የካፒታሊዝም ስርአትና ተቃርኖዎቹ

ካርል ማርክስ የተነተናቸው የካፒታሊዝም ስርአት ድክመቶችና ውስጣዊ ተቃርኖዎች አንዳንድ ፍንጮችን ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው፣ የካፒታሊዝም ስርአት ምርትንና ፍጆታን ማመጣጠን ስለማይችል ውሎ አድሮ ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ይፈጠራል የሚል ሲሆን በአሁኑ ወቅት በምእራቡ አለም ፣ በአውሮፓም በአሜሪካም መንግስት ሊገታው ያልቻለ የስራ አጥነት መጨመር መታየት ሲጀምር መንግስታት የመንግስት ወጪን በመጨመር ስራ አጥነትን እንቀንሳለን በሚል እርምጃን ሲወስዱ ይታያሉ ። የካፒታሊዝምን ስርአት ተቃራኒው የማርክሲዝም ስርአት እንደመሆኑ ፍልስፍናውን ለማነፃፀሪያ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ።

ምንም እንኳን  ስር ነቀል የሆነው የማርክሲዝም ስርአት ከአለም ላይ የተወገደ ቢሆንም ፣ እና ማርክሲዝምን እንከተላለን የሚሉትም እንደ ቻይና ፣ ቬትናም ፣ ኩባ የመሳሰሉት ፖለቲካውን ትተን ምጣኔ – ሀብቱን ብቻ ብንመለከት ሳይቀሩ ምጣኔ – ሀብታቸው በካፒታሊዝም ስርአት እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል ።፣ ይሁን እንጂ ካርል ማርክስ በካፒታሊዝም ስርአት ላይ የሰነዘራቸው ትችቶች ቀላል ቦታ እሚሰጣቸው አይደሉም ። በተለይም በምእራቡ አለም የምጣኔ – ሀብት ቀውሶችና መቀዛቀዞች በተደጋጋሚ እየጎበኛቸው ባለበት ሰአት አንዳንዶች ራሱን የካፒታሊዝምን ስርአት ደግመው ለመቃኘት ሙከራ አድርገዋል ።

ካርል ማርክስ በፃፋቸው በርካታ ዳጎስ ባሉ መፅሀፎቹ የካፒታሊዝምን ስርአት ያለምህረት መተቸቱ የሚታወቅ ሲሆን ፤ የማርክስ ትችት የካፒታሊዝም ስርአት ውስጣዊ ተቃርኖዎችን (Inherent Contradictions) ይዟል የሚል ነው ። ዋናው በማርክስ የተጠቀሰው የካፒታሊዝም ስርአት ያመረተውና የሚጠቀመው እኩል አይሆንም የሚል ነው ። ሌላው ደግሞ ሰራተኛው በላቡ በፈጠረው ሀብት ወይም እሴት አብዛኛውን ካፒታሊስቱ ወይም የምርት ሀይሎችን የተቆጣጠረው ነው እሚወስደው ነው ሰራተኛው ከላኑ በታች ነው ደሞዝ እሚከፈለው የሚል ሲሆን በዚህም ሰራተኛው ያመረተውን በመሰብሰብም ካፒታሊስቱ የሀብት ክምችትን (Capital Accumilation) እንደሚፈጥር ይታወቃል፣ ይህም ሰራተኞች ከጋገሩት ኬክ ውስጥ የነሱ ድርሻ እያነሰ መሄድ የሌለበት ሲሆን ፤ ሶስተኛው ደግሞ የካፒታሊዝም ስርአት የስራ አጥ ቁጥሮችን ይፈጥራል የሚል ነው ። የእሱ ትችቶችም የካፒታሊዝምን ስርአት ለመጠገንና ማሻሻያዎችን ለማድረግ ረድተዋል ። ኡደትን ጠብቆ በሚፈጠር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መዳከም (Recession) ምክንያት ከስራ እሚባረሩ ሰራተኞች ለጊዜውም ቢሆን (Welfare) እንዲከፈላቸው የመሳሰሉት ከማርክስ ትችቶች በመነሳት የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው ።

የማርክስ ፍልስፍና በኋላ ላይ የሌኒን ስም ቢጨመርበትም ዋናው ፈጣሪው ግን ራሱ ማርክስ መሆኑ አያጠራጥርም ፣ እንደ አንዳንዶች ማርክሲዝምን በሌኒንና በሌሎችም በተለይም የሩስያ ቦልሺቪኮች አስዋፅኦ ምክንያት እንደ ምስራቃዊ ፍልስፍና የሚቆጥሩት ያሉ ቢሆኑም ፣ ማርክሲዝም ግን መሰረቱ የምእራቡ ፍልስፍና ውጤት ሆኖ ከምእራባውያን ፍልስፍና ዘውግ የሚመደብ ነው ። ለዚህም አይነተኛው መከራከሪያ የሚሆነው ማርክሲዝም በዝግመተ – ለውጥ ፅንሰ – ሀሳብ ላይ ተመስርቶ የተገነባ ፍልስፍና መሆኑን በማየት ነው ።

ዋናው የማርክሲዝም ወደ ተግባር ሲቀየር ያለበት አንዱ ችግር አመራሩ በተመለከተ ነው ። ሁለት ፅንፎች ሊከተሉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል ፤ ለምሳሌ በአንድ በኩል ሲጀመር ወደ ብዙሀን አገዛዝ ወደ ሞብ አገዛዝ ሊቀየር ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ በጊዜ ሂደት ወደ ጥቂቶች ልሂቃኖች (Elits) አገዛዝ ሊቀየር ይችላል ። ይህም በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እንዲሁም በቻይና ፣ በቬትናም ያለው አገዛዛዝ ስልት ነው ። ብዙሀኑን መወከሉ ቀርቶ እዛው በስፈፃሚና በፖሊት ቢሮ ውስጥ በሚደረጉ የእርስ በእርስ መመራረጦች አመራሩ እዛው እርስ እርስ በእርሱ እየተተካካ ሊቀጥልና ፣ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ማድረግ የማይችልበት ግትር ወደ ሆነ አገዛዛዝ ሊቀየር ይችላል ።

ማርክስ የካፒታሊዝም ስርአት በአመፃ መለወጥ አለበት ብሎ የሚያምን ሲሆን ብር ፣ በርካታ የምእራብ የካፒታሊስት ምሁራን ይህንን የማርክስን ሀሳብ አይቀበሉትም ። ምንም እንኳን ካርል ማርክስ የካፒታሊዝምን ስርአትን ውስጣዊ ምንነትና አሰራርን የተነተነ ቢሆንም፤ ሀይል አዲሱን ስርአት ያረገዘው የአሮጌው ስርአት አዋላጅ ነች ብሎ ለሚያምነው ፣ እንዲሁም በዝግመተ – ለውጥ አስተሳሰብ ለሚያምነው እንዲሁም የሽረት ሽረት ህግ ስርአተ ማህበሮችን ይለውጣል ለሚለው ማርክስ በአመፃ የካፒታሊዝም ስር አት ተለውጦ ወደ ኮሚኒዝም መሸጋገር አለበት ቢል አስገራሚ አይሆንም ።

ነገር ግን እዚህ ጋ መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች አሉ ። አንዱ አንድ ስርአት ሊለወጥ የሚደርስበት ወቅት መቼ ነው ? ጠቢቡ ሰለሞን «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንደሚለው ሁሉ የአብዮቶችን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅት በራሱ ፈታኝ ነው ። ምንም እንኳን ሀይል የአዲሱ ስርአት አዋላጅ ብትሆንም ያ ስርአት ሊለወጥ በሚደርስበት እና በመቀጠል በማይችልበት ወቅት ብቻ ነው በተሳካ ሁኔታ አዲሱ ስርአት ሊተካ የሚችለው ። በማርክስ ትንተና መሰረት ስርአተ – ማህበሮች ከባርያ አሳዳሪው ወደ ፊውዳል ፣ ከፊውዳል ወደ ቡርዧ ወይንም ወደ ካፒታሊዝም ስርአት በሽረት ሽረት ህግ እየተተካካ መጥቷል ፣ ነገር ግን እነኚህ የስርአት መተካካቶች እንዲሁም ፣ አንዱ ስርአት አንዱን የተካበት መንገድ መንገድ በአዝጋሚ ለውጥ መሆኑንም ይታወቃል ። ነገር ግን ስርአተ – ማህበረች በአዝጋሚ – ለውጥ ብዙ አመታትን ሲተካኩ እንደመጡ እየታወቀ ፣ ከካፒታሊዝም ወደ ኮሚኒዝም ስርአት የሚደረገው ሽግግር ግን በአመፃና በአብዮት የሚሆንበት ምክንያት ነው ። ሌሎቹ ስርአቶች እንደተተካኩት በአዝጋሚ ለውጥ ሽግግሩ ለምን አይፈፀምም የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ።

ይሁን እንጂ ሌሎችም ምክንያቶች ቢኖሩም በምእራቡ አለም ካፒታሊዝም ይህንን በ2008 የተከሰተውን በአንድ ጊዜ ከቁጥጥር ውጪ እስከመውጣት ድርስ የሚያስፈራውን ቀውስን ያስከተለበት ዋናው ምክንያት በራሳቸው በምእራባውያን ኢኮኖሚስቶች አገላለፅ በጣም ልል የሆነ ፣ ቁጥጥር ሳይደረግበት የቀረ የገበያ በተለይም ልቅ የሆነ የፋይናንስ ስርአት የፈጠረው ነው ፤ በተለይም በገንዘብና በባንኮች ዘርፍ ሊደረግ ይገባ የነበረው የመንግስት ክትትል አለመደረግ ይህንን ቀውስ ፈጥሯል የሚል ነው ። ሌላው ምክንያት ወንጀል ሲሆን በተለይም በፋይናንሱ ዘርፍ የተፈፀሙ ወንጀሎች እንደ ፖንዚ ስኪም አይነቶች በርካታ የጡረተኞችን ገንዘብ በልቷል ፣ የፖለቲካ መሪዎቹ ሴናተሮች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ራሳቸው ከሀብታሙ መደብ የወጡ በመሆናቸው እና ለመመረጥም የሚረዳቸውን አብዛኛውን የገንዘብ ድጋፍን እሚያገኙትም ከኮርፖሬሽኖችና ከባንኮች ስለሆነ ፤ የፖለቲከኞችና የንግድ ኮርፖሬሽኖች እጅና ጓንት የፈጠሩበት ጥምረት ብዙሀኑን የመካከለኛውን መደብ እያደኀየው ሲሄድ ባለሀብቶችን ግን እየከበሩ እንዲሄድ አስችሏቸዋል ። አንዳንዶች ይህን አሰራር ተቋማዊ ሙስና (Institutional Corruption) በማለት ይጠሩታል ።

የሊበራሊዝም (Liberalism) ስርአት በራሱ ላይ መልሶ የሚባርቅ ነው ማለት ይቻላል ።  በአሜሪካን አገር መገናኛ ብዙሀን በመንግስት እጅ ሳይሆን በግል እጅ መሆኑ መንግስት ህዝቡን እንዳያፍንና ግዙፍ እንዳይ ሆን ይረዳል ፣ እንዲሁም መንግስት መረጃን በመቆጣጠር የህዝቡን ነፃነት እንዲያፍን ያደርገዋል በሚል መገናኛ ብዙሀን በግል ኮርፖሬሽኖች እጅ ነው ። ነገር ግን ይህ አሰራር ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎች የተለያዩ አ ክስዮኖችን በሚዲያ ተቋማት ውስጥ በመያዝ ፣ ወይም ሙሉ በሙሉ ንብረታቸው በማድረግ ፣ የመሪዎችን የምርጫ ሂደት መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ድረስ አድርሷቸዋል ። ለምሳሌ በእንግሊዝ  አገር የነበረው የሩፐርት መርዶክ ኩባንያ ኒውስ ኦፍ ዘወርልድ እጅግ ሀያልና የሚፈራ ከመሆኑ የተነሳ ፣ በአሜሪካም ሆነ በእንግሊዝ የእርሱን ጋዜጦችን ፣ ቲቪን ፣ ኦንትርኔትን ሚዲያዎችን ድጋፍ በማግኘት ከርእሰ – አንቀፁ ጀምሮ እንዲመረጡ የሚፈልጓቸውውን ፖለቲከኞች ድጋፍን ሲሰጡ ፣ በአንፃሩ የማይፈልጓቸውን ግን ስም የማጥፋት ፣ የማጥላላት ዘመቻ በማድረግ እንዳይመረጡ የማድረግ አቅም አላቸው ። ይህንንም በመረዳት የፖለቲካ መሪዎች መመረጥ በሚፈልጉበት ወቅት የግድ የእነኚህን መገናኛ ብዙሀንን ድጋፍን መለማመጣቸው እርግጥ ነው ያለበለዚያ ግን የራሳቸውን የፖለቲካ ህይወትና የፓርቲያቸውን እድልን እንደሚያበላሹ ያውቁታል ። 

ይህም የንግድ ኩባንያዎችና ኮርፖሬሽኖች አንድ ህግ ወይም ደንብ ኮንግሬሱ ሲያወጣ ኮርፖሬሽኖች በራሳቸው ድጋፍ አሰባሳቢዎች (Lobbyists) አማካይነት አይተውትና ደግፈውት ከዛ በኋላ ነው ኮንግሬሱ እሚያሳልፈው ። ይህ አሰራር ፖለቲከኞች የኮርፖሬሽኖችን ገንዘብ እና ድጋፍን የሚፈልጉ  ስለሆነ የነሱን ድጋፍ ማጣትን የማይፈልጉ ሲሆን ፣ በአንፃሩ ግን የብዙሀኑ ጥቅም ወደ ጎን እንዲገፋ ሲያደርግ ፣ በብዙሀኑ ጥቅም ኪሳራ ኩባንያዎቹ አትራፊ እንደሚሆኑ ግልፅ ነው ። ማንኛውንም ኮንግሬሱ የሚወጣውን ህግ ኩባንያዎቹ በሚቀጥሯቸው ድጋፍ አሰባሳቢዎች አማካይነት የሚያዩትና ፣ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲቀረፅ እሚያደርጉ ሲሆን ፣ ትላልቅ ባንኮችና የገንዘብ ተቋማት ፣ የመድሀኒት ፣ የኬሚካልና የምግብ አምራች ሁሉ በእንደዚህ አይነት መንገድእሚፈልጉትን ከህዝቡ በስተጀርባ በቀላሉ ሲያገኙ ኖረዋል ። ይህም ውሎ አድሮ ህዝቡና አገሪቱ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ሲሆን የህዝብ ተቃውሞን ፈጥሯል ።

ካፒታሊዝም ስርአት ካፒታሊስቶችን ምን ያህል ከለላ እንደማያደርግ ለመረዳት ፣ ኮርፖሬሽኖች እንደ አንድ ሰው ነው የሚቆጠሩት ። ይህም ማለት ኮርፖሬሽኖች ጥፋትን ቢያጠፉ ለምሳሌ በአካባቢ ላይ ጉዳትን ቢያደርሱ ፣ ወይም አጠቃላይ ማህበረሰቡን የሚጎዳ ነገርን ቢፈፅሙ እንደ አንድ ግለሰብ ተቆጥረው የሚጠየቁት ኮርፖሬሽኖቹ ናቸው እንጂ ወደ ባለቤቶቹ የሚመጣ ነገር የለም። ኩባንያዎቹም የራሳቸው ጠበቃና የራሳቸው የአስተዳደር ቡድን የመሳሰለው ራሳቸውን የሚከላከሉበት መንገድ ስላላቸው ብዙ ጊዜ ጥፋትን ሲያጠፉ እምብዛም ተጎጂ ሳይሆኑ ህልውናቸውን ማስጠበቅ ይችላሉ ።

ይህም ውሎ አድሮ በህብረተሰቡ ዘንድ ሁለት ፅንፎችን ይፈጥራል ። በአንድ በኩል በሶሻሊዝም ፣ በኮሚኒዝም እና በሰራተኛው መደብ እንቅስቃሴ ወዘተ አቀንቃኞች ሲፈጠሩ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የካፒታሊዝም አክራሪ ሀይሎች ፣ ወግ አጥባቂዎችና ሌሎችም አክራሪ ሀይሎች ይፈጠራሉ ፣ይህም በአሜሪካን አገር በ2008ዓ.ም ከተፈጠረው በኋላ ግራ ዘመም ሀይሎች ማለትም የአለም የገንዘብ ዝውውር ማእከል የሆነውን ዎል ስትሪትን መቆጣጠር ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቲ ፓርቲ እንቅስቃሴ የሚባለው የቀኝ አክራሪ ቡድንም በሪፐብሊካን ፓርቲው ውስጥ የባሰ አክራሪ ሆኖ እንዲወጣ አድርጎታል ።

በነገራችን ላይ የዚህ አይነት መሰረተ ሰፊ የሆነ ምጣኔ – ሀብታዊ ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት ፅንፍና ፅንፍ የሆኑ ፣ በሁለት አቅጣጫ የሚጎትቱ ሁለት ተቃራኒ ሀይሎች ይፈጠራሉ ። በ1930ዎቹ ተፈጥሮ በነበረው ታላቁ የአለም ምጣኔ – ሀብት መቀዛቀዝ ወቅትም እንዲሁ ሰራተኞችና ገበሬዎች የነበሩበት ሁኔታ አስከፊ የነበረ ሲሆንገበሬዎች መሬታቸው በባንክ እዳ የተያዘበትና ሰራተኞችም በገፍ ከስራ የተፈናቀሉበት ሁኔታ የነበረ ሲሆንበወቅቱ የነበረውም ሁኔታ አይን ያወጣ የሀብታሞች አገዛዝ (Plutocracy) ተቀይሯል ። ይህንን በመረዳት ጥቂቶች ስርአቱን ለዘብ በማድረግ የስርአቱን ህልውና ለማስጠበቅ ሲጥሩ ሌሎች ደግሞ ነባራዊውን ሁኔታ ባለመረዳት ጭራሽ ጨቋኝ የሆኑትን የስርአቱን ጎኖችን ይበልጥ በማጥበቅ ስርአቱን ወደ ባሰ ችግር ውስጥ የሚጨምሩ አሉ ።

ይህንም በመከተል በአንድ በኩል ፣ ሶሻሊስቶች፣ ኮሚኒስቶችና አናርኪስቶች አብዮት ማስነሳት እንችላለን ብለው ያስቡ የነበረበት ወቅት ነበረ ፣ በሌላው ፅንፍ ደግሞ ቀኝ አክራሪዎችና ፋሺስቶችና አፍቃሪ ናዚዎች ማቆጥቆጥ ጀምረው የነበረበት ወቅት ነው ። ይሁን እንጂ በወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የነበሩት ሩዝቬልት ከሁለቱም ፅንፍ አስተሳሰብ ተፅእኖ ስር ሳይወድቁ ፣ ነገር ግን የብዙሀኑን ህዝብ ችግርን የሚፈታ መንገድን በመከተላቸው ምክንያት በተሳካ ሁኔታ ያቺን አገር ከነበረችት አስከፊ ሁኔታ ማላቀቅ ችለዋል ።

ይህም የዲሞክራሲን ስርአት ከብዙሀን አገዛዝ ወደ ጥቂት ሀብታሞች አገዛዝ (ኦሊጋርኪ) እንዲቀየር ያደርገዋል ። ሀብታሞቹ በሚቆጣጠሯቸው ድርጅቶች አማካኝነት ፖለቲካውንም በእጃቸው በማስገባት ሀገሪቱን እነሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ እንድትመራ ማድረግ ችለዋል ። በነገራችን ላይ ከአሜሪካን ፕሬዝደንቶች ዊድሮው ዊልሰን በዚህ ማለትም የሀብታሞች አገልጋይ መሆናቸውን ያማርሩ የነበሩ በመሆናቸው ይታወቃሉ ። አንዳንድ ጊዜ አጠራሩ (Plutocracy) ሲሆን ይህም የሀብታሞች አገዛዝ በመባል የሚታወቅ የአገዛዝ ስልት ሲሆን ፣ የትኛውም ሀገር ግን ይህን በይፋ አያምነውም ፣ ካፒታሊዝም ባደገባቸው ሀገራት የሚታይ በተለይም እንደ አሜሪካ ባሉት ሀገራት ላይ በስፋት የሚታይ ነው ።

ከ2008 የአለም የገንዘብ ቀውስ ወዲህ የወጡ በርካታ ሪፖርቶች የጠቆሙት ይህ ብቻ ሳይሆን የፋይናንሱ ዘርፍ ፖለቲከኞችን በመደለል በጣም ልል የሆኑ ፖሊሲዎችን ማውጣታቸው ፣ ጋዜጠኞች እንደዘገቡት ከኮንግሬስ አባላት በላይ ቁጥር ያለካቸው ድጋፍ አሰባሳቢዎች (Lobbyists) በኮንግሬሱ ላይ ጫና እንዳደረጉ ፣ ሀገራትንም ሳይቀር እርስ በእርስ በማፎካካር በጣም አንዱ ካንዱ ልል የሆነ ፖሊሲን በማውጣት እንዲያወጡ ማድረጋቸው ፤ እንዲሁም የገንዘብ ዘርፉ በጣም የራሱን ሀገር በእዳ አበዳሪ በመሆና ፣እንዲሁም በወቅቱ የአሜሪካ የማእከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩት አላን ግሪንስፓን ለረጅም አመታት የወለድም ምጣኔውን በጣም ዝቅ በማድረግ የመበደሪያ ዋጋውን ከገበያው ዋጋ በታች እንዲሆን ለረጅም አመታት ዝቅ ማድረጉ ፣ የቤቶች ዋጋን ከሚያወጡት በላይ እንዲያሻቅብ በማድረጉ ምክንያት እንደ አንድ ምክንያት ይፈጠራል ። ለምሳሌ እንግሊዝን ብንወስድ ከሚሰበስቡት ታክስ ውሰጥ ሩብ የሚሆነውን የሚሰበስቡት ከገንዘብ ተቋማትና ከባንኮች ሲሆን ይህም የመንግስታቸው ዋናው የገቢ ምንጭ ነው ።

ለዚህ ቀውስ አስፈላጊ የነበረው ውሳኔ አሰጣጥ በዘመናዊው የዲሞክራሲ አለም ዝግ ያለ መሆኑ ራሱ አንዱ ችግሩን ያባባሰ ነው ። በፓርላማ ውስጥ ረጅም ሰአትን የፈጀ ውይይት ተደርጎ ፣ ጊዜ ተወስዶ አንዳንዴም ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ እስከመጠየቅ በመድረሳቸው እንደ ግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ያሉት ፓፓንድርዩ ያሉት ነገሩን ይበልጥ ማወሳሰብና የማባባስ ውጤትን አስከትሏል ።

በተለይም እ.አ.አ. ከ2008ቱ ከተከሰተው የአለም የፋይናንስ ቀውስ ወዲህ በምእራቡ አለም ከዚህ በፊት እንደትክክል ተደርገው ሲታመንበት የቆየው ካፒታሊዝም (Capitalism) ለምን ለውድቀት ዳረገን የሚሉ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ናቸው ። በተለይም ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ይሰራል ሲባል የነበረው ካፒታሊዝም አንዳንድ መርሆዎቹ ጥያቄ ውስጥ ወድቀዋል ። በአንፃሩ ደግሞ በአፍሪካና ፣ በእስያና በሌሎችም በማደግ ላይ ያሉ ናቸው በሚባሉት ሀገራት ይህንኑ የካፒታሊዝምን አስተሳሰብ በመጠቀም የምጣኔ – ሀብት እድገት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዳግም በማንሰራራት ላይ ይገኛል ።

በእርግጥ ሀገሮች ሁሉ የካፒታሊዝምን ወይም የነፃ ገበያ ስርአትን ቢከተሉም ሙሉ ለሙሉ ፍፁም ተመሳሳይ ፖሊሲንና አፈፃፀምን ይከተላሉ ማለት አይደለም ፣ በሀገሮችም መሀከል ልዩነት አለ ። ሜክሲኮና ብራዚል የነፃ ገበያን መርህ በመከተል እድገትን እያሳዩ ያሉ ሀገራት ሲሆኑ የገቢ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ቤተሰቦች በተለያየ መንገድ ድጋፍን ያደርጋሉ ። ስለዚህ ምንም እንኳን ሰፊ የገቢ ልዩነት በእነኚህ ሀገሮች የሚታይ ቢሆንም በምእራቡ አለም እንደሚታየው አይነት ካፒታሊዝም አይደለም ። በእስያም ያለው ካፒታሊዝም እንደ ምእራቡ አለም ካፒታሊዝም ሁሉን ነገር ለግሉ ባለሀብት ሳይሆን የበለጠ ቁጥጥርን ያሰፈነና የተሻለ ፍትሀዊ ነው ። እንደ ሲንጋፖር ፣ ደቡብ ኮርያ ያሉት ሀገራት ካፒታሊዝምን ሲጀምሩ በአንድ ወጥ አገዛዝ (Autocracy) ስር ሆነው ሲሆን የጀመሩት ፣ ነገር ግን ውለው አድረው ወደ ሙሉ የዲሞክራሲ ስርአት ሊሸጋገሩ ቢበቁም ፣ ነገር ግን እነሱም ቢሆኑ የአሁኑም ስርአታቸው ቢሆን እንደ ምእራቡ አለም ሁሉንም ነገር ነፃ እና ከቁጥጥር ውጪ ያደረገ አይደለም ።

ሁሉንም ነገር ነፃ ማድረግ ማለትም የኒኦ – ሊበራል አስተሳሰብ በአንድ በኩል እውነታውን ካለማወቅ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአለም ዙሪያ ገበያዎች ነፃ ቢደረጉ መወዳደር እንችላለን ብለው የሚያስቡ ግዙፍ አለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች ያስፋፉት አስተሳሰብ እንደሆነ መገመት ይቻላል ።

ወደ ምእራባውያን የካፒታሊዝም ስርአት ስንመለስ የስርአቱ ተቃርኖዎች ያሉት በምርት ሂደቱ ውስጥ ሲሆን ፣ ይህ ስርአት ጠንካራ ጎኖችም አሉት ። ተፈጥሮአዊ ከሆነው የሰው ልጅ ባህሪ ማለትም ፣ በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ፣ ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብትን እንዲሁም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እሚያከብር መሆኑ ፤ የስርአቱን ጥንካሬ ሲያሳይ ፣ ችግሮች ቢያጋጥመውም ለዘብ ያሉ ፖሊሲዎችን በመከተል ከችግሮች እየወጣ ላለፉት አምስት ለመቶ አመታት መጓዝ ችሏል ። ይህ ስርአት ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ራሱን እየቀየረና እያሻሻለ መጓዝ ችሏል ።     

ካርል ማርክስ በካፒታሊዝም ስርአት ውስጥ አሉ ብሎ የጠቆማቸው ተቃርኖዎች በካፒታሊስቱ አለም ለተከሰቱ ቀውሶችን ሊገልፁ ይችላሉ ። በእርግጥ ሌሎችንም በአለም ላይ የሰው ከልጅ የፈጠራቸውን ነገሮች ብናይ ብዙዎቹ ነገሮች በትክክል ሚዛናቸውን ጠብቀው የተገነቡ አይደሉም ። ለምሳሌ የአለምን አለም አቀፋዊ ግንኙነት ብናይ፣ አውዳሚ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ባለቤት ለመሆን እሚደረገውን እሽቅድምድም ፣ የአለማችን አየር ንብረት ለውጥ ፣ የአካባቢ መበከልን እነኚህ ሁሉ ሰውን ብቻ ሳይሆን ህይወት ያለውን ፍጥረት ከምድረ – ገፅ ማጥፋት እሚችሉ አደጋዎችን በውስጣቸው ያዘሉ ቢሆንም ፣ የሰው ልጅ ኑሮ ግን በእነኚህ ነባራዊ እውነታዎች ውስጥ ሆኖ ነው የሰው ልጅ የሚኖረው ።

ይህም የሚሆንበት ምክንያት የሰው ልጅ ማንኛውንም ነገር ሲሰራ በመጀመሪያ ከራሱ ጥቅም ስለሚነሳ መሆኑ ሲሆን ሌላው ደግሞ ካለማወቅ እንዲሁ ዘላቂ ያልሆኑ ነገሮችን ቋሚ እንደሆኑ አድርጎ የመውሰድ ሁኔታዎችም አሉ ። የአየር ንብረት ለውጥን (Climate Change) ብንወስድ ምንም እንኳን የአየር ንብረት እንዲበከልና ፣ የተፈጥሮ አካባቢ እንዲወድም እያደረጉ ያሉት ትላልቅ ኢንዱስትሪ ያላቸው በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገራት ቢሆኑም ፣ ብክለቱን ለማስቆም ግን ፋብሪካዎቻቸው ላይ ግብርን ለመጨመር ፣ ወይም ብክለትን እሚቀንሱ ውድ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም አይፈልጉም ። ምክንያቱም ወጪአቸውን ከፍ ስለሚያደርግና ትርፋቸውን ስለሚቀንስባቸው ሲሆን ፣ በማደግ ላይ ያሉትንም ሀገራት ብወስድ ደኖችን እየመነጠሩ ሰፋፊ ገንዘብ እሚያስገኙ እርሻዎችን እያስፋፉ ሲሆን ፣ በርካታ ኢንዱስትሪዎችንም በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ስርአት ህዝቡ ነቅቶ ካልጠበቀና ነገሮች ከእጅ ከመውጣታቸው በፊት ካልተከታተለ፣ ነገሮች ተበላሽተው ወደ ማይጨበጥ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ። ለዚህምምክንያቱ በአንድ በኩል ስርአቱን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚጠቀሙበት ሰዎች በራሱ በስርአቱ ውስጥ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ፣ ስርአቱን አቅጣጫውን በማስቀየር ከሀዲዱ የሚያስቱ ሀይሎች የመፈጠር እድላቸው ሰፊ ስለሆነ ነው ።

በእርግጥ እዚህ ጋ የአየር ንብረት ለውጥ በአለም ላይ እንዲከሰት ያደረጉት ሀገራት ያደረሱት ጉዳት የበለጠ በመሆኑ ለማስተካከያውም ሸክሙንም መሸከም የነበረባቸው ቢሆንም ፣ ችግሩን ለመቋቋም እሚያስፈልገውን ከፍተኛ ወጪ ማውጣት አይፈልጉም ። ስለዚህ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ሲገኝ ፣ ውሎ አድሮ መገታት ካልቻለ በአለም የግብርና ምርት ፣ በሰው ልጅ ጤንነት ፣ የንፁህ ውሀ አቅርቦት ፣ በእፅዋትና በእንሰሳት ህይወት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ። በተለይም ምእራቡ አለም ምጣኔ – ሀብታዊ ችግር ውስጥ በተለይም ምእራቡ አለም ምጣኔ – ሀብታዊ ችግር ውስጥ እገባ በሄደ ቁጥር መፍትሄው እየራቀና ይበልጥ እየተወሳሰበ እንደሚሄድ ገልፅ ነው ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s