትምህርቶች ፣ የወጠናቸው ሀሳቦች በእርሱ እድሜ ተሳክተው እማያልቁ ስለሆነ እና በርካታ አመታትንና ትውልዶችን ሊጠይቅ ይችላል ። ስለሆነም የትውልድ መተካካት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል ። መሪም ሰው እንደመሆኑ እንደሰው ይታመማል ብሎም ያልፋል ። ይሁን የምንወዳቸውም ይሁን የማንወዳቸው የኛም ሀገር ይሁን የውጪ ሀገራት መሪዎች እንደ ሰው ሲያልፉ ታሪካቸው በታሪክ መፅሀፍት ውስጥ ነው እሚገኘው ፣ ስለዚህ ጥሩ ለሰሩ እስከመቼውም ድረስ ሲመሰገኑ ይኖራሉ ፤ መጥፎ ከሰሩም እንደዛው እንደተቀሱና እንደተኮነኑ ይኖራሉ።

ለቀጣዩ የሀገር ወይንም የአንድ ድርጅት ቀጣይ ህልውና ሰላማዊና ፣ እንዲሁም አዲሱ መሪ ህጋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ሲባል በአንድ ድርጅት ውስጥ መተካካት ሲካሄድ ወይንም አንድ መንግስት በአንድ መንግስት ሲተካ መተካካትን ሲባል ህግንና ስርአቱን ተከትሎ መሄድ አለበት ። ይህም እጅግ በጣ ም አስፈላጊ ነው ። ህገ – ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ስልጣን የመጡ መሪዎች ያንን ያለፈ ታሪካቸውን መሸፈን የማያደርጉት ነገር የለም ። በሀገር ደረጃን ስናስበው ለምሳሌ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በ1980ዎቹና እስከ 90ዎቹ ድረስ መፈንቅለ – መንግስታት ይካሄዱ ነበር ነገር ግን ፣ አንደኛ ውጤቱ አጠራጣሪ ከመሆኑም በላይ ደም አፋሻሽም ጭምር በመሆኑ ፣ ሌላው ደግሞ ቢሳካም ባይሳካም ደም አፋሳሽ ከመሆኑ በተጨማሪ ፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ስልጣን የመጡ ሀይላት በተደጋጋሚ ወደ ስልጣን መ ጣን የሚሉት የቀድሞው መሪ አጠፋ የሚሉትን ሰበብ አድርገው ቢሆንም ፣ እነሱም በተራቸው መሪዎች በሚሆኑበት ወቅት የገቡትን ቃል ማክበራቸው በእጅጉ አጠራጣሪ ነው ። አፍሪካ ውስጥ በዚህ አይነት መንገድ ስልጣንን ያስረከቡ መሪዎች ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ነው ። ምክንያቱም ስልጣኑን እንዲይዙ ያደረጋቸው በራሳቸው ሀይልና ጉልበት ነው እንጂ በህዝብ ፈቃደኝነት ባለመሆኑ ለህዝብ ፍላጎት ጠብቀው መሄዳቸው አጠራጣሪ ነው ።

በዚህም በርካቶች ወደ ስልጣን መጥተው እነሱም ከእነሱ ቀድሞ ከነበረው ብሰው ቁጭ ያሉ ወይንም የማይሻልን ስርአትን የፈጠሩ መሪዎች በአለም ዙሪያ ተከስተዋል ። እነሱን ለማስወገድና በአዲሱ ስርአት ለመረዳት እንደገና ሰላምን ማጣትን ያስከትላል ። በእርግጥ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በህዝብ በተመረጠ መንግስት እንዲተካ ያደረጉና የተሳካላቸው በጣም ጥቂት መሪዎች አሉ ፣ ነገር ግን በአብዛኛው የዚህ አይነቱ መንገድ አጥፊ የሆነው ጎኑ ይብሳል ። በእርግጥ ዲሞክራሲ ባለበት ሀገር የመተካካት ስርአቱ ግልፅ ያለ በመሆኑ አሻሚ የሆኑ ሁኔታዎች አይፈጠሩም ። በመሆኑም አንድ መሪ ከእርሱ በኋላ የመተካካት ስርአት የሌለው ከሆነ ራሱ በስልጣን ላይ እያለ ፅኑና የማያሻማ የመተካካት ስርአትን ማቆም መቻል አለበት ። ልክ አንድ አባት ልጆቹ እርስ በእርሳቸው በንብረት እንዳይጣሉ ግልፅ ያለ ኑዛዜን አስቀምጦ እንደሚሄደው ሁሉ መሪም እንደዛው ማድረግ ፣ ስርአቱ ከሌለ ስርአቱ እንዲኖር ማድረግ በተጣለበት ሀላፊነቶች ዋነኛውና ትልቁ ነው ።

ሰላማዊ የመተካካት ስርአት እንዲኖር ሀገራት ጉዳዩን ግልፅና በማያሻማ ሁኔታ መሪዎች እንዴት እንደሚተኩ የሚገልፅ ህገ – መንግስትም ይሁን ሌላ የህግ ስርአት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ግልፅ ካልሆነ ግን በቀሩት መሪዎች መሀከል የስልጣን ሽኩቻና ትግል ፣ እንዲሁም አዲሱ መሪ ስልጣኑን አስረግጦ እስከሚያፀና ድረስ ትርምስና ውዥንብር እና ሌሎችም ጥፋቶቸ ሊከሰቱ ይችሉ ። ስለሆነም የመተካካት ስርአት ማስፈን ቁልፍና አስፈላጊ ከሆኑት የመሪነት ተግባራት ዋናው ነው ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት መሪዎች ወጣቶችን የማያቀርቡና ወደ ስልጣን የማያስጠጉ የነበሩ በመሆናቸው ያረጁት መሪዎች እርስ በእርስ እየተተካኩ አንድ በአንድ ሞተው ሲያልቁ ከእነሱ ቀጥሎ የሚረከብ ወጣት ትውልድን አላዘጋጁም ማለት ይቻላል ። ከብሬዥኔቭ ጀምሮ በተከታታይ ሶቭየት ህብረትን የመሩት ያረጁት መሪዎች እዛው እርስ በእርስ እየተተካኩ ሲቀጥሉ እነሱም ብዙም ሳይቆዩ በሞት ሲለዩ ፣ የሚተካቸው ወጣት ትውልድ አልነበረም ፣ሁሉም ሞተው ሲያልቁ ስርአቱን ሊያስቀጥል የሚችል ወጣት ትውልድን ግን አላዘጋጁም ነበረ ። በአንፃሩ ቻይናውያንን ብንወስድ የዚህም የመሪነትን ክፍተት በሚገባ ተረድተውት ነበረ ማለት ይቻላል ።

ከማኦ ዜዱንግ ሞት በኋላ የመጡት የቻይና መሪዎች በተለይም ዴንግ ዚያዎፔንግ ለወጣቶች በማስረከብ ለስልጣኑ ወንበር ገለል ሲሉ በኋላም በሞት ሲለዩ የተተኩትም መሪዎች ያንኑ መስመር በመከተል ፣ ተተኪ ወጣቶችን በመመልመል የቻይና የኮሚኒስት ስርአት አገዛዝን ማስቀጠል ችሏል ። በእርግጥ ምርጫው በራሱ በኮሚኒስቶት ፓርቲው ውስጥ እርስ በእርስ የሚከናወንና በዲሞክራሲያዊ መንገድበህዝብ የተመረጡ አይደሉም የሚል ትችት ሊቀርብበት ቢችልም በአንፃሩ ግን ስርአታቸውን ማዳንና ማስቀጠል ችለዋል ። በተመሳሳይም የሳኡዲ አረቢያ መሪዎችም የዚህ አይነቱ ሁኔታ ዋና ዋናዎቹ ልኡላንና አልጋ ወራሾች በሞት ሲያልፉ የሚተካ የቅርብ ወጣት የሌላቸው ከመሆኑ የተነሳ አዲሱን ትውልድ አቅርበው ወደ ስልጣን ባለማስጠጋታቸው የተነሳ እንደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ውስጥ የተፈጠረው አይነት የስልጣን ክፍተት ሊፈጠርባቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል ።
ብዙውን ግዜ በምእራባውያን ሀገራት በተደረጉ ጥናቶች በተደጋጋሚ እንደታየው አንድ ሁነኛ ስራ በአራት ትውልድ ውስጥ ፍርስርሱ እንደሚወጣ መረዳት ተችሏል ። የመጀመሪያው ትውልድ ያንን ነገር ጥሮና ተጣጥሮ ያንን ነገር የገነባና የፈጠረ ሲሆን ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ የመጀመሪያው ትውልድ የገነባውን ያሳደገና ያደራጀ ሲሆን ሶስተኛው ትውልድ ግን ብዙም እድገትን ሳያመጣ ነገር ግን ባለበት እንዲቀጥል ያደርገዋል ፣ በአራተኛው ትውልድ ዘመን ግን በግዴለሽነትና ባለማወቅ ፣ በስንፍና አራተኛው ትውልድ ሁሉንም ነገር ያፈራርሰዋል የሚል ሀሳብ አለ ። በእርግጥ ሁሉም አራተኛ ትውልዶች ያንን ነገር ያፈራርሱታል ማለት አይደለም ከተረከቡት አስበልጠው ማሳደግና መምራት የሚችሉ በርካታ አራተኛ ትውልዶች እንዳሉም ይታወቃል ። በእርግጥ ይሄ ሀሳብ ማጠቃለያ አይደለም ።

በመሆኑም ምንም እንኳን አንድ መሪ መተካት ቢኖርበትምና ፣ እርሱን ለመተካት አስፈላጊው ምክንያት ከበቂ በላይ ቢኖርም የሚተካበት መንገድ ህጋዊ መሆን መቻል አለበት ። ይህም ለቀጣዩ ስርአት ለወደፊት ህጋዊ ተቀባይነትና የህዝብ ይሁኝታ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ።
መሪው ትቶት የሚያልፈው አሻራ የሚመራው ድርጅት ፣ ወይም ሀገር እንዳለበት ሁኔታና ፣ ችግር ውስጥ ካለም እንዳለበት ችግር ይወሰናል ። ስለዚህ ያንን ተቋም ችግር በመፍታት ችሎታውና ብቃቱ ነው (legacy) የሚወሰነው ።

የመሪነት እሴቱ ትቶት የሚሄደው አሻራ (Legacy) ሲሆን ፣ አንድ መሪ ስልጣን የሚቆይበት ዘመን የትየለሌ ከሆነውና መጨረሻ ከሌለው ጊዜ አንፃር ስናየው በጣም አጭር ሲሆን ፣ እንኳን አንድ መሪ ስልጣን ላይ የሚቆይበት ቀርቶ የሰው ልጅ እድሜም የተገደበ ነው ። የእርሱ በሀላፊኔት መቆየት በተወሰኑ አመታት የተገደበ እንደመሆኑ ፣ለሚቀጥለው ትውልድ ትቶት የሚሄደው እሴት ይኋውነ አሻራው ነው ።የየትኛውም መሪ አቅም በጊዜ ውሱንነት በተገደበ ነው ። የመሪው እድሜ ስናስበው ለረጅም ጊዜ ፀንቶ የሚቆይን ስራ መስራት መሪው ከአንድ ሰው ህይወት በላይ የዘለቀ እንዲሆን ያደርገዋል። መጽሀፉ «የሰው ሁሉ እድሜ የተወሰነ ነው» እንደሚለው መሪም ሰው እንደመሆኑ እድሜውም ሆነ የስራ ዘመኑ በጊዜ ውስጥ የተወሰነና የተገደበ ነው ። ስኬታማ የሆኑና በብዙ ትውልዶች ተወዳጅ የሆኑ መሪዎች ይህንን ቀላል የሆነ ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች ትልቅ ስልጣንንና ዝናን ሲቀዳጁ በቀላሉ የሚዘነጉት ሀቅ ነው ።

የውጪ ምእራባውያን ጋዜጠኖች አንድ ተለቅ ያለ መሪን ቃለ – መጠይቅ ሲጠይቁ ብዙ ጊዜ የሚጠይቁት ጥያቄ ውስጥ ምን አይነት አሻራን ወይም ቅርስን ትተህ ማለፍ ትፈልጋለህ ? በታሪክ ውስጥ እንዴት ለመታወስ ወይም ምን አይነት ቦታ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ ? የሚል ነው ። ይሄም ውሎ አድሮ መሪው የሚሰራው ስራ ወደ ሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ ስለሆነ የወደፊቱ መጪው ትውልድ በምን አይነት እንዲያስታውሰውና ፣ ለመጪው ትውልድም ባለው ትልቅ ቦታና ተሰሚነት ምንን ትቶ ወይም አውርሶ ማለፍን እንደሚፈልግ ለማወቅ የሚደረግ ጥያቄ ነው ። በተዘዋዋሪም አሁን እየሰራው ያለው ስራ ለወደፊቱ የሚኖረውን በጎም ይሁን አሉታዊ ተፅእኖን ራሱ መሪው እንዴት እንደሚረዳው ለማወቅ የሚደረግ ነው ።
የአገር መሪ ከሆነ ፣ መሪው ትቶት የሚሄደው ቅርስ ወይም አሻራ ከሀገሪቷ ካለችባቸው መሰረታዊ ችግር ይመነጫል ።

ለምሳሌ አሜሪካን በኢራቅና በአፍረጋኒስታን ጦርነቶች ውስጥ በተዘፈቀችበት ወቅት ተመርጦ ለሚመጣው መሪና ለሀገሪቷም አንገብጋቢ የሆነው ጦርነቶቹን ማስቆምና ፣ ሀገሪቷን ከእነኚህ ጦርነቶች ውስጥ ማውጣት ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ችግርም ካለ የወጣት ስራ አጥ ቁጥሩ ከፍተኛ ከሆነ የስራ እድሎችን መፍጠር ፣ እና ሌሎችንም ችግር መፍታት ነው ። በአሁን አለማችን ብዙም የተለመደ ባይሆንም አንድ ሀገር የውጪ ወረራ ካጋጠማት ወረራውን መመከትና የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበርም ሊሆን ይችላል ። እነኚህ ሁሉ የመሪውን ትቶት የሚያልፈውን የታሪክ አሻራ አይነት ይወስናሉ ። ትቶት ስለሚሄደው አሻራ እሚወስነው ራሱ መሪው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ለአጭር ግዜ ግብ ወይም ለአጭር ጊዜ የፓርቲ ጥቅምን እሚያስገኙ ሆነው ፣ነገር ግን በረጅም ጊዜ የመሪውን አሻራ እሚጎዱ ፣ መልካም ስሙን ጥላሸት የሚቀቡ ነገሮች ይከሰታሉ ። ለምሳሌ ፕሬዝዳንት ቡሽ ትንሹ አሸባሪዎችን በጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ውስጥ ያለ ፍርድ ሲያጉሩና ፣ በእስረኞች ላይ ስቃይ እንዲፈፀም ሲፈቅዱ ፣ አንዳንድ የራሳቸው ባለስልጣኖች ሳይቀሩ የፕሬዝዳንቱን በታሪክ የሚኖራቸው ቦታን (Legacy) ይጎዳል ብለው ተከራክረዋል ። በእርግጥ በዚህ መንገድ አሜሪካ በርካታ ጠቃሚ መረጃዎችን ፣

ቢንላደንን ለማግኘት ያስቻላትን መረጃ ጭምር በዚህ መንገድ ለማግኘት ብትበቃም የአሜሪካንን አለም አቀፋዊ ገፅታ ግን ክፉኛ ጎድቷል ። አንድ መሪ ትቶት የሚያልፈው አሻራ መሪው ካለፈም በኋላ ቢሆን ፣ የታሪክሰዎችን ሊያወዛግብ ይችላል ። ለምሳሌ ለሚመራው ህዝብ እንደ ጀግና የሚታይ ሲሆን ፣ ለጠላቶቹ ግን የተጠላ ሊሆን ይችላል ። ለምሳሌ የዘመናዊቷ ቱርክ መስራች አባት በመባል የሚታወቁት ከማል አታ ቱርክ ለቱርካውያን እንደ ብሄራዊ ጀግናና እንደ ሀገሪቱ አባት ተደርገው የሚታዩ ቢሆንም ለአርመናውያን ግን በርካታ አርመናውያን በመጨፍጨፋቸው እንደ ወንጀለኛ ነው የሚታዩት ፣ይህ ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ቱርክ በአታቱርክ ዘመን የተፈፀመውን የአርመናውያንን የዘር ማጥፋት አምና ይቅርታ እንድትጠይቅ ከአውሮፓውያን ግፊት እየተደረገባትና ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ማለትም ያንን የዘር ማጥፋት አድርገው ከተቀበሉ ሀገራት ከአውሮፓውያን ጋር ያላትን ግንኙነት እያበላሸባት እና የአውሮፓ ህብረት አባል የመሆን እድሏን እየተፈታተነባት ይገኛል ።

ይህ በታሪክ የሚተወው አሻራ በተከታታይ በሚመጡ ትውልዶች በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም ይችላል ። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የቀድሞው የፕሩስያ ወይንም የጀርመን መሪ የነበረው ኦቶ ቮን ቢስማርክ ሲሆን ፣ እርሱ የገነባው የጀርመንን ብሄረተኝነት ስሜት እንዲያንሰራራ በማድረግ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ የረዳና በአውሮፓ የተከበረች የተዋሀደች ሀገር እንድትሆን ለማድረግ ያስቻለ ቢሆንም ፣ ከእርሱ ህልፈት ከብዙ አስርት አመታት በኋላ የመጡት ናዚዎች እርሱ የገነባውየጀርመንን የብሄረተኝነት ስሜትን የጀርመንን ህዝብ ለመቀስቀስእና ወደ ስልጣን ለመምጣት ተጠቅመውበታል ። አንዳንድ የታሪክ ፀሀፊዎች ለናዚዎች መፈጠር ቢስማርክ ትቶት የሄደው አሻራ አስተዋፅኦ አድርጎ እንደሆነ ብለው ይጠይቃሉ ።

አዲሱ ትውልድ መሪው ትቶት የሚሄደውን አሻራ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ነው የሚተረጉመው ። መሪው የሰራውን ፍርስርፈሱን ሊያወጣው ይችላል ወይንም የተሻለ አድርጎ ሊያሳድገው ይችላል ። ለምሳሌ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መሪ የነበሩት ብሮንዝ ቲቶ ምንም እንኳን በዘመናቸው የሶሻሊስት ሀገራት በተለይ ሁኔታ ሀገራቸውን ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ በተሻለ የኢኮኖሚ አቅም መምራት ቢችሉም፣ የቀድሞዋን ዩጎዝላቪያን በአለም የተከበረች እና ከቀዝቃዛው ጦርነት ገለልተኛ አድርገው አገራቸው እንዳትጎዳ አድርገው ቢመሩም ፣ እርሳቸው ህልፈት ህይወት በኋላ ግን የእርስ በእርስ ጦርነት ተካሂዶ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ምድር ታይቶ የማይታወቅ ጦርነትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የተፈፀሙባትና የተበታተነች ሀገር ልትሆን በቅታለች ። ይህም የሚያሳየው ምንም እንኳን መሪዎች በትክክለኛ መንገድ እየመራን ነው ከኛ በኋላም እኛ የጀመርነው ይቀጥላል ብለው ሊያስቡ ቢችሉም እነሱ እንደሚያስቡት ላይሆን እንደሚችልና ፣ ከባሰም ተቃራኒ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ነው ።

በታሪክ ፀሀዩ ንጉስ በመባል የሞታወቀው የፈረንሳዩ ንጉስ ሊዊስ 14ኛ ከሀምሳ አመት በላይ የዘለቀ የስልጣን ዘመኑ ፈረንሳይን ወደ አውሮፓ ሃያል ሀገርነት የለወጠና ፣ በአውሮፓም ሀብታሟ ሀገር አድርጎ ማብቃት የቻለ ቢሆንም ፣ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ የእርሱን መንገድ በመከተል ማለትም ጨቋኝ የነበረውን ስርአት ምንም ባለማሻሻልና ፣ አንዳንዴም ባስ ባለ ጨቋኝ በሆነ መንገድ መምራታቸውን በመቀጠላቸው በምእራቡ አለም የመጀመሪያው የሆነው የፈረንሳይ አብዮት ሊካሄድና የዘውዳዊ ስርአቱ ከመሰረቱ ሊናድ በቅቷል ። መሪው ራሱ በዚያ ዘመን ቢኖር እንኳን እንደዛ ይደረግ ላይል የሚችለውን ነገር ተተኪዎቹ በቀድሞው መሪ በእርሱ ዘመን ስለተሳካ በዛ መንገድ መሄድ የለባቸውም ፣ ራሱ መሪው እንኳን በዛ ዘመን ቢገኝ እንደዛ ይደረግ ላይል ይችላል ።

መሪው የስልጣን መተካካትን ሲያደርግ በትክክለኛው መንገድ መተካካቱን ማድረግ አለበት ። በአብዛኛው ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት ውስጥ ህዝቡ አዳዲሶቹን መሪዎችን ስለሚመርጥ መሪዎች እከሌ ይተካኝ ማለት አይችሉም ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ መሪዎች የሚተካቸውን ሊመርጡ ይችላሉ ነገር ግን ተተኪው ህጋዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ መከናወን አለበት ። ሰዎች የግል ንብረታቸውን ፣ ሀብታቸውን ንብረታቸውን ለልጆቻቸው ማውረስ ሲችሉ ፣ መንግስት ስልጣንን ግን ማውረስ አይችሉም – ነገስታት ካልሆኑ በስተቀር ። በ 2012 የተነሳውን የአረብ አመፅ ብንወስድ ፣ አንዱ አመፁ የተነሳበት ምክንያት በምእራባውያን ድጋፍ መሪዎቹ ራሳቸው ለአስርት አመታት ስልጣን ላይ መቆየታቸው ሳያንስ ፣ ልጆቻቸውን ለመተካት ማሰብ መጀመራቸው ተስፋ የቆረጠው ህዝብ አማራጭ በማጣት ወደ መመለሻ ወደ ሌለው አመፅ በማምራት ጨርሶ የመንግስታቱን መወገድ አስከትሏል ።

ይህም መሪዎች የሚገነቡት መሰረት በትክክለኛ መሰረት ላይ መጣሉን ማረጋገጥ አለባቸው ፣ በትክክለኛ መሰረት ላይ ያልተጣለ ከሆነ ፣ ወይንም ለጊዜው በይድረስ ይድረስ ድረስ የተገነባ ከሆነ ጠንካራ መሰረት የሌለው ነገር በቀላሉ እንደሚፈርሰው ሁሉ የመሪው ስራም እርሱ በማይኖርበት ወቅት በቀላሉ ይናዳል ። ብዙውን ጊዜ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ያላቸው ሀገራት በጊዜ ሂደት ስርአታቸው እየተጠናከረ ሲሄድ ፣ ዲሞክራሲያዊ የልሆኑ ስርአቶች በአንፃሩ ግን እድሜአቸው ረጅም አይደለም ። መሰረታቸው ጠንካራ የሆኑ ስርአቶች በጊዜ ሂደት እንደውም እየተጠናከሩና እየዳበሩ ይሄዳሉ ፣ ለምሳሌ የአሜሪካንን የዲሞክራሲ ስርአትን ብንወስድ በጊዜ ሂደት ውስጥ ይበልጥ እየተጠናከረ መሄዱ የሚታይ ሀቅ ነው ፣ ለዚህም አንዱ ማሳያ የሚሆነው ቀድሞ በስርአቱ ውስጥ መመረጥም ሆነ መምረጥ የማይችሉ የነበሩ ጥቁሮችና ሌሎችም ዘሮች መብታቸው መከበሩና የስርአቱ አካላት መሆን መቻላቸው ነው ።

ዲሞክራሲ ባልተጠናከረባት ሀገር ውስጥ አንድ መሪ የዲሞክራሲ እድገቱን ቸል ብዬ ምጣኔ – ሀብቱን ብቻ አሳድጋለሁ ቢል ፣ አግባብ መሆኑ አጠያያቂ ነው ። ለዛች ሀገር በጣም አንገብጋቢው ጉዳይ የዲሞክራሲ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ምጣኔ – ሀብቱን ካሳደኩ የዲሞክራሲውን ጉዳይ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ጎን ማድረግ እችላለሁ ብሎ ቢል ትቶት በሚሄደው አሻራ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ያሳርፋል ። ይህ ማለት የምጣኔ – ሀብቱ እድገት አያስፈልግም ማለት ሳይሆን እድገቱ እንዳለ ሆኖ ይበልጥ ግን ትኩረት ማድረግ ያለበት በዲሞክራሲው እድገት ላይ መሆን አለበት ። በምጣኔ – ሀብት ማሳደጉ ሊሳካለት ቢችል እንኳን ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ በማተኮሩ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ግን ምሉዕ የሆነ በጎ አሻራውን ማሳረፍ ሳይችል ይቀራል ።

መሪው ትቶት የሚያልፈው አሻራ የሚመራው ድርጅት ፣ ወይም ሀገር እንዳለበት ሁኔታና ፣ ችግር ውስጥ ካለም እንሳዳለበት ችግር ይወሰናል ። ስለዚህ ያንን ተቋም ችግር በመፍታት ችሎታውና ብቃቱ ነው በታሪክ ትቶት እሚያልፈውን ቦታ (Legacy) የሚወሰነው ። ያም ሆኖ ግን የቀድሞ መሪዎች በጅምር ትተዋቸው ሳይቋጯቸው ያለፏቸው ጉዳዮችም ይኖራሉ ፣ እነኚህ ጅምር ስራዎችንም በአግባቡ የመቋጨትና የመጨረስ ጉዳይም የአዳዲስ መሪዎች ተግባር ነው ።

መሪው ትቶት የሚያልፈው አሻራ እጅግ ትልቅ ተፅእኖ ያለው ነው ። ለምሳሌ ታላላቅ ሀይማኖቶችን ብንወስድ ለሺዎች አመታት መቆየት የቻሉት ዋናዎቹ መስራቾች መሪዎች ትተውት ባለፉት አሻራ ነው ። እነኚህ ሰዎች እጅግ ሀያል ከመሆናቸው የተነሳ መንፈሳቸው ለሺህ አመታት በሰዎች ልብ ውስጥ እድሮ ሰዎችን ይገዛል ። ለምሳሌ ብንወስድ እየሱስ ክርስቶስ ፣ ሙሴ ፣ ቡድሀ ፣ ጋንዲ እንዲሁም ከቅርባችን ከደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላን ብንወስድ የዚህ አይነት መሪዎች ተፅእኗቸው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የብዙዎችን ልብ በተስፋ የሚያሞቁ ናቸው ። ከአገራት መሪዎችም እንዲሁ እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን ያሉት የተውት አሻራ ነው የዛሬይቱን ታላቋን አሜሪካንን የፈጠረው ፣ አሜሪካኖች እንደ ቅዱስ መፅሀፍ የሚቆጥሩት ህገ – መንግስታቸውም የተረቀቀው በነ ጆርጅ ዋሽንንግተን መሆኑ ይታወቃል ።

አንድ መሪ መቼ ስልጣኑን መልቀቅ እንዳለበት ማወቅ አለበት ። በትክክለኛው ወቅት ስልጣና ቸውን የለቀቁ ፣ መሪዎች መቼም ቢሆን ሲደነቁ ይኖራሉ ።አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ምንም እንኳን በርካታ ጥሩ ነገርን ያበረከቱ ቢሆንም ፣ ነገር ግን ብዙ ከመቆየት መልካም ስራቸው ሁሉ ተቃሎ ይታይባቸዋል ። ነገር ግን በትክክለኛው ወቅት ከዛ ቦታ ራሳቸው ገለል ማለት ይበልጥ ከዚያ በኋላ እንዲደነቁና እንዲከበሩ ያደርጋቸዋል ።

ለውጥ ከሁለት አቅጣጫ የሚመጣ ሲሆን ፤ ከላይ ወደታች (Top Down) እና (Bottom Up) ወይም ከላይ ወደታች ነው ። ከላይ ወደ ታች እሚመጣው የለውጥ አይነት በመሪዎች የራስ ተነሳሽነት የህዝቡ ግፊት ቢኖርም ባይኖርም ራሳቸው መሪዎቹ አምነውበት የሚገፉት የለውጥ አይነት ሲሆን ፣ ሁለተኛው አይነት ለውጥ ደግሞ ከራሱ ከህዝቡ በራሱ ግፊት የሚመጣና ሀገሩ የምትሄድበትን አቅጣጫ ራሱ እሚመራበትና እሚጠቁምበት ነው ። ብዙ ጊዜ ከታች የሚመጣን የለውጥ ግፊት ከላይ ያሉ መሪዎች የማይቀበሉ ወይም ለማዘግየት የሚሞክሩ ከሆነ ከብዙ ትእግስት በኋላ የለውጥ እንንቅስቃሴዎች ብሎም አብዮቶች ሁሉ ሊካሄዱ ይችላሉ ።

ስለዚህ ምንግዜም ቢሆን መሪው የለውጡን አቅጣጫና አካሄድ አስቀድሞ መገመትና መጠበቅ መቻል ሲኖርበት ፣ በአንድ በኩል የለውጡን ጥቅም ማየት ከቻለ ምንም እንኳን የራሱን ግላዊ ስልጣን እሚቀንስና እሚያሳጣ ሆኖ ቢገኝ ነገር ግን በታሪክ የሚኖረውን ስፍራውን በመልካም ለማስፈርና አይቀሬም ከሆነም ያንን ለውጥ ለማገዝ መደገፍ አንድ አማራጭ ሲሆን ፣ ነገር ግን የለውጡ ፍላጎት የብዙዎች ሆኖ እሱ ብቻውን ለማስቆምና ለመግታት ከሞኮረ ግን በታሪክ የሚኖረውን ቦታ ማበላሸት ብቻ ም ሳይሆን መሪነቱን ፍፃም ጥላሸት ሊቀናባው ፣ እና ቀድሞ የሰራቸውን ጥሩ ስራዎች ሊጋርድበትና ይችላል ። በእርግጥ ሀገራት ወደ ጥሩ ብቻ ሳይሆም ወደ መጥፎም አቅጣጫ ሊያመሩ ይችላሉ ፣ መሪው መጥፎው አቅጣጫ ማስቀየር እና ከመጥፎው ጎዳና መመለስ አንዱ ሀላፊነቱ እንደመሆኑ የለውጡን ምንነት ከሌሎች በተሻለ ሊረዳ የሚችልበት ቦታ ላይም እንደመሆኑ ተቋሙን ከመጥፎም መንገድ መጠብ ቅ አንዱ ሀላፊነቱ ነው ።

ሌላው ደግሞ አንድ መሪ ውድድሩን ካጠፋ ፣ የራሱን የሚመራውን ተቋም እድገት ያቀጭጨዋል ። ለተቋሙ ወይም ለሀገሪቱ የፖለቲካ እድገት እገዛን ሊያደርግ ይችል የነበረውን ፣ እንዲሁም ለወደፊቱ ሽግግር ወቅት ሲመጣ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችለውን ተቋማዊና ፣ እውቀትና የሰው ሀይል እድገት እንዲቀጭጭ ነው እሚያደርገው ። የጤናማ ውድድር መኖር ለተቋማትም ሆነ ለመንግስታት እድገት አስፈላጊ ነው ። በውድድር ባለበት አለም ውስጥ የመጨረሻ አሸናፊና ተሸናፊ እሚባል ነገር የሌለ ሲሆን በየትኛውም ውድድር ምንግዜም ጊዜያዊ ተሸናፊና ጊዜያዊ አሸናፊ ናቸው ያሉት ።

የውድድር አለመኖር ሊተካ የሚችልን ተቋማት አለመኖርን ያስከትላል ። ልዩነቶች መጠበቅና መኖር ሲኖርባቸው ። ልዩነቶችን ማጥፋት ወይም እንደሌሉ መቁጠር አማራጭ ሀሳብ እንዳይኖር ያደርጋል ። ለምሳሌ አንድ ሀሳብ መስራት ቢያቅተው እሱን የሚተካነ ወይም ያ ያልሰራውን ነገር ፣ በሌላ ሀሳብ እንዲቀጥል የሚያደርገው ሀሳብ ሊመጣ የሚችለው የተለየ ሀሳብ ካለው ተቋም ነው የሚሆነው ፣ ስለዚህ ልዩነቶች ምንግዜም መኖር ሲኖርባቸው ፣። ለምሳሌ በምእራቡ ኦመ አለም ብንወስድ በተለያየ ጊዜ የተለያየ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው ስልጣን የሚይዙት ፣ ሌላው ቀርቶ በአንድ መንግስት ውስጥ እንኳን ህግ አውጪው ወይም ፓርላማው በሌላ ፓርቲ ሊያዝ ይችላል ፤ ስለዚህ በመደራደርና ሰጥቶ በመቀበል ይመራሉ ።

ስፖርትን እንኳን ብንወስድ አንድ ቡድን በአንድ ውድድር ቢያሸንፍ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ሌላው ያልተጠበቀው ቡድን ያሸንፋል ፣ስፖርትን በውድድሩ ወቅት ካለው ትእይንት በተጨማሪ አጓጊ የሚያደርገው ይሄው ያልተጠበቀው ማሸነፍና መሸመፍ ናቸው ። በመሪነት ውስጥም ያልተጠበቀው ፓርቲ ተመርጦ ወደ ስልጣን ሊመጣ ሲችል ፣ የተጠበቀው ፓርቲ ደግሞ ሊሸነፍ ይችላል ። ስለዚህ ሽንፈትን እንደ መጨረሻ መወሰድ የሌለበት ሲሆን ማሸነፍም እንዲሁ ዘላለማዊ አይደለም ። አሁን ያሸነፈ ፓርቲ ከጥቂት አመታት በኋላ ተሸናፊ ሆኖ እሚገኘው እሱ ይሆናል ፤ ተሸናፊውም በሚቀጥለው ጊዜ ድሉ የእርሱ ይሆናል ።

ለምሳሌ በምእራባውያን ሀገራት በእንግሊዝ ሀገር ሌበር ፓርቲ ወደ ስልጣን ሲመጣ ለንደንን የአለም አቀፍ የፋይረናንስ ማእከል ሲያደርግ ወደ ግራ ዘመም የሆነው ይሄው ፓርቲ የወሰደው አቋም ፣ ወግ አጥባቂዎቹ ወደ ስልጣን ቢመጡ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሲሆን ይህም በሁለቱ ፓርቲዎች መሀከል ልዩነትን ሲያጠብ ለመራጩ ህዝብም አማራጩን ይዘጋበታል ። ምክንያቱም በሁለቱ መሀከል ስልጣን ሲይዙ ልዩነታቸውን ማወቅና አማራጭ ፖሊሲ አይኖርም ።

በአሜሪካን አገርም እንዲሁ በሁለቱ መሀከል ያለው ልዩነት ግብርን በመጨመር ፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ ላይ ሲሆን ከዚያ ውጪ ግን በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ልዩነታቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ሲሆን ፤ አንዱ የጀመረውን ጦርነት ስልጣን ከመያዙ በፊት ሌላኛው ቢያወግዘውም እርሱም በተራው ስልጣን ሲይዝ ግን ጦርነቱነን አባብሶ ይቀጥለዋል ። ይህም በቀድሞው ፕሬዝደንት ቡሽ የተጀመረውን ጦርነት ስልጣን የተረከቡት ዲሞክራቶች ከማስቆም ይልቅ ይበልጥ በተለያየ መንገድ እየተዘፈቁበት ስለመጡ አንዱ የህዝብ ደስተኛ አለመሆንና መራጩ ህዝብ ሊኖረው የሚችለውን አማራጭ ከማጥበቡም በላይ ፅንፈኛ ቡድኖች ተሰሚነታቸው እየጨመረ ስለሚመጣ ለፖለቲካ ስርአቱ ጤናማነት አደጋን ይደቅናል ።

ሌላው አንድ መሪ የሚመራበትም ዘመንም ራሱ ይወስነዋል ። ለምሳሌ የሰላም ዘመን መሪ ፣ ለጦርነት ጊዜ ላይሆን ይችላል ። የጦርነት ጊዜ መሪ ደግሞ የሰላም ዘመን መሪ ላይሆን ይችላል ። የችግር ጊዜ መሪዎች በአብዛኛው ሀይለኛና ፣ሌሎችን የሚጫኑ ሊሆኑ ይችላሉ ። በጦርነት ወይም በእግር ሰአት በእርግጥ የዛ አይነት አመራር ሊያስፈልግ ይችላል ። ይሁን እንጂ የዚህ አይነት መሪዎች ችግሩ ካለፈ ፣ በኋላ ግን በቀድሞው የአመራር ዘያቸው መቀጠል አይችሉም ። ሁኔታዎች ስለተቀያየሩ ፣ የአመራራቸውም መንገድ መቀየር ሲኖርበት በቀድሞው በችግሩ ሰአት ይሰጡት የነበረውን የአመራር መንገድ ከተከተሉ ግን እንደ ቀድሞው ውጤታማ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው ።

ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሆኑት ዊኒስተን ቸርችል ሲሆኑ እንግሊዝን ከናዚ መንጋጋ ማዳን ቢችሉም በሰላሙ ጊዜ ግን በምርጫ ተሸንፈዋል ። በእርግጥ ቸርቺል ድጋሚ ያልተመረጡት መራጩን ህዝብ ውለታ ቢስ ስለሆነ ሳይሆን በጦርነት ጊዜ አንድ መሪ የተከተለው ስረትራቴጂና በሰላም ወይም ትልቅ ችግር በሌለበት ሰአት የሚኖረው የአመራር ስልት የተለያየ ስለሆነና መሪው ራሱን ለሁኔታዎች ጋር ካለማዛመድና ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ። ጥሩ የአብዮት ወቅት መሪም ብቃት ያለው የሰላም ጊዜ መሪ ላይሆን ይችላል ፤ ብዙ መሪዎችን አብዮትን በመምራት የተዋጣላቸው አብዮቱን ካሳኩ በኋላ ግን በሰላሙ ጊዜ ግን እንደ ቀድሞው ስኬታማ መሆን ሲያቅታቸው በታሪክ በተደጋጋሚ ተስተውሏል ።

አንዳንዶቹ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ትተውት ወይንም ጥለውት ስለሚሄዱት አሻራ (legacy) ወይም የታሪክ ቅሪት ብዙም አይጨነቁም ። ከዚያ ይልቅ የሚያስጨንቃቸው ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት ነው ። አፍሪካ ውስጥ በርካታ መሪዎች ከ30 አልፎ አልፎም አንዳንዶቹም ከ40 አመት በላይ ስልጣን ላይ መቆየት የቻሉ እንዳሉ የታወቀ ነው ። ይሁን እንጂ ለአንድ ፓርቲ የበለጠ በታሪክ ቦታ የሚያሰጠው ነገር ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየቱ ሳይሆን ለዛ ሀገር ምን ዘላቂ ነገር ትቶ ሄደ የሚለው ነው ። ይሄም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲ ባላደገባቸውና ገና በጅምር ደረጃ ባለባቸው ሀገራት ውስጥ ስልጣን አንድ ግዜ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ከገባ ከሌላው አማራጭ ዘግተው ለረጅም ግዜ ስልጣን ላይ ይቆያሉ ፣ አንድ ግዜ ስልጣናቸውን ካጡ የሚደርስባቸውን ግለሰባዊ የሆነ ኪሳራ ስለሚረዱ በተቻለ መጠን ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት ጥረት ያደርጋሉ ።

ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካን መሪዎች ብንወስድ አንዳንዶቹ በትጥቅ ትግል ስልጣን የያዙ ሲሆኑ ከሌላው የአፍሪካ ሀገራት ደካማ የዲሞክራሲ ሂደት የሚታየውም በዚሁ አካባቢ ነው ። በአንድ በኩል ክልሉ ከአፍሪካ በጣም አደገኛው እንዲሁም አለምን የሚያሳስቡ ተደጋጋሚ ድርቅና ረሀብ ፣ የሰብአዊ ድቀት የሚታይበት ክልል መሆኑ አይካድም ።

በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙ አለማቀፋዊ ውግዘትንና በመፍራትና ወታደሮችም ስለሆኑ አገር ለመምራት የሚያስችለው ህዝባዊ ይሁንታና ውክልና (legitimacy) ስለማይኖራቸው ፣ የአገር ውስጥ ተቀባይነትን በማጣት ስልጣንን ሲያስረክቡ ብዙውን ጊዜ በትጥቅ ትግል ስልጣን የያዙ ግን በምርጫ ቢሸነፉ እንኳን በቀላሉ ስልጣን አያስረክቡም ። በእርግጥ የአሁኖቹ የአፍሪካ መሪዎች ከቀደምቶቹ አንፃር የልማትን አስፈላጊነት የተገነዘቡ ናቸው ይሁን እንጂ የዲሞክራሲውም ጉዳይ መዘንጋት የለበትም ።

የአንድ መሪ ስራ ለበርካታ ዘመን ዘላቂ ሊሆን የሚችለው የእሱ የጀመረውን ነገር ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ካስቻለ ብቻ ነው ። ለምሳሌ የታላላቅ ሀይማኖት መስራቾች ብንወስድ እነሱ ካለፉ በኋላ እነኛ ሀይማኖቶች ዘላቂ ሆነው ለሺ ዘመናት ሊዘልቁ የቻሉበት አንዱ ምክንያት በአንድ ሰው ግርማ ሞገስና ሀያል ከሆነ ከተፈጥሮ ልእልና በላይ ከሆነ ካገኘው ሀይል በተጨማሪ ውጪ በሰዎች ዘንድ ያ ነገር ተቋማዊ መሆን በመቻሉ ነው ። እና ተቋማዊ በሆነ መንገድ አስተምህሮቶቹ ፣ አስተሳሰቡና አደረጃጀቱ በተቋም መልክ ሊተላለፍ በመቻሉ ነው ።
ለምሳሌ የሀያሏን ሀገር አሜሪካንን ብንወስድ ፕሬዝዳንቶቿ ስልጣን ላይ እሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ሲሆን ቢበዛ ከስምንት አመት አይበልጥም ። ይሁን እንጂ በአለም ላይ ሀያል እንደመሆኗና በብዙ ነገር ላይ መሪዎቹ አሻራቸውን አሳልፈው ስለሚሄዱ ትተውት የሚሄዱት አሻራ ግን ለረጅም ጊዜ ይቆያል ።

አንዳንድ ጊዜ ለአጭር ጊዜ ግብ ወይም ለጊዜው አማላይ መስለው ለሚታዩ ነገሮች ተብለው እሚደረጉ ነገሮች በረጅም ጊዜ የመሪውን የታሪክ አሻራ ወይም ትቶት ሊሄድ የሚችለውን መልካም ስምና ዝና የሚያበላሹ ሊሆኑ ይችላሉ ። በመጀመሪያ የዚህ አይነት ነገሮችን መሪው በሚገባ መረዳት አለበት ። ከፍተኛ ጥንቃቄንና ብስለትንም የሚጠይቅ ሁኔታን ይፈጥራል ። ለምሳሌ መሪው ጊዜያዊ ዝናን የሚያስገኝለትን ፣ ወይም ስልጣኔን ያስጠብቅልኛል በሚል ወደፊት ስሙን በመልካም እንዲነሳ የማያደርጉትን ነገሮች ሊፈፅም ይችላል ።

ትቶት ስለሚሄደው አሻራ እሚወስነው ራሱ መሪው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ለአጭር ግዜ ግብ ወይም ለአጭር ጊዜ የፓርቲ ጥቅምን እሚያስገኙ ነገር ግን በረጅም ጊዜ የመሪውን አሻራ እሚጎዱ ነገሮች ይከሰታሉ ። ለምሳሌ ፕሬዝዳንት ቡሽ አሸባሪዎችን በጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ውስጥ ያለ ፍርድ ሲያጉሩና ፣ በእስረኞች ላይ ስቃይ እንዲፈፀም ሲፈቅዱ ፣ አንዳንድ የራሳቸው ባለስልጣኖች ሳይቀሩ የፕሬዝዳንቱን በታሪክ የሚኖራቸውን ቦታወይም የታሪክ አሻራቸውን (legacy) ይጎዳል ብለው ተከራክረዋል ። በእርግጥ በዚህ መንገድ አሜሪካ በርካታ ጠቃሚ መረጃዎችን ፣ ቢንላደንን ለማግኘት ያስቻላትን መረጃ ጭምር በዚህ መንገድ ለማግኘት ብትበቃም የአሜሪካንን አለም አቀፋዊ ገፅታ ግን ክፉኛ ጎድቷል ።

የዚህ አይነቱን አሻራ የሚወርስ መሪ ለወራሹ መሪ መልካም አይደለም ። ኦባማን የወረሱት የቡሽን ውርስ ሲሆን ለማስተካከል 4 አመት ስላልበቃ መራጩ ህዝብ ጨምሮላቸዋል።በአራት አመት ውስጥ ከችግሩ ጥልቀት የተነሳ ማስተካከል አለመቻሉን የተረዳው ህዝብ ። መሪዎች ስማቸው ተያይዞ እንዲነሳ የማይፈልጉትን የታሪክ ውርስ በሚወርሱበት ወቅት ከዛ ከወረሱት መልካም ካልሆነ ነገር ጋር ለመላቀቅ ጥረትን ማድረግ ይገባቸዋል ። ሌላው ከጆን ኤፍ ኬኔዲ በኋላ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት የነበሩት ሊንደን ቢ ጆንሰን ምንም እንኳን በአሜሪካ ታሪክ የሁለተኛውን የአለም ጦርነትን አሜሪካንን መርተው በድል የተወጡትን እንዲሁም አለምን ከናዚዎችና ከፋሽስቶች መንጋጋ ነፃ ያዉ ካወጡት ከፍራንክሊን ሩዝቬልት ቀጥሎ በ20ኛው ክፍል ዘመን በርካታ ቁም ነገሮችን ለሀገራቸው ያከናወኑ ናቸው ። ነገር ግን ምንም እንኳን ጆንሰን በወቅቱ አሜሪካንን አብጠው የነበሩትን ችግሮችን ማለትም የአፍሪካ አሜሪካውያንን መብትን የሚያስከብሩ በርካታ ህጎች የወጡበትና ስራ ላይ የዋሉበት ሲቪል መብቶችን ፣ ሲሆን ነገር ግን ምንም እንኳን የቬትናም ጦርነት ቀድሞ በነበሩት በኬኔዲ አማካይነት የተጀመረ ቢሆንም ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው ግን በእርሳቸው ዘመን በመሆኑ አሜሪካ በዚህ ጦርነት ከባድ ዋጋንና ብሎም ሽንፈትን ልትከናነብ ብቅታለች ። በዚህም በመላው አሜሪካን የተማሪዎችና የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ የተጥለቀለች ሲሆን አንዳንዶቹም ለወታደርነት ምልመላን በመስጋት ወደ ካናዳና ስዊድን ወደ መሳሳሉ አገራት ለመሰደድ በቅተዋል ። በዚህም ጆንሰን በድጋሚ ላለመወዳደር ወስነው ራሳቸውን ከፖለቲካው አግልለዋል ። በታሪካቸውም ምንም እንኳን በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ያከናወኑ ቢሆንም ይህ ጦርነት በሀገራቸው ላይ ያስከተለው ጠባሳ ግን በታሪካ ያላቸውን አሻራ ሊያደበዝዘው በቅቷል ።

መሪው ራሱ በረጅም ጊዜ ሊተወው ስለሚችለው የታሪክ አሻራ ላይም ማሰብ አለበት ። በዚህም ምክንያት ብዘዉን ጊዜ መሪዎች የተደበላለቀና እርስ በእርሱ የሚጋጭ (Mixed Legacy) ትተው ሊያልፉ ይችላሉ ። ይኀውም ለአጭር ጊዜ ጥቅም ወይም ግብ ሲሉ በሚፈፅሟቸው ድርጊቶች የተነሳ ነው ። ነገር ግን አንድ መሪ ዘመን አይሽሬ በሆነ ሁኔታ በበጎ መነሳት ከፈለገ ቀላሉ መንገድ መሰረታዊ ለሆኑ መርሆዎች ራሱን ማስገዛት ነው ። ይህም ከመርህ ያፈነገጡ ፣ እንዲሁም ጉዳትን ሊያደርሱ የሚችሉ ድርጊቶችን ከመፈፀም ይጠብቀዋል ። በታሪክ ጥፋትን ያስከተሉ ድርጊቶች ፣ ከመርህ እጅግ ያፈነገጡ ፣ ድርጊቶች ናቸው ። ለምሳሌ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች በአውሮፓ አህጉር የፈፀሙት ወንጀል ፣ አውሮፓ ከምታምንበት ከክርስትና ሀይማኖትም ሆነ ከደግነት ወይንም ከሰብአዊነት (Humanism) ፍልስፍና በእጅጉ ያፈነገጠ ድርጊትን በመፈፀማቸው ታሪክ የማይረሳውን አሰቃቂ ወንጀልን በመፈፀም በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ ጨለማ የሆነ የታሪክ ቅርስን ትተው አልፈዋል ።

የሀገር መሪ ከሆነ ሀገራት ካላቸው በሺዎች አመታት ከሚቆጠረው ዘመናት ውስጥ ፣ አንድ መሪ በስልጣን ላይ የሚቆይበት ዘመን እጅግ በጣም አጭር ነው ። እድሜ ጠገብ ከሆኑት ሀገራት አንፃር እንደ ቅፅበት የሚቆጠር ነው ፣ ለዚህም ነው መሪው ትቶት የሚያልፈውን አሻራ መጠንቀቅና ማሰብ የሚኖርበት ።

መሪው የሚተወው አሻራ የራሱ ህሊናዊ ንቃት ደረጃ ይወስነዋል ። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለሺዎች ዘመናት የቆየ የታሪክ አሻራን ትትው ያለፉ ሰዎች ከፍተኛ ህሊናዊ ንቃት ያላቸው ሰዎች ናቸው ። እነኚህም ሙሴ ፣ ቡድሀ ፣ ክርስቶስ፣ ባሀኡላ የመሳሰሉት ረቂቅ መንፈሳውያን (mystics) የነበራቸው ንቃተ – ህሊና ከፍተኛ በመሆኑ ትተውት ያለፉት መንፈሳቸው ለሺዎች አመታት የዘለቀ ነው ። በእርግጥ መሪዎች የዚህን ያህል ንቃትና ግንዛቤ ይኑራቸው ባይባልም በተወሰነ ደረጃ ህሊናዊ ንቃት ቢኖረው ግን በተሻለ ሁኔታ ሊመራና ፣ መልካም የታሪክ ቅርስን ትቶ እንዲያልፍ ያስችለዋል ።

አንድ መሪ የሚመራበትም ዘመን ራሱ ይወስነዋል ። ለምሳሌ የሰላም ዘመን መሪ ፣ ለጦርነት ጊዜ ላይሆን ይችላል ። የጦርነት ጊዜ መሪ ደግሞ የሰላም ዘመን መሪ ላይሆን ይችላል ። የችግር ጊዜ መሪዎች በአብዛኛው ሀይለኛና ፣ሌሎችን የሚጫኑ ሊሆኑ ይችላሉ ። በጦርነት ወይም በእግር ሰአት በእርግጥ የዛ አይነት አመራር ሊያስፈልግ ይችላል ። ይሁን እንጂ የዚህ አይነት መሪዎች ችግሩ ካለፈ ፣ በኋላ ግን በቀድሞው የአመራር ዘዬአቸው መቀጠል አይችሉም ። ሁኔታዎች ስለተቀያየሩ ፣ የአመራራቸውም መንገድ መቀየር ሲኖርበት በቀድሞው በችግሩ ሰአት ይሰጡት የነበረውን የአመራር መንገድ ከተከተሉ ግን እንደ ቀድሞው ውጤታማ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው ።

ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሆኑት ዊኒስተን ቸርችል ሲሆኑ እንግሊዝን ከናዚ መንጋጋ ማዳን ቢችሉም ሰላም ከመጣ በኋላ ግን በምርጫ ተሸንፈዋል ። ቸርቺል ድጋሚ ያልተመረጡት መራጩን ህዝብ ውለታ ቢስ ስለሆነ ሳይሆን በጦርነት ጊዜ አንድ መሪ የተከተለው ስትራቴጂና በሰላም ወይም ትልቅ ችግር በሌለበት ሰአት የሚኖረው የአመራር ስልት የተለያየ ስለሆነና መሪው ራሱን ለሁኔታዎች ጋር ካለማዛመድና ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ። ጥሩ የአብዮት ወቅት መሪ ብቃት ያለው የሰላም ጊዜ መሪ ላይሆን ይችላል ፤ ብዙ መሪዎችን አብዮትን በመምራት የተዋጣላቸው አብዮቱን ካሳኩ በኋላ ግን በሰላሙ ጊዜ ግን እንደ ቀድሞው ስኬታማ መሆን ሲያቅታቸው በታሪክ በተደጋጋሚ ተስተውሏል ። የፈረንሳይ ፕሬዝደንት የነበሩትም ደጎልም እንዲሁ ሀገራቸውን ከወራሪዎቹ ናዚዎች ነፃ ማውጣት ቢችሉም እንዲሁ በህዝብ ምርጫ ከውድድሩ ሜዳ ተወግደዋል ።

መሪዎች የመምራት ህጋዊ ተቀባይነታቸውንና ውክልናቸውን የሚያጡት በርካታ ስህተቶችን ከሰሩና የሚመሩትን ሀገር ወይም ድርጅት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ በመምራት ብዙ ዋጋን ካስከፈሉ በኋላ ሲሆን ከብዙ ትእግስት በኋላ ፣ ህዝቡ በሚነሳባቸው ወቅት የመምራት ፣ ህጋዊ ተቀባይነታቸውንና ውክልናቸውን (Legitimacy) ለማጣት ይገደዳሉ ። ይህ ብቻ ሳይሆን እየቆዩ በሄዱ ቁጥር ስህተታቸውና አጓጉል ስራም ከሰሩ የስራቸው ውጤት ቁልጭ ብሎ መታየት ስለሚጀምር የተቃውሞ ድምፆች እየበረታባቸው ይሄዳል ። በተለይ ለአንድ መሪ አነሳስ በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው ። ሲጀመር ስህተቶችን የሰራ መሪ ከዛ በኋላ ለማስተካከል በጣም ይቸገራል ።

ልክ ሯጮች አነሳስ ላይ እንደሚጠነቀቁት ፣ አነሳሳቸው ከተሳሳተ ከውድድር ወጪ እስከመሆን ወይም በሌላው ሊደርሱበት በማይችሉበት ሁኔታ መቀደም ደረጃ ድረስ ይደርሳሉ ። በተለይም ከሰው ልጅ ስነ – ልቦና ጋር የተያያዙ ነገሮች አጀማመራቸው በጣም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ።ምክንያቱም ከአንድ አዲስ ሰው ፣ወይም ህዝብ ጋር ስንተዋወቅ ትውውቃችን በጥሩ መንገድ ከተጀመረ ከዛ በኋላ በጥሩ የመቀጠል እድሉ ሰፊ ነው ፣ ስህተቶች በኋላ ላይ ቢሰሩም መጀመሪያ ላይ ከሚሰሩት የበለጠ ትኩረት አይደረግባቸውም ።

በነገራችን ላይ የአሜሪካን ፕሬዝዳንቶች ልክ ተመርጠው እንደመጡ ፣ የህዝብ ድጋፍ ሳይቀዘቅዝ አወዛጋቢ ሊሆኑ የሚችሉ ህጎቹን ኮንግሬሱ እንዲያሳልፍ እሚያደርጉት ። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ መሪዎች አወዛጋቢ የሆኑ ውሳኔዎቻቸውን በእለተ – አርብ ይፋ ማድረግም የተለመደ ነው – ቅዳሜና እሁድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስለሚዘጉ ወዲያውኑ የከረረ ተቃውሞ እንዳይገጥማቸው በመፍራት ።እየቆዩ ሲሄዱ የህዝብ ድጋፍ እየተዳከመ ስለሚሄድ መጀመሪያ የነበራቸው ድጋፍ ስለሚቀንስ ፣ ቆየት ብለው ከሚያደርጉት ይልቅ ወዲያው እንደተመረጡ ብዙም ሳይቆዩ እነዛን በኋላ ላይ ቢሆን አጨቃጫቂ ፣ አወዛጋቢ ሊሆኑ የሚችሉ አዋጆችን እሚያሳልፉት ፣ ይሄ በሎችም ዘርፎች በደንብ የሚሰራ ነው ።

አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ከተነሱበት አላማ የመዘናጋት ፣ ብሎም የመውጣት አዝማሚያዎች ሊፈታተኗቸው ይችላሉ ፤ ብዙውን ጊዜ ለማሳካት ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለባቸው ስኬቶች ዘላቂ የሆነ አላማቸውን አሻራን ጥለው ማለፍ አለባቸው ። በመሰረታዊነት የተነሱበትን ግብ መቼም ቢሆን መሳት የለባቸውም። ብዙ ሰዎች ያን ያህል መስዋእትነት እሚከፍሉት የዛን ሀሳብ ዘላቂነትና ዘመን ተሻጋሪነት በመረዳት ነው እንጂ ትልቅ አላማ ለሌለው መጀመሪያም ቢሆን ብዙ ደጋፊዎችንና መስዋእትነትን እሚከፍሉ ሰዎች አያገኝም ፤ በእንደዚህ አይነት መስዋእትነት የተገኙ ድሎች እንደ ታሰበላቸው አላማ ዘመን ተሻግረው መሄድ አለባቸው ። ስለዚህ የዚህ አይነት ድሎች መሰረታዊ አላማቸውን እንዳይስቱ ጥረት መደረግ አለበት ። ይሄ መሪው እሱም ሆነ ሌሎች ከተነሱበት አላማና ግብ ላለመውጣት ከሀዲዱ ላለመውጣት መሪ አቅጣጫ ይሆነዋል ።

አንድ መሪ ለሚፈጠሩ ችግሮች ወይንም ለፈተጠሩ ችግሮች ምንም እንኳን ፣ አመርቂ ምክንያት ንና ትንታኔን መስጠት የሚችል ቢሆንምና ፣ ትንታኔ ቢሰጥም ፣ ነገር ግን ውሎ አድሮ ግን እውነተኛ መፍትሄን መስጠት መቻል አለበት ። እንጂ ችግሩ በተደጋጋሚ ሲቀርብለት ምክንያትን ቢደረድርም ፣ ነገር ግን በተግባርም ምላሽን እና መፍትሄን ማግኘት መቻል አለበት ።ይህም ብቻ ሳይሆን ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄን ያልሰጠ መሪ ፣ ምንም እንኳን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እርሱ የተስማማው ቢሆንም ፣ ወቅታዊ የሆነው ነባራዊ ሁኔታ (Stasus Quo) ግን ዘላቂ አይሆንም ።ምላሽን መስጠት ካልቻለ ግን የመ ሪነት ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ሌል ሎች የጠቃውሞ ድምፆች ተሰሚነት እያገኙ እንዲሄዱና በአመራር ብቃቱ ላይ ጥርጣሬን እንዲያጭር ያደርጋል ።

ስለሰዎች ባህሪ የተለያዩ አስተሳሰቦች ያሉ ሲሆን ፣ hይማኖቶችን ብንወስድ ሰዎች በመሰረቱ ጥሩዎች ናቸው ነገር ግን ከእነሱ ፍላጎት ውጫዊ ሀይል ወይም የሚገፋፋቸው ነገር ሰይጣን ያሳስታቸዋል የሚል ነው ። ሌላው ደግሞ ሰዎች ላያውቁ ይችላሉ (Unconscious) ሊሆኑ ስለሚችሉ ለሚያደርጉት ነገር ትልቅ ሀላፊነት ሊጣልባቸው አይችልም ፣ ስለዚህ በትክክለኛው መንገድ አቅጣጫ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው ፣ ሌላው ደግሞ ከቅንነት ልቦና ውጪ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ስለዚህ መሪው ይህንን እውነታ በመረዳት ፣ ያንን ሊያስቀር የሚችል አካሄድን መከተል አለበት የሚል አሰተሳሰብ አላቸው የሚሉም አሉ ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s