ሶሻሊዝም ወይም ህብረተሰብአዊነት

ሶሻሊዝም በዘመኑ በርካታ ምሁራኖችንና አሳብያኖችን ያፈራና ያስከተለ ማህበረ – ፖለቲካዊና- ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና ሲሆን አሁን ግን የድሮውን ዝናውንና ስሙን ደብዝዟል ማለት ይቻላል ። በ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አሁንም ድረስ የሶሻሊዝምን ስም የያዙ ፓርቲዎች ያሉ ቢሆኑም ስር – ነቀል (Radical) ከሆነው ማርክሲዝም ግን በእጅጉ የተለዩ ናቸዉ ። ከርሱ በፊት በርካታ የሶሻሊዝም ምሁራኖችና በተግባርም ሞካሪዎች የነበሩ ቢሆንም ሶሻሊዝምን (Socialism) በተቀናጀና ስልታዊ በሆነ መልኩ የተነተኑት ካርል ማርክስና ፍሬደሪክ ኤንግልስ ሲሆኑ ማርክስ አብዛኞቹን ሀሳቦች ከዴቪድ ሪካርዶና ከአዳም ስሚዝ ወስዷል ።ሶሻሊዝምን በተግባር ከመሩ ሰዎች አንዱ ጆሴፍ ስታሊን አንዱ የነበሩ ሲሆን አወዛጋቢ ስብእናም ጭምር ነው ። በአንድ በኩል ሶሻሊዝምን ያጠናከረና ከምእራቡ አለም እኩል ተወዳዳሪ ማድረግ የቻለ ተብሎ ሲሞገስ በዚህ ምክንያት ምእራባዉያን ለሱ ከፍታኛ ጥላቻ ቢኖራቸዉ አስገራሚ አይሆንም ። በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊዝምን ወደ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ስርአት በመቀየሩ ፣እንዲሁም በዙሪያውየተክለ – ሰውነት ግለሰባዊ የሆነ አምልኮን (Cult) በማበረታታቱ ፣ ለሶቭየት ህብረት ስጋትን ደቅኖ ለነበረው ለናዚዎች የወረራ ስጋት ምንም ዝግጅት አለማድረጉ ፣ በሀሰት በተቀነባበሩ ውንጀላዎች ቀደምት የሆኑ በርካታ የራሱን ፓርቲ አባላትን ማስወገዱ ፣ የጀርመንን ግንብ በመገንባት አውሮፓን ለሁለት እንድትከፈል ማድረጉ፣ በርካታ የራሱን ዜጎች በመጨፍጨፉና ወደ ሳይቤሪያና የጉልበት ስራ ወደ ሚሰራባቸው ካምፖች (Labor Camps) በማጋዙ ሲወቀስ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም ሶቭየት ህብረትን ወደ ኢንዱስትሪ ሀገር ደረጃ በማሳደጉ እንዲሁም የናዚዎችን ወረራ በተሳካ ሁኔታ በመመከቱ በታሪክ እንደ ጥንካሬ ይታይለታል ።

በርካታ አይሁዳውያን የሶሻሊዝምን ፅንሰ – ሀሳብ በማሰራጨትና ወደ ተግባር ለመለወጥም በመታገል ይታወቃሉ ፣አንዳንዶች ሶሻሊዝምን የአይሁዳዉያን ሴራ አድርገዉ የሚወስዱ ሰዎች አሉ ። ለምሳሌ ናዚዎች የቦልሽቪክ አብዮትን የአይሁዳውያን አለም አቀፋዊ ሴራ አድርገው ነው የቆጠሩት ። በዛንወቅት አይሁዳውያን ሀገር ስላልነበራቸው በሶሻሊዝም አለም – አቀፋዊነት ባህሪ መሳባቸው የጣወቀ ነው ። በነገራችን ላይ አይሁዳውያን በሶሻሊዝም ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፋዊ ካፒታሊዝምም ጭምር ስማቸው አብሮ ተያይዞ የሚነሳ ነው ። ሶሻሊዝም በውስጡ ብዙ አይነት ውላጆችን የያዘ ነው ፣ ከአናርኪስቶች ጀምሮ በአውሮፓ ስልጣን እሚይዙት ሶሻል ዲሞክራቶችን ብንወስድ ከሶሻሊዝም አብራክ የተፈጠሩ ናቸው ። ንሂሊስቶችም (Nihilists) ከዚሁ የሚመደቡ ናቸው ። ተምኔታዊ ሶሻሊዝም የሚባሉትም የዚሁ ዘውግ አባል ናቸው ።

ከእርሱ በኋላ አንዳንድ ሶሻሊስቶች የስታሊንን ምሳሌ በመከተል በአለም ዙሪያ በርካታ መንግስታትን መስርተዋል ይሁን እንጂ አሁን እየወጡ ያሉ የምርመራ ዉጤቶች እንደሚያሳዩት አንጎሉን በመመርመር የተወሰዱ ምስሎች እንደሚያሳዩት ስታሊን አእምሮዉ ጤነኛ እንዳልነበረ የሚጠቁሙ ሆነዉ ተገኝተዋል። የቀድሞዋሶቭየት ህብረትን እሚያክል ሀያል ሀገር በእንደዛ አይነት ሰውትመራ የነበረች መሆኗ ሳይንቲስቶችን በእጅጉ አስገርሟል። ይሁን እንጂ ሁሉንም እሚያስማማው የስታሊን አምባገነናዊ ስርአት ሶሻሊዝም እንዴት በአምባገነን ግለሰቦች ሊቀለበስ እንደሚችልና የራሱን ፍልስፍናውን ለህዝቦችና ለሀገራት የሚያስገኘውን ጥቅም ጥያቄ ውስጥ እስከማስገባት ደረጃ አድርሷል ።

በስታሊን ላይ ሁለት አይነት ክርክሮች የነሳሉ በአንድ በኩል ከነበረው የምእራባውያን ጥንካሬና ውድድር አንፃር ሶሻሊዝምን ያጠናከረው እሱ ነው የሚሉ አሉ በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊዝምን ወደ ግለሰባዊ አምባገነናዊ ስርአት የቀየረውና አለም አቀፋዊ ገፅታውን ያሳጣው እሱ ነው ስለዚህ ለሶሻሊዝም ውድቀት ተጠያቂ የሚሆነው እሱ ነው እሚሉ አሉ ። ስታሊናዊ አምባገነናዊ ስርአት ብዙዎችን ህይወት በመብላቱ እንዲሁም አለም አቀፍ ሲሶሻሊስቶች የሱ ፖሊሲዎች የሶሻሊዝምን ውድቀት ጉድጓድ የቆፈሩ ናቸዉ በሚል ሶሻሊዝምን ስርአት እንደቀለበሰ ይቆጥሩታል ።

ከእርሱ በኋላ የመጡምመሪዎች የሱን መንገድ በመከተላቸው ስርአቱ ለአስርት አመታት ምንም አይነት ማሻሻያዎችን ባለማድረጉ ምክንያት መጨረሻ ላይ ሊንኮታኮት በቅቷል ።

አንዱ የካፒታሊዝም ስርአት ጥንካሬው ራሱን ከሁኔታዎችና ከጊዜው ጋር ማስማማት መቻሉ (Adapt) ማድረጉ ሲሆን በአንፃሩ ግን የኮሚኒዝም ስርአት ይህንን ለማድረግ የሚያስችል መዋቅራዊም ሆነ ስልታዊ አካሄድ የለዉም።የካፒታሊዝም ወይንም የነፃ ዲሞክራሲ ስርአት (Liberal Democracy) ነጻ ምርጫዎችን ስለሚያካሂድና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትን ስለሚፈቅድ በዛዉ ስርአት ውስጥ ማሻሻያዎችንና ለውጦችን እያደረገ ሲቀጥል በአንፃሩ የኮሚኒዝም ስርአት ግን ለዚህ የታደለ አይደለም። ቻይናን ራሱ ብንወስድ ምንም እንኳን ቻይና መሪዎቿን በየአስር አመቱ እርስ በእርስ በመመራረጥ የምትተካ ቢሆንም በተግባር ግን መሪዎቹ አዲስ ለውጥን በማካሄድ የፖለቲካ ስጋት እንዲፈጠር አይፈልጉም ፤ ከዚያ ይልቅ የነበረውን ስርአት ባለው መንገድ እንዲቀጥል የማድረግ ስራን ነው የሚሰ ሩት ። ይህም ውሎ አድሮ የህዝብ ተስፋ መቁረጥንና ችግሮችም መፍትሄ ሳያገኙ እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው ።

ስልጣኑን በግለሰብ ወይንም በጥቂት ግለሰብ ቡድኖች እጅ ስለሚገባና ስልጣናቸውን ማጣት ወይንም መቀነስ ስለማይፈልጉ ማሻሻያዎችን ሳያደርጉ ለብዙ አመታት ስለሚቆዩ መጨረሻ ላይ ነገሮች ከቁጥጥር ዉጪ የሚሆኑበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ። በአስገራሚ ሁኔታ ግን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ይህንን አደጋ የተረዳ ይመስላል ፣ለዚህም በተደጋጋሚ ጥገናዊ ለውጦችንና ማሻሻያዎችን በማድረጉ በአለም ላይ ከታዩ የኮሚኒስት ስርአቶች ሁሉ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት ችሏል።  ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ የዲሞክራሲ ስርአቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታት ህልውናቸውን አስጠብቀው አሁንም ድረስ መቀጠል ሲችሉ በአንፃሩዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ የኮሚኒስትና ፣ ምርጫን የማያካሂዱ አምባገነናዊ የሆኑ ስርአቶች ግን መጨረሻ ላይ በሚወገዱበት ወቅት ከሚፈጥሩት ቀውስ በተጨማሪ ፤እድሜአቸው ከጥቂት አስርት አመታቶች በላይ ሊዘል አልቻለም ።

ከሶሻሊስቶች ከማርክስና ከኤንግልስ ቀጥሎ ሌኒን የጠቀሳል ። ምንም እንኳን ሌኒን የካርል ማርክስን ያህል የሶሻሊዝም ርእዮተ – አለም ዋነው ፈጣሪው ባይሆንም፣ ምሁር የነበረና በርካታ ፅሁፎችን ያበረከተ እንዲሁም በርካታ ቋንቋዎችን ጀርመንኛንና ሌሎች የአውሮፓውያንን ቋንቋ የሚያውቅ እና አቀላጥፎ የሚፅፍና የሚናገር ሲሆን በተለይም ማርክስ በንድፈ – ሀሳብ ደረጃ ያስቀመጣቸውንና ያን ግዜ ካፒታሊዝምና ባላደገባትና ፊውዳል በነበረችው ሩሲያ የማርክስን የሶሻሊዝም ንድፈ ሀሳብ ወደ ሶሻሊዝም በተግባር እንዲቀየር በርካታ ሀሳቦችን ያመነጨ ሰው ነዉ ።

ማርክስ በአብዛኛው ያቀረባቸው ሀሳቦች ካፒታሊዝም ከፍተኛ ደረጃ ለደረሰባቸው በኢንዱስትሪ ለዳበሩትና ብዛት ያለው የኢንዱስትሪ ሰራተኛ ላላቸው እንደ ፈረንሳይ ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ለመሳሰሉት የአውሮፓ ሀገራት እንጂ በፊውዳል ስርአት ለነበሩና በኢንዱስትሪ ላልዳበሩ እንደ ሩስያ ላሉ ሀገራት እልነበረም ።

ምእራባውያን ግን በአንድ ወቅት በሜሊኒየሙ መጨረሻ የወጣ ያታይም መፅሄት ሌኒንን ዘመናዊ የጭቆና መሳሪያዎችን የፈለሰፈ ወይንም የፈጠረ በማለት ይገልፀዋል። ሌኒን በርካታ የጭቆና መሳሪያዎችን ይፈልስፍ እንጂ ፣ ረጅም ስልጣን ዘመን የነበረው በመሆኑ በተግባር ላይ ያዋላቸው ስታሊን ነው ። ሌላው የሶሻሊዝምን ስርአት ድክመት የነበረው የሰው ልጅ በተፈጥሮው ግላዊ (Individualistic) ሲሆን ሶሻሊዝም ያንን ግላዊ የሆነ ባህሪውን በማጥፋት ወደ ጋራ የሚቀይር በመሆኑ መጀመሪያ ላይ አማላይ ሆኖ በተቀበሉት ሀገራት ሳይቀር የኋላ የኋላ ተቀባይነትን እያጣ እንዲመጣ አስተዋፅኦ አድርጓል ።

ማርክስ የሶሻሊዝምን ሀሳብ ሲያመነጭ የምርት ሀይሎች  (Factors of Production) ያላቸው ጉልበትን፣መሬትንና ካፒታልን ሲሆን በዛን ወቅት ነበረው የማርክስም ሆነ የሌሎች የብሉይ ዘመን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች  (Classical Economists)ስራ -ፈጠራን ወይም ኢንተርፐርነርሽፕን ከፍ ያለ ግምት ውስጥ አልሰጡትም ። ይሁን እንጂ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሹምፔተር ግን የስራ ፈጠራ ጥበብን (Entrepreneurship)የምርት ሀይል አካልነት አስረግጦ ማስረዳት ችሏል ። ስለዚህ አንድ ካፒታሊስት ሀብቱን የሚያካብተው ሰራተኞቹን በዝብዞ ነው የሚለው አስተሳሰብ ነገሮችን በጣም አቅልሎና አድበስብሶ ማየት ሊሆን ይችላል ።

የሰራተኞቹን ጉልበት መጠቀሙ እንዳለ ሆኖ ፣ አብዛኛውን ሀብቱን ስራን በመፍጠር ፣ የነበረውን በማሻሻል ፣ወይንም አዲስና ያልነበረ ነገርን በመፍጠር ሊያገኝ ይችላል። ሶሻሊስቶች እንደሚሉትና በርካታ ተከታዩቹም ያምኑ እንደነበረው ከፍተኛው ዲሞክራሲ የሚሰፍነው በሶሻሊዝም ስርአት ነው ። ይህ ሀሳብ ይሁን እንጂ ሀሳባዊ (Ideal) እና ተምኔታዊ (ዩቶፒያን) ነው እንጂ በተግባር የሶሻሊዝም ተከታዮች ነን በሚሉት አገራት አልታየም ፣ ምክንያቱም ከሰው ልጅ መሰረታዊ ከሆነው ራስ ወዳድ ከሆነው ባህሪ በመነሳት ሶሻሊዝም በተለይም ማርክሲዝም ያለው የዲሞክራሲ አይነት አልታየም ። እንደውም ከሊበራል ዲሞክራሲ በባሰ ሁኔታ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተፈጠሩት አምባገነኖች ከናዚዎችና ፋሺስቶች እሚገዳደሩ አምባገነናዊ ስርአቶች በማርክሲስቶች ተፈጥረዋል ። ይኀውም የሰው ልጅ ማንኛውንም ነገር እሚያደርገው ከራሱ ባህሪ በመነሳት ነው ።

በአሜሪካን በኮምፒውተር ሳይንስና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በርካታ አዳዲስ ኩባንያዎችን ያቋቋሙትና አሜሪካን በዚህ ዘርፍ አለምን እንድትመራ ያደረጉት የግል ኢንተርፐርነሮች ወይንም ስራ ፈጠራ ጥበበኞች ናቸው  ። እንደ ጎግል፣አፕል ፣ ማይክሮሶፍት  ፣ ያሆ  ፣ ዴል እና ፌስቡክ የመሳሰሉት በዚህ መንገድ የተቋቋሙ ሲሆን እነኚህም በርካቶቹ የኮሌጅ ትምህርታቸውን አቋርጠው የወጡ ወጣቶች ሲሆኑ በቤታቸው ውስጥ ባደረጓቸው ሙከራዎችና ምርምሮች አለምን የለወጡ ግኝቶችንና ፈጠራዎችንለማግኘት ችለዋል።እነኚህ ኢንተርፐርነሮች (Enterperuners) በርካታ ሀብት ማጋበሳቸው አሌ ባይባልም ለማህበረሰቡ ፣ለሀገራቸውና ለአለም የፈጠሩትን ተጨማሪ እሴት ግን ማንም ሊክደው አይችልም ።

አንዳንዶቹ ሀብታቸውን ለበጎ አድራጎት እንዲውል ያደረጉ ሲሆን የማይክሮሶፍቱ መስራችና ባለቤት ቢል ጌትስ ከእነዚህ አንዱ ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀብት ያላቸው ሰዎች ከመንግስት ብቻ ከመጠበቅ ተላቀው ሀብታቸውንም ስራ ላይ አውለው ለሌሎች ሰዎች የስራ እድልን እንዲፈጥርና እንዲንቀሳሰቀስ ማድረጋቸው ፣ እንዲሁም ብዙ ማሰብንና ጥረትንና ፣ ጭንቀትን ተቋቁመው ስራ መስራታቸውና ሀብት መፍጠራቸው በአጭር ጊዜ ሰዎቹ ራሳቸው እሚጠቀሙ ቢመስልም ፣ ውሎ አድሮ ግን ሀገርንና ወገንን እንዲሁም መጪውን ትውልድ እሚጠቅም ነው ።

ይሁን እንጂ ኒዎ – ማርክሲስቶች ይህንን ክርክር እንደማይቀበሉት እንደማይቀበሉት የታወቀ ሲሆን ፤ የለብለብ ወይም የጥራዝ – ነጠቅ ኢኮኖሚስቶች (Vulgar Economists) ክርክር ነው ይሉታል ። እንደ እነሱ አባባል የቡርዧ ኢኮኖሚስቶች ትርፍን ትክክለኛ ወይም ፍትሀዊ ለማድረግ በርካታ ሀሳቦችን አመንጭተዋል ይላሉ እነኚህም ካፒታሊስቱ ከእለት ፍጆታው ቆጥቦ ባስቀመጠው ገንዘብ እናአደጋን ተጋፍጦ እና«ሪስክን» ወስዶ ነው እነኚህን ድርጅቶች ያቋቋመው ስለዚህ መጀመሪያ ሲያቋቁም አደጋን ስለተጋፈጠና ቢከስርም ኖሮ ከስሮ ይቀር ነበረ እንጂ እሚያገኘው ትርፍ ነገር የአልነበረም ስለዚህ ትርፉ አደጋን የተጋፈጠበት በገንዘቡ ፣ በጊዜውና በማንኛውንም ነገር ፣ የሚለውን የካፒታሊስት ኢኮኖሚስቶችን የመከራከሪያ ሀሳብ ቢያጣጥሉትም ፤ እንደ ማርክሲስቶች አባባል ግን የሶሾሊዝም ስርአት የሚመሰረተው ግን የካፒታሊዝም ስርአት በፈጠረው የሀብትና የእውቀት ክምችት ላይ መሆኑ ግን የሀብት ክምችትን (Capital Accumulation) ቅድመ – አስፈላጊነት ማርክሲስቶችም እንደሚረዱት መገመት ይቻላል ።

ይሁን አንጂ ባለሀብቶች እሚከፍሉት ግብርና ሰራተኞች እሚከፍሉት ግብር ላይ ክርክሮች አሉ ። ለምሳሌ አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ከሰራተኞች ጋር ሲነጻጸር ሀብታሞች የሚከፍሉት የግብር ምጣኔ አነስተኛ ነው ብለዋል ። ይሁን እንጂ ባለሀብቶች የሚከፍሉት ግብር (Capital Gains) ግብር ሲሆን ሰራተኞች ደግሞ የደሞዝ ገቢ ግብር ነው ። በእርግጥ ባለሀብቱ ከዚህ በላይ ክፈል ቢባል ወይም ግብር ቢጨመርበት ገንዘቡን ይዞ ወደ ሌላ አነስተኛ ግብር ወደሚከፈልበት አገር ሊሄድ ይችላል ፣ ስለዚህ ግብር ሊጨመርነት አይገባም የሚል ሀሳብ አለ ። ነገር ግን የግብር ምጣኔው ነው እንጂ በአጠቃላይ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ ሲታይ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ሰዎች የሚከፍሉት ግብር የተቀረው ከሚከፍለው የግብር መጠን የበለጠ ነው ።

በዚህ ምክንያት አለአግባብ ከፍ ያለ ግብር ባለሀብቶችንና ስራ ፈጣሪዎችን እንዲሸሽና እንደሚያሰንፍ ይታወቃል ። በነገራችን ላይ ይሄ ጉዳይ በአሜሪካን አገር ሰፊ ክርክርን የፈጠረና በምርጫ ዘመቻ ወቅት ዋነኛ ጉዳይ ሲሆን ሪፐብሊካኖች ግብር እንዳይጨመር ከተቻለም እንዲቀነስ ፣ ዲሞክራቶች ደግሞ በበኩላቸው ግብር እንዳይቀነስ ፣ ሲሆን ሲሆን እንዲጨመር ነው ክርክራቸው ። ሁለቱን ፓርቲዎች በሀገር ውስጥ ጉዳይ የሚለያያቸው ዋናው ጉዳይ ከሆነም ውሎ አድሯል ።ምጣኔ – ሀብታዊ ከሆኑ ጉዳዮችጋር ብቻ ሳይሆን ፣ የግብር መጨመርና አለመጨመር ጉዳይ ከመንግስት ወጪ እና ካለበትእዳ አንፃርም ጭምር የሚታይ ነው ። ይህም ብቻ ሳይሆን ጉዳይ ምጣኔ – ሀብታዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ጉዳዮችን ሊያካትት ይችላል ።

በካፒታሊዝም ስርአት የፖለቲካ ምጣኔ – ሀብት (Political Economy) ውስጥ ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ በካፒታል (በገንዘብ) ባለቤትነት እና በጉልበት ባለቤትነት መሀከል ማስታረቅ አለመቻል ነው ። ካርል ማርክስ በሁለቱ መሀከል ሊታረቁ ስለማይችሉና የካፒታሊዝም ስርአት በውስጡ ውስጣዊ ቅራኔዎች ተቃርኖዎች የተሞላ ነው ። ስለዚህ የዚህም ለማስታረቅ ስለማይቻል የካፒታሊዝምን ስርአት በአመፃ ማስወገድ ነው የሚል ድምዳሜን  አቅርቧል ።በነገራችን ላይ ይህ ተቃርኖ ለምሳሌ ምን ያህል ግብር ማን ይክፈል በሚባልበት ወቅት በሌላ መንገድ የሚንፀባረቅ ነው ።

ነገር ግን የሊበራል ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሀገራት የሚታይ ሌላም ችግር አለ ፣ ይኀውም የፖለቲካ መሪዎች በኮርፖሬሽኖች ተፅእኖ ስር መሆናቸውና የትላልቅ ግዙፍ ባንኮችንና የትላልቅ ኩባንያዎችን ጥቅም በዋናነት ለማስከበር መነሳሳታቸው የዚህ ስርአት ዋነኛ ችግር ነው ። የዚህን አስተሳሰብ በሚያንፀባርቁ ሰዎች እንደሚሉት የመንግስት ቁጥጥር ከላላላቸው የንግድ ኩባንያዎች እና ኮርፖሬሽኖች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው የበለጠ ትርፍንና የስራ እድልን ይፈጥራሉ የሚል ሲሆን ፣ ይህንን አስተሳሰብ በመደገፍ በተለይም የአሜሪካ የሁለቱም ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ይህን ሀሳብ በስልጣን ዘመናቸው አስፈፅመዋል ። ነገር ግን ይህ ፖሊሲ በአንደ በኩል የኑሮና የገቢ ልዩነትን በዜጎቻቸው መሀል ሲፈጥር በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ ቁጥጥር ወደ ማይደረግበት የአገራቸውንም ሆነ አለምን ኢኮኖሚ ጤንነት በቀጥታ የህዝብ ተጠያቂነት በሌለባቸውና ለራሳቸው ትርፍ በዋናነት በሚንቀሳቀሱ በግል ኩባንያዎች መዳፍ ስር እንዲወድቅ አድርጎታል ።

ጥንታዊው ታላቁ የግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ አንዳስቀመጠው ፈላስፋው ንጉስ መሆን አለበት ሲል ፣  ማህበረሰብን በሶስት ሲከፍል ፈላስፋው ንጉስ፣ ነጋዴው ፣ እና የወታደር ክፍሎች ሲሆኑ እንደሱ አባባል ነጋዴው (ካፒታሊስቱ) ለትርፍ ስግብግብ ስለሆነ ከዛ ጥቅሙ ውጪ ሌላ ነገርን ስለማያስብ በፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም የሚል አቋም ነበረው ። ወታደሩም ሀገርን መጠበቅ ነው እንጂ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም ይላል ። አርቲስቶችንም ዝቅ ያለ ቦታ የሚሰጣቸው ሲሆን ፕሌቶ ለአርቲስቶችም ቢሆን ብዙም ቦታ አይሰጣቸውም ነበረ ። ነገር ግን ፈላስፎች ግን ለአመራር ቦታ መታጨት አለባቸው ብሎ ያምን ነበረ ።

በአሁኑ አለም ባሉ የዲሞክራሲ ስርአቶች ፕሌቶ ከሚለው በእጅጉ የተለየ ሲሆን ፣ ወደ  መንግስት ስልጣን መምጣት የለባቸውም የሚላቸው ነጋዴዎች በእጅ አዙር ፖለቲካውን መዘውር  የሚቆጣጠሩ ናቸው ። ውስጥ ግን የንግድ ኮርፖሬሽኖች ፖለቲከኞችን ድጋፍ በመስጠትና መንሳት ወደ ስልጣን ማምጣት ብቻ ሳይሆን እንደ አሜሪካን አገር ባሉ ሀገራት ፣ የመገናኛ ብዙሀኖቹ ፣ ጋዜጦች ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎችም ጭምር በግል ኩባንያዎች የተያዙ በመሆኑ የነሱን ድጋፍ ያላገኘ የፖለቲካ ሰው ወደ ስልጣን ሊመጣ አይችልም ። ይህም እ.ኤ.አ. በ2012 በተደረገው በታላላቅ የምእራብ ሀገራት በተደረጉ ሰልፎች ይኀው ተንፀባርቋል ።

ሀብታሞቹ የተለያዩ ኩባንያዎችን በመቆጣጠር እርስ በእርስ የሚደጋገፉ ሲሆን ፣ የተቀረው ብዙሀኑ ህዝብ ግን ጉልበቱን ሸጦ እና ያለማቋረጥ ሁለትናሶስት ስራዎችን ሰርቶ እሚያድር እንዲሆን ፣ ገንዘቡ በጥቂት ካፒታሊስቶች እጅ መከማቸት ሰርአቱ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጥቂቶችን ብቻ ወደሚያገለግል ተቋምነት እንዲቀየርና የተቀረው ወደ ባይተዋርነት እንዲቀየር ሊያደርግ የሚችል ነው ።

በአሁኑ ወቅት በርካታ አንተርፐርነሮች ኢኮኖሚያቸው እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ እየወጡ ይገኛሉ ። ለዚህም አይነተኛ ምሳሌዋ ቻይና ስትሆን እያደገ ባለው ግዙፍ ኢኮኖሚዋ በርካታ አንተርፐርነሮች እየወጡ ይገኛሉ ። ስራ ፈጣሪዎች እያገደ ባለ ምጣኔ – ሀብት ውስጥ በቀላሉ ድልን የማግኘት እድል ሲኖራቸው ፣ እድገታቸውን በጨረሱና እድገታቸው እየተጓተተ ባሉ የምእራብ ሀገራት ግን አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች ወደ የነበረውን  ገበያ ደርሻ ነው እሚቀራመቱት ፣ ምክንያቱም ምጣኔ – ሀብቱ እያደገ ባለመሆኑ አዳዲስም ሆነ ነባር ኩባንያዎች በነበረው የገበያ ድርሻ ላይ በመወዳደር ፣ የተካረረ የገበያ ውድድር በማድረግ አንዱ አንዱን ከገበያ የማስወጣት ደረጃ የደረሰ የገበያ ውድድር ያደርጋሉ ።

ማርክስ የሰው ልጆችን በተለይም የሰራተኛውን የህብረተሰብ ክፍል በወቅቱ ከነበረው አስከፊ ብዝበዛና ከጭቆና ነፃ ለማውጣት ፣ ቀና ከሆነ አቅጣጫ የነደፈው ንድፈ – ሀሳብ ነው ። የማርክስ ሀሳብ ከዘመኑ የቀደመ ሀሳብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ፣ ለዚህም አንዱ ምክንያት እርሱ ያቀረባቸው ሀሳቦች ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ወቅት በአለም ሀገራት ላይ መታየት የጀመሩ ናቸው ፣ ለምሳሌ የካፒታል መከማቸት ፣ የስራ አጥቁጥር መጨመር የመሳሰሉት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየታየ ያለ ሲሆን የካፒታሊስት ሀገራት ማሻሻያዎችን ካላደረጉ ይበልጥ የካፒታሊዝምን ስርአት ተቀባይነትን የሚያሳጡ ጉዳዮች ይበልጥ ጎልተው እየታዩ እንደሚሄዱ ዛሬ ላይ ሆኖ መገመት ከባድ አይ ሆንም ።

እጅግ በርካታ መስዋእትነት የተከፈለ ሲሆን በሁሉም ታላላቅ አህጉራት በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካማርክሲዝም ነው ትክክለኛው ፍልስፍና ብለው ያመኑ እጅግ በርካታ ሰዎች ለተግባራዊነቱ ይህ ነው እማይባል ከባድ መስዋእትነትን ከፍለዋል ። በኮሚኒስት ወይም በማርክሲስት ስርአቶች ዲሞክራሲ ማለት ድርጅታዊ ዲሞክራሲን ይወክላል ። ከድርጅቱም በማእከላዊ ወይም ዋና ውሳኔ ሰጪ የሆን አካል ውሰጠ – ዲሞክራሲ ማለት ሲሆን ፤ ከዛም ውስጥ ደግሞ ፣ ስልጣኑ ከኮሚቴው አልፎ በቡድን ወይም በአንድ ጠንካራ መሪ ስር ይወድቃል ።

የዲሞክራሲ አተረጓጎሙም ሆነ አሰራሩ ከምእራቡ አለም የሊበራል ዲሞክራሲ አንፃር በእጅጉ የተለየ ሲያደርገው ፣ በታሪክም በተደጋጋሚ እንደታየው ፣ በቀላሉ ወደ አምባገነናዊ ወይም ቡድናዊ ፈላጭ ቆራጭ ወደ ሆነ ስርአት የመቀየር እድሉ ሰፊ ነው ። ይህም የኮሚኒዝም ስርአቶችመሰረታዊ የሆነ ውስጣዊ ድክመት ሲሆን የማርክሲስት ስርአቶች ውስጣዊ ዲሞክራሲ ስላልነበራቸው አብዛኞቹ ፈራርሰዋል ። የተራረፉትም ቢሆኑ ብዙ ማሻሻያዎችን አድርገውና ፣ በተለይም በምጣኔ – ሀብት አስተዳደሩ በኩል እንደ ቻይና ፣ ቬትናም ያሉት በርካታ የነፃ ገበያ ሀሳቦችን ወስደው ነው ። ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልገው ለዘብተኝነትና ፣ አማራጭ ፖሊሲዎችን መሞከርም ሆነ መቀበል በኮሚኒዝም ስርአት ውስጥ አይታወቁም ። ይሄም ለብዙዎቹ ስርአቶች መፈራረስ ምክንያት ሆኗል ።

ማርክስ የካፒታሊዝምን ስርአት ያለምህረት የተቸ ሰው ሲሆን ፣ የካፒታሊዝምን ስርአት ውስጠ – አሰራሩን በተመለከተ ከፍተኛ እውቀት እንዳለው እና ተመስክሮለታል ፣ ምሁራዊ ሀቀኝነቱም እንዲሁ የተመሰከረለት ነው ። ማርክሲዝም ንድፈ – ሀሳባዊ ይዘቱበአብዛኛው ትክክል ቢሆንም ድምዳሜው ግን ማለትም የካፒታሊዝም ስርአትን በአመፃ ጥሎ የወዛደሩን አምባገነናዊ ስርአት ይመሰርታል እሚለው ግን በአያሌው አወዛግቧል ፣ ይህ አስተሳሰብ ችግሮቹ አንዱ ቀዳሚውን ስርአት በአመፃ መጣል የሚለው ሲሆን ቀጥሎም የወዛደሩን አምባገነናዊ ስርአት ይተካል የሚል ነው ።

የቦስራት ንድፈ – ሀሳብ ከማልተስ ሀሳብ ተቃራኒ ቢሆንም ማርክስና ኤንግልስ ግን የማልተስን  ሀሳብ ያጣጥሉታል ። እንደውም ማርክስ የማልተስን ሀሳብ የተማሪ ስራ ነው በማለት ያጣጥለዋል ። ለማርክስ ህዝብ ብዛት ማልተስ እንዳለው በሞራል ጉድለት የሚመጣ ሳይሆን የካፒታሊዝም ስርአት የፈጠረው ነው ።

ይህም እሚሆነው የካፒታሊዝም በፈጠረው ወይም ባከማቸው ካፒታልና ፣እውቀት ላይ ሲሆን የካፒታል መከማቸትም ቀጣዩን የሶሻሊዝም ስርአትን ለመገንባት የሚያስችለውን መደላድል ይፈጥራል ። በእርግጥ እዚህ ጋ ሶሻሊዝም ስርአት የሚገነባውው የካፒታሊዝም ስርአት ባከማቸው ሀብትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ነው መባሉ ፣ በሶሻሊዝም ስርአት ፍትሀዊነት ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል ። ነገር ግን እዚህ ጋ  ማርክስ የኮሚኒዝምን ስርአት ከገነባባቸው ፅንሰ -ሀሳቦች አንዱ የዝግመተ – ለውጥ (Evolution)አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ ነው ። ስለዚህ እንደ ማርክሲስቶች አባባል ካፒታሊዝም ስርአት የፊውዳሉን ስርአት እንደተካው ፣ ፊውዳሊዝምም የባርያ አሳዳሪውን ስርአት እንደተካው ሁሉ ፣ ቀደምት ስርአተ – ማህበራትም በአዝጋሚ ለውጥ እየተተካኩ እንደመጡት ሁሉ ሶሻሊዝም የካፒታሊዝም ስርአትን ይተካዋል የሚል ነው ፤የማርክሲዝምን ስርአት አወዛጋቢና ስር ነቀል (Radical) ከሚያደርጉት ጉዳዮችም አንዱ ይሄ ነው ።

በእርግጥ ቀደም ያሉት በረጅም ጊዜ አዝጋሚ – ለውጥ ከባርያ አሳዳሪው ወደ ፊውዳሊዝም ፤ ሲሸጋገር ቀስ በቀስ በብዙ አስርት እና መቶ አመታት አዝጋሚ ለውጥ ነው እንጂ ማርክሲስቶች እንደሚሉት ቅፅበታዊ ወይም ግብታዊ በሆነ አብዮት አይደለም ። ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ስርአትም የተሸጋገረው የምርት ዋነኛ የምርት ግብአት ማለትም መሬት መሆኑ ቀርቶ ኢንዱስትሪ እየሆነ ሲመጣ ባለኢንዱስትሪዎች ፣ ባለገንዘቦችና የባንክ ባለቤቶች ከመሬት ከበርቴው ወይም ከባላባቱ የበለጠ የኢኮኖሚ ውሎ አድሮም የፖለቲካ ሚዛን እየደፉ ስለመጡ በርካታ አመታትን በፈጀ አዝጋሚ – ለውጥ ወደ ቡርዧ ወይም ወደ ከበርቴ ስርአት ተሸጋግሯል ።

በነገራችን ላይ የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና የስነ – ህይወት ተመራማሪዎች ደርሰውበት ነገር ግን ሶሻሊስቶች በዛን ወቅት ሰራተኞች የካፒታሊዝምን ስርአት አፍረስው ኮሚኒዝምን ይገነባሉ ተብሎ ይታመን ስለነበረ ዝግመተ – ለውጥን ይፋ ለማድረግመጀመሪያ ላይ ራሱ ቻርልስ ዳርዊንም ሆነ ሌሎቹ የእንግሊዝ የገዢው መደብ አባላት ግኝቱ ይፋ እንዲሆን አልፈለጉም ነበረ ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ማርክስ ሶሻሊዝም ካፒታሊዝምን ይተካዋል ያለው ፤ ካፒታሊዝም ካደገ በኋላ በሶሻሊዝም ስርአት ይተካል ማለቱ ነው ። ስለዚህ ለሶሻሊዝም ስርአት መፈጠር ያደገ የካፒታሊዝም ስርአት ቅድመ -ሁኔታ ነው ማለቱ ነው ። ይህ ማለት ያደገ የካፒታሊዝም ስርአት ያላቸው እንደ ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ ለመሳሰሉት አገሮች ነው ። ይሁን እንጂ ማርክሲዝም ተግባራዊ የተደረገባቸው እንደ ሩስያ ፣ ቻይና የመሳሰሉት ሀገሮች ግን ማርክሲዝም ስራ ላይ ሲውልባቸው የፊውዳል ስርአት ያላቸው ሀገራት ነበሩ እንጂ በኢንዱስትሪ የበለፀጉና ብዛት ያለው የፋብሪካ ሰራተኛ ያላቸው አልነበሩም ። ይህን ችግር የተረዳው ሌኒንም የሩስያን የቦልሺቪክን አብዮት ሲመራ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ፍልስፍናን በመፍጠር አብዮታዊ በሆነ ሁኔታ የካፒታሊዝም ስርአት ባይዳብርም ከፊውዳሊዝም ወደ ሶሻሊዝም  ይደረግባቸዋል ያላቸውን ሀሳቦችን አፍልቋል ፤ ይህም በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረትና በመጀመሪያ አካባቢ ቻይናና በሌሎች አገራት ተግባራዊ ተደርጓል ።

ምንም እንኳን ሶሻሊዝም በንድፈ – ሀሳብ ደረጃ ከካፒታሊዝም ስርአት በበለጠ ማራኪ ሆኖቢቀርብም ፣ በተግባር ሲታይ ከካፒታሊዝም በበለጠ በተግባር ለማዋል አስቸጋሪና ውስብስብ ስርአት ነው ። በተለይም ዲሞክራሲን የማስተናገድ አቅሙ ከካለፒታሊዝም ስርአት በእጅጉን ያነሰ ነው ።

ይህም ማርክስ የሽረት ሽረት ህግ በማለት ገለፀው ሲሆን ፣ አንድን ስርአተ – ማህበር የሻረና የተካ እሱም በተራው በሌላ ስርአት  ይሻራል ወይም ይተካል እንደማለት ነው  ። ይህ ህግ ማቆሚያና መጨረሻ በሌላው ሁኔታ የሚሰራ ሲሆን አዲሱ አሮጌውን እየተካና እየሻረ ይቀጥላል። አንድ መንግስት ስልጣን ላይ በቆየ ቁጥር የሚፈጥራቸው የፖሊሲ ስህተቶችም ይሁን በሌላ ምክንያት ቅራኔዎች ይፈጠሩና ህጋዊ ተቀባዩነቱን ከእለት ወደ እለት እየሸረሸሩት ይመጡና  የሚፈጠሩት ቅራኔዎች ለሚቀጥለው ስርአት ምቹ መደላድልን መፍጠር  ይጀምራሉ ። ይህም ለበርካታ አምባገነኖች መፈጠር ሰበብ ሆኗል ። ወታደራዊ አምባገነኖች ሳይቀሩ በአለም ዙሪያ መንግስት ገልብጠው የኮሚኒስት ስርአትን መስርተናል እያሉ አምባገነናዊ ስርአቶች ተፈጥረው ቆይተዋል ። ነገር ግን ይህ ወደ ተግባር ሲመነዘር የመጣ ነው እንጂ ከንድፈ – ሀሳቡ እሚመነጭ አይደለም ። ነገር ግን ማርክስ ወዛደራዊ አምባገነንነት የሚለው ትክክለኛ ንቃትና ብቃት ያለው አመራር ብቻ ነው በአምባገነንነት ሊንቀሳቀስ የሚችለው እንጂ ወታደራዊ መሪዎችም በሶሻሊዝም ስም መንግስትን ገልብጠው አምባገነኖች ቢሆኑ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ። ማርክስ ግን መሪው ሙሉ ብቃት አለው ከሚል ግንዛቤ በመነሳት ነው ሰራተኛው አምባገነነት መምራት አለበት የሚለው ። ይህም አስተሳሰቡ ከሄግል መሪውን መንፈስ ይመራዋል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ሄግልም ቢሆን ይህንን ሀሳብ ሲያቀርብ መሪው ሙሉ ግንዛቤ አለው ፣ ለመምራት አስፈላጊው ክህሎትና ችሎታ አለው ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው እንጂ እንደው ዝም ብሎ መሪ ስለሆነ ብቻ አምባገነን መሆን ይችላል ማለቱ አልነበረም ። ይሁን እንጂ ሶሻሊዝም ራሳቸው ተከታዮቹ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱትና እንዲተረጎሙት ካደረጉት  አደናጋሪ የሶሻሊዝም ፅንሰ – ሀሴቦች ይኀው የሰራተኛው አምባገነንነት የሚለው ነው ።

ሶሻሊስቶች ማርክስን ሄግልን ሀሳባዊ «idealist»  ነው በማለት ያጣጣሉት ሲሆን ፣  ምንም እንኳን ማርክስ የሄግልን ዲያሌክትቲክ የአመክንዮ ትንተናን ቢወስድም በቁስ አካላዊ ፍልስፍና ለሚያምነው ማርክስ የሄግልን ሀሳባዊነት ውድቅ እንዳደረገው የታወቀ ነው ። የማርክስ ሀሳቦች ግን የካፒታሊዝምን ስርአት ማሻሻያዎችን ለማድረግ ረድተዋል ። ለምሳሌ የካፒታሊዝም ስርአት ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥርም እንደሚፈጥር ማርክስ ተገንዝቦታል ፤ ምክንያቱም አሰሪዎች ልክ እስከሚፈልጉት ድረስ ብቻ ሲሆን ሰራተኞችን የሚቀጥሩት ከዛም በላይ ወጪን ለመቀነስ በቴክኖሎጂና በማሽኖች ሰራተኞችን ቁጥር ቀዝቅ ሊያደርግ እንደሚችሉም ግልፅ ነው ። ማህበራዊ ዋስትና ስርአት የተጀመረው የማርክስን ትችቶች መሰረት በማድረግ ሲሆን ፣ ቀደም ባለው ጊዜያት ሰራተኞች ስራ ካጡ ወይን ከስራ ከተቀነሱ ምንም ገቢ እማይኖራቸው ሲሆን በዚህም ምክንያት በርካታ የሰራተኞች አመፅንና ይፈጥር ነበረ ። ሌላው ደግሞ የሰራተኞች የመደራጀት መብትም እንዲሁ ቀደም ባለው ጊዜያት የማይፈቀድ የነበረ ሲሆን ውሎ አድሮ ግን ሰራተኞች ተደራጅተው መብታቸውን ማስከበራቸው ያለውን ጥቅም በመረዳት በብዙ የአለም ሀገራት መደራጀት የተፈቀደ ሆኗል ። በዚህም ሰራተኞች መደራጀት መቻላቸው እና ህጉን ተከትለው መብታቸውን ማስከበራቸው፣ ችግሮች ውስጥ ውስጡን የማይብላሉ ከመሆኑም በላይ ሰራተኞች አለአግባብ መብታቸውን እንዳይነካ ስለሚያደርግ መኖሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ።

በአውሮፓም በርካታ የሶሻሊስት ፓርቲዎች ሲኖሩ በምርጫ የሚወዳደሩና ባለው ስርአት ውስጥ እሚንቀሳቀሱ ናቸው ። የአሜሪካኖችን ስርአት ስናይ ግን ሙሉ ለሙሉ በንፁህ የፈጠጠ የካፒታሊዝም ስርአት መሆኑ ግልፅ ነው ። የአውሮፓውያን ስርአት ለዘብ ያለ እና ሶሻሊዝምን በተወሰነ ደረጃ እሚያስተናግድ ሲሆን ፣ እንደ ጀርመን ፈረንሳይ ባሉት በብዙ የአውሮፓ ሀገራትም ሶሻል ዲሞክራቶች አሉ  የአሜሪካኖቹ ግን የፈጠጠ የካፒታሊስት ስርአት ነው ተብሎ ይተቻል ። የሰሜን አውሮፓ ሀገራት የማህበራዊ ደህንነት ዋስትና ያላቸው ሲሆኑ (Welfare States) በመባልም ይታወቃሉ ።

ይሁን እንጂ ይህ ፍልስፍና በርካታ ደጋፊዎች በተለይም በወጣት ተማሪዎችና ምሁራን ዘንድእ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ በአለም ዙሪያ የጋለ ድጋፍን ቢያገኝም ወደ ተግባር ሲመጣ ግን በቀላሉ በስልጣን ጥመኞች ሊጠለፍና ሊቀለበስ የሚችል በመሆኑ ምክንያትና ለመሪዎቹ ግላዊ ጥቅም ሲባል አብዛኛውን አቅጣጫውን በመሳት ፣ በብዙ ሀገራት ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነትና አስከፊ የሆኑ አምባገነናዊ ስርአቶች እንዲፈጠሩ ስላስቻለ ደጋፊዎቹ እየተመናመኑ ሄዱ ፣ በውጪ ከመጣበት ጫና ይልቅ በራሱ ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት በበርካታ ሀገራት ሊፈረካከስ በቅቷል ። በአሁኑ ወቅትም ንድፈ- ሀሳባዊ ክርክሮች በትምህርት ተቋማት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በተግባር እንደ ቀድሞው በአለም ላይ በተግባር የሚለውልበት እድል እየጠበበ ሄዷል ።

በ2011 የወጡ ጥናቶች እንደጠቆሙት የአለምን 90 በመቶ ሀብት የሚቆጣጠሩት 10 በመቶ የሚሆኑት የአለማችን ሀብታሞች ከ20 አመታት በፊት የነበራቸው ሀብት ፤ አሁን ካላቸው ሀብት ጋር ሲነፃፀር በ500 ፐርሰንት ጨምሮ ሲገኝ ፤ በአንፃሩ ከአለማችን ሀብት 10 በመቶ ብቻ የሚሆነውን የሚጠቀሙት 90 በመቶ የሚሆኑት የአለማችን ህዝቦች ያላቸው ሀብት ከ20 አመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር አሁን ያላቸው ሀብት በአያሌው ቀንሶ ተገኝቷል ። ይህም በአለማችን ያለው የሀብት ክፍፍሉና ፤ ሰፋ ባለ ሁኔታ እየተዛባ እንደሄደናየመካከለኛው መደብ የህብረሰብ ክፍል በቁጥርም ሆነ በኑሮ ደርጃው እየተዳከመ እንደሄደ ሲያሳይ የደሀው የህብረተሰብ ክፍል ግን ወደ ባሰ ድህነት ሊወርድ እንደሚችል መገመት ይቻላል ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s