ፈላስፋውን እናስተዋውቃችሁ

‹‹የተግባራዊ የመሪነት ጥበብ›› መፅሀፍ ከደራሲና ፈላስፋ ከስሜነህ ተረፈ ጋር ኢቦኒ መፅሄት ያደረገችውን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን ፡፡
አዲስ የፃፍከውን መፅሀፍ አስመልክቶ የተደረገ ኢቦኒ መፅሄት ከደራሲው ጋር ያደረገችው ቆይታ፡፡ የተደረገ ቃለ ምልልስ
ስለ አንተ ማንነት ግለፅልን ? ከዚህ በፊት የነበረህ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ስሜነህ ፡- የስነ – ፅሁፍ ስራ ውስጥ ነው ያለሁት ፤ በኢኮኖሚክስ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲና ከዩኒቲ ዩንቨርስቲ የተመረቅሁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መፅሀፍቶችን በማሳተም ስራ እና የራሴን የግል ስራ በመስራት ነው ያለሁት ፡፡ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ነኝ ማለት እችላለሁ ፡፡
ኢቦኒ ፡ – መፅሀፉን ስትፅፍ ርእሱን እንዴት ሰጠኸው ? በገመድ ላይ የሚራመድ ሰውን የሚያመለክተውን የሽፋን ስእል ለምን መረጥከው ?
ስሜነህ ፡- የመፅሀፉን ርእስ ስመርጥ ተግባራዊ የምትለዋን ቃል በተለይ የመረጥኩብት ዋናው ምክንያት መፅሀፉ አላማ በተግባር ሊሰራ የሚችልን ሀሳብን ለመስጠት ነው ፡፡ በዚህ ዘርፍ በርካታ መፅሀፍት ተፅፈዋል ፤ ብዙዎቹ ትኩረት የሚያደርጉት ንድፈ-ሀሳባዊ የሆኑ እና ሲነገሩ ምክንያታዊ የሚመስሉ ነገር ግን በተግባር ሊውሉ የማይችሉ ወይም መተግበራቸው አጠራጣሪ የሆኑ ሀሳቦችን ሲያንፀባርቁ ይስተዋላል ፡፡ አንዳንዶቹ እንደዚህ አድርጉ ፤ እንደዚህ አታድርጉ የሚል ዝርዝር መመሪያን የሚሰጡ ናቸው ፡፡ ነገር ግን የኔ ዓላማ በተግባር መሪው ራሱ እንደ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ማድረግ ያለበትን እንዲያደርግና ይህን አድርግ ፤ ይህን አታድርግ በሚል መመሪያ ሳይታጠር በአስፈላጊ ሰዓት በአስፈላጊ ነው የሚለውን እንዲያደርግ እና ራሱን ሊያጋጥመው ከሚችለው ፈተና መወጣት እንዲችል ነው ፡፡ መሪነት ጥበብ ነው የሚለውን ሀሳብም የመረጥኩት ያለምክንያት አይደለም ፡፡ በዓለም ላይም ሆነ ባገራችን እጅግ ሰፊ የሆነ እውቀት በተለያየ የሙያ ዘርፍ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ ፡፡ ነገር ግን እነኚህ ሁሉ ሰዎች እውቀት ስላላቸው ብቻ ብቁና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሪዎች ይወጣቸዋል ማለት አይደለም ፡፡ መሪነት የፖለቲካ ተቀባይትን ፤ ህጋዊ የስልጣን ምንጭን ፤ ተከታይ ማፍራት መቻልንና ድጋፍን ጠብቆ ማቆየትን ይጠይቃል ፡፡ ስለዚህ መሪነት ጥበብ ስለሆነ ጥበብ ያላቸው ጥበበኛ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡
የሽፋን ስእሉ በድንገት እንደ ቀልድ የመጣልኝ ሀሳብ ነው ፤ በገመድ ላይ የመራመድ ስፖርትን በቴሌቪዥን እንከታተላለን እና መሪም ልክ በገመድ ላይ እንደሚራመድ ሰው በጥንቃቄና አመዛዝኖ እና ሚዛኑን ጠብቆ መጓዝ አለበት ከሚል የመነጨ ነው ፡፡ ከገመዱ ስር ያሉ ሰዎች የሰውየውን አረማመድ በጉጉት ይከታላሉ፡፡ በገመድ ላይ የሚራመድ ሰው ሚዛኑን ከሳተ እንደሚወድቀው ሁሉ መሪም ሚዛኑን በሚስትበት ወቅት ውድቀት ሊያጋጥመው ይችላል – ያን ለማመልከት ነው ፡፡
ኢቦኒ ፡ – የመፅሀፉ ስያሜ ከፖለቲካ ጋር ምን ያህል ተያያዥነት አለው ?
ስሜነህ ፡- መፅሀፉ ከፖለቲካ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥት የለውም ፡፡ መሪነት የንግድ ፤ የፖለቲካ ፤ የስነ- ጥበብ ፤ የስፖርት፤ ሀይማኖት ወዘተ… ሲሆን ማንኛውም ዘርፍ ውስጥ አመራር እስካለ ድረስ መሪዎች ይኖራሉ ፡፡ የትኛውም በሰዎች የተደራጀ አሰራር ያለመሪና አመራር ሊሰራ አይችልም ፡፡ ስለዚህ መፅሀፉ ስለ ፖለቲካ ሳይሆን በየትኛውም ዘርፍ ውስጥ ስላለ አመራር ሁሉንም ነገር አንስቻለሁ ባልልም ምን መምሰል እንዳለበት ግን ለመጠቆም የሚሞክር ነው ፡፡
ኢቦኒ ፡ – ለመሪነት የስልጣን ምንጮች ምን ምን ናቸው ?
ስሜነህ ፡- የስልጣን ምንጭን በተመለከተ የፖለቲካና የንግድ ስራ አመራር የየራሳቸው ተመሳሳይትም ሆነ ልዩነት አላቸው ፡፡ የፖለቲካ አመራ በህዝብ ይሁንታን ያገኘ የስልጣን ምንጭ ሲያስፈልገው በአንፃሩ የንግድ ስራ አመራር ግን አንድ ሰው የራሱ ድርጅት ካለው ያለውን የሀገሪቱን ህግ እስካከበረ ድረስ በሚፈልገው መንገድ መምራት ይችላል – ለራሱ ያዋጣኛል እስካለ ድረስና በአመራሩም የሚመጣን ኪሳራን ለማስተናገድ ፈቃደኛ አስከሆነ ድረስ ፡፡
የፖለቲካ አመራር ግን የጋራ ስምምነትን ፤ የብዙሀኑን ይሁንታን፤ የመገናኛ ብዙሀንን አስተያየት ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚደረግ ነው ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኦባማ ከኮንግሬሱ ጋር በነበራቸው አለመግባባባት ምክንያት የአሜሪካ ኮንግሬስ የአሜሪካ የፌደራል መንግስቱን ባጀቱን በመከልከል ግማሽ በግማሽ ሊያዘጋው በቅቷል ፡፡ ይህም በአሜሪካ ህገ መንግስት መሰረት ፕሬዝዳንቱ ባጀትን በተመለከተ የኮንግሬሱን ድጋፍንና ይሁንታን ሊያገኙ የሚገባ በመሆኑ ነው ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ መሪዎች ትክክለኛ ስልጣን ምንጭ መኖር ብቻ ሳይሆን እንዴት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብተው መስራት እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው ፡፡

ኢቦኒ ፡ – ይህን መፅሀፍ እንዴት ልትፅፍ ቻልክ ?
ስሜነህ ፡- ይህን መፅኀፍ የፃፍኩት የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብና እንዲሁም የተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀንን በመከታተል ፤ እንዲሁም ኢንሳይክሎፒዲያዎችን በማንበብ የሀገራትን ታሪክ እንዲሁም የተለያዩ ሰዎች ግለ – ታሪክ (Autobiography) በማገናዘብ ነው ፡፡ የተለያዩ የአገራችንንም ሆነ የሌች ሰዎችን ግለ – ታሪክ ማንበብና መከታተል ፤ ስራዎቻቸውን ማየት እወዳለሁኝ ፡፡ በተለይም ጎላ ያሉ የታሪክ የአመራር ሰዎችን የህይወት ታሪክ ማጥናት ያስደስተኛል ፡፡ ምን አድርገው እንደተሳካለቸው ፤ ምን ስላደረጉ ደግሞ በህይወታቸው እንዳልተሳካለቸው እንዲሁም በምን ምክንያት ውድቀት በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ እንዳስከተሉ ማወቅ ያስደስተኛል ፡፡ የአገር ውስጥና የአለም አቀፍ ሚዲያዎችም እንዲሁ ስለምከታተል በመሪነት ድክመት ምክንያት በዚህ አገር ይሄ ችግር ተከሰተ ፤ የኢኮኖሚ ውድቀት ሆነ ፤ የፋይናንስ ማጭበርበርና ኪሳራ ተከሰተ ሲባል በየቀኑ የምንሰማው ነው ፡፡
ኢቦኒ ፡ – መፅሀፉን ለመፃፍ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ ? የተጠቀምክበት ምንጭስ ምንድነው?
ስሜነህ ፡- መፅሀፉን ለመፃፍ ሶስት አመታት ፈጅቶብኛል ፡፡ በዚያ ወቅት ሁለተኛ ዲግሬዬን በምጣኔ – ሐብት ልማት (Development Economics) የትምህርት ዘርፍ በዩኒቲ ዩንቨርስቲ እየተማርኩ በነበረበት ወቅት ከትምህርቴ ጋር ጎን ለጎን አድርጌ ነበረ ስሰራው የነበረው ፡፡ ዲቭሎፕመንት ኢኮኖሚክስ በቀጥታ ከመሪነት ጋር ባይገናኝም ነገር ግን የምጣኔ – ሀብት አስተዳደር ግን ከአመራር ጋር ተያያዥነት ስላለው በዓለም ላይ በርካታ ልማታዊ የምጣኔ – ሀብት ፍልስፍናዎች ቢኖሩም ስኬትን ያስመዘገቡ ግን ጥቂት ናቸው እና ይህንን በማየት ለአንድ አገር ምርጥ የተባለ በኢኮኖሜትሪክስ ሂሳባዊ ቀመርና ሞዴል የተደገፈ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ብቻውን ስኬታማ የአመራርን ውጤትን ሊያስገኝ እንደማይችል ከጥናቴ ለመረዳት ችያለሁ ፡፡ እናም ለስኬታማ አመራር ከኢኮኖሚ ርእዮተ – ዓለም በተጨማሪ ምንድነው የሚያስፈልገው የሚለው ጥያቄ ራሴን እጠይቅ ነበረ ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. የ2008 በአለም አገራት ላይ ከባድ ኪሳራ ያስከተለውን የአለም የገንዘብ ቀውስን ብንወስድ ከዚያ ሁሉ ኢኮኖሚስትና ባለሙያ አስቀድመው ይህንን ቀውስ ሊከሰት ይችላል ብለው የተነበዩ ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ ፡፡ እነሱንም በወቅቱ የሰማቸው ሰው አልነበረም ፡፡ ቀውሱ ከተከሰተ በኋላ ግን እነኚህ ሰዎች በአንድ ጊዜ ዝነኛ ሆነዋል ፡፡

ኢቦኒ ፡ – በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተተረጎሙ ያሉትን የራስ – አነፅ (Self Help) መፅሀፍትን በተመለከተ ምን አስተያየት አለህ?
ስሜነህ ፡- በአሁኑ ወቅት ራስ አገዝ የሆኑ በርካታ መፅሀፍት በብዛት በመተርጎም እና በመፃፍ ላይ ይገኛሉ ፡፡ ይህም መልካም ሲሆን ሲሆን በአንድ በኩል ለሰዎች የራስ መተማመን ስሜትን በመፍጠር ፤ እንዲሁም በህይወታቸው ውስጥ የሚጎድላቸውን እና ማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ቀለል ባለና በተሳካ ሁኔታ ለማግኘት ያስችላቸዋል ፡፡ በህይወት ውስጥ ማንኛውንም ነገር የራሱ አካሄዶችና ጥበቦች ያሉት ሲሆን ያንን ነገር ዝም ብሎ የመጣና የራሱ መንገድ እንዳለው ሌሎች ላያውቁ ይችላሉ ፡፡
በዚህ መስክ በምእራቡ ዓለም የተፃፉትን መተርጎም ጥንቃቄ የሚያሻ ሲሆን አንዳንዶቹ ወደ ሀገራችን ‹‹እንደወረደ›› እየተተረጎሙ ያሉ አሉ ፡፡ ለምሳሌ እንደ ሮበርት ኪዮሳኪ ያሉትን ብንወስድ ምንም እንኳን ይህ ደራሲ በአሜሪካን አገር በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ‹‹ቤስት ሴለር›› ወይንም ብዙ ኮፒ መፅሀፍትን የሸጠ ቢሆንም ነገር ግን አስተምህሮቶቹ ግን ምን መሆናቸውን ከግንዛቤ ማስገባት ያሻል ፡፡ (Rich dad Poor Dad) ‹‹ሪች ዳድ ፑር ዳድ›› በተሰኘው እና በሌሎችም መፅሀፍቱና ፅሁፎቹ የኪዮሳኪ አስተምህሮ እንድ ሰው ህይወቱን በቀለም ትምህርት ማሳለፍ አይጠቅመውም ፤ ሀብትን መሰብሰብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው ፤ በተለይም ወጣቶች ከለጋ እድሜአቸው ጀምሮ ከትምህርት ይልቅ ሀብት ለመሰብሰብና ዝነኛ ለመሆን ትኩረትን ቢሰጡ የተሻለ ነው የሚል አስተምህሮ ይዘት ያለው ነው ፡፡ ይህ ግን ችግሩ ምንድነው ቢባል ሀብት ራሱ የሚፈጠረው በእውቀት ነው ፡፡ እውቀት ከሌለ ሀብት ሊፈጠር አይችልም ፤ በሳይንስም ይሁን በቴክኖሎጂ ወይ በህክምናው ዘርፍ እውቀት መሰረት ነው ይህም እውቀት በአመታት በትምህርት የሚገኝ ነው እንጂ በቀላሉ እንደማይገኝ የታወቀ ነው ፡፡ የኪዮሳኪ አባባል በአቋራጭ ስኬትን ለሚፈልጉ ሊረዳ ይችል ይሆናል እንጂ የጥቂት ሰዎች ብቻ ብዙ ሀብት መሰብሰብ አንድ ማህበረሰብን ሊጠቅም መቻሉ አጠራጣሪ ነው ፡፡ ከሮበርት ኪዮሳኪ አስተምህሮ በበጎ ሊገለፅ የሚችለው በአሁኑ ዘመን አንድ ሰው የገንዘብ ነክ እውቀት ‹‹Financial Intelligence›› ያስፈልገዋል የሚለው ነው ፡፡
ይህ መስክ ከማንኛውም በዓለም ላይ ሀሳብን ከማስፋፋት አንፃር ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚሻው ዘርፍ ነው ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አንዳንዶቹ ሀይማታዊ ይዘት እያላቸው ሆነው ሳለ ነገር ግን ራስ አገዝ ብቻ ሆነው ወይም መስለው መቅረባቸው ግን ለአንባቢው ምርቱን ለግርዱ ለመለየት አዳጋች ያደርገዋል ፡፡ ለምሳሌ የፍልስፍና ዘመነ – ሐዲስ (New Age) አስተሳሰቦችና አስተምህሮዎች እንደ ራስ አነፅ መፅሀፍት ሆነው ይቀርባሉ ፡፡ አንዳንዶቹ መፅሀፍት በመፅሀፍቶቻው ላይ ዘመነ ሐዲስ የሚለው ቃል በግልፅ የሰፈረባቸው ናቸው ፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ አምላክን ወይም አንድ ፈጣሪን መሰረት ያደረጉ ሀይማቶች ፈተና የሆነው ይሄው የዘመነ – ሐዲስ እንቅስቃሴ (New Age Movement) የሚባለው ሀይማኖታዊና መንፈሳዊ ይዘት ያለው ዓለም ዓቀፋዊ እንቅስቃሴ ነው ፡፡ ይሄው እንቅስቃሴ ከምስራቃውያን ፍልስፍና የተቀዳ ሲሆን የምእራብን ‹‹ጁዶ-ክርስትያን›› ሀይማኖቶችን ከምስራቅ መንፈሳዊ እምነቶች ጋር በማቀላቀል የተፈጠረ አዲሱ ገዢ የዓለም አስተሳሰብ ከሆነ ውሎ አድሯል ፡፡ አንድ ሰው ከተለያዩ መንፈሳዊ አካላት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚፈቅድ ሲሆን ለምሳሌ ሀብትን ሚፈልግ ሀብትን ከሚያድል መንፈሳዊ አካል ጋር ግንኙነትን ማደረግ ይችላል ፤ ፍቅርን የሚፈልግ ፍቅርን ከምታድል አማልክት ወይም መንፈሳዊ አካላት ጋር በመንፈስ መገናኘት ወይም ግንኙነት ማድረግ ይችላል ይህን በማድረግም ማግኘት የሚፈልገውን ነገር በቀላሉ ወደ ራሱ ‹‹ጎትቶ›› ማምጣት ይችላል የሚል አንድምታ ያላቸው ናቸው ፡፡ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የጥንት ሮማውያንና ግሪካውያን አማልክቶች ሀብትን ፤ ፍቅርን የሚያድሉ ሲሆን ‹‹አፍሮዳይት›› የተባለችው አማልክት ፍቅርን የምታድል እዲሁም አቴናና ሜርኩሪ የተባሉት አማልክቶችንም እንዲሁ የየራሳቸው ለተማፃኞቻው የሚያስፈፅሙት ነገር አላቸው ይህ አስተሳሰብ ከጁዶ – ክርስትያን (Judo – Christian) አስተሳሰብ ላይ ከተመሰረቱት በአሀዳዊ አንድ አምላክ (Monotheism) ከሚያምኑ ሀይማኖቶች ጋር እንደሚፃረር መገንዘብ ይቻላል ፡፡
ሌሎች ሀይማኖታዊ እንዲሁም መንፈሳዊ መፅሀፍት ሆነው ነገር ግን ፤ አንዳንዶች በራስ አገዝ ወይም ራስ – አነፅ (Self – Help) በሚል ዘውግ ውስጥ እየተተረጎሙ ያሉት መፅሀፍት ሀይማታዊ ይዘት ያላቸው መሆኑን ብዙዎቹ የሀገራችን አንባቢዎች ልብ ላይሉት ይችላሉ ፡፡ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌዎች የሚሆኑት የራምፓ፤ የፋሉን ጎንግ ፣የኤክሀርት ቶሌን መፅሀፍቶችን ብንወስድ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውና አንባቢው እነዚህን መፅሀፍት ሲያነብና በህይወቱ ሲተገብር ከሚያውቀውና ከለመደው ከራሱ እምነትም ሆነ ሀይማኖት የተለየ መንፈሳዊ ተሞክሮ ውስጥ እየገባ እንዳለ ላይረዳ ይችላል ፡፡ ኤክሀርት ቶሌ የተባለው ካናዳዊ ፀሀፊም (The Power of Now) ‹‹የአሁንነት ሀይል›› የመሳሰሉ መፅሀፍትን የፃፈ ሲሆን እርሱም አይነተኛ የዘመነ – ሐዲስ መፅሀፍ ነው ፡፡ ራምፓ መፅሀፍቶች የቲቤት ቡድሂዝም መንፈሳዊ ጥበብን የሚያስተምር ነው ፤ በመፅሀፍቶቹም አንድ ሰው በአየር ላይ ሲራመድ እንዲሁም አንድ ሰው ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ነገሮች ሲፈፅም ወዘተ… ይገልፃል እነኚህ ነገሮች ሊሆኑ የሚችሉት አንድ ሰው በእነኚህን መንፈሳዊ ልምምዶችን ካደረገ ብቻ ነው ፡፡ እነኚህ መጥፎ ናቸው ለማለት ሳይሆን ነገር ግን አንባቢው የሚያነበውን ሀሳብና ምንነት እንዲሁም ወዴት ሊመራው እንደሚችል መረዳት መቻል አለበት ፡፡ በነገራችን ላይ መቀመጫዋን በቫቲካን ያደረገችው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የክርስትና ሀይማኖትን አስተምህሮዎችን የሚገዘግዝና የሚያፋልስ ይዘት ያላቸውን የኤክሀርት ቶሌንና የዳን ብራውንን ስራዎችንና ፊልሞችን ማውገዟ ይታወቃል ፡፡
ለምአሳሌ ‹‹ሚስጥሩ›› ወይም (The Secret) የተሰኘውን መፅሀፍን ብንወስድ ግን እንዲሁ መፅሀፉ ከመታተሙ በፊት ብዙ ብዙ ተብሏል ፡፡ ይህ መፅሀፍ በአለም ላይ ከተፃፉ ታላላቅ ራስ አነፅ መፅሀፍት አንዱ ሊሆን በቅቷል ፡፡ ለምሳሌ (The Science of Getting Rich) የተሰኘውን መፅሀፍ ብንወስድ እንዲሁ በአለም፣ ላይ ሰዎች ስለ – ሀብት ፈጠራ ቢያውቁ ግን በአለም ላይ ፍትህ ይሰፍናል ሀብትን በተመለከተ የሚል አቋምን ያንፀባርቃል መፅሀፌ እደንደሚለው በአለም ላይ ሰዎች ይህንን ቢያውቃ ዋሽንግተን ዲሱን የሚ ያህል ዘመናዊና ሀብታም ግዚግ ዙፍ ከተማን በአለም ላይ በብዙ አገራት መገንባት ይችላል ባይ ነው ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሀብት በብዝበዛ ነው የተገኘው ከሚለው የማርክሲዝም ፍልስፍና ጋር ይጋጫል ፡፡ በነገራችን ላይ የራስ አነፅ መፅሀፍት ደራሲዎች በአብዛኛው አካዳሚሺያኖች ወይንም ከቀለም የትምህርት ዘርፍ የመጡ አይደሉም ፡፡
ኢቦኒ ፡ – በሀገራችን ያለው የአመራር ባህልና ልማድ ምን ይመስላል ?
ስሜነህ ፡- በሀገራችን መሪነትን በተመለከተ በልማድ ነው እንጂ በእውቀትና በተረጋገጠ ልማድ ላይ የመሰረተ አሰራር ገና አልዳበረም ማለት ይቻላል ፡፡ የአመራር ጥበብ ወይም መሪነት የሚባለው ነገር ቀደምት መሪዎች ባደረጉትና ሌሎች ሲያደርጉ በታዩት ወይም አደረጉ በተባለው ነው እንጂ ትክክለኛው የመምራት መንገድ የቱ ነው በሚል የመስራት ልማድ የለም ማለት ይቻላል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገራችን አርቆ የማየት ልማድ (Foresightedness) አነስተኛ መሆን እንዲሁም የአመራር ልምድ ቢኖረንም የአሁኑ ትውልድ ግን የሆነ ቦታ በመቋረጡ ምክንያት ይህን ለረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የአመራር ልምድ አያውቀውም ፡፡ ሀገራችን በዓለም ላይ በቅን ፍትሀዊ ዳኝነቷ ትታወቅ የነበረች ነች ፡፡ በዚህም በሀበሻ ምድር ያለው ንጉስ ፍትሀዊ ነው ብለው ከአረብ ሀገራት በሀይማኖት ተቸግረው በተሰደዱበት ወቅት የመረጡት ሌሎች በመልአ ምድራዊ አቀማመጥ የሚቀርቧቸው እያሉ ባህረ ተሻግረው የመረጡት ኢትዮጲያን ነበረ ፡፡ ፍትሀ ነገስትና ክብረ ነገስትም ነገስታት ሰማያዊ ብቻ ሳይሆን ዓለማዊውን አመራር ምን መምሰል እንዳለበት የሚስረዱ ጥንታዊ ፅሁፎች ናቸው ፡፡ ክብረ ነገስት ለምሳሌ ነገስታት እንዴት በመንገስ እንዳለባቸው የአነጋገስ ስርአቱ ፤ የስልጣኑ ምንጭና የመተካካት ስርአቱ እንዲሁም አንድ ንጉስ በሚሞትበት ወይም በሚወርድበት ጊዜ ስልጣን ከአንድ ንጉስ ወደ ሚቀጥለው ንጉስ እንዴት መተላለፍ እንዳለበት ፤ የነገስታት ዳኝነት ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር የሚስቀምጥ ነው ፡፡ በጥንት ጊዜ አንድ ንጉስ በሚሞትበት ወቅት ‹‹የሞትንም እኛ ፤ ያለንም እኛ›› ብለው አዋጅ ያስነግሩ ነበረ፡፡ በዚህም ሰላማዊ የሆነ ሽግግር እንዲካሄድ ያስችል የነበረና ለክፍለ ዘመናት ሲሰራበት የኖረ ነው ፡፡ ነገር ግን እነኚህ ሁሉ መልካም የታሪካችን ገፅታዎች አልቀጠሉም ፤ ከዚያ ይልቅ እርስ በእርስ መፋጀትና አለመተማመን ሲከተል ሽግግሮች የስርአት መፍረስን የሚያስከትሉና ደም አፋሳሽ እየሆኑ ሄዱ፡፡

ኢቦኒ ፡ – ራስንና ሌሎችን የመረዳት አስተውሎት ወይንም ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ (Emotional Intelligence) ማለት ምን ማለት ነው?
ስሜነህ ፡- ሌሎችንና ራስን መረዳት (Emotional Intelligence) የሚለው ፍልስፍና በአንድ የዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር የተፈጠረ ፅንሰ – ሀሳብ ነው ፡፡ ይህም ለአንድ መሪ በጣም ቁልፍ ተግባር ሲሆን ራሱንና በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታን የሚረዳ መሪ ስኬታማነቱ እንዲጨምር ያደርገዋል ፡፡ የዚህ አስተውሎት ባለቤት የሆኑ ሰዎች በማህበራዊ ህይወታቸውም ጭምር የተሻለ ስኬት ያላቸው ናቸው ፡፡ ይህ ችሎታ አንዳንድ ሰዎች ጋር በተፈጥሮ ያለ ሲሆን አንዳንዶች ጋር ግን በተፈጥሮ ላይታደሉት ይችላሉ ፤ ነገር መልካሙ ዜና ማንም ሰው በቀላሉ ሊማረው የሚለው ክህሎት መሆኑ ነው ፡፡ ራሱንና ሌሎችን በአግባቡና በቅጡ የማይረዳ መሪ ስኬትን ሳይሆን ውድቀትን በሚመራው ተቋምና በራሱ ላይ ይጋብዛል ፡፡
ኢቦኒ ፡ – ለውጥን መምራትን በተመለከተ በመፅፍህ ውስጥ ለምን የተለየ ትኩረትን ሰጠኸው ?
ስሜነህ ፡- ለውጥን መምራት በመሪነት ውስጥ ቁልፍ ከሆኑ ተግባራት አንዱ ሲሆን ፤ አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ራሳቸው ለውጥን እየመሩ እንዳሉና የተለየ ጥንቃቄን ማድረግ እንዳለባቸው የማይረዱበት ጊዜ የበዛ ነው ፡፡ ለዚህም ነው ትኩረትን የሰጠሁት ፣ ዩኒቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ለውጥንና አዲስ ፈጠራን በተመለከተ እንዴት መሪ ሊመራ እንደሚገባ አንድ ኮርስ ወስጄ ነበረ ፡፡ እናም የተረዳሁት ነገር ምንድነው? ቢባል ለውጥን መምራት በተመለከተ ምእራባውያን በርካታ ፅሁፎችን እንደፃፉና ብዙ ምርምርን እንዳደረጉ መረዳት ችያለሁ፡፡ በኩባንያዎች ውስጥም ሆነ በአገር ደረጃ ለውጥን ማካሄድ ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳሉትና ይህንን የማያውቅ መሪ ስኬታማ መሆኑ የሚያጠራጥር ነው ፡፡
ኢቦኒ ፡ – መፅሀፉ ምን ያህል የአመራርነት ጥበብን ያሳያል ?
ስሜነህ ፡- መፅሀፉ የአመራር ጥበብን የሚያሳየው በጣም ምክንያተዊ አሳማኝ ከሆኑ ነገሮች ይልቅ በጥበብ ሊፈፀሙ የሚገባቸውን ለምሳሌ ለውጥን ማካሄድ ብንወስድ ለውጥ በጥበብ የሚከናወን ነው ፤ ለውጥ መደረግ ያለበትና አሳማኝ ቢመስልም ለመፈፀም ግን ጥበብንና እውቀትን ይጠይቃል ፡፡ ሌላው መተካካትም እንዲሁ በጥበብና በዘዴ የሚከናወን ነው እንዲሁም መሪዎች ትትውት የሚያልፉት የታሪክ አሻራም እንዲሁ መሪዎች በስልጣን ዘመናቸውና እንዲሁም በህይወት እያሉ በብልሀት የሚከውኑት እና በጥንቃቄና በብልሀት የሚቀርፁት ነው ፡፡

ኢቦኒ ፡ – መፅሀፉ በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ ነው ?
ስሜነህ ፡- መፅሀፉ በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ የዋለ ሲሆን ፤ ያነበቡት ሰዎችም መልካም አስተያየቶችን ሰጥተውኛል ፡፡
ኢቦኒ ፡ – በሀገራችን ያለው የመፅሀፍ ገበያ ምን ታዝበሀል ? ምን ትላለህ ?
ስሜነህ ፡- በሀገራችን ያለው የመፅሀፍ ገበያ ገና ብዙ ይቀረዋል ፡፡ አሳታሚ ማግኘት ፤ አከፋፋይ ማግኘት በወቅቱ ደራሲው ገንዘቡን መሰብሰብ የመሳሰሉት ጉዳዮች ገና በትክክል መስመር አልያዙም፡፡ በምእራቡ አለም ለምሳሌ አማዞን በመጠቀም አንድ ሰው የሚፈልገውን ርእስ በአሳሽ ድረ – ገፅ ውስጥ በመክተት ብቻ ርእስ መርጦ የሚፈልገውን መፅሀፍን ማግኘትና የተሻለ ዋጋንም ጭምር ማነፃፀር ይችላል ፡፡ በዚህ መንገድ ከረጅም አመታት በፊት ከህትመት ውጪ የሆኑ መፅሀፍትንም ጭምር ማግኘት ይችላል ፡፡ አንባቢው ከድረ – ገፅ መፅሀፍትን ማዘዝና መግዛት በመቻሉ ምክንያት ፤ የመፅሀፍ መሸጫ ሱቆች እስከመዘጋት ደርሰዋል ምክንያቱም ሰዎች በቀላሉ በድረ ገፅ መፅሀፍትን መግዛት ስለሚችሉ ፡፡ እንዲሁም ኢ – መፅሀፍት (E – Book) ስላሉ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ የቢሊዮን ዶላሮች ንግድ ሆኗል ፡፡ ለጊዜው እዚህ ሁሉ ደረጃ ባንደርስም በተለመደው መፅሀፍት በማከፋፈል ማለትም በመሸጫ ሱቆች እንኳን ለደራሲውና ለአንባቢው አመቺ በሆነ መንገድ ማሰራጨትና ማሳተም ደረጃ እንኳን ገና በደንብ አልደረስንም ማለት ይቻላል ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የህትመት ዋጋ መናር ለደራሲው ለማሳተም ዋጋውን ሲጨምርበት ፤ መፅሀፉም ሲሸጥ እሱም በተራው በአንባቢው ላይ ይጨምረዋል፡፡ ይህም መፅሀፍቶችን የመግዣ ዋጋ ውድ እንዲሆኑ እያደረገ ነው ፡፡ ደራሲው ለተለያዩ አከፋፋዮች መፅሀፉን ከበተነ በኋላ እንደገና ሽያጩንና ያልተሸጠውን መፅሀፍት ለመሰብሰብ አድካሚና ስርአቱ የተዘበራረቀ ነው ፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን አሳታሚዎች በብዛት ቢኖሩና ራሳቸው አሳታሚዎች አሳትመው ቢያከፋፍሉት የደራሲውን ድካም ይቀንሳል ፡፡
በአሁኑ ወቅት ሌሎች የጥበብ ስራዎች ለባለሙያዎቻው የተሻለ ገቢን ማስገኘት ጀምረዋል ፤ ለምሳሌ ፊልምን ብንወስድ የፊልም ሰሪዎች የተሻለ ገቢን እያገኙ እንዳሉና ለተዋንያኖችና ለፊልም ፅሁፍ ደራሲዎች ይህን ያህል ከፈልን ሲሉ ይሰማል ፡፡ ደራሲ እንደማንኛውም ሰው ለመኖር ወጪዎች አሉበት ይበላል ፤ ይጠጣል ፤ የመሳሰለው ሁሉ የኑሮ ፈተናዎች አሉበት ፡፡ ከገቢ አንፃር የስነ – ፅሁፍ ስራ እንደማንኛውም ስራ ፀሀፊው አስተማማኝ ገቢን ማግኘት አለበት ፡፡ ይህም ብቃት ያላቸው ደራዎች እንዲወጡና የትርፍ ጊዜ ደራሲዎችን ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ደራሲዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል ፡፡ የስነ – ፅሁፍ ስራ ጥናትንና ምርምርን፤ ብዙ ማንበብን እንዲሁም ለረጅም ሰአታት ቁጭ መፃፍን የሚጠይቅ ሙሉ አትኩሮትን የሚፈልግ ስራ ነው ፡፡ ብርሀኑ ዘሪሁን ፤ ‹‹የታንጉት ሚስጥርን›› እና ሌሎችን ስራዎችን የሰራው ታዋቂው የሀገራችን ደራሲ ‹‹የኢትዮጲያን ስነ -ፅሁፍ ለማሳደግ የሙሉ ጊዜ ደራሲዎች ያስፈልጋሉ›› ይል እንደነበረ ይነገራል ፡፡ በቅርብ ካሉት ደራሲዎቻችን ራሱን የሙሉ ጊዜ ደራሲ ነኝ ሲል የሰማሁት በእውቀቱ ስዩምን ብቻ ነው ፡፡ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡
ኢቦኒ ፡ – ስለ ኢትዮጲያ ፍልስፍና ምን አስተያየት አለህ ?
የኢትዮጲያ ፍልስፍና ከሀገሪቱ ታሪካዊነት አንፃር ረዘም ያለ ጊዜ ያለው ነው ፡፡ ከኢትዮጲያ ፈላስች መሀከል ዘርአያቆብ እንዲሁም የእርሱ ተማሪ የነበረው ወልደ ህይወት ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ የኢትዮጲያ ፍልስፍና ያለውን አስተሳሰብ የመቃረን አዝማሚያ የሚ ታይበት ነው ፣ ተፃራራ መስሎ የሚታይ እንዲሁ በዘመናት ውስጥ ራሱን ወደ ዋናው ማህበረስብ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት አለበት፡፡
አንዲት ፈረንጅ በአንድ ወቅት ወደ ሀገራችን መጥታ በነበረባት ወቅት ‹‹ፈላስፋ የላችሁ ፣ ሲምፎኒ የላችሁ›› የሚል አስተያየትን ሰጥታለች ፡፡ በሀገራችን ፍልስፍና እንደ ያለውን አስተሳሰብ መቃረን ተደርጎ ይታሰባል ፡፡ ፈላስፎች እንደ እብድና ቂዥቢ ተደርገው የሚታዩበት ሲሆን አንድ የፍልስፍና መምህርም በአንድ ወቅት መዝገበኞች ለተሰኘ ለአንድ መፅሄት በሰጡት አስተያየት ላይ የሀገራችን የስራ ገበያ የፍልስፍና ትምህርትን አያውቀውም ብለዋል ፡፡
የዘርአያቆብ ፍልስፍና ከክርስትና ሀይማኖት አስተምህሮዎች ጋር የሚቃረን ነው ፣ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ፡፡ ለምሳሌ አለቃ ገብረሀናን ብንወስድ የነበረውን መንግስታዊና ሀይማኖታዊ አደረጃጀትን የመቃረን መንገድ ነበረው ፡፡ ያም ሆኖ አለቃ ገብረሀና በኋላ ላይ ከማህበረሰቡም ተገልለው ለመኖር ተገደዋል ፡፡ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁም እንዲሁ በጉዱ ካሳ የመሰሉት ገፀ ባህሪያቸው ራሳቸው በአንድ መፅሀፋቸው መግቢያ ላይ እንደገለፁት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውንና እስከ አብዮቱ ድረስ የዘለቀውን መሻሻል ያስፈልገው የነበረውን የፊውዳላዊውን ስርአት ውስጣዊ አሰራርን የጠቆመ ነው ፡፡ በርካታ የጉዱ ካሳ ንግግሮችም ይህንን ስርአት በመመርመር መሻሻል እንዳበት የጠቆሙ ናቸው ፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ እንደ ‹‹እብድ›› በሚታየው ጉዱ ካሳን በመጠቀም ስርአቱ ሊሻሻል ይገባዋል ያሉትን መጠቆማቸው የደራሲውን ረቂቅ ችሎታን የሚያሳይ ነው ፡፡ ደራሲው በዚህ ስራቸው ከአፄ ሀይለስላሴ እጅ ሽልማትን ማግኘታውም ይታወቃል ፡፡ በአንፃሩ ክቡር ደራሲ ከበደ ሚካኤልን ብንወስድ ከብዙ ንባብ ያገኙትን ስርአቱን የመፃረርም ሆነ እንደ ሀዲስ አለማየሁ የማሻሻል ሀሳብን በማንሳት ላይ ሳይሆን የነበረውን የንጉሰ ነገስታዊውን ስርአት ሳይነኩ ነገር ግን በማስተማርና ታላላቅ የአውሮፓ ፈላስፎችን፣ የታሪክ ሰዎችን ስራዎችን ለትውልዱ በማስተማርና በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ጃንሆይ በአሜሪካን አገር›› የተሰኘው ስራቸው ሀይለስላሴ በአሜሪካን አገር ያደረጉትን ጉብኝት በፎቶዎችም ጭምር አስደግፎ የሚያስረዳ ነበረ ፡፡ ‹‹ታላላቅ ሰዎች›› በተሰኘው የአውሮፓን የታሪክ ሰዎችን ስራ በሚተነትነው መፅፋቸው ላይ ለንጉሰ ነገስቱ አስተዳር መገዛትን ፣ ስርአትን በመከተል በመሳሰሉት ላይ ትኩረትን የሚያደርግ ነው ፡፡
ከመንግስታዊ አስተዳርና ኢኮኖሚ ነክ ፈላስፎች ከሀገራችን ተጠቃሹ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ናቸው ፡፡ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ የሀገራችን ፈር – ቀዳጅ የፖለቲካና ምጣኔ – ሀብት ‹‹ፖለቲካል ኢኮኖሚ›› ዘርፍ ፈላስፋ ናቸው ፡፡ የእርሳቸው ስራ በአንዲት መፅፍ ብቻ አራት ወይም አምስት የሚሆኑ ዋና ዋና የሆኑና በኋላ ላይ በምእራባውያን የምጣኔ – ሀብት ባለሙያዎች የተደረሰባቸውና የኖቤል ሽልማት ምእራባውያኑ የወሰዱባቸውን ንድፈ – ሀሳችን የቀመሩ ናቸው ፡፡ የነጋድራሱን ከፍተኛ ግንዛቤና እውቀትን እና የላቀ የማሰብ ደረጃን ያመለክታል ፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባልታወቀ ምክንያት ምናልባትም ተመርዘው ሊሆን ይችላል በሚባል ሁኔታ ህይወታቸውን ማጣታቸው ሲሆን በዘመኑ የልጅ ኢያሱ ደጋፊ ናቸው ተብሎ ይታመን ስነበረ በመፅሀፋቸው ላይም ጃንሆይ እያሉ የፃፉት ለልጅ ኢያሱ ምክር እንዲሆን ነው ይባላል ፡፡ ነገር ግን ‹‹ጃንሆይ›› የሚለው ቀቃል ለተከታታይ ነገስታት የተሰጠ ስያሜ እንደመሆኑ ቀጥለው ለነገሱት ንጉስ ሀይለስላሴ የተሰጠ ምክር ይመስላል ፡፡ ይህም ገብረ ህይወት ባይከዳኝ የንጉሱን ስም በቀጥታ ከመጠቀም ይልቅ ነገስታት የሚጠሩበትን ‹‹ጃንሆይ›› የሚለውን ቃል በመጠቀማቸው ለመጪዎቹ ወገንተኛ ሳይሆኑ ለነገስታት ምክር እንደሰጡ ይቆጠርላቸዋል ፡፡
ነገር ግን ሀገራችን ስራዎች በዚያ መልክ አልቀጠሉም ፡፡ ለምሳሌ ከሀራችን ደራሲዎች ከነበሩት መንግስት ጋር ባለመግባባትም ይታወቃሉ ፡፡ ለምሳሌ በአሉ ግርማ ከደርግ መንግስት ጋር ተስፋዬ ገብረ አብ ከኢህአዴግ መንግስት ጋር ባለመግባባት የራሳቸውን አዳዲስ አስተሳሰብን ያንፀባረቁና በዚህም ምክንያት ከነበሩት መንግሰትታ ጋር ተለያይተዋል ፡፡
ዳኛቸው ወርቁ የተባለው የሀገራችን ደራሲ በ1962 ዓ.ም. በፃፈው አደፍረስ በተሰኘው መፅሀፍ ላይ በተማሪውና በወታደሩ መሀከል ልዩነት እንደሚፈጠርና ተማሪው ችኩልና ስሜታዊ ሲለው ወታደሩን ደግሞ አልበሰለም ይላል ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጲያን በራሱ ገፀ ባህሪ መስሏታል ፡፡ ‹‹አደፍርስ›› የተሰኘው መፅሀፍ የወደፊቱን ትንቢታዊ በሆነ መንገድ በሚተነብየው መፅሀፍ ላይ ይህን ይዘረዝራል ተምሳሌታዊና ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ፡፡

Advertisements