ግርማ ሞገሳዊ አመራርና (Charismatic Leadership) ጎጂ ጎኑ ኖቹ

ምንም እንኳን ካሪዝማ ለመሪነት ስኬት አስተዋፅኦን ከሚያደርጉ ነገሮች እንደ አንዱ ተደርጎ ሊቆጠር ቢችልም ፣የራሱ የሆኑ አደጋዎች አሉት ። የማክስ ዌበር ካሪዝማቲክ ስብእናን አስመልክቶ መሰረታዊ የሚባል ጥናትን ያጠና ሲሆን ፣ ጠንካራ እንዲሁም ደካማ ጎኖቹን ተንትኗል ። ይኀውም የዚህ አይነት መሪዎች አደጋን የመጋፈጥ ፣ ከእነሱ በፊት ያልተሞከረውን የመሞከርና የማድረግ አዝማሚያው አላቸው ።

ግርማ ሞገስ ወይንም ተክለ – ሰውነት (Charisma) ምንነት ብዙ ተብሏል ። ይህም ካሪዝማ ማለት የአንድ ሰው በቦታው የመገኘትና የመኖር እንዲሁም ጎልቶ የመታየት ስብእና ሲሆን በብዙ ሰዎች ላይም የሚገኝ ነገር አይደለም ፣ ነገር ግን ተክለ- ሰውነት በአብዛኛው በተፈጥሮ አብሮን የሚፈጠር ነገር ሲሆን ፣ በተፈጥሮ ከሌለ ግን ማምጣት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ። ነገር ግን አንድ መሪ በተፈጥሮ ባይኖረው እንኳን ተክለ – ሰውነትን በተለያዩ መንገዶች ኮትኩቶ ሊያሳድግ ይችላል ። ይሁን እንጂ ግርማ ሞገስ በራሱ በፈጣሪውና በኮትኳቹ መሪ ቁጥጥር ስር መዋል ያለበት ነገር ነው ። ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ግርማ – ሞገስ ለራሱ ለመሪውም ሆነ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት አደገኛ ነው ሊሆን ይችላል ። ተክለ – ሰውነት ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሰፊ የሆነ ተከታይንና አድናቂን ይፈልጋሉ ።

ተክለ – ሰውነት ምትሀት አይደለም ። ከዚያ ይልቅ እንደማንኛውም አይነት መሪ ካሪዝማቲክ መሪዎች ከሌሎች መሪዎች በበለጠ ጥንቃቄን ማድረግ ይገባቸዋል ። ማንኛውም መሪ ልክ እንደ አንድ ሰው ሊያደርግ እና ሊያደርጋቸው የማይችላቸው ነገሮች ሲኖሩ ፣ ተክለ – ሰውነት ያላቸው መሪዎች ብዙውን ጊዜ ለራሳቸው በሚሰጡት ከፍ ያለ ግምት ሌሎች ሊያደርጉ የማይደፍሩትን ነገር ለማድረግ ሊደፋፈሩ ይችላሉ ። ነገር ግን የዚህን መፈታተን አደጋውን ከተረዳ መሪው ከእንደዚህ አይነት አወዛጋቢ ነገሮችን ከማድረግ በመቆጠብ ሊመጣ ከሚችል አደጋ ራሱን ሊጠብቅ ይችላል ፣ ከዚያ ይልቅ እንደውም ጥንቃቄን አክሎ ፣ ተግባራዊ (Practical) ሆኖ መምራት መቻል አለበት ።

እነኚህ ሰዎች በታሪክ በብዛት የሚከሰቱ ካለመሆናቸው ምናልባት በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ሊከሰቱ ፣ ወይንም በጣም በረጅም ጊዜ ውስጥ አንደ ጊዜ ብቻ የሚፈጠሩ አይነት ናቸው ። ሄግል እንደሚለው መሪን የሚመራው «መንፈስ» ከሆነ እነዚህ አይነት መሪዎች መሆን አለባቸው ። ሄግል የሚለው መንፈስ ያለባቸውና ያ «መንፈስ» ያዘዛቸውን እንደሚፈፅሙ የሚቆጠሩ ናቸው ።የዚህ አይነት መሪዎች ላለው ህግ ፣ ለተለመደው አካሄድ ተገዢዎች አይደሉም ። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ህግን በመጣስ ብዙ የመሰላቸውን ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ ። ነገር ግን ይሄ በርካታ ተቃውሞን ያመጣባቸዋል ። እነኚህ መሪዎች እንደ «ታሪክ ክስተት» የሚቆጠሩ ናቸው ። ብዙ አመታት አንድ ጊዜ የሚከሰቱና አዲስ መንገድን የሚቀዱ ናቸው ፣ ይህም ሲያደርጉ ግን ብዙ ጠላቶችን ሊያፈሩ እንዲሁም ከተለመደው አሰራረው ወጣ ሊሉ ይችላሉ ። በእርግጥ ይሄ ነገር ውሎ አድሮ ለወድቀታቸው አስተዋፅኦን ያደርጋል ። የዚህ አይነት መሪዎች ጠላትን ሲፈጥሩ እጅግ የመረሩ ጠላቶችንም የሚያፈሩ ናቸው ። ስለዚህ ይህንን የራሱን ልዩ ባህሪን ራሱ መሪው ከተረዳው በቁጥጥር ስር ሊያውለውና ወደ አላስፈላጊ መንገድ ከመግባት በመቆጠብ ረዘም ላለ ጊዜ ለመቆየት የሚያስችለው ነው ።

የዚህ አይነት በታሪክ በብዛት አይከሰቱም ። ነገር ግን በሚከሰቱበት ወቅት ቀድሞ የነበረውን አስተሳሰብም ሆነ አሰራር ለመለወጥ የሚነሱና በተወሰነ ደረጃ የሚሳካላቸው በተወሰነ ደረጃም ሣይሳካላቸው ይቀራል ። ብዙውን ጊዜ ግን አሳክተውት የሚሄዱት ነገር እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ብዙውን ጊዜ ለመሰረታዊ ለውጥ የቆሙ ከሆኑ ፣ በዘመናቸው ከባድ ተቃውሞን ቢያስተናግዱም ካለፉ በኋላ ግን ከአመታት በኋላ የሰሯቸው ስራዎች እንደ ትንግርት (Legend) የሚቆጠርላቸው ናቸው ። በዘመናቸው መረደግ አለበት ብለው የሚያምኑትን ማንኛውንም ነገር አድርገው የሚያልፉ ሲሆን ፣ አንዳንዴ የሚያደርጉትን በቅጡ ከማወቅ ሲሆን ፣ አንዳንድ ግዜ ግን ራሳቸው እንኳን ልብ ብለው በማይገነዘቡበት መንገድ ያደርጉታል ። ይህም ለሌላ ሰው በቀላሉ የሚታዩ ነገር ግን ለእነሱ የማይታዩ ስህተቶችን ሰርተው ያልፋሉ ።

የዚህ አይነት ሰዎች መድረኩን ለብቻቸው መቆጣጠር የሚፈልጉ ሲሆን ፣ ሌላ ተፎካካሪን አይፈልጉም ። ለራሳቸው ከፍተኛ ግምት ያላቸው ብዙ ምኞትና ህልም ያላቸው «ናርሲስትቲክ» የሆኑ መሪዎችም ከዚህ ተርታ የሚመደቡ ናቸው ።

ባለተክለ – ሰውነት መሪዎች ብዙውን ጊዜ በቀላሉ አይን ውስጥ ስለሚገቡና እንዲሁም ከፍተኛ የመናገርና የማሳመን ችሎታን የተካኑ ከሆኑ ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስልጣን የመምጣት እድል አላቸው ። ለምሳሌ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት ባራክ ኦባማ ብዙም ከማይታወቅ የሴኔት አባልነት ተነስተው ወደ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ሊበቁ የቻሉት ባላቸው የመናገር ችሎታና በግርማ – ሞገስ ስብ እናቸው ነው ።

ግርማ ሞገስ ወይንም ተክለ -ሰውነት (Charismatic) ባለው መሪ የሚመሩ እርሱ እሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል እንደሆነ ተቀብለውየሚኖሩበት ጊዜ ይኖራል ።እነኚህ ብዙውን ጊዜ በመሪነት ደረጃ ጅማሬው አካባቢ ያሉ ናቸው ይሁን እንጂ በምእራቡ አለም ብንወስድ አንድ መሪ የፈለገ ተክለ – ሰውነት ፣ ግርማ – ሞገስ ቢኖረው ስህተትን ከሰራ ስህተቱን ነቅሰው ያወጣሉ እንጂ አያልፉትም – ያገር መሪም ሆነ የኩባንያ መሪ ። ይሁን እንጂ በታዳጊ ሀገራት ፣ እና ዲሞክራሲ ባልዳበረባቸው ሀገራት ግን ብዙውን ጊዜ የመሪዎች ስህተት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የፈፀሙት ነገር ይደበቃል ወይም ተድበስብሶ ያልፋል – ስለዚህ ብቃት የሌላቸው መሪዎች በዛ ቦታ ላይ ካሉ ለረጅም ጊዜ ያለተጠያቂነት(Impunity)ስህተቶች ወይም ጉዳቶች የመፈፀማቸው እድል የሰፋ ነው ።

በነገራችን ላይ የዚህ አይነት አመራር በውስጡ ከባድ አደጋንም አዝሏል ። ብዙ ጊዜ ተክለ – ሰውነታቸው ጎልቶ የሚታዩ መሪዎች በአንድ በኩል ከፍተኛ የማሳመን ሀይል ስላላቸው በተለይም በችግር ጊዜ ለመውጣት ወጥ የሆነና አንዳንዴም አስገዳጅ በሆነ ስብእናቸው ሀገርን ወይም ሌላ እሚመሩትን ተቋም ወደ ከችግር የማውጣት ሀይል አላቸው ፤ በሌላ በኩል ከትክክለኛው መስመር ከወጡ የዛኑ ያክል ሊደርስ የሚችል ጉዳትን ያስከትላል ። የጥንት ግሪካውያን አማልክትና ጀግኖች ሳይቀሩ ከተረጋገጠው መንገድ ውጪ ከሄዱ ውድቀት እንደሚያጋጥማቸው በተለያዩ ተረቶቻቸው ፣ እና ምሳሌያዊ አነጋገራቸው የገለፁት ጉዳይ ነው ።

በግለሰብ ላይ የተመሰረቱ ስርአቶች ሁልጊዜም ቢሆን የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ነው ። በግለሰብ ላይ የተመሰረተውን ወደ ተቋማዊ ወደ ሆነ አሰራር መለወጥ ከቻሉ ህልውናቸው ሊቀጥል ይችላል ። ሆኖም ግን ራሳቸውን በግለሰብ ላይ ከመመስረት ይልቅ ወደ ተቋማዊነት መለወጣቸው ህልውናቸው ዘላቂ አእንዲሆን ያደርጋል ። ይህ ሀሳብ ለየትኛውም ተቋም ይሰራል የሀይማኖት ተቋም ይሁን የፖለቲካ ፓርቲ ይሁን ሀሳቡ ይሰራል ። ማክስ ዌበር የተባለ የማህበረሰብ ሊቅ እንደሚለው በካሪዝማቲክ በሆነ አመራር በአብዛኛው ጠንካራ ተቋም በሌለባቸው ሀገራት በግለሰብ ላይ የተመሰረተ ነው ሆኖም ግን ያን አመራር ራሱን ወደ ተቋማዊነት መቀየር የቻሉ ቀጣይነታቸውን ያረጋግጣሉ ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የአለማችን ታላላቅ ሀይማኖቶች የገዘፈ ተክለ – ሰውነት በነበራቸው ነቢያቶች እና የእግዝአብሄር መልእክተኞች የተመሰረቱ ሲሆን እነሱ ባለፉበት ወቅት ወደ ተቋማዊ አደረጃጀት በመለወጣቸው በርካታ ትውልድን አልፈው በሺዎች ለሚቆጠሩ አመታት ክብራቸውና ተቀባይነታቸው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ሲሄድ አልታየም ።

የገዘፈ ተክለ ሰውነት ከነበራቸው መሪዎች ሙሴን ብንወስድ ህይወቱ ሊያልፍ በተቃረበበት ወቅት እስራኤላውያን በምን አይነት መንገድ ራሳቸውን መምራት እንዳለባቸው በፅሁፍ አድርጎ ያስተላለፈላቸው ሲሆን ፣ የሙሴህግጋት ለእስራኤላውያንና ለክርስትና ሀይማኖት ተከታዮችአሁንም ድረስ መመሪያ እንደሆኑ ይታወቃል ። ይህም ከእርሱ ህልፈት በኋላ እስራኤላውያን ችግር ላይ እንዳይወድቁና ፣ እርሱ ያሳያቸውን መንገድ ቢከተሉ ችግር እንዳይገጥማቸው የገለፀበት ነው ።

የዚህ አይነቱ የአመራር ስልት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ራሳቸው መሪዎቹ ተክለ – ሰውነት ብቻ ሳይሆን በትክክል የመምራት ብቃት ፣ ችሎታውና መልካም ፈቃዱ ያላቸው በትክክልም ወደ ትክክለኛው በቦታ የሚመሩትን ተቋምም ሆነ አገር የሚመሩ ከሆነ የነሱ አመራር አገራትን ፣ ኩባንያዎችን እና የሚመሩትን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንደመሩ በታሪክ ታይቷል ። ለምሳሌ የአፕል መስራችን ባለቤት የነበረው ስቲቭ ጆብስን ፣ የማይክሮሶፍቱ ባለቤት ቢል ጌትስ እንዲሁም ከአገራት መሪዎችም ስማቸው ገኖ የሚጠቀስ በርካቶች አሉ ።

ይህ አይነቱ አመራር በተለይም የሰዎችን ድብቁን ህሊናን (Sub – Conscious) በመቆጣጠር ላይ የተመሰረተ ከሆነና ብስለት ያለው አቅጣጫ ከሌለው ሊያስከትለው የሚችለው አደጋ የከፋ ነው የሚሆነው ። ይህም በርካታ አምነባገነኖች ተክለ – ሰውነትና የመናገር ችሎታን በመጠቀም ወደ ስልጣን እንዲመጡና ብዙ ጥፋትን እንዲያስከትሉ በታሪክ በተደጋጋሚ ተከስቷል ።
ሌላው የዚህ አይነት መሪዎች ካለፉም በኋላ ትተውት የሚሄዱት ክፍተት ቀላል አይደለም ። አዲሱ መሪ የእነሱን ያህል ተክለ – ስብእና ባለቤት ካልሆነ በተለይ የሚፈጠረው የባዶነት እና የማጉደል ስሜት ከፍተኛ ነው ። ነገር ግን አዲሱ መሪ የቀድሞው መሪ በሄደበት አቅጣጫ ለመሄድ መሞከር የለበትም ። ከዚያይልቅ የራሱን መንገድ መቅደድና በዚያ መጓዝ አለበት ። ለዚህ ምክንያቱ ሁለት ሰዎች አንድ አይነት ሊሆኑ ስለማይችሉ ፣ አንዱ የቀደመው መሪ በቀደደው መንገድ ልሂድ ቢል የሱን ቦታ ሊሞላው ስለማይችል በሰዎች ዘንድ ቅሬታን ይፈጥራል ።

አዲሱ መሪ የቀደመውን መሪ ለመምሰል መሞክር የለበትም ከዚያ ይልቅ የራሱን መንገድ ለመከተልና በታሱ ራሱ መንገድ ተክለ – ሰውነትን ለመፍጠር መሞከር ነው ያለበት ።

የዚህ አይነት መሪዎች ካለፉ በኋላ ሊተካቸው የሚችለው ፣ የጋራ አመራር ነው የሚሆነው ። መጀመሪያ የጋራ አመራር ፣ ቀጥሎም አበንድ ተክለ – ሰውነት ባለው መሪ ስልጣኑ መጠቃለል ፣ ቀጥሎም እሱ ካለፈ በኋላ ወደ ቀድሞው የጋራ አመራር መመለስ ነው ። ለምሳሌ ማኦን ብንወስድ ምንም እንኳን ትግሉን የጀመሩት ማኦ ብቻቸውን ባይሆኑም ውለው አድረው ግን ወደ አንድ ሰው አመራር ለውጠውታል ፣ እርሳቸው ካለፉ በኋላም ወደ ቀድሞው የጋራ አመራር ተመልሷል ። እነኚህ ሰዎች በቀላሉ የሚተኩ ስላልሆኑና የገዘፈ ጫማ ያላቸው ስለሆኑ እነሱን ልክ በእነሱ መንገድ መተካት ስለማይቻል ወደ ቀድሞው የጋራአመራር (Collective Leadership) መመለሱ አይቀሬ ነው ። ማኦን የተኩት ዴንግ ዚያኦፔንግ ምንም እንኳን ከማኦ ብዙም ያልተናነሱ ቢሆንም የማኦን አይነት ስርአትን ግን አላሰፈኑም ። ይህ ሀያል የሆነ መሪ ቢታመም ወይም ቢሞት የሚፈጠረው የስልጣን ክፍተት ሰፊ ስለሚሆን ፣ በአንድ ሰው ተይዞ የነበረን በርካታ ቦታ በቀለሉ መተካት አስቸጋሪ ነው ። ለተቋማቱም በአንድ ሰው ላይ መተማመን ያለውን አደጋ ስለሚያሳይ ወደ ቀድሞው በአንድ ሰው ላይ ብቻ የተመሰረተ አሰራር መመለስ የሚፈጥረውን ክፍተት ስለሚረዱ ተቋማት ራሳቸው ወደዛ አሰራር አይመለሱም ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s