የስርአተ – መንግስት መግባባት መስፈን

ቀድሞ በነበረው አስተሳሰብ አንድ ሰው ወይም አንድ ፓርቲ አንዴ ስልጣን ላይ ከወጣ ምንም ነገር እንደማይነቀንቀውና እስከፈለገው ድረስ እንደሚቆይ ይገመት ነበር ። በፖለቲከኞች መልካም ቃላት ብቻ ነገሮች እንደማይሻሻሉና እንደማይለወጡ የተረዳው ህዝብ በከተማ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መንግስታት ይለወጣሉ ተብሎ አይታሰብምየነበረ ሲሆን አሁንግን ራሱ ህዝቡ ሀላፊነቱን በመውሰድ የማይፈልጋቸውን መሪዎች በሰሜን አፍሪካ ያስወገደ ሲሆን በዛ ቀዳዳ ውስጥ ሌላ አምባገነን እንዳይተካ ካለፉት ልምዶች ከፍተኛ ጥንቃቄዎችን በማድረግ የአንድን ሀገር የፖለቲካ ስልጣን እንደ ቀድሞው በጥቂት ግለሰቦች መልካም ፈቃድ ስር ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ተቋማዊ ማድረግን ፣ ስልጣንን የመገደብን አስፈላጊነት ተገንዝቧል ።

 

በአጠቃላይ ሲታይ ፖለቲካ በልሂቃኑ ወይም ኤሊት በሚባሉት የአንድ ሀገር ማህብረሰቦች መሀከል የሚደረግ ትግል ሲሆን ፣ አንድን አዲስ የሆነን አስተሳሰብ ወደ ዋናው ማህበረሰብ ለማስረፅ ረጅም ጊዜን ይወስዳል ። ይህ በተለይም ዲሞክራሲ ባልጠነከረባቸው ሀገራት ሀሳቦች በቀላሉ ወደ ዋናው ማህበረሰብ አይሰራጩም ። ንጉሰ ነገስቱ ውሎ ባልለየለት ሁኔታ ስደት ወይንም ሽሽት በሚል ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጲያን ሲወር አገር ጥለው ወጥተዋል ።

 

በግብፅ በተካሄደው ህዝባዊ አብዮት እ.ኤ.አ. በ2011 የግብፁ ፕሬዝዳንት ከወረዱ በኋላ የተደረገው የመጀመሪያው ህዝብ ውሳኔ የፕሬዝዳንቱን የስልጣን ገደብ መወሰን ነበረ። አንድ ሀገር በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ይልቅተቋማዊ በሆነ አደረጃጀት መመራት ለዛ ሀገር ህልውና እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ። አንድ አንድ የንግድ ድርጅት እንኳን እንደ ተቋም ካልተመራ አደጋ እንደሚገጥመው በሀገር ደረጃ ያሉ ጉዳዮችም ከፍተኛ ጥንቃቄንና ብስለትን ይጠይቃሉ ።

 

ምንም እንኳም አሜሪካኖች የራሳቸውን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የአለምን ችግር ለመፍታትና በአለም ላይ ህግና ስርአትን ለማስፈን ጥረት ቢያደርጉምና ለዛም ከፍተኛ እንቅስቃሴን ቢያደርጉም የአለም ችግር ግን በአንድ ሀያል ሀገር እንቅስቃሴ ብቻ ይፈታል ማለት አስቸጋሪ ሆኗል ። ይህንንም ምእራባውያንም ሆነ የተቀረው አለም እየተረዳው የመጣው ሀቅ ሆኗል ። ለዚህም ዋናው ምክንያቱ ችግርን ፈተዋል የተባሉ ፖሊሲዎች ፣እንደ አዲስ እየፈረሱ ቋጠሮው እየተፈታ በመሆኑ ነው፣ እንዲሁም የተምታታ የውጭ ግብንኙነት ፖሊሲን መከተላቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ ተቀራራቢ የኢኮኖሚም ሆነ ወታደራዊ አቅም ያላቸው ሀገራት በአለም ዙሪያ መፈጠር በመጀመራቸው ነው።በተመሳሳይም የአለማችን ችግር በአንድ ሀያል ሀገር ጥረት ብቻ አይፈታም ።

አንድ ሰው ብቻውን አንድ መምጣት ያለበትን ለውጥ ማስቆም አይቻለውም ። ነገሮች ምንግዜም ቢሆን አዲስ ነው እሚሆኑት ። ችግሮች መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ከተፈቱ ድረስ ብቻ ነው ተመልሰው እማይመጡት እንጂ አገም ጠቀም የተደረገ ነገር ይብስኑ አገርሽቶ ተመልሶ መምጣቱ አይቀሬ ሲሆን   መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ከስር መሰረቱ መፍትሄ የመስጠት ልማድን ማዳበር ያስፈልጋል ።

በአንድ ወቅት የሚገኝ የህዝብ ድጋፍ ብዙውን ጊዜ ለረጅም ጊዜ እሚዘልቅ ላይሆን ይችላል ።አንዳንድ ጊዜ በአንድ ወቅት የነበረ የህዝብ ድጋፍ በሌላ ጊዜም ላይኖር ወይም ላይቀጥል ይችላል ። ይህ ዲሞክራሲ ባለባቸውም በሌለባቸውም ሀገራት የሚታይነው ።የአሜሪካንን መሪዎች ብንወስድ ሲመረጡ የነበራቸው የህዝብ ድጋፍ ወዲያውኑ በጥቂት ወራት ውስጥ እያቆለቆለ ይሄዳል ።ስለዚህ መሪዎች የህዝብን ዘንድ ያለውን የህዝብ ድጋፍ ለሁልግዜም ያለ (for granted) አድርገው መውሰድ የለባቸውም ። ህዝቡምቢሆን ድጋፉን ከየትም አያመጣውም ፣ ከመሪዎቹ ስራ በመነሳት ነው ድጋፉን የሚሰጠው እንጂ መሪዎቹ ትክክለኛውንና የህዝቡን ጥቅም የሚያስከብርን ነገር ካላደረጉ ህዝቡ ድጋፍ ሊሰጥ አይችልም ። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብ ከመሪዎቹ ይልቅ ለዘብ ያለ ነው ። መሪዎቹ ግትር በሚሆኑበት ህዝብ ግን እንደመሪዎቹ ሳይሆን ለቀቅ ፣ ለዘብ የማለት ባህሪ አለው ።

አንድ መንግስት ጠንካራና መሰረት ያላቸው ትችቶች እሚቀርቡበት ከሆነ ውሎ አድሮ ለነዛ ትችቶች እጅ መስጠቱ የማይቀር ሲሆን ፣ ሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸውን ሀሳቦችን የሚያራምዱ ክፍሎችም እንደዚሁ እየዋለ እያደረ በህዝብ ዘንድ ተሰሚነትን እያገኙ ወደ ስልጣን መንበር መምጣታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው ። አንዳንድ ጊዜ መሰረታዊ የሆነውን የህዝቡን መሰረታዊ የዲሞክራሲያዊ ጥያቄን ያልመለሱ መንግስታት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ህዝባዊ ድጋፍን ሊያገኙ ይችላሉ ። የዚህም ዋናው ምክንያት ህዝቡ የረጅም ጊዜ የሀገሪቱን ጥቅም በማሰብ የሚሰጣቸው የህዝብን ድጋፍ ሲሆን መሪዎቹ ግን የዘለቄታ የህዝብ ድጋፍ መስሏቸው ሊዘናጉ ይችላሉ ።

በሀገራችን ውስጥ በጣም መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት አለመኖሩ ለወደፊቱ የሀገሪቱ ህልውና አሳሳቢ ነው ።ባለፈው ታሪካችን አተረጓጎምና አረዳድ ላይ ራሱ ሰፊ ልዩነት መኖሩ አስገራሚ ነው ።በፖለቲካ ፓርቲዎች መሀከል የአስተሳሰብና የፍልስፍና ልዩነቶች ያሉና የተለመዱ ቢሆንም ቅሉ የዛን ሀገር ህልውና በረጅም ጊዜ ሊፈታተኑ የሚችሉ መሆን የለባቸውም ። ለምሳሌ በአሜሪካን ሀገር ብንወስድ አንዱ ፓርቲ ታክስ ይቀነስ ይላል ፣ ሌላው ፓርቲ ደግሞ ታክስ ይጨመር ይላል ። ይሄም የአጭር ጊዜ የዛን ሀገር ወቅታዊ ችግር መፍቻ ነው እንጂ ፣ ከሁለቱ የተሻለ ሆኖ የተገኘው ስራ ላይ ስለሚውል ከረጅም ጊዜ የሀገሪቱ ጥቅም አንፃር ሲታይልዩነት የለውም ።ፖሊሲው አልሰራ ያለው ፓርቲም በቀላሉ በምርጫ ተሸንፎ ከስልጣን ስለሚሰናበት ፣ የተሻለ ዝግጅትና አቅም ያለው ፓርቲ ወደ ስልጣን ስለሚመጣ ችግሮች በአስተማማኝ ሁኔታ ተፈተው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ ።

በኢትዮጲያ ተደጋጋሚ የስርአት መውደቆች ተከስተዋል ፣ ለዚህም የራሱ ምክንያት ያለው ሲሆን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለዘብ (Flexibile) አለማለት አለመሆንና ፣ ግትርነት እና ስርአቶቹ ራሳቸው መጀመሪያ ሲቋቋሙ የብዙሀኑን አስተሳሰብና ፍላጎት በሚወክል ሁኔታ የሚቋቋሙ አለመሆን ፣ ከዚህም ሌላ ስርአቶቹ ሊቀጥሉ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ የመደራደርና ሰጥቶ የመቀበል (Compromising) ልማድ አለመኖሩ፣ እና አሸናፊው ሁሉንም ጠራርጎ የሚወስድበት መሆኑ ፣ በቅናትና ምቀኝነት ሊጠቅሙ የሚችሉ ሀሳቦችን ማጨናገፍ ችግሮች ሳይፈቱ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና እማይመለሱበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አስተዋፅኦ አለው።

ይሁን በአንድ ሀገር ሲታይ የስርአት መፍረስ በስሩ ያሉትን በርካታ ተቋማትን መፍረስንና የዜጎችን ኑሮም ያናጋል ። በርካታ ሰዎች በአንድ ጀንበር ስራቸውንና መተዳደሪያቸውን ሁሉ ሊያጡ ይችላሉ ። በብዙ ወጪና በብዙ አመታት ጥረትና ስራ የተቋቋሙ ጠቃሚ ተቋማትም ሊፈርሱና ባለሙያ ግለሰቦችም በፖለቲካ ምክንያት አትፈለጉም ሊባሉ ይችላሉ ፣ ይህም በሀገሪቱ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው  ። በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው የማህበረ – ኢኮኖሚና – ፖለቲካዊ መናጋቶች ከፍተኛ በመሆናቸው በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው መሸማቀቅና መሳቀቅም ትራውማ ቀላል እማይባል ሲሆኑ ። የስርአት መፍረስም የነበረውንና ቀድሞ የተገነባውን እያፈረሱ እንደ አዲስ መገንባት ሁሉ ይከተላል ። ስለዚህ ከዚህ አዙሪት ሁነኛ የመውጫ መንገድ መቀየስ አለበት ። ተቋማትን የመመሰስረት ባህላችን ደካማ ነው ።

አንድ ሀገር ችግር በአንድ ፓርቲ ፣ በአንድ ቡድን ወይንም በአንድ በጥቂት ሰዎች አይፈታም ። ስለዚህ ብዙዎችን ማሳተፍና ያ ችግር እንዲፈታ መደረግ አለበት እንጂ በጥቂቶች ብቻ ጨርሶ ሊፈታ አይችልም ። ጥቂት ሰዎች ብቻ ለችግሩ ቢጨነቁ ፣ ቢጠበቡ ለዛ ችግር ብቻቸውን መፍትሄን ሊያመጡ አይችሉም ። በተለይም ሰፊ የፖለቲካ የአስተሳሰብም ሆነ የፍልስፍና ልዩነት በሚታይባቸው ሀገራት ውስጥ የሀገራቱ ችግር በአንድ ፓርቲ ወይም በአንድ ፍልስፍና ብቻው አይፈታም ።

የቀድሞ የነገስታቱን ስርአቶች ትተን እንኳን ከዛ በኋላ ለታዩት ፣ ለተደጋጋሚ የስርአት መፍረሶች ምክንያት ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ስርአቶቹ ገና ሲመሰረቱ ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ አሳታፊ ሆነው አለመመስረታቸው፣ከአሸናፊዎች ከራሳቸው አመለካከትና ጥቅም ተነስተው መቋቋማቸው፣ስርአቶቹ ውስጣዊ ችግር -በፓርቲም ሆነ በመንግስት ውስጥ – ሲገጥማቸው ችግራቸውን የሚፈቱበት ጠንካራ ውስጣዊ የዲሞክራሲያዊ ስርአት አለመኖር እና አንድ ፓርቲ ወይም መንግስት ያገሪቱን ችግር መፍታት ካቃተው ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንድ ለሌላው እድል አለመስጠት ወይም ሌላው በሰላም የሚተካበት ባህልና ልምድ አለመኖር ፣ እና የፖለቲካ ። ከሁሉ በላይ ግን ለተደጋጋሚ የስርአት መፍረሶች ዋነኛው ምክንያት የብሄራዊ መግባባት አለመኖር ነው ።

 ብሄራዊ መግባባት ማለት ከፖለቲካ ልዩነት በላይ የሆነ ነገር ሲሆን ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መስመር ልዩነት ላይ ሳይሆን ፣ በአገር ጥቅም ላይ የተመሰረተ የጋራ አመለካከትን መያዝ ማለት ነው ። ስልጣን ላይ ያሉት ብሄራዊ መግባባት ማለት የገዢውን ፓርቲ አቋም መደገፍ ማለት ይመስላቸዋል ፣ ተቃዋሚዎቹም ብሄራዊ መግባባት ማለት የተቃዋሚዎችን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ መደገፍ ማለት አድርገው ያዩታል። ለምሳሌ በምእራቡ አለም ፓርቲዎች ልዩነት እንዳላቸው የታወቀ ሲሆን ፣ በአለም አቀፍ ፖሊሲያቸው ግን የምእራብ ሀገራት ፖሊሲ እምብዛም ሲቀያየር አይስተዋልም ። ለዚህ ምክንያቱ የትኛውም ፓርቲ ወደ ስልጣን ሲመጣ የውጭ ፖሊሲውን በሀገሩ ጥቅምላይ በመመስረት ስለሚቀርፅ ሌላውም ሲመጣ ይህን ያህል ልዩነት ስለሌለው ፖሊሲው መሰረታዊ በሆነ መንገድ አይለወጥም ። በእነዚህ ምክንያቶች ስርአቶቹ እስከመጨረሻው እስከሚፈራርሱና ፣ እስከሚወድቁ ድረስ የመጠበቅ ሁኔታ ይከሰታል ።

 

የስርአት መፍረሶች የሚከሰቱበት በርካታ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ለምሳሌ ችግሮችን መፍትሄ አለመስጠት ፣ ዋና ዋና አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮችን ማድበስበስ ፣ መሰረታዊ ከሆኑ የረጅም ገዜ ያገሪቱ ጥቅሞች ይልቅ ለአጭር ጊዜ አላማና ግብ ማተኮር ፣ ጨርሶ አለማንሳት ወይም ማቃለል ፣አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ የሆነ ውይይትም ሆነ መግባባት ሳይኖር ለረጅም ጊዜ መቆየት ፤ፓርቲዎች በረጅም ጊዜ በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ላይ ሊያሳርፉ የሚችሉትን በጎ አሻራ (Legacy) ከማሰብ ይልቅ የአጭር ጊዜ ግቦችንና ጥቅሞችን ማስቀደም ናቸው ።

 

ከዚህም ሌላ ደግሞ በተለይም ቀይ ሽብር ካደረሰው የሞራል ድቀትና ፣ የፍርሀት አዙሪት ፖለቲካና ኮሬንቲ በሩቁ በሚል አስተሳሰብ የተማረውና አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል ከፖለቲካና ከመንግስት ጉዳይ ርቆ በግልና በመንግስታዊ ባልሆኑ ስራዎች መሰማራት ፣ የተቀረውም ከሀገር ውጪ በተለያዩ ሀገራት መሰራጨት ፣ በፖለቲካው መስክ ብቃትና አቅም ያላቸው በርካታ መሪዎችንና ተከታዮችን ለማፍራት ያስችል የነበረውን እድል አጥቦታል ።ይህም ብቻ ሳይሆን በፖቲካው አለም ያሉት ዋና ዋና ተዋናዮች በአንድ የታሪክ ወቅትና አጋጣሚ የነበረው ትውልድ አባላት በመሆናቸው ፣ እርስ በእርስ እስከመጋጨትና የደረሱ በመሆናቸው የፖለቲካ ልዩነታቸው ከአብዮቱ ማግስት ጀምሮ የተፈጠረና እየተብላላ የመጣ ሲሆን ድርጅቶቹ እርስ በእርስ ግጭትም ድረስ የተዳረሱ ነበሩ ።

 

 ዲሞክራሲ ባደገባቸው ሀገራት ብንወስድ የምርጫ ዘመቻ ሰሞን ዋናው ክርክር የሚካሄደው በፖሊሲ፣በህግ ፣ በአፈፃፀም፣በስትራቴጂና ከአተገባበር ጋር በተገናኘ ባሉ ጉዳዮች ላይ ነው እንጂ ዋናው የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ህገ – መንግስቱ ጉዳይ ላይ አይደለም ። ነገር ግን ብሄራዊ መግባባት በሌለባቸው ሀገራት በህገ – መንግስቱ ላይ ሙሉ ስምምነት የለም ።    

 

ህገ – መንግስትን ብንወስድ የብዙሁኑ ዜጎች መግባባትን የሚጠይቅ ሲሆን ፣ በአንድ ሀገር ምርጫ ሲመጣ  አብዛኛው ክርክር የሚካሄደው በህገ – መንግስቱ ዙሪያ ሲሆን ሲጀመርም ብሄራዊ መግባባት ቢኖር ኖሮ በህገ – መንግስቱም ላይ ያን ያህል ልዩነቶች ባልታዩ ነበር ።

 

በዚህ በኩል ምእራባውያንን ብንወስድ ብዙ ጊዜ የረጅም ጊዜ ግብንና አላማን ነው የሚተከሉት ። በዚህ በኩል የረጅም ጊዜ ልምድና ተሞክሮው አላቸው ። አንድን ነገር ሲሰሩ በረጅም ገዜ ዘላቂ መሆኑን በማየት ነው ። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አሜሪካኖች ጃፓንን አሸንፈው አገሪቷን ሲቆጣጠሩ ፣ የጃፓን ንጉስ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ስለሚያውቁ የጃፓንን ንጉስ ለማዋረድም ሆነ ለፍርድ ማቅረብ አልደፈሩም ። ሌሎች የጦር አዛዦች ለፍርድ ሲቀርቡና ሲጠየቁ እንኳን የንጉሱን ስም እንዳያነሱ ተደርጓል ። የተያዙት ጄኔራሎች ለፍርድ ቀርበው በሞት ሲቀጡ የነሱ ሁሉ የበላይ አዛዥ የነበረውን ንጉሰ ነገስት ግን አልነኩትም ።

 

ይህም የጃፓን ንጉስ ለጄኔራሎቹ የጦርነቱን ፈቃድ የሰጠ መሆኑን አጥተውት አይደለም ። ነገር ግን የጃፓን ንጉስ የፀሀይ ልጅ ነው ተብሎ በህዝቡ ይታመን ስለነበረ ያንን የህዝቡን እምነት ላለመንካትና የጃፓንን ህዝብ ድጋፍ ለመያዝ እንደሚያስችላቸው በሚገባ በመረዳታቸው ነው። ይህንን በማድረጋቸው ንጉሰ ነገስቱን ባለመንካታቸው ፣ የጃፓንን ህዝብ ባለማዋረዳቸው ከዚያ በኋላ ጃፓንና አሜሪካ ያላቸው ግንኙነት በአለም ላይ ካሉ ሀገራት እጅግ በጣም የጠበቀ የጋራ ጥቅምንና ትብብርን የያዘ የሚባል  ግንኙነትን ለመመስረት ችለዋል። በእስያ ሀገራት ካሉ ሀገራት  ጃፓን ዋናዋ የአሜሪካ ሸሪክና ወዳጅ ነች ።

 

በተመሳሳይም አሜሪካኖች ኢራቅን ወረው ሳዳም ሁሴንን ከስልጣን ሲያስወግዱ ሱኒዎችን የሳዳም ደጋፊ አድረገው በመውሰድ ስልጣኑን ለሺአዎች ነበረ የሰጡት ይሁን እንጂ ከዛ በኋላ የተፈጠረው አመፅ በርካታ ሺ ዜጎችን ያለቁበት የእርስ በእርስ ጦርነትን ፈጥሯል ። ሆኖም ወዲያውኑ ችግሩን የተረዱት ፣ ሱኒዎችን በመንግስት ስልጣን ውስጥ እንዲሳተፉ በማድረግ የሱኒዎችን አመፅ ማለዘብ ችለዋል ።ይሁን እንጂ አንዱ ወገን ብቻ ስልጣኑን ይዞ ቢቀጥል ኖሮ ያቺ ሀገር ሰላም አይኖራትም ነበረ ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s