ታሪካዊ ጉዟችንና ዳራዎቻችን

በአብዮቱ መባቻ ወቅት ፣ ለሶስት ሺ ዘመናት ኢትዮጲያን የገዛው የዘውድ አገዛዝ ህጋዊ ተቀባይነቱን «ሌጂቲሜሲ» ውን እያጣ በመጣበት ወቅት የሀገሪቱን አመራር ተረክቦ የሚቀጥል ሀይል አልነበረም ። በዚህም ምክንያት ከወታደሩ በስተቀረ የተደራጀ  ሀይል ባልነበረበት ሁኔታ ከየክፍሉ የተውጣጡ የጦሩ አባላት በቀላሉ ወደ ስልጣን ሊመጡ በቅተዋል። የደርግ መንግስት በኮሚቴነት ከተለያዩ የጦር ክፍሎች ተመርጠው በመጡ የደርግ አባላት ሲቋቋም ከዚያ በኋላ በስልጣን ሲቀጥሉ ፣ ተቃውሞ ሲገጥማቸው ደርግ ያካሄደው የቀይ ሽብር ተቃውሞውን አላጠፋውም ፣ ከዚያ ይልቅ በከተማ መታገል የሚያስኬድ አለመሆኑን የተረዱት ወጣቶች ከቀይ ሽብር በኋላ ደርግ አስር አመት የቆየ ሲሆንበትግል የደርግን መንግስት ጥለውታል ። የደርግ ቀይ ሽብር ለጊዜው ድልን ቢሰጠውም ውሎ አድሮ ግን የትግል ስልቱን የቀየረ ፈተና ነው የገጠመው።ያም ብቻ ሳይሆን በታሪክ ውስጥ ያለውንም ቦታ አጥልቶበታል።

ደርግ ህጋዊ የሆነ የህዝብ ተቀባይነትና ይሁንታ (Legitimacy) ችግር የገጠመው ገና ሲጀመር ጀምሮ ነው ። በአንድ በኩል ወታደር በመሆኑ ሀገርን የመምራት ህጋዊ ውክልና ከህዝብ ያላገኘ መሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሀገሪቱን የሚመራበት ፍልስፍና ፣ ርእዮተ – አለምም (Ideology) ሆነ ዝግጅት አልነበረውም ። ለዚህም አማራጭ አድርጎ የወሰደው አብዮቱን የቀሰቀሱትና የመሩትን ተማሪዎችንና ምሁራንን ፍልስፍናና የፖለቲካ አስተሳሰብን በሀይል መንጠቅ ነበረ ። በዚህም ሀገሪቱ ያፈራቻቸውናን አሉ የተባሉትን ወጣቶችንና ምሁራንን ያለምህረት መፈጀትና እልቂት ነበረ።

ይህ ብቻም ሳይሆን በምሁራኑ መሀከል ከአብዮቱ በኋላ ሀገሪቱ በምን አቅጣጫ መመራት እንዳለባት መግባባትና ስምምነት አለመኖሩ ፤ ሁሉም የየራሳቸውን የፓርቲ የበላይነት ለማስፈን መነሳታቸው በቀላሉ ለመከፋፈልና ለውድቀት ዳርጓል ። ይህም ከባድ መዘዝን ይዞ የመጣ ሲሆን በአንድ በኩል በራሳቸው  በተረፉት በምሁራኑና መሀከል የፖለቲካ መስረመርን ልዩነትን ሲፈጥር አንዳንዶቹ ሀገር ጥለው ሲወጡ የተቀሩት ደግሞ ወደ ትጥቅ ትግል ተሰማሩ ። የደርግም የስልጣን እድሜ ብዙም ሳይቆይ እንዲቋጭ ሆኗል ።

ህዝባዊ ይሁንታን ለማግኘት ከዚያ በኋላ መጀመሪያ ኢሰፓአኮን ከዚያም ኢሰፓን ብሎም የኢህዲሪ ህገ – መንግስትን አርቅቆ ስራ ላይ ቢያውልም እና የኢሰፓን መንግስት ቢመሰርትም እነኚህ ሁሉ ሲጀመር ጀምሮ ምንም አይነት ህዝባዊ ውክልና የሌለውን መንግስት ህዝባዊ ውክልና ሊያስገኙለት አልቻሉም።የህዝባዊ ተቀባይነትና ውክልና አለመኖር የደርግ ስርአት ችግር ሆነው እስከመጨረሻው የስልጣን ዘመኑ ድረስ ዘልቀዋል ።

ዘመነ መሳፍንት መኳንንቶችና መሳፍንቶች ከንጉሰ ነገስቱ በላይ ስልጣንና ሀይል ባለቤት የሆኑበት ዘመን ነው ። በነገራችን ላይ ይህ ታሪክ በፊውዳላዊት አውሮፓም የተከሰተ ሲሆን የነገስታት መዳከም የመሳፍንትንና የመኳንንትን ሀይል ማደግንና ከንጉሰ ነገስት የበለጠ ሀይል ስለሚኖራቸው ከቻሉ የንጉሰ ነገስቱን ዘውድ ለመውሰድ ፣ ካልቻሉም  ሰፊ ግዛትንና ሀይልን ለመፍጠር የእርስ በእርስ ጦርነትን ያስነሳሉ ። ለምሳሌ በፈረንሳይ ሀገር ፎንዴ በመባል የሚታወቀውን ሁከት ያስነሱት መሳፍንትና መኳንንቶች ናቸው ።

ራሳቸው የኢትዮጲያ ነገስታት በወቅቱ ስለአለም ፖለቲካ በቂ ግንዛቤ ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም ። ለምሳሌ አውሮፓውያን ክርስትያኖች ስለሆኑ ለክርስትያን ያግዛሉ ብለው ያምኑ የነበረ ቢሆንም አውሮፓውያን ግን ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው እንጂ በሀይማኖት ላይ የተመሰረተ አልነበረም ፖሊሲያቸው ። አውሮፓውያን በርካታ አብዮቶችን አካሂደው ሀይማኖትንና መንግስትን ለያይተው ተግባራዊ የሆነ የቅኝ ግዛት ፖሊሲን ይከተሉ እንደነበረ የሚታወቅ ነው ። ለዚህም አፄ ቴዎድሮስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ለምሳሌ ለንግስት ኤልሳቤጥ በፃፉትደብዳቤዎች ላይ ይቆጧቸው የሚሉ ሀረጎች ነበሩባቸው ፣ ይሁን እንጂ በተደጋጋሞ ደብዳቤዎችን ቢፅፉም ምንም መልስ ባለማግኘታቸው በኋላ ላይ በእንግሊዞችና በአፄ ቴዎድሮስ መሀከል እሰጥ አገባና ብሎም ለመቅደላው ጦርነትና ኢትዮጲያ በእንግሊዝ ለመወረር በር ከፍቷል   ።

አፄ ምንሊክ በውጫሌ ውል ከኢጣሊያኖች ጋር ሲዋዋሉ ጣሊያን ኤርትራን እንዲያስተዳድር ፈቅደዋል ።ጣሊያን ግን ኤርትራን ብቻ ሳይሆን መላዋን ኢትዮጲያን በእጁ ለማስገባት ሲል የውሉን አንድ አንቀፅ ማለትም አንቀፅ 17 አጣሞ ለራሱ እንደሚመቸው በመተርጎሙ ምክንያት የኢትዮጲን የውጪ ግንኙነት በማበላሸቱ ለአድዋ ጦርነት በርን ከፍቷል ። ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በቅኝ ግዛት ስር ሲያስገቡ ከወታደራዊ ሀይል በተጨማሪ በማታለልና ውሸት ስምምነቶች አማካይነት ሲሆን ፣ ከዚህ ቀደምም አፄ ዮሀንስን እንደዚሁ የሂወት ስምምነት በሚባለው ተዋውለው ነገር ግን ውላቸውን በማጠፍ ጣሊያንን በኤርትራ ተክተው ወጥተዋል ።

አፄ ቴዎድሮስ ደብዳቤ ለእንግሊዟ ንግስት እና ለነገስታቱ ይፅፉ የነበረ ቢሆንም በእርግጥ ለነገስታቱ ሊደርስ ቢችልም ውሳኔ ሰጪዎቹ ግን በተለይ በእንግሊዝ እንደሚታወቀው ሚኒስትሮችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ናቸው ። ስለአውሮፓ ውስጣዊ የፖለቲካ አሰራር ነገስታቶቻችን የነበራቸው ግንዛቤ በቂ እንዳልነበረ መገመት ይቻላል ። በዚህም ቢሆን ሀገሪቱ ተገልላና  በወቅቱ ከነበረው ግንዛቤ በመነሳት ነው ። ለአገራው ቀናኢ መሆናቸው ፣ ዳር ድንበሯን ለማስከበር የነበራቸው ቁተርጠኝነት ግን ተወዳዳሪ እንዳልነበረው መረዳት አያዳግትም ። በዛን ወቅት አውሮፓውያን ብዙ ሰልጥነው ብዙ ሀሳቦችንና በፖለቲካው ፣ በሳይንስ ዘርፍ ብዙ ነገርን የፈጠሩበትና ብዙ ቀድሞ ሚስጥር የነበሩ ነገሮችን የደረሱበት ጊዜ ነበረ ።

የግራኝ መሀመድን ወረራንና የእርስ በእርስ ጦርነትን ተከትሎ ፣ የሀይማኖት ክፍፍል ተፈጥሮ ለበርካታ አመታት በኢትዮጲያ የቤተክህነትና የመንግስት አስተዳደርንና ሲያናጋና እርስ በእርስ ሲያዋጋ ኖሯል ። ለምሳሌ በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የውጪዎቹን ሀይማኖት ንጉሰ ነገስቱ በመቀበላቸው በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ዋናዎቹ ነገስታት በመዳከማቸው ምክንያት ነው ።

በኢትዮጲያም ምንም እንኳን መኳንንቱ ለመንገስ በህዝቡም ሆነ በቤተክርስትያን ህጋዊ ተቀባይነትና ውክልና (Legitimacy) ከነገስታቱ ወገን ማለትም ከሰለሞናዊ የዘር ሀረግ መመዘዝን ስለማያሟሉ ፣ አሸናፊ የነበሩ መኳንንቶች አማራጭ ስላልነበራቸውከዛቀው የዘር ሀረግ የሚመዘዙ ነገስታትን በቤተመንግስት ውስጥ በማስቀመጥ ለራሳቸው የራስ ቢትወደድ ማእረግን በመስጠት አገር ያስተዳድሩ ነበር ። መቀመጫውን  ጎንደር ላይ አድርጎ የተቀመጠው ይሄው ስርአት ራስ ቢትወደድ ማለት በአሁኑ አጠራር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ማለት ሲሆን አስገራሚው ነገር ቤተ – መንግስት እሚቀመጠውን ንጉሰ ነገስት እሚመርጠው ወይም እሚሾመው ራስ ቢትወደዱ ነበር ።

በአጠቃላይ ግን ይሄ ስርአት በእርስ በርስ የስልጣን ሽኩቻ የተጠመደ ስለነበረ ሀገሪቱ በወቅቱ ዙሪያዋን እየተጠናከሩ የነበሩትን ቅኝ ገዢዎችና ሀያላንን ልትከላከልና ራሷን ልትቋቋም ትችል የነበረውን ጊዜና አቅምን አሳጥቷታል ። በተለይም በሰሜናዊ ኢትዮጲያ እየተጠናከሩ የመጡትን ግብፆችን ፣ መሀዲስቶችን እንዲሁም በአካባቢው ያንዣብቡ የነበሩትን አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችን እንደ እንግሊዝና ግብፅ የመሳሰሉት አገሪቱን ያለመከላከያ ያገኙበት ወቅት ነበረ ።

በነገራችን ላይ ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የነገሱት የኢትዮጲያ መሪዎች አፄ ቴዎድሮስም አፄ ዮሀንስም ሆኑ በኋላ ላይ ዐፄ ምንሊክ የአገሪቷን ዳር ድንበር በመከላከል ነበረ አብዛኛውን ጊዜአቸውን ያሳለፉት ። በዘመነ መሳፍንት ግን የአገሪቱን ዳር ድንበር በመከላከል በተቀናጀ መንገድ የተደረገ ብዙም ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል ። ከዚያ ይልቅ የአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች በዙሪያዋ እየተጠናከሩ የመጡበት ጊዜ ነበረ ።

አፄ ቴዎድሮስ የጎንደርን መኳንንቶችንና መሳፍንቶችን እና የዘመነ – መሳፍንትን የሀያላን ጦረኞች አገዛዝን በጦር ሜዳ አሸንፈው አንድ ማእከላዊ መንግስትን መመስረት ችለዋል ። ይህም ከነበረው የስልጣን ሽሚያና የእርስ በእርስ ጦርነት አንፃር አፄ ቴዎድሮስ በራሳቸው ተነስተው ንጉሰ ነገስት እስከመሆን ደረጃ መድረሳቸው የነበራቸውን ትልቅ ሀሳብ ሲያሳይ ፣ በሌላ በኩል እሳቸው በታላቅ ትግል የጣሉትን መሰረት በኋላ የመጡት የኢትዮጲያ መሪዎችም ተከትለውታል ። አፄ ቴዎድሮስ በመበጣበጥና  በስልጣን ሽኩቻ የተሞላውን የዘመነ መሳፍንትን ስርአት አሰስወግደው ከብዙ አመታት ደም አፋሳሽ ትግል በኋላ አሃዳዊ የሆነውን የኢትዮጲያን ስርአተ – መንግስት መመለሳቸው ፣ እንዲሁም ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር የነበራቸው ቁርጠኝነት ከእሳቸው በኋላ በመጣ ንጉሰ ነገስት አልታየም ቢባል ማጋነን አይሆንም ። አፄ ቴዎድሮስም ሆኑ ፣ ከሳቸው በላይ የመጡትን ነገስታት ያደረጉትን መረዳት የዘመነ መሳፍንት ዘመን መረዳት ያሻል ። ዘመነ – መሳፍንትን ለማስቆምና ጠንካራ ማእከላዊ መንግስትን ለመመስረት አፄ ቴዎድሮስ ከባድ ጭካኔን መጠቀማቸውን አሌ ማለት አይቻልም ።

የቴዎድሮስ ስርአት በእንግሊዝ ጦር ሲወረር ፣አፄ ዮሀንስ የተተኩ ሲሆን ምንም እንኳም አፄ ዮሀንስ ለድንበር መከበር በነበራቸው ቁርጠኝነት ከደርቡሾች ወይም መሀዲስቶች ጋር በነበራቸው ትግል ሱዳንን ወረው የነበሩትን ግብፆችን በምፅዋ በኩል እንዲወጡ የግብፅ ቅኝ ገዢ ከሆነችው እንግሊዝ ጋር ተዋውለው በመፍቀዳቸው የድርቡሾችን ቂም ሲያተርፉ በአንፃሩ ግን እንግሊዞች ለኢትዮጲያ ቦጎስን ለማስረከብና ፣ የምፅዋ ወደብን በነፃ እንድትጠቀም ሊፈቅዱ የነበራቸውን ስምምትን ሙሉ በሙሉ በማጠፍ ጣሊያንን በኤርትራ ተክተው ወጥተዋል ።

አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በተለያየ መንገድ ቅኝ እንደገዙ የሚታወቅ ሲሆን በማታለልም ጭምር እንደሚጠቀሙ የሚታወቅ ሲሆን ፣ ለምሳሌ ጣሊያኖችም ከአፄ ምንሊክ ጋር የውጫሌ ውልን በመዋዋል ሀገሪቱን በቅኝ ለመግዛት ሞክረዋል ለማስገባት ሞክርዋል፣ ጉዳዩ ግን ውሎ አድሮ ደርቡሾች ቂም ይዘው ከአፄ ዮሀንስ ጋር የመረረ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ከዚያ በኋላም እንዲሁ ለአገሪቱ ብዙ መዘዝን ይዞ የመጣ ጉዳይ ነው ፣የአፄ ዮሀንስ ስርአትም ከጎረቤት ደርቡሾች ወይም መሀዲስቶች ጋር እያደረጉ በነበረው ጦርነት ምክንያት በጦርነቱ ህይወታቸውን ሲያጡ ፣ ኑዛዜ አድርገው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ስርአታቸው ጠንካራ በነበሩት በአፄ ምንሊክ ንግስና ተተክቷል ።

በእነዚህ የስርአት ሽግግሮች የምናየው ነገር አንዱ ንጉሰ – ነገስት ሲወድቅ ዙፋኑ በዛው በስርአቱ ውስጥ መተካካት ሳይሆን ከውስጥ በተነሳ በእርስ በእርስ ጦርነት ፣ ወይም የውጪ ወራሪዎች ንገስታቱንብሎም ሀገሪቱን በሚያዳክሙበት ወቅት በሌሎች የተሻለ ጥንካሬ በነበራቸው የጦር አበጋዞች እየተተካ ሲቀጥልቆይቷል ።አፄ ምንሊክ ጋ ሲደርስ የዚህን ትርምስ በሚገባ ይረዱ ስለነበር ግልፅ በሆነ ኑዛዜ ወራሻቸውን ያስታወቁ ሲሆን ኢትዮጲያውን አንድ እንዲሆኑና ወንድሜ ወንድሜ እንዲባባሉ በማሳሰብሲያልፉ፣በኢትዮጲያ ታሪክ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ የመጀመሪያው እሚባለው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተካሄደው ከአፄ ምንሊክ ወደ አቤቶ ኢያሱ ነበረ ።በነገራችን ላይ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ በኢትዮጲያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ ስልጣን ሽግግር የተካሄደው ከአፄ ምንሊክ ወደ ልጅ እያሱ ነው።

የምንሊክ ፖሊሲም ትኩረቱ ወደ መሀል አገር ነው እንጂ ወደ ሰሜን አልነበረም ማለት ይቻላል ። ሁለት ፖላንዳውያን የታሪክ ፀሀፊዎች የኢትዮጲያ ታሪክ በተሰኘ መፅሀፋቸው ይህን ጉዳይ ገልፀውታል ። ጥቂት ዘግየት ብሎም ቢሆን የተፈራው የስልጣን ሽኩቻ አልቀረም ፤ ይህም በአቤቶ ኢያሱና በተፈሪ መሀከል ሲሆን እንደ ቀድሞው ድብልቅልቅ ያለ የእርስ በእርስ ጦርነት ባይነሳም የተወሰነ ቁርቋሶ  ነበረ ።የመጀመሪያው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተባለው ስልጣንም በአቤቶ ኢያሱ እጅብዙም አልቆየም ከጥቂት አመታት በኋላም ንግስተ – ነገስታት ዘውዲቱ ተረክበዋል ።

ያም ሆነ ይህ ስልጣኑ ከንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ህልፈት በኋላ ሙሉ በሙሉ በተፈሪ መኮንን እጅ ሲገባ እስከ ፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ድረስ ሀገሪቷ በአንፃራዊንነት የተረጋጋችና ሰላም ነበረች ። ጣሊያን ከወጣ በኋላም የመጀመሪያው ህገ – መንግስት የተረቀቀ ሲሆን ፣ ነገር ግን አንዳንድ ተቺዎች ህገ – መንግስቱ የንጉሰ ነገስቱን ስልጣን ለማጠንከር ረዳ እንጂ ፣ ለህዝብ እሚሰጠው ይህ ነው እሚባል መብትና ተሰሚነት አልነበረም ተብሎ ይተቻል ። በዚሁ ህገ – መንግስት አየሩም ፣ መሬቱም፣ባህሩም ሁሉም የንጉሰ ነገስቱ ነው ብሎ ነው እሚነሳው ።

ይሁን እንጂ ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር በእነኚህ ሁሉ አመታት አልታየም ። ይበልጥ አሸናፊዎች የራሳቸውን የበላይነት እሚጭኑበት ሂደት ነው የነበረው ። ከዚያም በኋላ ወታደራዊው መንግስት ወደ ስልጣን መጥቶ የንጉሰ – ነገስቱን ስርአት ሲተካ ፣ እንዲሁ የደርግም ስርአት በኢህአዴግ ተተክቷል ። በእነኚህ ሁሉ አመታት የዘመነ መሳፍንቱን የአለመረጋጋት እና የእርስ በእርስ የስልጣን ሽሚያ ዘመን እና ከአፄ ምንሊክ ወደ ልጅ ኢያሱ የተደረገውን ዘላቂ ያልሆነ የአጭር ጊዜ የስልጣን ሽግግርን ትተን ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እንኳን ብንቆጥር ከ150 አመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ኢትዮጲያ ውስጥ ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር አልታየም ።

ባለፉት የ150 አመታት የነገስታት ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ ብንጀምር በኢትዮጲያ የነገስታት ታሪክ በስነ – ስርአት የተቀለሰላቸው በክብር የቀብር ስነ – ስርአታቸው የፈፀመላቸው መሪ ንግስተ -, ነገስታት ዘውዲቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው ። በእነኚህ ሁሉ ጊዜያት ሁሉ የስልጣን መተካካት እንጂ የስልጣን ሽግግር በኢትዮጲያ ታሪክ አልታየም ። ከንግስት ዘውዲቱ ወደ ተፈሪ የተካሄደው የስልጣን መተካካት «ሰክሴሽን» ሲ ሆን ፣ ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይላለማርያም ደሳለኝ የተካሄደውም እንዲሁ የስልጣን መተካካት ነው እንጂ ሽግግር አይደለም ።

ከንግስተ ነገስታት ዘውዲቱና ወደ አልጋ ወራሽ ተፈሪ የተላለፈው ስልጣን ሰላማዊ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ሊያከራክር ይችላል ። በአንድ በኩል የንግስቲቷ ባለቤት ራስ ጉግሳ  ከሀይለሰስላሴ ጦር ጋር በተደረገ ውጊያ መገደላቸው ፣በሌላ በኩል የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ እውነተኛ ስልጣን ንግስቲቷ ነበራቸው ወይ ? የሚል ሲሆን ፣ ሌላው ደግሞ የራሳቸው የንግስቲቷ አሟሟት ራሱ በምን ምክንያት እንደሆነ አወዛጋቢነቱእንዳለ ሆኖ ማለት ነው ።

ከአድዋ ድል በኋላም ቢሆን አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ለኢትዮጲያ አላረፉም ፣ ኢትዮጲያን ለሶስት ለመከፋፈል አንግሊዝ ፈረንሳይና ጣሊያን ሲዶልቱ ቆይተዋል ፣ በ1906 ፣ በዚህ ዱለታ ላይ አፄ ምንሊክ ፊታቸውን ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ ይልቅ ወደ ጀርመን ለማዞር ሲገደዱ ወራሻቸውም ልጅ ኢያሱም ከጀርመን ጋር ወዳጅነት ቀጥለውበታል ፣ ሆኖም ግን የአለም ሁኔታ በተለወጠበት ሁኔታ በወቅቱ በአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅት የፈረንሳይና የእንግሊዝን ጠላት የነበረችውን ጀርመንንና እና የእሷን ወዳጅ የነበረችውን ቱርክን በመደገፋቸው ምክንያት ለልጅ ኢያሱ ውድቀት የራሱን አስዋፅኦ አድርጓል።

ፋሺስት ኢጣሊያ ዘግይታ ፣ ተዋህዳ አንድ በምትሆንበት ወቅት እንግሊዝና ፈረንሳይ በአለም ዙሪያ በርካታ ቅኝ ግዛቶችን ይዘው የነበረ ሲሆን ጀርመንና ኢጣሊያ ግን ምንም አይነት ቅኝ ግዛት አልነበራቸውም ። በተለይ ኢጣሊያ በአንድ በኩል በአድዋ ጦርነት በመሸነፏ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሙሶሎኒ ወደ ስልጣን ሲመጣ ይሄንን ኢትዮጲያን በቅኝ ግዛት ስር ማዋል  የጋለ ፍላጎት ማገርሸት ሲጀምር ፣ ኢጣሊያ በአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅት እንግሊዝን በመርዳቷ እንግሊዝ ለዛ ውለታ ብላ ከሶማሊላንድ ቆርጣ ግዛትን ስትሰጥ ፣ ከዛም በላይ እንዲሁ ከግብፅ ቅኝ ግዛቷ ላይ ቆርጣ ለም የሆነውን ምእራባዊውን የግብፅን ግዛት ለኢጣሊያ ሰጥታለች ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ማባበያ ጣሊያንን ሊያረካ ስላልቻለ ፣ ሙሶሎኒ ኢትዮጲያን ለመውረር በኤርትራና በሶማሊላንድ ሰራዊት ማከማቸት ጀመረ ። ጣሊያን ከዚያ ቀደም ብሎ በአውሮፓ በተደረገ ስብሰባ ላይ ጅቡቲ ትሰጠኝ ብሎ ፈረንሳይን ሲጠይቅ ፣ የፈረንሳዮች በቁጣ ነበር  የመለሱት ፣  ጣሊያን ከዚያ በኋላ ስለ ጅቡቲ ሳያነሳ ቀርቷል ።

ፋሺስት ኢጣሊያ ግን ዋና ትኩረቱ የነበረው የአባይ ምንጭ የነበረችውንና የጣና ሀይቅ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጲያን በቅኝ ግዛትነት መያዝ ነበረ ። ነገር ግን እንግሊዞች ራሳቸው በዛን ወቅት ሱዳንንና ግብፅን ይገዙ ስለነበረ፣ የእነኚህ ሀገራት የህልውና መሰረት የሆነው የአባይ ወንዝ ምንጭ ከሀይለስላሴ ይልቅ ጠንካራ በሆነው በሙሶሎኒ እጅ መግባቱ እምብዛም አላስደሰታቸውም ።ኢትዮጲያን ሲወርም በአንድ ጊዜም ድጋፍን አልሰጡትም ፣ ነገር ግንውለው አድረው ወደ ናዚ ጀርመን እንዳይጠጋ ለማባባል ዘግየት ብለው ድጋፋቸውን ሰጥተውት የነበረ ቢሆንም ሙሶሎኒ ግን ከናዚዎች ጋር ሲወግን ወዲያውኑ በሱዳን ያለውን ሀይላቸውን አደራጅተው የኢትዮጲያን አርበኞችን ወደ ማገዝ እና ሀይለስላሴን ወደ ስልጣን ለመመለስ እንቅስቃሴ ወደ ማድረግ ተሸጋግረዋል ።  ንጉሰ ነገስቱ ውሎ ባልለየለት ሁኔታ ስደት ወይንም ሽሽት በሚል ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጲያን ሲወር አገር ጥለው ወጥተዋል ።

ሀይለስላሴ ብንወስድ ምንም እንኳን ዘመዶቻቸውን ፣ ወራሾቻቸውን ከዋናው ስልጣን አግልለው አቆይተዋቸዋል ፣ አንዳንዶቹም አምባሳደር አድርገው ለአገር አገር ያንከራትቷቸው ነበረ ፣ ራስ  እምሩን በሩስያና በመሳሰሉ የውጭ አገራት ለዘመናት ከአጠገባቸው እንዲርቁ ሲያደርጓቸው ቆይተዋል ። ከዚያ ይልቅ ለዘውዱ ምንም ወራሽነት የሌላቸውን ባእዳን የሆኑና ዘመዶቻቸው ያልሆኑ ምሁራንን አስጠግተው ይሰሩ ነበረ ። እነ አክሊሉ ሀብተ ወልድና ወንድማቸውን መኮንን ሀብተወልድን የመሳሰሉት ምንም አይነት የስጋ ዝምድና የሌላቸው ነበሩ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የነበሩት ። በዚህ የስልጣን አያያዝ የሀገራችን መሪዎች የተካኑ ናቸው ። ከእሳቸው በኋላም የመጣው ደርግ በባሰ መንገድ ስልጣኑን ለመከላከል የሚችለውን ሲያደርግ ተስተውሏል ።

በሀገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዳይኖር ዋና ዋና የሆኑት ምክንያቶችን ለመጥቀስ ያህል ፣ አንዱ የጠነከሩ ተቋማት አለመኖር ሲሆን ለምሳሌ መከላከያውንና በአጠቃላይ የፀጥታውን ክፍል ብንወስድ ተጠሪነቱ ለህገ – መንግስቱ መሆኑና የፖለቲካ ወገንተኛ አለመሆን ሲጠበቅበት ፤ ሌላው ምክንያት ደግሞ ህግና ህገ – መንግስት ላይ የተመሰረተ የሽግግር ስርአተ – ደንብ አለመኖር ፣መዋቅራዊ አደረጃጀቱን የጠበቀ የስልጣን ተዋረድ አለመኖር ፣ ለምሳሌ በአሜሪካን አገር ፕሬዝዳንቱ ህይወቱን ቢያጣ በምክትል ፕሬዝዳንቱ የሚተካ ሲሆን ፣ ሁለቱም በአንድ ጊዜበአደጋ ወይም በሆነ ምክንያት ህይወታቸውን ቢያጡ በኮንግሬሱ አፈ – ጉባኤ ይተካሉ እንደዛ እያለ እስከ አራትና አምስት ደረጃ ድረስ ያለውን የስልጣን ተዋረድ በመከተል ያልተጠበቀ የስልጣን ክፍትተ ቢፈጠር እንዴት እንደሚሞላ ህገ – መንግስቱ ላይ  በማያሻማ ሁኔታ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል ።

ዲሞክራሲ ባልጠናባቸው ሀገራት ግን የቀድሞውን የግብፁን ፕሬዝደንት ሆሲኑ ሙባረክን ለምሳሌ ምንም እንኳን በህገ – መንግስቱ ፕሬዝዳንቱ አንድ ነገር ቢያጋጥመው የሚተካው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ነው ቢልም ፕሬዝዳንቱ ግን ለረጅን ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳይሾሙ የቆዩ ሲሆን ፣ ስለዚህ የሆነ የስልጣን ክፍተት ቢከሰት ማን ማንንእንደሚተካ እሚታወቅ ነገር አልነበረም ማለት ነው ።

ሌላውደግሞ የሰላማዊ ሆነ የስልጣን ሽግግር ባህልና ልምድ አለመኖር ነው። ለምሳሌ በአውሮፓና በአሜሪካ ምርጫዎችን በማካሄድ በታሪካቸው በመቶ አመታት እሚቆጠር ሰፊ የሆነ የስልጣን ሽግግርን በማካሄድ ተሞክሮ ስላላቸው ባህሉና ልምዱ በተቋማቶቻቸው ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎቻቸው፣ በህዝቡ ዘንድ በሰፊው የሰረፀ ጉዳይ ነው ። በዚህ አይነት ሁኔታ እንዲህና እንዲያ እያለ የ19ኛውና 20ኛውና ክፍለ ዘመን የኢትዮጲያ ታሪክ ተጉዟል ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s