ሀብትን መፍጠር

ሀብትን መፍጠር የሚችለው የሰው ልጅ ብቻ ነው ። የማሰብ ችሎታ ያለው ብቸኛው ፍጡር የሰው ልጅ እንደመሆኑ በማሰብ ችሎታው ሀብትን ይፈጥራል ። እንሰሳትን ብንወስድ ደመ – ነፍሳዊ በሆነ መንገድ ምግባቸውን ለችግር ጊዜ ያከማቻሉ ፣ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ያዘጋጃሉ ፣ ወይም መርጣሉ ። ለምሳሌ ንቦች ፣ ጉንዳኖችና ሌሎችም ነፍሳት ለችግር ጊዜ ምግብን ቢያከማቹና ታታሪ ሰራተኞች ቢሆኑም ስራቸው ግን እንደ ሰው ልጅ አውቀውና ተረድተው እሚሰሩት ሳይሆን ፍፁም ደመ – ነፍሳዊ ነው።

በአንፃሩ የሰው ልጅ በደግ ጊዜ ያመረተውን በጎተራ አከማችቶ ፣ የሚመገበውን አዘጋጅቶ ፣ የሚኖርበትን ቤት ሰርቶ ይኖራል ። ከዚያም አልፎ የስራ ክፍፍልን በመፍጠር ሁሉም የሰው ልጅ በአንድ ዘርፍ ተሰማራ እንዳይሆን በማድረጉና በየራሱ ሙያ የላቀን ችሎታ በመፍጠሩ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ምርታማ እንዲሆን አድርጓል ። የስራ ክፍፍል ባይኖር ኖሮ የዚህን ያክል ምርታማነትና ሀብት አይፈጠርም ነበረ ።አዳም ስሚዝ ይህንን የስራ ክፍፍል በመረዳት ለምጣኔ ሀብት የትምህርት ዘርፍ አንዱ መሰረታዊ እሳቤ ለመሆን በቅቷል ።

ሀብትን መፍጠር ለአንድ ማህበረሰብ የተደላደለ ህይወት እንዲኖርና የማህበረሰቡ ህይወት እንደዲቀጥል አስፈላጊ ነው ። ይሁን እንጂ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሀብትን መፍጠር የሚችሉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ የተቀረው የህብረተሰቡ ክፍል ከነሱ ጋር አብሮ በመስራት ኑሮው የተደላደለ ያደርጋል ።ባደጉት ሀገሮች ሳይቀር ሀብትን መፍጠር የሚችሉት ዜጎች ቁጥር ብዙ አይደለም ። ብዙዎቹም ስራ ፈጣሪዎች ኢንተርፐርነሮች ሲሆኑ የተቀሩትም ሳይንቲስቶች ፣ አርቲስቶች ፣ባለሀብቶች ፣ የፖለቲካ መሪቀዎች ፣አንዲሁም አንዳንድ የላቀ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ናቸዉ።

አዳም ስሚዝ የሀገሮች ሀብት በተሰኘው ምጣኔ – ሀብት እንደሙያ መስክ መወለድ አስተዋፅኦን አድርጓል ተብሎ በሚታመነው ፈር – ቀዳጅ መፅሀፉ ይህንን የሀገሮችን ሀብት ምንነትና ምንጭ በመረዳት መተንተን በመቻሉ የምጣኔ ሀብት የትምህርት ዘርፍ ተወለደ ።አንዳንዶች የአዳም ስሚዝን መፅሀፍ የካፒታሊዝም መፅሀፍ ቅዱስ በማለት ይገልፁታል ። በአብዛኛው የፈረንሳይ ፈላስፋዎችን መሰረት በማድረግ መፅሀፉን እንደፃፈው ይታመናል ። ምጣኔ – ሀብትን ፈጠሩ እሚባሉት ፈረንሳውያን ፈላስፋዎች ሲሆኑ በተደራጀና ደርዝ ባለው መልክ ግን ያቀረበው አዳም ስሚዝ ነው ። አዳም ስሚዝ የእንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰቦች አስተማሪ ስለነበረ ከንጉሳውያኑ ጋራ በአውሮፓ በተለይም ጉብኝቶችን ያደርግ በመሆኑ ከአውሮፓ ፈላስፎች ጋር የመወያየትና በርካታ ሀሳቦችን የመለዋወጥ እድል ነበረው ።ይሁን እንጂ በርካቹን ዋናዎቹን ቀደምት ሀሳብ አፍላቂዎችን ባለመጥቀሱ በጥቂቱም ቢሆን መወቀሱ አልቀረም ።

ከሱ ቀደም የምጣኔ ሀብት አንደ የስነ – ምግባር (ethics) የትምህርት ዘርፍ አካል ተደርጎ ይቆጠር ነበረ ።ማንኛውም የማህበረሰብ እሴት በግለሰቦች አስተዋፅኦ (contribution) እየዳበረ የሚሄድ ነገር ነው ።  

       ሀብት በሁለት መንገዶች ይፈጠራል ። አንዱ ምርታማነትን በመጨመር ሲሆን ሌላው ደግሞ አንዲት ሀገር ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመሸጥ ወይም በማከራየት ነው ። ምርታማነትን ለመጨመር አንዲት ሀገር አዳዲስ ቴክኖሎጂን በመፍጠር ፣ በስራ ፈጠራን (Enterperunrship) አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችንና አሰራሮችንበማስፋፋት ፣ ዘመናዊ ማሽኖችንና ፋብሪካዎችን በመትከል ሲሆን የተፈጥሮ ሀብቷን ነዳጇን በመሸጥ ወይም መሬቷን በማከራየት ልክ የአፍሪካ ሀገራት እንዳደረጉት ወይም ያላቸውን ነዳጅም ይሁን ወርቅ አልማዝ ፣ ለገበያ በማቅረብና በመሸጥሊሆን ይችላል ። እንደ አንዳንዶች ግምት አሁን ታዳጊ ሀገራት እያገኙ ያሉት ፈጣን የምጣኔ – ሀብት እድገት የተፈጥሮ አካባቢ ላይ በደረሰ ጉዳት አማካይነት የመጣ እንዳይሆን ስጋት ያላቸው አሉ ።

ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ሀብትን ስለመፍጠር መንግስትና ህዝብ አስተዳደር በተሰኘ መፅሀፋቸው እንዲህ ይላሉ ፣ ሀብት ማለት የተከማቸ ስራ ነው ፣ ይላሉ ያ ማለት አንድ ሰው ብዙ እውቀት ባለቤት በሆነ ቁጥር በርካታ ስራን ማከማቸት ይችላል ስለዚህ በቀላሉ ሀብትን መፍጠር ይችላል ። ለምሳሌ አንድ በጃፓን ውንም በጀርመን ያለ ፋብሪካ በሰአታት ውስጥ በርካታ ሀብትን መፍጠር ይችላል ። ወይንም አንድ ሀኪም በአንድ ሰአት ውስጥ የሚያገኘው አንድ የቀን ሰራተኛ በቀን ውስጥ ተቀጥሮ ከሚያገኘው ይበልጣል ምክንያቱም ሀኪሙ በአመታት ውስጥ በርካታ እውቀትን ስለሰበሰበ በአጭር ጊዜ ውስት ያንን እውቀቱን ወደ ተከማቸ ስራ ማለትም ወደ ሀብት መቀየር ይችላል ማለት ነው ።

የተከማቸ ስራ የሚፈጠረው ከተከማቸ እውቀትና የአካላዊ ስራና እንቅስቃሴ ሲሆን ፣ የዴቪድ ሪካርዶ ፍቺ ጋራ ተመሳሳይ ነው ። እሴት ማለት በእሴት ውስጥ ያለ ጉልበት ነው የሚል ፍቺ ነው ። እዚህ ጋ ምንድነው ጊዜን እማንጨምረው ቢባል ጊዜ ደሞዝን ወይም ምንዳን ወይም ኪራይን ለማስላት ነው የሚጠቅመው ። በእርግጥ አንድን እሴት ለመፍጠር ጊዜ የሚያስፈልግ መሆኑ ይታወቃል ፤ የጊዜ ስሌት ደግሞ ምንዳን ወይም ደሞዝን ለማስላት ነው የሚጠቅመው ።

የተፈጥሮ ሀብቶችን ብንወስድ ምንም እንኳን ውድ ማእድናት ነዳጅም ይሁን ወርቅ ወይም አልማዝ እነዚህን ማእድናት መጀመሪያ ለመፈለግ ፣ ለማግኘት ብሎም ለማውጣት ስራ መስራትን ይጠይቃል ። ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብትም ቢሆን እሴቱ ወይም ዋጋው እሚተመነው በወጣበት ጉልበትና እውቀት ልክ ነው ። ለምሳሌ አልማዝን ወይም ወርቅን ለማግኘት በጣም አድካሚ ሲሆን ከአፈርና ድንጋይ አላቆ ፈልፍሎ ለማውጣትም እንደዛው ብዙ ድካምን ይጠይቃል ስለዚህ ዋጋው በጣም ውድ ይሆናል ።

ስለዚህ ማንኛውም የሰው ልጅ ሀብት እሚለው ነገር የተፈጠረው በጉልበት እና በእውቀት ነው ። ለምሳሌ በመሬት ላይ ያደገ ዛፍን እንኳን ብንወስድ ለመትከልና ለማሳደግ ጉልበት ሲያስፈልግ በራሱ በተፈጥሮ ያደገ ነው ብንል እንኳን ለመቁረጥ ጉልበት ያስፈልጋል ፣ እሚተካ ዛፍ ካልተተከለበት ደግሞ የነበረውን ወሰድነው እንጂ አዲስ ሀብትን አልፈጠርንም ፣ ወደ ፊት ሌላ እንጨትን አይሰጥም ።

ሀብት የሚፈጠረው ከጉልበት ነው እሚመነጨው ። ይህን ዴቪድ ሪካርዶ የጠቀሰው ሲሆን ፤ ካርል ማርክስም የጉልበት እሴት ንድፈ – ሀሳብ ከሪካርዶ አስተሳሰበች የተቃኙ መሆናቸው ይታወቃል ። በነገራችን ላይ ካርል ማርክስ የኮሚኒዝምን ንድፈ- ሀሳብ የገነባው ዴቪድ ሪካርዶ ባስቀመጠው መሰረተው ጉልበት የእሴት ዋጋ ንድፈ – ሀሳብ በላይ በመመስረት ነው ። በምጣኔ – ሀብት ውስጥ የጉልበት ዋጋ እሴቱም ሆነ አንድምታው በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው ። 

አሁን ካለው የቀደሙትን የሰው ልጆች አኗኗራቸውን ብናይ በብዙ መልኩ ከአሁኑ ያነሰ ሲሆን ፣ የነበራቸው ሳይንሳዊ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ መጓጓዣ፣ ወዘተ ከአሁኑ በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ምክንያት የሀብት ደረጃቸውም ከአሁኑ አነስተኛ ሆኖ ኖሯል።

በሀገርም ደረጃ ተመሳሳይ ነው ። ብዙ እውቀትንና ክህሎትን የሰበሰበ ሀገር ፣ ከፍተኛ ሀብትን ያገኛል ። ከመላው አሉ የተባሉ በአሜሪካን ሀገር መሰባሰባቸው ለአሜሪካ ትልቅ እሴትንና ሀብት ን ፈጥሯል ። ለምሳሌ አሜሪካንን ብንወስድ ሆሊወድንና ብንወስድ ከፍተኛ እውቀትና ሙያ ባላቸው ሰዎች የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሲሆን ፣ በካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኘው ፣ ሲልከን ቫሊ በመባል የሚታወቀው የኮምፒውተር ፣ የመገናኛና የሞባይል ቴክኖሎጂን እሚያንቀሳቅስ ኩባንያዎች እሚገኙት በዚሁ አካባቢ ሲሆን አሜሪካ ባላት በተከማቸ እውቀቷ በመጠቀም ከአለም ግዙፍ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን መመስረት ችላለች ፣ ምንም እንኳን ትችት ቢቀርብባቸውም የፋይናንስ ተቋማቷም እንዲሁ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚያደርጉ ናቸው ። ይህም ብቻ ሳይሆን በታላላቅ ኩባንያዎቿ አማካይነት ባላት የባለቤትነት መብት ለምሳሌ እንደ ኮካ ኮላ ፣ ፔፕሲ እና በሌሎችም ከፍተኛ ሀብትን ያገኛሉ ያንቀሳቅሳሉ ።

በአለም ደረጃም ስናየው አሁን ያለው የአለም ህዝብ ሀብት እያደገና እየተመነደገ ይሄዳል ። ቀድሞ የሰው ልጅ ከነበረበት የሀብት ደረጃ ሲታይ ፣ አነስተኛ ሀብት የነበረው ምክንያቱ ዋናው በዛን ዘመን የነበረውም እውቀት አነስተኛ ስለሆነ የሀብት ደረጃም አነስተኛ ነበረ ። ከዚህ በኋላም የሚመጡት ትውልዶች ከፍተኛ የእውቀት ደረጃ ላይ ስለሚደርሱ ፣ የሚያፈሩት ሀብትም እንደዛው እያደገ ይሄዳል ። የእውቀት ደረጃቸው እየጨመረ ስለሚሄድ የኑሮ ፣ የጤና ፣ በአጠቃላይ አኗኗራቸው ሁሉ አሁን ካለው የላቀ እየሆነ ይሄዳል ።

ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2050 አለማችን ምን ትመስላለች ፣ ወይም ምን አይነት ልትመስል ትችላለች ተብሎ ሲታሰብ ለምሳሌ የአሜሪካን ምጣኔ – ሀብት አሁን ካለበት 15.5 ትሪሊየን ዶላር አካባቢው አመታዊ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) ወደ 27 ትሪሊየን ሲደርስ ፣ የቻይና የህንድም ምጣኔ – ሀብትም እንደዛው ከፍ ይላል ። በአጠቃላይ የአለም ምጣኔ – ሀብት ከእጥፍ በላይ እንደሚያድግም ይጠበቃል ። ይሁን እንጂ በአካባቢ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን ግን ከወዲሁመገመት አያስቸግርም ።   

የተፈጥሮ ሀብት መሟጠጥንም እንደዛው እየተባባሰ የሚሄድ ሲሆን ለምሳሌ ነዳጅን ብንወስድ የአለም የነዳጅ ዘይት ሀብት መሟጠጡና ብሎም ማለቁ አይቀርም ፣ ነዳጅንም ፍለጋ በጣም ሩቅ የሆኑና የሰው ልጅ በቀላሉ የማይደርስባቸው አካባቢዎች ጭምር የፍለጋ ማእከል ሲሆኑ ፣ በሰሜንና በደቡብ ዋልታዎች ያሉ አካባቢዎች እንዲሁም የውቅያኖስ ወለሎችም ነዳጅንም ሆነ ሌሎች ማእድናትን ፍለጋ የሚታሰሱ ይሆናሉ ። የነዳጅ ዘይት በስፋት ስራ ላይ መዋል የጀመረው ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ሲሆን ፣ ከዚያ በፊት የኢንዱስትሪው አብዮት ሲጀመር የድንጋይ ከሰል፣ የእንፋሎት የሀይል ሳይቀር ምንጭ ሆኖ አገልግሏል ። ስለዚህ ነዳጅ ዘይትም ሆነ ድንጋይ ከሰል ቢያልቅ ሌላ የሀይል አማራጭ መፈለጉ አይቀርም ። ይህም ከአሁኑ ታዳሽ የሆኑትን የፀሀይ ብርሀንን ፣ የንፋስ ሀይልን ፣ የባህር ማእበል ሞገድ ግፊትን በመጠቀም ሀይል ማመንጨት የተጀመረ ሲሆን ፤ ወንዞችንም ለሀይል ማመንጪያነት ስራ መዋላቸው ይታወቃል ። ከዚህም ሌላ የኒውክሊየር ሀይል ምንም እንኳን አካባቢ ላይ አደጋን ሊፈጥር ቢችልም፣ ማመንጫ ራሱ ለኤሌክትሪክ ማመንጪያነት በበርካታ ሀገሮች ስራ ላይ እንደዋለም ይተወቃል።

ይሁን እንጂ ነዳጅ ከአለማችን ላይ ቢጠፋ የአለም ምጣኔ – ሀብት አይቆምም ፣ ከዛ ይልቅ በሌላ ቴክኖሎጂ መተካቱ የማይቀር ሲሆን ፣እንደውም በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትም ሊቀንሰው ይችላል ተብሎ ይገመታል ፣ በመጪዎቹ ክፍለ ዘመን በአለም ላይ ያለው የነዳጅ ዘይት በሙሉ ተሟጦ ያልቃል ተብሎ በሳይንቲስቶች ይገመታል። አሁን እንኳን ነዳጅን በኤሌክትሪክ መኪኖች የመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ፣ ታዳሽ የሀይል ምንጮችንም ለማሳደግ ሀገራት ተግተው እየሰሩ ነው ። ያም ብቻ ሳይሆን ወደፊት ከነዳጅ ዘይት ይልቅ የተፈጥሮ ጋዝ የበለጠ ተፈላጊ እንደሚሆን ይገመታል ፣ ዋጋው ርካሽ ከመሆኑና ፣ አካባቢን እንደ ነዳጅ  ዘይት የማይበክል እንደመሆኑ ከድንጋይ ከሰልም ሆነ ከነዳጅ ዘይት ተፈላጊ እንደሚሆን ይጠበቃል ።

የወደፊቱ ትውልዶች በእውቀታቸውም ሆነ በሀብታቸው ከፍተኛ ደረጃላይ ስለሚደርሱ ምናልባትም በጨረቃ ላይ ከተማ ሊሰሩና ፣ ኑሯቸውን በጨረቃ ወይም በሌላ ፕላኔት ላይ ሊያደርጉ ይችላሉ ። እነኚህ ሁሉ የሚሆኑት የተከማቸ እውቀት ስለሚጨምር ፣የአለም ሀብትም ቴክኖሎጂም ከፍ ከዛ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ይወዳደራል ።

ሌላው ደግሞ ከመንግስታት ይልቅ ግለሰቦች ሀብት በመፍጠር የተሻለ ብቃትና ስሉጥነት (Efficiency) ያላቸው ሲሆኑ ፣ መንግስታትም ሀብትን የሚፈጥሩ ቢሆንም አዳዲስ ፈጠራን በመፍጠርና አዲስ መንገድን በመቀየስ ግለሰቦች የበለጠ አቅምና ብቃት አላቸው ። መንግስት ይበልጥ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያተኩር ፣ ህግና ስርአትን ማስፈንና የተደላደለ የውድድር ሜዳን ማዘጋጀት ነው ። ለምሳሌ ሀብትን መፍጠር ምጣኔ – ሀብትንና ሳይንስን ፣ ቴክኖሎጂን ፣ አስተዳደርን ሲመለከት ፣ ያንን የተፈጠረውን ሀብትን ማከፋፈል ግን ፖለቲካ ነው።

ስለሀብት መፈጠር ካነሳን ስለ ሀብት ክፍፍልም ማንሳት በተገቢ ይሆናል ። የአፍሪካ ሀገራት ምጣኔ – ሀብታቸው ቢያድግም በሀብት ክፍፍሉ በኩል ግን ይቀራቸዋል ። በእርግጥ ገና እያደገ ባለ ምጣኔ – ሀብት በቂ ሀብት ሳይፈጠር ስለ ሀብት ክፍፍል ማውራት ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ማስቀደም ሊሆን ይችላል ። ጥቅሉ ምጣኔ – ሀብት (Macroeconomy) በውጪ ባለሀብቶች ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎት እያደገ ሲሄድ እያደገ ይሄዳል ። ነገር ግን ከአንድ አማካይ የኑሮ ደረጃ ባለው ዜጋ ቦታ ላይ ሆነን ስናየው የአንድ ሀገር ምጣኔ – ሀብት በዚህ መቶኛ በአመት አደገ ሲባል ለሱ ምን ትርጉምን ነው እሚሰጠው ? የዛ እድገትስ ወደሱ ኑሮ እንዴት ነው ሊመነዘር የሚችለው ?እነኚህ በፖለቲካ መሪዎች ተስማሚ በሆነ መንገድ ሊደረጉ የሚችሉ ናቸው ።

በደሀ ሀገራትም የሀብት ክፍፍል ማድረግ አብንገብጋቢ ጉዳይ ሊሆን ይችላል ። ይህም ሊሆን የሚችለው ያቺ ሀገር ያላት የተፈጥሮ ሀብት ወይም መሬት በጥቂቶች እጅ ውስጥ ከገባና የተቀረው ህዝብ መፈናነፈኛ ካጣ የሀብት ክፍፍል ማድረግ ግድ የሚልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ።በሀገራችን በ1966 ዓ.ም. የተካሄደው አብዮት ዋነኛው ምክንያት ሰፊው መሬት በጥቂት የመሬት ከበርቴዎች እጅ መውደቁና ብዙሀኑ ህዝብ ጭሰኛ የሆነበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነበረ ። በወቅቱ በሀገራችን ላይየተዛባ የሀብት ክፍፍል እንደነበረ መገመት ይቻላል ። ዋና የሀብት ምንጭ የሆነው መሬት በጥቂቶች መያዙ ለተዛባ የሀብት ክፍፍል መንስኤ የነበረ ሲሆን ፣ ወደፊትም ይኀው የመሬት ጉዳይ ለሀብት መዛባት መነሾ ሊሆን ይችላል ።

አንድ እማይካድ ነገር በአለም ዙሪያ በግርድፉ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሀብት ከ10 በመቶ ባልበለጡ ሰዎች እጅ ነው እሚገኘው ። ይህም የሀብት ክፍፍል በአሁኑ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ባለበት ዘመን በተለይም እየሰፋ ነው የመጣው ። ስራ – ፈጣሪዎች ሊያገኙ የሚችሉት ሀብት አንድ ሰራተኛ ከሚያገኘው እጅግ የበዛ ነው ። ዋናው ነገር ግን ለማንም ክፍት የሆነና ማንም ሰው ችሎታውና ትጋቱ እስካለው ድረስ ያለ ሌላ አድልኦ ማለትም በዘሩ ፣ በፆታው ፣ በመሳሰሉት መድልኦ ሳይደረግበት ማደግ የሚችልበትን ፍትሀዊ ስርአት መዘርጋቱን ማረጋገጥ ነው ፣ ሀብትን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ በማከፋፈል ዘላቂ መፍትሄን ማምጣቱ አጠራጣሪ ነው ።

የፖለቲካ ስርአታቸው በማይፈቅድባቸው ሀገራት ውስጥ ፣ ግብርን በመጠቀም ቋሚ የሆነ ሰፊ መሰረት ያለውን የሀብት ክፍፍልን ማድረግ አይቻልም ፤ በአንፃሩ በአንዳንድ ሀገራት ለምሳሌ በስካንድኔቪያ ሀገራት ከፍ ያለ ግብርን በመጣል ተቀራራቢ የኑሮ ደረጃን መፍጠር ችለዋል ። በአንፃሩ በአሜሪካን አገር አንደኛው ፓርቲ ግብር ይጨመር ሲል አንደኛው ይቀነስ ስለሚል አንዱ የጨመረውን ግብር ሌላው ሲመጣ ይሽረዋል ።በዚህ ምክንያት የመካከለኛውና የደሀው ህብረተሰብ ክፍል ገቢ መንግስትም ቢሆን በግብር ያን ያህል ሊያቀራርበው  አይችልም ። ከልክ በላይ ግብርን ልጨመር ቢል ባለሀብቶቹም ግብር ወደ ማይከፈልበት ፣ ግብር አነስተኛ ወደ ሆነበት አካባቢ ስለሚሄዱ፣ እና ሀብታቸውን ስለሚያሸሹ ይህንን ስለሚፈራ ነው ። ስለዚህ ነገሩ በጣም ውስብስብና የፖለቲካ መግባባት እና ስምምነት የሌለበት እንደሆነ መገመት ይቻላል ።

ፖለቲከኞች ተሰብስበው ምን ያህል የግብር ምጣኔ መጣል እንዳለበት ፣ ማን ምን ያህል መክፈል እንዳለበት የሚወስኑት እነሱው ሲሆኑ እንደሚመሩበት ፍልስፍናና ርእዮተ – አለም የተለያየ አቋም ሊኖራቸው ይችላሉ።ባደጉትና በበፀጉት ሀገራት የግብር ጭማሬና ቅናሽ ጉዳይ ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ሲሆን ፣ በፓርቲዎቹም መሀከል ጉልህ ልዩነት እሚንፀባረቅበት ነው ። በእነሱ ምጣኔ – ሀብት 1በመቶ እንኳን ግብር ቢጨምር ወይም ቢቀንስ በምጣኔ – ሀብቱ ከላይ ጉልህ ተፅእኖ ይኖረዋል ። ገና ታዳጊ በሆነ  ሀገር ግን እዛ ደረጃ አልተደረሰም ።

ሌላው ደግሞ አንድ ማህበረሰብ ሀብቱ በጥቂቶች እጅ ተጠቃሎ ሲገባ ፣ እንዲሁም መሀከለኛው መደብ ማህበረተሰብ እየደኀየና ፣ ወቶ ወርዶ ተወዳድሮ አዲስ ሀብትን መፍጠር እያቃተው ሲሄድ፣ የዛ ህብረተሰብ ልሂቃኑ ተጨማሪ ሀብትን ከመፍጠር ይልቅ ያለውን ሀብት ላይ ግመታናአየር ባየር ስራ (Speculation) እንዲሁም በኪራይ ሰብሳቢነት (Rent Seeking) ውስጥ በመሰማራት ፣ ከአዲስ ሀብት ፈጠራ ይልቅ ስለሀብት ክፍፍል ትኩረትን ማድረግ ይጀምራል ። ይሄ አሁን በምእራቡ አለም በመታየት ላይ ያለ ክስተት ሲሆን ፣ በአንፃሩ በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉት (Emerging Markets) በሚባሉት ደግሞ ፈጣን የሆነ የአዲስ ሀብት ፈጠራ ስራ እየተከናወነ ነው ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s