እኩልነትን ማስፈን

በአለም ላይ በየትኛውም አገር ያለው ዋነኛ ፖለቲካዊ ሆነ ምጣኔ-ሀብታዊም ሆነ ሌላ ጥያቄ እኩልነትን ማስፈን ነው ። ታላቁ ግሪካዊ ፈላስፋ ፕሌቶ ሪፐብሊክ በተሰኘው ታላቁ ስራው ላይ ዋነኛው ጥያቄው የነበረው የፍትህ መስፈን ነው ። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ እኩልነትን ማስፈን በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ጉዳይ ነው ። ወደ ኋላ መለስ ብለን የሰውን ልጅ ሰብአዊ መብትን በማስከበር በኩል እጅግ ተራምደዋል የምንላቸውን ምእራባውያንን ታሪክ ብንመረምር አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ እንኳን በቀላሉ አልደረሱም  ። ምእራቡ አለም ሰውን በባርነት የሸጠበትና የገዛበት ፣ በባርነት የሰዎች  ጉልበት በነፃ የተበዘበዘበት ፣ ሰዎች እንደ እቃ የተሸጡበት ዘመን በጣም ሩቅ አይደለም ። ከዚያም በኋላ ቢሆን በአሜሪካን አገር ያሉ ጥቁሮች መብታቸውን ለማስከበር እጅግ መራራና ፣ እልህ አስጨራሽ ትግልን አካሂደዋል ። የሴቶችንም መብት ብንመለከት ሴቶች ከወንድ እኩል መብታቸውን ለማስከበር እንዲሁ ትግልን አካሂደዋል ። አውሮፓዊቷ ስዊዘርላንድ እንኳን ሴቶች የመምረጥ መብታቸውን ያረጋገጠችው እ.ኤ.አ. በ1974 እንደሆነ በታሪክ የተመዘገበ ነው ።

የእኩልነት የመስፈን ጥያቄ የህግ ፣ የፖለቲካ ወይንም የአንድ ሰው ወይንም ግለሰብ መብት የመከበር ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የአጠቃላይ የማህበረሰብ ደህንነትና ፣ የአንድ ማህበረሰብ ሞራል «ስነ- ምግባር» የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ።

መብቶች በህግና በህገ-መንግስት ቢረጋገጡም ወደ ተግባር መለወጡ ግን ሌላ እጅግ ፈታኝ ስራ ነው ።  ይህም በአሜሪካን አገር በግልፅ የሚያታይ ነው ። ምንም እንኳን አሜሪካ በህግ ለአፍሪካ አሜሪካውያን ከነጩ እኩል መብታ ቸውን ያረጋገጠች ብትሆንም ፣ እንዲሁም ጥቁሩ ባራክ ኦባማ ተመርጠው ዋይት ሀውስ ገብተው አሜሪካንን መምራት የቻሉ ቢሆንም ፣ በተግባር የጥቁሮች የኑሮ ደረጃ ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጣቸው ቦታ አሁንም ብዙም አልተለወጠም ፣ ገና ብዙ የሚቀረው ነው ። በዚያች አገር ብዙዎች በድህነት የሚማቅቁት ፣ በእስር ቤቶች ውስጥ በብዛት የሚገኙት እንዲሁም ከፍተኛው የስራ አጥ ቁጥርና የመሳሰሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በጥቁሮች ዘንድ ጎልተው ይታያሉ ።

የእኩልነት መከበር ጉዳይ በአንድ ወቅት  ተከብሯል ተብሎ የሚዘጋ ሳይሆን በዘመናት ሂደት ውስጥ ቅርፁንና ይዘቱን እየቀየረ የሚመጣ ጉዳይ ነው ። በነገራችን ላይ ምእራባውያን አሁን የደረሱበት ደረጃ ከፍተኛ ቢሆንም አዳዲስ የመብት ጥያቄዎች በራሱ ምእራቡ አለም ዘንድ እያቆጠቆጡ ነው ። ለምሳሌ በማይድን ህመም የሚሰቀዩ ሰዎች የመሞት መበት ፣ አደንዛዥ እፆችን የመጠቀም መብት፣ የማስወረድ መብት፣ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ጥያቄና እንዲሁም የማደጎ ልጅ የማሳደግ መብት ወዘተ የመሳሰሉት አሁንም ድረስ የምእራብ አገራትን የፖለቲካ ምርጫ ውጤትን የሚወስኑ እና የምእራባውያንን ህብረተሰብ እኩል በእኩል የሚከፋፍሉ ጉዳዮች ከሆኑ ውለው አድረዋል ።    

እኩልነት በፆታዎች መሀከል ፣ በተለያዩ ዘሮች ፣ በተለያየ የሀብት ደረጃ ባላቸው መሀከል ፣ የተለያየ የእውቀት ደረጃ ባላቸው ፣ የተለያየ ሀይማኖትን በሚከተሉ ማህበረሰቦች መሀከል እኩልነትን ማስፈን በሰው ልጅ የታሪክ ዘመን የነበረና ወደፊትም የሚኖር ጉዳይ ነው ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s