የህይወት ትርጉም

በአጠቃላይ ፍልስፍና በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሊታይ ይችላል ። አንደኛው ለህይወት ትርጉምን እሚሰጠው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለህይወት ምንም አይነት ትርጓሜን እማይሰጥና ፣ ማንኛውም ነገር ዞሮ ዞሮ ጥቅም የለውም አያስፈልግም የሚል አይነት ነው ። ነገር ግን ገኖና ተቀባይነትን አግኝቶ የወጣው የፍልስፍና ዘርፍ ለህይወት ትርጓሜን የሚሰጠው ነው ።

አንድ ሰው ለምንድነው እምትኖረው ወይንም ህይወትህ ግብ ወይም አላማ ምንድነው ተብሎ ቢጠየቅ የተለያየ ሰው የተለያየ ምላሽን ሊሰጥ ይችላል ። የሆነ የህይወት ግብ ወይም አላማ ያላቸው ሰዎች የተሻለ ደስተኛ ህይወትን መምራት ሲችሉ የህይወት ግብ የሌላቸውና የኔ የሚሉት አላማ የሌላቸው ሰዎች ግን በአንፃሩ ደስተኝነት የራቀውን ህይወት መግፋት ግዴታቸው ነው ።

በነገራችን ላይ ጊዜ ማንኛውንም ነገር እንደሚያጠፋና እንደሚሽር የምስራቅ ፈላስፋዎች ብቻ ሳይሆን ከጥንት ግሪካውያን ጊዜ ጀምሮ የነበሩት ምእራባውያን ፈላስፎችም ጭምር ጠንቅቀው የተረዱት ነገር ነው ። ዳቬንቺ ይጠቀሳል ፣ ጊዜ የሁሉም ነገሮች እኩይ አጥፊ ነው (time is the evil destroyer of everything) ። ዳቬንቺ ይህን ያለበት ምክንያት ሲኖረው ጊዜ በጥሩ ሁኔታ የተሰሩና የተሳኩና የተደላደሉ ለነገሮችን ሁሉ እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል ከሚል ግንዛቤ በመነሳት ነው ። ባሀኢም እንደሚለው የህይወት ትርጉም በሞት ይጠናቀቃል ይላል ።

ይህም ይሁን እንጂ ጊዜ አጥፊ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችንም ያመጣል ። አዲስ የመጡት ነገሮች ጥሩም ፣ መጥፎም ሊሆኑ ይችላሉ ። አሮጌው ይፈርሳል ፣ አዲስ ይፈጠራል ፣ የታመመ ይድናል ፣ የቆሰለው ይሽራል ። የተሻለ ነገር ሊፈጠር ይችላል ወይም የባሰ ነገር ሊመጣ ይችላል ። ሀያሉ ይደክማል ፣ የደከመው ይነሳሳል ።

ለምሳሌ ከጥንት ግሪካውያን ፈላስፎች አሪስቶትል የህይወት ትርጉሟ መደሰት ወይንም ደስታ ነው ሲል ፣ ለኒቼ ደግሚ የህይወት ትርጉም ስልጣን መደሰት ነው ብሏል ። ሌላው የስነ- ልቦና ሊቅ ደግሞ በበኩሉ የመኖር አላማው የህይወትን ትርጉምን ማግኘት ነው  ።

ህይወት ማመጣጠንን የምትፈልግ ነገር ስትሆን አንደ ሰው አንድ ነገርን ብቻ ለማድረግ ወይንም አንድ ነገርን ብቻ ለመሆን የሚኖር ከሆነ በሌላው የህይወት ዘርፎች ብዙ ነገሮች ያመልጡታል። ለምሳሌ ስራውን ብቻ የሚያተኩር ከሆነ ጓደኛ ለመያዝ ፣ ቤተሰብ ለመመስረት ወይንም ለመማር ትርፍ ጊዜ ሊኖረው አይችልም የሚያመልጠውም ነገር እርሱ ትልቅ ነው ብሎ ከያዘው ነገር የበለጠ ሊሆን ይችላል ። በአሁኑ በዚህ ዘመናዊ አለም ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ በማመጣጠን መኖር  ሲያቅታቸው ይስተዋላል ።

ህይወት እንኳን በአመታት ቀርቶ በቀንና ሌሊት እድሜ ሳይቀር የራሷ ትርጉም ሊኖራት ይችላል ። ለምሳሌ አንድ ሰው ቁርሱን ካልበላ ሌሊትም እረፍቱን በእንቅልፍ ካላሳለፈ ፣ቀኑን ንቁ ሆኖ መዋልና ስራውን መስራት ወይም መንቀሳቀስ አይችልም ፣ ስለዚህ እንኳን በአመታት ውስጥ የምትቆጠረዋን የአንድ ሰውን ህይወት ትተን በቀን ውስጥ ያሉ ነገሮች እንኳን አስፈላጊ መሆናቸውን እንረዳለን ።

አንድ ሰው ህይወት ትርጉም የላትም ብሎ ካሰበ በተዘዋዋሪ መንገድ ህይወት አትጣፍጥምም ፣ አትመርምም ማለት ነው ። አትጣፍጥም ብሎ ስለሚያስብ ፣ ህይወቱን ጣፋጭ ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩ  እድሎችን ሳይጠቀም ይቀራል ፣ ስለዚህ ለመራራው የህይወት ጎን ራሱን እያዘጋጀ ይሄዳል ፣ መራራ የሆነው የህይወት ክፍል ብቻ ነው እሚደርሰው ።

የህይወት ትርጉም ግልፅ ያለ አንድ አይነት ትርጉም የለውም ። ለምሳሌ አንድ ሰው በሆነ ነገር ታዋቂ መሆንን ከፈለገ ወይም በሆነ ነገር ስኬታማ ለመሆን ከተነሳ ያ ለሱ የህይወትን ትርጉም የሚሰጠው ነገር ነው ፤እንጂ የህይወት ትርጉም አንድ አይነት አለም አቀፋዊ (Universal) የሆነ ትርጉም የለውም ። ሀይማኖቶችን ብንወስድ ሀይማኖት በራሱ ለህይወት ትርጉምን የሚሰጥ ነገር ነው ።

የህይወት ትርጉም በማህበረሰብ ደረጃም አለ ፤ አንድ ሀገር ራሱን በኢኮኖሚ ማሳደግና ገናና ማድረግ ከሆነም ወይንም ጠፈርን ለመርገጥም ከሆነ ያ ነገር ለህይወቱ አላማን ወይንም ትርጉምን ይሰጠዋል ። የህይወት ትርጉም ማለት አንድ ሰው በዚህች ምድር የሚኖርለት ነገር ወይንም አላማ ማለት ነው ። ያ አላማ ትልቅ ነገር ሊሆን ይችላል ወይንም ተራና ቀላል ነገር ሊሆን ይችላል ለምሳሌ ቤተሰባዊ ነገር ሊሆን ይችላል እንደ ልጆቹን ማሳደግ፣ ቤተሰቡን መምራትም ሊሆን ይችላል እነኚህ ሁሉ ለአንድ ሰው የመኖር ትርጉምን የሚሠጡ ነገሮች ናቸው ። በነገራችን ላይ ምእራባውያን ብዙ ነገርን የፈጠሩትና አሁንም ለመፍጠር ቀንና ሌሎት የሚዳክሩት ለህይወታቸው ትርጉም ለመስጠት ነው ።

ብዙውን ግዜ ብኩን ወይም ከንቱ የሆነ ኑሮን የሚመሩ በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ ይኖራሉ ። ያ ማህበረሰብም በርካታ ዜጎቹ ብኩን ህይወትን በመሩ ቁጥርም የዛ ሀገር ህዝብ የእድገትና የኑሮ ደረጃ የወረደ ይሆናል። ስለ ህይወት የምንሰጠው ትርጉም የህይወታችንን አቅጣጫ ይወስናል ።ይሄም አውዳሚነት ወይም ከንቱነትን የያዘ የአኗኗር ዘይቤ ሲሆን ለምሳሌ አንድ ሰው ስራ አይጠቅምም ብሎ ስራውን ቢተው ቀሪውን ህይወቱን ሲማቅቅ ይኖራል ፣ ሌላ ገቢ እሚያገኝበት አማራጭ እስከሌለው ድረስና ፣ ከለቀቀ በኋላ ምን እንደሚሰራ አስቦ ካለቀቀ በስተቀረ ድረስ ስቅን መቅመሱ አይቀሬ ነው ። በሌላም በኩል አንድ ወጣት ተማሪ ትምህርት እይጠቅምም ብሎ ትምህርቱን ቢተው ፣ ቀሪውን ዘመኑን ማግኘት ያለበትንእውቅት አግኝቶ በጥሩ በተሻለ ሁኔታ የመኖር ተስፋውን ያጨልማል ። ስለዚህ በአጠቃላይ ማንኛውም ነገር ወይም ህይወት ራሷ ትርጉም የላትም ብሎ ማሰብ ወደ ገደል እሚጨምር አስተሳሰብ ነው ።

ወደ ሀገርኛው አባባል ስንመልሰው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለች በቅሎ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው ። ይሄ ነገር የግብፁ ፈርኦን በቀን በሺ የሚቆጠሩ በቅሎዎች ፣ በጎችና ፍየሎች የሚቀርቡለት የነበረ ቢሆንም እኔ ከእኔ በኋላ ግን ግብፅን የአባይ ውሀ ይብላት ይል እንደነበረ ይነገራል ።

ስራን ብንውሰድ አንድ ሰው ከስራ ሲባረር ወይንም ሲቀነስ ለምንድነው ሞራሉ የሚወድቀውና በአንድ ጊዜ ቅስሙ የሚሰበረው ብንል የሚኖርለትን ነገር በማጣቱ ወይንም ያ የለመደው ነገር ስለተወሰደበት  ነው ።

በሌሎች ሰዎች ላይ ከልክ ያለፈ የስሜት ጥገኝነትን (Emotional Dependence) መፍጠር እነዛን ሰዎች በምናጣበት ወቅት ህይወታችን እንዲመሰቃቀልና ሰማዩ የመደፋት ስሜት እንዲፈጠርብን ያደርጋል ። በጣም የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ፣ ወይም ወደ ሌላ ሀገር ሲሄድ ፣ ወይንም ስንለያይ በጠብ ወይንም በሌላ ነገር የዛን አይነት ስሜትን ይፈጥራል። ስለዚህ ቀድሞ ወደ ነበረን ስብእናና ማንነት ለመመለስ የተወሰነ ጊዜን ሊወስድብን ይችላል ።የለመድነውን በምናጣበት ወቅት በውስጣችን የሚፈጠረው የስሜት መሳቀቅና መረበሽ ቀላል አይደለም ።

ህይወትን በረጅም ጊዜ ስናስበው ትርጉም የላትም ማለት ይቻላል ። ነገር ግን ይሄ እውነት የሚሆነው በረጅም ጊዜ ስናስበው ነው እንጂ በአጭር ጊዜ ህይወት የራሷ ትርጉም ፣ ጣእም ፣  መርሪርነትና ማንኛውም ሊሰማን የሚችል ስሜት ሁሉ አላት ። በረጅም ጊዜ ስናየው ማን ትክክል ፣ ማን ስህተት መሆኑ ራሱ ልዩነትን አያመጣም ለምሳሌ ጠቢቡ ሰለሞን እጅግ የላቀ እውቀት የነበረው ፣ እጅግ የበዛ ወርቅ ፣ እንቁ ፣ በአይነቱም ሀበት የነበረው ንጉስ የነበረ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ እቁባቶችና ሚስቶች የነበሩት ፣ የላቀ እውቀት የነበረው ንጉስ ነበረ ። ነገር ግን እርሱም የደረሰበት «ሁሉም ነገር ከንቱ ፣ የከንቱ ከንቱ ነው» የሚል ድምዳሜ ላይ ነበረ የደረሰው ።

ለአንድ ሰውህይወት ፍፁም ስትሆን ፣ አንድ ሰው ሁሉንም ነገር ቢያውቅ ፣ ህይወት ምንም ጣእምና ትርጉም ላይኖራት ይችላል ። ህይወት ፍፁም አለመሆኗ ፣ አንድ ሰው በብዙ መልኩ ህይወትን ለማስተካከል በሚያደርገው ጥረት ህይወት ጣእም እንዲኖራት ያደርጋል ። ነገር ግን ሁሉም ነገር ለአንድ ሰው ቢሟላለት ህይወት አሰልቺ ትሆንበታለች ። ለምሳሌ በቀድሞው ዘመን የነበሩ ነገስታት ብዙውን ጊዜ በድብርትና በመሰላቸት ይሰቃያሉ ፤ እነኚህ ነገስታት የሚፈልጉት ሁሉም ነገር የተሟላላቸው ሲሆኑ ፣ የነገሮች መሟላት ምንም አይነት ደስታን ሳያጎናፅፋቸው ከአንዱ ደስታ ወደ ሌላው በመሰላቸት ሲቀያይሩ ይኖራሉ ። 

ይሁን እንጂ ህይወት ትርጉም የላትም ብሎ ማሰብ እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት ፣ ወይንም ሌሎችን ገድለው ራሳቸውን የሚያጠፉትባዶነት ሲሰማቸውና የመኖር ትርጉም ሲያጡ ነው ፣ ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳት ነው ። አንዳንድ ሰዎች የነበራቸውን ነገር ሲያጡ ህይወት ባዶ ትሆንባቸዋለች ። ከዚያ በኋላ የመኖር ትርጉሙን ያጡታል ።

ህይወት ትርጉም የላትም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ማንም ሊያደርገው የማይደፍረውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ ስለማይሉ ቀስ በቀስ ከማህበረሱ እየተገለሉና እየራቁ ይሄዳሉ ። የማህበረሰቡን ተቀብሎት የኖረውን ነገር ይህ ነው የሚባል ትርጉም በሌለው ሁኔታ ስለሚጥሱና የተሻለ ነገርንም ስለማያቀርቡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በህብረተሱ እየራቁ ይሄዳሉ ።

ሌላው ደግሞ የተሸናፊነት ስሜት ሲሰማን ትክክል ያልሆኑ ነገሮች ሲደረጉ ዝም ብሎ የማለፍ ፣ እና ቸል የማለት ስሜት ይፈጥርብናል ። ህይወት ትርጉም የላትም የሚለው አስተሳሰብ ከተንበርካኪነት ስሜት ሊመነጭ ይችላል ። አንድ የማንፈልገውን ወይም ደስ እማይለን ነገር ሲደረግ ማስቆም ሲያቅተን የተሸናፊነት ስሜት ይሰማናል ። ስለዚህ ዋጋ ወይም እሴት ያላቸው ነገሮች ሲጣሱ ወይንም ሲረገጡ የማስቆም ወኔውም ሀይሉም አይኖረንም ።

ጀርመናዊውን ፈላስፋ ኒቼን ማንኛውም ነገር ትርጉም የለውም ብሎ ማሰብ «ንሂሊዝም» አስተሳሰብ መስራች አድርገው ይወስዱታል ። ይሁን እንጂ የንሂሊዝምን አደጋ ካዩና ከተረዱ ሰዎች አንዱ ነው ። ከምእራባውያን ፈላስፎች ኒቼም ሆነ ኪርኪጋርድ ህይወት ትርጉም የላትም የሚለው አስተሳሰብ አደገኛ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

ህይወት ምንም ትርጉም የላትም ብሎ ማሰብ ወደ ንሂሊዝም የሚያመራ መሆን የለበትም ። ንሂሊዝም ከተሸናፊነትና ከተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚመነጭ ነገር ስለሆነ ነው አንድ ሰው የዚህን አይነት ስሜት ለውስጡ ለማስወገድ መጣር አለበት ። ለንሂሊስቶች ነገን እማያውቁ በመሆናቸው ፣ አንድ ነገር ሲፈጠርም ጀምሮ ቦታን አይሰጡትም ።  በተለይም ባልሰለጠኑ ማህበረሰቦች ዘንድ ይሄ አስተሳሰብ በጣም የተንሰራፋ ነው ፣ ነገ ትርጉም የለውም ብለውም ስለሚያሰቡ አንድነገር ውሎ አድሮ ሊያደርስ እሚችለው ጥቅምንም ሆነ ጉዳት አይለዩትም ። በሀገራችን አባባል እኔ ከሞትኩ ሰርዶ እብቀል አለች በቅሎ እንደሚባለው ነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን ለነገ ውሎ አድሮ ጥቅም እሚሰጥ ነገርን ሲሰሩ ወይም ሲወጥኑ አይታዩም ፣ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ደግሞ ሀይማኖታቸውን በጣም በማጥበቅ ብቻ ያልሰለጠኑ ማህበረሶች ሀይማኖታቸውን በጣም ስለሚያጠብቁ በአለም ላይ ላለው ችግር ሁሉ መፍትሄውን እነሱ ብቻ የጨበጡ ይመስላቸዋል።

ለንሂሊስቶች ነገ የሚባል ነገር የሌለ ሲሆን ሁሉም ነገር ዛሬ ተጀምረ ዛሬ የሚያበቃና ነገ የሚባል ቀን የማይመጣ ይመስላቸዋል ፤ በዚህም ቀላል እማይባሉ ጥፋቶችን፣ ወይም ስህተቶችን ለመፈፀም ይዳረጋሉ ። ሌላው ደግሞ የዚህ ባህሪ መገለጫ ደግሞ ከንቱነት ነው ። ይህም ዋሾነት ፣ ስርቆት፣ አላማ የለሽነት ፣ ጠጪነት ፣ብኩንነት እና የመሳሰሉት እነኚህ ሁሉ የንሂሊዝም መገለጫዎች ናቸው ።

ንሂሊስቶች የአንድ ነገርን የነገን ጥቅም መረዳት አይችሉም ። አንድ ነገር ውሎ አድሮ ሊሰጥ የሚችለውን ነገር ለመረዳት ያስቸግራቸዋል ። ስለዚህ በረጅም ጊዜ እሚጠቅም ነገርን ለማድረግ አይችሉም ።

ሌላው ደግሞ ህይወት ትርጉም የላትም ብሎ እሚያስብ ሰው ሌሎች ሰዎች በጥረታቸው የፈጠሩትን ነገር ለማጥፋትና ለማበላሸት አይጨነቅም ። ያ ነገር ለራሱ ትርጉምን ስለማይሰጠው ለሌሎች ሰዎች ስራም ሆነ ኑሮ ደንታ አይኖረውም ። ለምሳሌ በቀላሉ ለመግለፅ አንድ ዛፍ ዛሬ ቢተከል ዛሬውኑ ፍሬን አይሰጥም ለማደግና ፍሬ ለማፍራት አምስት አመታት ሊፈጅበት ይችላል። ነገር ግን አንድ የነገሮችን ትርጉም ለሚረዳ ሰው ዛሬ የሚተከለው ውሎ አድሮ ፍሬን የሚያሰጥና የሚጠቅም መሆኑን ይገባዋል ። ነገር ግን ምንም ነገር ትርጉም የለውም ብሎ እሚያስብ ሰው ግን ቢተከል ምን ይጠቅማል ሊል ይችላል ። ዛሬ የሚተከለው ውሎ አድሮ ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም አይረዳም ወይም መረዳት አይችልም ።

ህይወት ትርጉም የማይኖራት በጣም በረጅም ጊዜ ካሰብነው ነው እንጂ በአጭር ጊዜ ህይወት ትርጉምም ፣ ጣእምም ፣ መሪርነትም ሁሉም ነገር አላት ። ለምሳሌ ከአንድ ሺ አመት በፊት የአንድ አገር መሪ እከሌ ሆነ ፣እከሌ ነበረ ቢባል አሁን ላለው ትውልድ ምንም ለውጥን አያመጣም ፣ ወይም ከአንድ ሺ አመት በኋላ ምናልባት ስርወ – መንግስቱ ነው እንጂ የአንድ ሀገር መሪ ማን ይሁን ማ አሁን ላለው ትውልድ ትርጉም የለውም ። ስለዚህ በረጅም ጊዜ ከታሰበ ዛሬ የሆነ ነገር ሊረሳ ወይም ያ ነገር ጨርሶ እንደተፈጠረም ወይም እንደተደረገ ማንም አያስታውሰውም ።

የአለምን ካርታ ከአንድ ሺ ወይንም ከአምስት መቶ አመታት በፊት የነበረውን ብናይ ከአሁኑ ጋር ጨርሶ የማይገጥም ሆኖ እናገኘዋለን ። ይሁን ኦንጂ አንዳንድ እኛ ሰዎች ስንባል አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ዘላቂና ዘላለማዊ መስሎ ሊታየን ይችላል ። ይሁን ጊዜው ትንሽ ራቅ ሊል ቢችልም ነገሮች እነኛ ከምናስባቸውንም ሆነ ልናስብ ከምንችለው በላይ ሊለዋወጡ እንደሚችሉ መገመት አያዳግተንም ።

በነገራችን ላይ ምእራባውያን ይሄን ሁሉ ሳይንስ የፈጠሩትን ይሄን ሁሉ ቁሳዊ ሀብት ለኑሮ መደላድል የሆነ የፈጠሩት ለህይወት ትርጉም ለማስገኘት በነበራቸው ያልተቋረጠ ጥረት ሲሆን በአንፃሩ በሀይማኖትና በመንፈሳዊነት የተሞሉ ሀገራት ግን የምእራባውያንን ያህል ቁሳዊም ሆነ ሳይንሳዊ እድገት ላይ አልደረሱም ። የምእራባውያን ይበልጥ ምድራዊ ስኬትን ሲያጎናፅፋቸው መንፈሳዊ የሆኑ ሀገራት ደግሞ ድህነትንና መንፈሳዊነትን ለዘመናት ወርሰው ኖረዋል ።

ፍልስፍና በሁለት ፅንፎች የተጋለጠ ሲሆን ፣ በአንድ በኩል ለህይወት ትርጉም ለመስጠት ጥረት የሚያደርገው ሲሆን በሌላ በኩል ያለው ደግሞ ለህይወት ምንም አይነት ትርጉምን የማይሰጡ ናቸው ። ትርጉም ወዳላቸው ነገሮች ብናደላ  ለእነኛ ነገሮች ከራሳችን የበለጠ ትርጉምን ልንሰጣቸው ስለምንችል ፣ በሌላ በኩል ህይወት ትርጉም የለውም ብንል ደግሞ ወደ ከንቱነትና ወደ ግራ ወደ ተጋባ ሁኔታ ይመራናል  ። ኒቼ ምንም እንኳን ህይወት ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርገውን የክርስትና ሀይማኖትን ቢተችም ፣ በአንፃሩ ግን የሱ ፍልስፍና ወደ ህይወት ትርጉም የላትም ወደ ሚለው ድምዳሜ ያመራል ። ስለዚህ መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄ ተደርጎ የሚወሰደውን ጥያቄ ፈቶታል ወይም አጥጋቢ መልስ ሰቶታል ለማለት አይቻልም ። ይሄም የፍልስፍና ልዩነት እንዴት ወደ አኗኗርና እድገት ልዩነትን እንደሚያስከትል የሚያሳይ ነገር ነው ።

ሳይንስ እንደሚነግረን የዚህ አፅናፈ – አለም እድሜ በቢሊዮኖች የሚገመት ነው ። የሰው ልጅ በአንድ ወቅት ያለና ፍጡር ሲሆን ። ለምሳሌ ፀሀይን ብንወስድ ልክ ማታ የአምፖል ብርሀንን እንደምናበራው ፀሀይም ልክ እንደዛ የአምፖል ብርሀን በዚህ ምድር ላይ ላለ ማንኛውም ነገር የህይወት ምንጭ ነች ።ቀደምቱ ሰው ይህንን እውነታ በመረዳት የሚያመልከው በፀሀይ ሲሆን የፀሀይ አምልኮ ስርአት ነበረው ።

በዚህ ምድር ላይ መንቀሳቀሻ ሀይል ወይንም ጉልበት ምንጩ ከፀሀይ ሲሆን ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች እንደሚነግሩን ፀሀይም ብትሆን ዘላለማዊ አይደለችም ። በእርግጥ ያ ጊዜ በጣም ቅርብ ሳይሆን ከቢሊዮኖች አመታት በኋላ ነው ። እውነታው ግን ፀሀይም ሆነች በእርሷ ዙሪያ ያለው  ስረአተ – ፀሀይ ስርአት መጨረሻ ላይ እድሜውን ሲጨርስ ሊበታትን እንደሚችል የተደረሰበት ነገር ነው ። ከዚህም በመነሳት የሰው ልጅ የወደፊት እጣ ፈንታው ያለው በዚህ ምድር ላይ ሳይሆን በጠፈር ላይ ነው ማለት ይቻላል ። ለዚህምከሰው ልጅ በስተቀርም በዚህ አፅናፈ – አለም ም ሆነ በስርአ ተ – ፀሀይ ውስጥ ሌላ ምንም አይነት ህይወት አልተገኘም ። ሳይንቲስቶች ድምፅን መስማት የሚችሉ መሳሪያዎችን በመግጠም ፣ ከዚህ ምድር ውጪ ህይወት እንዳለ ፍተሻ ቢያደርጉም ከመሬት ውጪ ከሌላ ጠፈር የመጡ ፍጡራንን ድምፅ መስማት አልቻሉም ። ይህም እስካሁን ባለው የሰው ልጅ ቴክኖሎጂ ከመሬት ውጩ ሌላ ምንም አይነት ህይወት እንደሌለ ማረጋገጫ ነው ።

በ2012 ዓ.ም. የአሜሪካን ሳይንቲስቶች ማርስ ላይ የላኩት መሳሪያ ማርስ ላይ በተሳካ ሁኔታ ማረፍ መቻሉ ትልቅ የሳይንስ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል ፣ ይህም ምናልባት ከመሬት ውጪ ሌላ ህይወት አለ ወይስ የለም የሚለውን ጉዳይም ለማወቅ መረጃን ይሰጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ። ይ ህም ብቻም ሳይሆን ምንም እንኳን ለሰው ልጅ ተስማሚ የሆች ፕላኔት ባትሆንም በማርስ ወለል በታች ግንባታዎችን በማካሄድ የሰው ልጅ ሊሰፍር የሚችልበት እድልም ሊኖር ይችላል ተብሎም ተስፋ ተጥ ሎበታል ።  

ለህይወት ትርጉም እንዲኖራት ያደረጉ ታላላቅ ፀሀፍት ፣ ፈላስፋዎች ፣ ደራሲዎች ፣የጥበብ ሰዎች፣ የፖለቲካ ሰዎች በህዝብ ተወዳጅነትን የሚያገኙበት ሚስጥር ትርጉም የሌለውን ነገር ትርጉም እንዲኖረው በማድረጋቸው ነው ። በአጠቃላይ ስናየው ግን ህይወት ትርጉም ከማይኖራት ይልቅ ትርጉም ቢኖራት የተሻለ ሲሆን ፣ ለምሳሌ ሀይማኖት ያላቸው ከሌላቸው ፣ ቤተሰብ ያላቸው ወይም እሚኖሩበት አላማ ያላቸው ፣አላማ ከሌላቸውና ሀይማኖት ከሌላቸው የተሻለ ረጅም ጊዜን የመኖር እድሜ ይኖራቸዋል ፣ ይህ በሳይንሳዊ ግኝቶች የተረጋገተ ሀቅ ነው  ።

ብዙዎቹ የአለማችን ታላላቅ ሰዎች ችሎታቸውንና ክህሎታቸውን እንኳን ለሚቀጥሉት ከአብራካቸው ለወለዷቸው ልጆቻቸው እንኳን ማውረስ አይችሉም ።

ብዙ ጊዜ ያልተለመደ አፈጣጠር ፣ አስተዳደግ ፣ ትምህርትና ከህይወት ልምድ የሚገኝ ሲሆን ይሄም በአንድ ሰው ውስጥ ተሟልተው የመገኘት እድላቸው እምብዛም ነው ። ስለዚህ አንድ  ሰው ያፈራውን ሀብት ፣ ንብረት ፣ እንዲሁም ማንኛውም ቁሳዊ ነገር ለልጆቹ ሊያወርስ ቢችልም እንኳን እና ልጆቹ ቢወርሱም በተጀመረው አቅምና ጉልበት መቀጠላቸው አጠራጣሪ ሲሆን ያ የተጀመረ ነገርም በጊዜ ሂደት መረሳትና ማን እንደፈጠረው እንኳን የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ሁሉ ይደርሳል ።

ስለዚህ ቁሳዊ ከሆነ ነገር ይልቅ ረጅም እድሜ ሊኖረው የሚችል ነገር ሀሳብ ወይንም እውቀት ሲሆን እሱም ቢሆን በጣም በረጅም ጊዜ ሊረሳ ፣ ከሱ የተሻ በሆነ በሌላ ሊተካ ፣ ወይም የተሳሳተ ወይንም ኋላ ቀር ሊባል ሁሉ ተብሎ ሊጣል ይችላል ። አሁን የምናደንቃቸው አዋቂዎች ሰዎች በሙሉ ከተወሰኑ ሺ አመታት በኋላ ሊረሱ ወይንም በሌሎች ከነሱ በበለጡ ሰዎች መዋጣቸውና መዘንጋታቸው አይቀርም ።

ይሄ ሁሉ የህይወት ትርጉምን የሚያሳጣው ነገር ጊዜ መሆኑን ለማሳየት የቀረቡ ምሳሌዎች ሲሆኑ ጊዜ በምድር ላይ ትልቅ ዋጋ የምንሰጠውን ማንኛውንም ነገር እንደሚያፈራርስና እንደሚያስረሳ የሚገልፅነው ።

አንዳንድ ሰዎች በህይወታቸው ማድረግ ፣ መሆን ፣ መስራት የሚፈልጉትን አድርገው የህይወታቸው ፍፃሜ ቢደርስ ብዙም ላይቆጩ ይችላሉ ። ነገር ግን ማድረግ የሚፈልጉትን ሳያደርጉ ፣ መሆን የሚፈልጉትን ሳያደርጉ እድሜአቸው ፍፃሜ መቃረቡን ሲረዱ የሀዘን እና የፀፀት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል ። እውነተኛው ሰው መሆን ራስን መፈለግና ራስን ማግኘት ነው ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s