የምጣኔ ሀብት አስተዳደር

የምጣኔ ሀብት አስተዳደር ከፖለቲካ አስተዳደር የተለየ ሲሆን ማንኛውም የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረታዊ የሆነውን ህግ ማለትም የአቅርቦትንና የፍላጎትን ህግ መፃረር የሌለበት ሲሆን የሚወጡ አዋጆችና ደንቦችም ከዚህ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም። ለአንድ ሰሞን ተብለው የሚወሰዱ በጥናት ያልተደገፉ ከሆነ ገበያውን በማዛባት ከዚያ በኋላ ወደ ነበረበት ለማስተካከል ረጅም ጊዜን ይፈጃሉ። የምጣኔ – ሀብት አስተዳደር በትእዛዝ የሚመራ ነገር አይደለም ፣ መሰታዊ የሆኑ የምጣኔ – ሀብትበህ ህግጋትን መጠበቅ ነው እንጂ ያለበት ።
በሀገራችን የግብይት ስርአቱ ለረጅም ጊዜ ችግር የነበረበት ሲሆን እየጨመረ ከመጣው ዋጋና ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር በህዝቡ ኑሮ ላይ አሉታዊ ተፅእኖው እየጎላ ስለመጣ የመንግስትን ትኩረት እሚስብበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል ፤ ለዚህ የግብይት ስርአት ችግር በርካታ ምክንያቶች አሉት ። በተለያየ ወቅት በባለሙያዎች የተጠኑ ጥናቶች በርካታ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል ።
ማንኛውም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይሄንን መርሆ የሚጥስ ከሆነ ለረጅም ጊዜ መስራት መቻሉ ያጠራጥራል ። መሰረታዊ የሆኑ የምጣኔ ሀብት ህግጋት በተለይም የአቅርቦትና የፍላጎት ህግ እንደ ተፈጥሮ ህግ ተደርጎ የሚወሰዱ ናቸው ። ለምሳሌ የዋጋ ቁጥጥርን ብንወስድ በረጅም ጊዜ መስራቱ ከጥያቄ ውስጥ እሚገባ ነው እሚሆነው ። እንደ ኢትዮጲያ ባለ የነፃ ገበያ በደንብ ባልተደራጀባት ሀገር ጥቂት ሻጮች ወይም አቅራቢዎች(Monopoly) ብቻ መኖርችግሮችን እንደሚፈጥር የታወቀ ሲሆን ለዚህም ገበያው በነጻ ውድድር ላይ እንዲመሰረትና በርካታ ሻጮችና አቅራቢዎችን ወደ ገበያ ውድድሩ ማምጣት ያስፈልጋል ።
ሌላው የባንክ የወለድ ምጣኔ (Interest Rate) ከዋጋ ግሽበት ምጣኔው ማነስ የሌለበት ሲሆን እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ገንዘብ ባንክ ከመቀመጥ ይልቅ ወጪ አድርጎ የሆነ ነገር መግዛት የተሻለ ስለሚሆን ይበልጥ ዋጋ ግሽበቱን የማባባስ ውጤት ሊኖረው ይኖረዋል ። የዋጋ ግሽበቱ አራት ዋና ዋና መነሾ ይኖሩታል አንዱ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ የሚዘዋወረው የገንዘብ ህትመት ሲጨመር ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ዝውውሩ ፍጥነት (Velocity) ኢኮኖሚው ከሚችለው በላይ ሲጨምር ወይም ፣ በሀገር ውስጥ የሸቀጦች አቅርቦት ሲቀንስ ወይም ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች እንደ ነዳጅ ዘይት የመሳሰሉት አቅርቦታቸው ሲቀንስ እና ዋጋቸው ሲጨምር ነው ።
የኋላ ኋላ ቻይናና ህንድም ለዚህ አሳሳቢ ለሆነ ዋጋ ግሽበት ምላሽ ሰጥተዋል ። ይህንንም ያደረጉት እድገታቸውን በመቀነስ ወይም በማቀዝቀዝ ሲሆን ለምሳሌም እ.ኤአ. በ 2012 የቻይና መሪዎች አመታዊ የምጣኔ – ሀብት እድገታቸውን ወደ 7.5 በመቶ ዝቅ በማድረግ የዋጋ ግሽበቱን ወደ 4 በመቶ ለማውረድ እንደሚሰሩ ሲገልፁ ይህም በሁለት አሀዝ ሲያድግ ለቆየው የቻይና ምጣኔ ሀብት ከስምንት አመታት ወዲህ አነስተኛው የምጣኔ ሀብት እድገት መሆኑ ነው ። በተመሳሳይም ህንድም እንዲሁ እድገቷን ዝቅ በማድረግ የዋጋ ግሽበትን ዝቅ ለማድረግ እንደምትሰራ ገልፃለች ።
ይህም የአለም ምጣኔ – ሀብት ትስስር መኖሩ ምንም እንኳን ብሪክስ የተባሉት ሀገራት አለምን ከምጣኔ – ሀብት ቀውስ ያወጣሉ ቢባልም ፣ ራሳቸውም ቢሆኑ የአለም ኢኮኖሚ አካል እንደመሆናቸው በምእራቡ አለም የተፈጠረ የኢኮኖሚ ቀውስ እነሱንም ውሎ አድሮም ቢሆን እንደማይምር ያሳየ ነው ።
በነገራችን ላይ የነፃ ገበያ ውድድር አለመኖር ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን በፊትም በኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ላይ ቀድሞም ቢሆን በጉልህ ይታይ የነበረ ችግር ነው ። አንዳንዴ ሲታሰብ ሀገራችን ነጋዴዎች የተጋነነ (Excessive) ትርፍን የሚያገኙ ይመስላል ይህን የበዛ ትርፍ በመቀነስሸማቹ እንዳይጎዳ ማድረግ የሚቻለው በገበያ ውስጥ ተጨማሪ የገበያ ውድድር እንዲኖር በማድረግ ብቻ ነው ።
ሌላው ደግሞ የንግድ ልውውጡን ዋጋ (Transaction Cost) እንዲቀነስ በማድረግ ነው ። ይኀውም አንድ ሸቀጥ ከተመረተበት ቦታ ተነስቶ ለተጠቃሚው እስከሚደርስ ድረስ ለግብይት የሚፈጀው ጊዜ ፣ ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ለሸቀጦች ዋጋ መወደድ አንዱ ምክንያት ነው ። ሌላው ለግብይት ዋና መናር ምክንያት ደግሞ በተለይ ከውጪ ለሚገቡ ሸቀጦች በአንድ ጊዜ በብዛት አለመገዛት አንዱ ምክንያት መሆኑ በባለሙያዎች ተደርሶበታል ። ገንዘቡ በኢኮኖሚው ውስጥ እሚሽከረከርበት ፍጥነትም የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ። ፈጣን የገንዘብ መሽከርከር በሌለበት ገንዘብ ቢታተምም ግሽበትን አያመጣም ተብሎ ሊታሰብ ይችላል ።
ሌላው ደግሞ ህገወጥነት ሲሆን በንግድ ስርአቱ ላይ ህገ – ወጥነት በሰፊው የሚታይ ነው ። መጠናቸውን ባልጠበቁ በተሳሳቱ ሚዛኖች መመዘን ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ሸቀጦች ቀናቸውን ቀይሮ እንደ አዲስ መሸጥ፣ ከጥራታቸው በታች የሆኑ ሸቀጦችን ያለምንም ሀፍረት ወደ ገበያ ማቅረብ፣ለምግብነት እሚቀርቡ ሸቀጦችን ለጤና ጎጂ ከሆኑ ነገሮች ጋር መቀላቀል እና የመሳሰሉትእነኚህ ሁሉ ለአንድ ሰሞን ዘመቻ ይደረግባቸውና ከዚያም ተመልሰው ይረሳሉ ።
ሌላው ደግሞ እሴትን የሚጨምሩ (Value Add) ፋብሪካዎችና ማቀናበሪያዎች በሀገራችን በብዛት አለመኖር ሲሆን የዛ አይነት ተቋማት ቢኖሩ ከሀገር ውስጥ ግብአቶችን ወይንም ከውጪ ጥሬ እቃን በማስገባት በቀላሉ እዚህ እሴትን በመጨመር የመጨረሻ ምርት አድርጎ በማውጣት ከውጪ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን የስራ እድሎችንም መፍጠር ያስችላል ። በኢንዱስትሪ ያደጉት ሀገራት ብዙም በጥሬው እንዳለ እሚልኩት ነገር የለም ማለት ይቻላል ፣ በርካታ ግብርና ምርቶችን አምራቾች ቢሆኑም አብዛኛውን እንዳለ ወደ ውጪ አይልኩትም ፣ ለእርዳታ ከሚልኩት ከስንዴ ፣ ከበቆሎ ከመሳሰለው በስተቀር ፣ የተቀረውን በሙሉ እዛው በሀገራቸው ውስጥ አቀናብረው ፣ እሴት ጨምረው ነው ወደ ውጪ እሚልኩት ።
ቡናን ብንወስድ ከታዳጊ ሀገራት ወስደው በሀገራቸው ማቀናበሪያዎች ነው እሚያቀናብሩት ፣ እንጂ የቀዝቀዝ ያለ የአየር ንብረት ባለቤት የሆኑት ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ሀገራት ቡና አምራቾች አይደሉም ።
እዚህ ላይ ስለ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማንሳት ይቻላል ። የምጣኔ ሀብት አቅማቸው በግብርና፣ በማእድን ወይንም በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሀገሮች የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው የሚሆነው ወይንም ከፍተኛም ቢሆን እንኳን የነዳጅ ላኪ ሀገራት እንደሆኑት ቀጣይነቱ ያጠራጥራል ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሰፊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሚዛኑን የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ ፣አንዱ ዘርፍ ላይ የሚደርስ ኪሳራ ወይም በአለም ገበያ የዋጋ መዋዠቅ ቢያጋጥም የዛ ሀገር ገቢ ክፉኛ ይጎዳል ፣ ለምሳሌ ነዳጅ ላኪ የሆኑ በርካታ ሀገራት ዋናው ገቢያቸው ከነዳጅ ከመሆኑና ነዳጅ ዘይት ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆናቸው ፣ ባጀታቸውን በነዳጅ ዋጋ ላይ ተመስርተው እንደሚመድቡ ይታወቃል። በሌሎች ዘርፎች ላይ ምጣኔ – ሀብታቸውን እያሰባጠሩ ካልሄዱ እነሱም ቢሆኑ ውለው አድረው ነዳጅ በሌላ የሀይል ምንጭ ሊሰጥ በሚችል ነገር ቢተካና ዋጋው ቢወድቅ ወይም ያላቸው የነዳጅ ሀብት ጨርሶ ተሟጦ ቢያልቅ አማራጭ የገቢ ምንጮች ከሌሏቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት እድል ሊፈጠር ይችላል ። ብዙዎቹ ደሀ ሀገሮች የምግብ ፍላጎታቸውን ከውጪ ነው የሚያስገቡት ።
የኢንዱስትሪ እሴት የመጨመር አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ የተቀረው አለም ከሚያደርገው እሴት ጭማሪ እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የአፍሪካ ሀገራት ጭማሬ 1% ብቻ መሆኑ ነው ። በምጣኔ ሀብት አስተዳደር ውስጥ በመሬቱ ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታና ሁነት እንደሌለ አድርጎ መውሰድ ጎጂ ነው ።
አንድ ፖሊሲ እማይሰራ ከሆነና አለመስራቱ በግልፅ የሚታይ ከሆነ ይሰራል ብሎ በዛ ነገር መግፋት ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አያመጣም ። ዋጋዎችን ብንወስድ ትልቁ ማበረታቻ ዋጋ ሲሆን የዋጋ ማበረታቻን የማያቀርብ ፖሊሲ ግን ውጤትን አያመጣም ። ለምሳሌ የቀድሞው የእርሻ ሰብል ድርጅት ከገበያ ዋጋ ባነሰ አነስተኛ ዋጋ ከገበሬው ወስዶ በርካሽ ዋጋ ለከተማ ነዋሪ ይሸጥ ስነበረ የእየቆየ ሲሄድ የአርሶ አደሩን ለማምረት የሚያነሳሳውን ማበረታቻ አጠፋው ፣በዚህ ብቻ ሳይገታ በአርሶ አደሩ ለመንግስት የነበረውን ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዲቀንስም አድርጓል ። በእርግጥ ይህ ፖሊሲ ለከተማ ነዋሪው የምግብ ሰብል በርካሽ እንዲያገኝ አስችሏል ቢባልም ፤ ከሀገሪቱ ህዝብ አብዛኛው በሆነው እስከ 80 በመቶ ይደርስ ከነበረው ከአርሶ አደሩ ዘንድ ግን ድጋፍን እንዲያጣ ካደረጉት የፖሊሲ ግድፈቶች እንደ ዋናው ተደርጎ በበርካታ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የተገለፀ ነው ።
ራሳቸው ትልቅ አቅም ያላቸው ምእራባውያን ሳይቀሩ የማይሆነውን ነገር ይሆናል ብለው ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን አያባክኑም ። የሚሰራውንና ሊሆን የሚችለውን ብቻ ነው እሚከተሉትም ስራ ላይ እሚያውሉትም ።
ሌላው ፖሊሲ አውጪዎችን ሊፈታተን የሚችለው ነገር ገንዘብ ማተም ሲሆን ገንዘብ ማተም በምጣኔ – ሀብት ላይ በቀላሉ የማይስተካከል የዋጋ ግሽበትን ይፈጥራል ። በተለይም አብዛኛው ግብይቱ በገንዘብ ላይ የተመሰረተ (Monitised) አይደለም ፣ መደበኛ ያልሆነ የምጣኔ – ሀብቱ ዘርፍ ሰፊ ነውተብሎ በሚገመት ምጣኔ – ሀብት ውስጥ ገንዘብ ቢታተም ያን ያህል የዋጋ ግሽበትን አይፈጥርም ተብሎ ስለሚታሰብ ፖሊሲ አውጪዎች ገንዘብ ማተም ያን ያህል የገንዘብ ግሽበትን አያስከትልም ሊሉ ይችላሉ። ይሁን ውጤቱ ያልተጠበቀ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።
አንድ ሀገር እድገቷን ለማፋጠን የገንዘብ ምንጭን በምታስብበት ወቅት ሌላው የሚመጣው አማራጭ ብድር መበደር ነው ። ሀብታሞቹ ሀገራትም ጭምር ሳይቀሩ ብድርን የሚበደሩ ሲሆን የትኛውም ሀገር ብድር የሚበደር በመሆኑ አስገራሚ አይሆንም ፣ ነገር ግን ይኀው ከፍተኛ ብድር ውስጥ መዘፈቅ ከተከተለ ደግሞ ፣ ለአንድ ሀገር ለመወጣት አስቸጋሪ የሆነ የእዳ ማጥ ውስጥ መዘፈቅን ያስከትላል ። ይኀውም ለሀብታሞቹ ሀገገራትም ጭምር የብድር መብዛት ለመውጣት የሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ሲዘፍቅ በተደጋጋሚ ታይቷል ።
በተለይም የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው ሀገራት ፈጣን እድገትን ለማስመዝገብ ከሚሰማቸው ጉጉት የተነሳ በአንድ በኩል የዋጋ ንረት ውስጥ መዘፈቅ ወይንም በእዳ ውስጥ የመዘፈቅ አደጋ ውሰጥ ሊገቡ ይችላሉ ። በአፍሪካ እንደ አንደ አንጎላ ያሉት ሀገራት በአንድ አመት እስከ 35በመቶ የምጣኔ – ሀብት እድገትን በአንድ አመት ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን ፣ የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው ሀገራት ግን ለፈጣን እድገት የሚያስፈልገውን የገንዘብ ምንጭ ለማፈላለግ ብድርን አንዱ አማራጭ አድርገው ሊወስዱት ሲወስዱት ይታያሉ ።
በምእራቡ አለም አንድ ምጣኔ – ሀብት ውስጥ ምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት ማእከላዊ ባንኮች ገንዘብ ሊያትሙ ፣ ወይም ተጨማሪ ገንዘብን በተለያየ መንገድ ወደ ምጣኔ – ሀብቱ ሊለቁ ይችላሉ ፣ ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (Monetery Easing) በመባል የሚታወቀው ሲሆን ። ይሁን እንጂ ልክ ምጣኔ ሀብቱ መነቃቃት ሲጀምር በተፈጠረው የፍላጎት ማደግ ምክንያት ከዛ ገንዘቡ ተመልሶ መሰብሰብ (Contract) አለበት ። ያን ለማድረግም የሚያስችል ጠንካራ የገንዘብ ፣የአክስዮን፣ እና የካፒታል ገበያዎች (Capital Market) በአጠቃላይ የዳበረ የካፒታሊስት የገበያ ስርአት ስላላቸው በተወሰነ ደረጃ ማስተካከል ቢችሉም ፣ ለነሱም ቢሆን ግን ገንዘብ ማተም የሚያስከትለው ችግር ማስከተሉ አይቀሬ ነው ።
በነገራችን ላይ የኬነዢያን ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች (Kenysian Economists) ምጣኔ ሀብቱ ችግር ውስጥ በሚገባበት ወቅት የመንግስትን ወጪ መጨመርን ወይም በተወሰነ መልኩ ገንዘብ ማተምን ያበረታታሉ ። በእርግጥ መጀመሪያ አካከባቢ አንድ ገንዘብ ሲታተም ፍላጎትን ያነቃቃል ይሁን እንጂ የታተመውን ገንዘብ የሚያክል ምርትና አገልግሎት በኢኮኖሚው ውስጥ አለመኖሩ ጉልህ ሆኖ መታየት ሲጀምር ግን የዋጋ ወይንም የገንዘብ ግሽበት መታየት ይጀምራል ። ስለዚህ የዋጋ ወይንም የገንዘብ ግሽበት መታየት ይጀምራል ። ስለዚህ ወዲያው ወደ ኢኮኖሚው የተለቀቀው ገንዘብ ተመልሶ መሰብሰብ አለበት ። ግን ይሄም ፖሊሲ እሚሰራው የዳበረ የነፃ ገበያ ስርአት ወይም የካፒታሊስት ስርአት ሲኖር ሲሆን የወድ ምጣኔው ፣ የብድር አቅርቦቱና የአክስዮንና የካፒታል ገበያ የመሳሰሉትም ለዚህ ምላሽን የሚሰጡ መሆን አለባቸው ።
በኋላ ላይ የተነሱት የኬነስ ተከታዮች በኋላ የተነሱት ሞኒተርስቶች (Moniteristts) የተባሉት (Neo – Classical) የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማሳየት እንደቻሉት ደግሞ (Inflation is a Monetary Phenomenon) የገንዘብ ማተም ክስተት ከመሆኑን ማስረዳት ችለዋል ። ስለዚህ የኬኒዢያኖቹ ሀሳብ በምእራቡ አለም አገራት በ1970ዎቹ የገንዘብ ግሽበትን ማስከተል ሲጀምር ደግሞ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው መርጨትን ማቆም ጀምረዋል ። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ ሊስተካከል የማይችልና ከቁጥጥር ውጪ የወጣ የዋጋ ግሸበት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በምጣኔ – ሀብቱ ላይ ያለውን አመኔታ ይሸረሽራል ፣ ብሎም ኢንቨስትመንትን በማዳከም ወደ አጠቃላይ ምጣኔ – ሀብታዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ያመራል ። ስራ አጥነትን ለመቀነስ ሲሉ መንግስታት ተጨማሪ ገንዘብን ወደ ምጣኔ – ሀብቱ ስለሚለቁ የዋጋ ግሽበትን ይፈጥራል ፣ ስለዚህ የዋጋ ግሽበት በፖሊሲ አቅጣጫ መሳት እሚፈጠር ነገር ነው እንጂ እንደ ስራ አጥነት በራሱ እሚፈጠር አይደለም ። የገንዘብ ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት ያንን እንዲሁለማስተካከል በሚወሰዱ እርምጃዎች የዋጋ ግሽበትን ይፈጥራል ።
የተረጋጋ የዋጋ ምጣኔ (ስቴብል ኢንፍሌሸን) የተሻለ ነው ። በሀምሌ 2012 በወጡ መረጃዎች መሰረት ቻይና የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን ፣ በአንፃሩ ግን የአውሮፓውያን በእዳ ሰበብ ምንክንያት ኢኮኖሚያቸው ችግር ውስጥ መግባት የወጪ ንግዷን በመጎተቱ የዋጋ ባለበት መቆም ብሎም መቀነስ (ዲፍሌሸሽን) በቻይና መከሰት ጀምሯል ። የዋጋ ግሽበቷም በ2.5 በመቶ ደረጃ ማውረድ ችላለች ። በተለይም የምግብ ዋጋ መቀነሱ ጥሩ ዜና ቢሆንም በአንፃሩ ግን አጠቃላይ ምጣኔ – ሀብተ ግን ወደ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቷል ። ከ2008 በኋላ የተደረገውም ለቀቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲም በቀጥታ ገንዘብ አትሞ በምጣኔ – ሀብቱ ውስጥ መልቀቅ የዋጋ ንረትን እንደሚያመጣ ግን አጠራጣሪ አይደለም ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s