Ethiopian Constitution and Courts Law የኢትዮጲያ ህግና ህገ መንግስት

ፍትሕ አተረጓጎም
ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ መጋት 5 ፣ 2007 ዓ.ም በፃፉት ፅሁፍ ላይ ‹‹በፍትሕ ኀልዮት ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ድርሳናት የጻፉ ሰዎች እንደሚያቀርቡት፣ ‘ፍትሕ’ በጥቅሉ ኹለት ዐበይት መደቦችን የያዘ ፅንሰ ሐሳብ ነው፤ እኒኽም ‘ሰብስታንቲቭ ጀስቲስ’ (ፍሬ-ነገራዊ ፍትሕ) እና ‘ፕሮሲጀራል ጀስቲስ’ (ወጋዊ ፍትሕ) ይባላሉ። ከኹለቱ የፍትሕ አመለካከቶች በመነሣት በአገራችን ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ለማሳየት እሞክራለሁ። ስለ ‘ሰብስታንቲቭ ጀስቲስ’ በምናወራበት ጊዜ፣ በርእሰ ነገሩ ላይ ወሳኝ ድርሳን የጻፉትንና ለብዙ ዓመታት በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩትን ጆን ሮውልስን ሳንጠቀስ አናልፍም። ‘የፍትሕ ንድፈ ሐሳብ’ (A Theory of Justice) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ጆን ሮውልስ ፍትሕን በተመለከተ ባስቀመጡት አስተምህሮ፣ አንድን ሥርዐት ፍትሐዊ ነው የምንለው÷ ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኹሉም ተቋማት ውስጥ ገብተው ሥራ ለመያዝ ወይም ለመገልገል (በጨረታም ኾነ በሌላ መልኩ ለመሳተፍ) በፆታ፣ በብሔር እና በመደብ ሳይኾን እንደየችሎታቸው ብቻ ተመርጠው ለመሳተፍ ሲችሉ ነው። የአገራችን ብሂል “ከዕንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት” ይለዋል፤ የጆን ሮውልስን ሐሳብ።››
‘ፕሮሲጀራል ጀስቲስ’ን በተመለከተ፣ ዕውቅ አስተምህሮ የጻፈው ፕሮፌሰር ስቱዋርት ሃምሻየር (Stuart Hampshire) “ፍትሕ ግጭት ነው” (Justice is Conflict) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚሉት፣ የሰው ልጅ ከጭቅጭቆችና ከግጭቶች ነጻ ባይኾንም፣ ፍትሕ ርትዕ ይሰፍን ዘንድ ኹሉም ወገኖች የሚደመጡበትና ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ሲኖር ነው፤ ካሉ በኋላ፣ የጥንት ሮማውያንን አባባል፣ “የሌላውንም ወገን ድምፅ ስማ” (Audi alteram partam) የሚለውን ምክር ይለግሳሉ።
ፕሮፌሰሩ፣ ‘’የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ምን ያኽል ዴሞክራሲያዊ ነው?’’ (How Democratic is the American Constitution?) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች አቅርበዋል። አንደኛ፣ ዐሥራ አንድ ስቴቶች እና ሠላሳ ዘጠኝ እንደራሴዎች ብቻ ከዛሬ ኹለት መቶ ዓመታት በፊት ያረቀቁትንና የፈረሙትን ሕገ መንግሥት ዛሬ ለምን እንቀበላለን? እውን፣ አብዛኞቹ አሜሪካውያን እንደሚሉት፣ ሕገ መንግሥቱን የምንከተለው የዜጎችን ኹሉ ቅቡልነት ስላገኘ ነውን? ብለው ይጠይቁና ምላሹን ለማግኘት ሌላ ጥረት ሳያስፈልጋቸው፣ ግን እስኪ፣ ይህን መጽሐፍ ከምታነቡ ዜጎች መካከል ምን ያኽላችሁ ለሕገ መንግሥቱ ቅቡልነትን ትሰጡ ዘንድ ተጠይቃችኹ ሰጥታችኋል? ሲሉ ይሞግታሉ።
«ኹለተኛ፣ አንዳንድ አሜሪካውያን፣ የምንከተለው ሕገ መንግሥት ከዓለም ምርጡ ነው፤ ብለው እንደሚናገሩ ፕሮፌሰሩ ያወሱና ይህ አባባል እውነት ከኾነ፣ ለምን ኻያ ሦስት የዓለም ታላላቅ ዴሞክራሲዎች የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ነጥብ በነጥብ አልገለበጡም? ሲሉም ይጠይቃሉ። የፕሮፌሰር ሮበርት ዳል ዋነኛ ዓላማ፣ የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን ማስቀየር ሳይኾን፣ ሕዝቡ ስለ ሕገ መንግሥቱ ያለውን ዶግማዊ አመለካከት ሽሮ ዳግም ወደ ውይይትና ፍተሻ ይገባ ዘንድ ለመጎትጎት ነው። ኹለት መቶ ዓመታት የሞላውና በዓለም ላይ አድናቆትን ያተረፈው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ጥያቄና ትችት የሚቀርብበት ኾኖ ሳለ፣ ኻያ ዓመታት ብቻ ያስቆጠረው የአገራችን ሕገ መንግሥት ላይ ጥያቄ በሚነሣ ጊዜ፣ ሕገ መንግሥቱን “ለማፍረስ (ለመናድ)” በሚል ፈሊጥ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ውይይት የሚያደርጉባቸው መንገዶች መዘጋት የለባቸውም። »ይላሉ ዶክተር ዳኛቸው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፋቸው ።
በኢትዮጲያ የንብረት ባለቤትነት ህግና
አንድ የፍርድ ቤት ሙግት በርካታ ወራትን ብሎም አመታትን የሚፈጅ ሲሆን ይህም ማለት ይህ ጉዳይ ፍርድ ቤት ይዞታል በሚል ብቻ እውነቱ እስከሚወጣ ድረስ አመታትን መፍጀቱ የንብረት ባለቤትነት መብትን ህጉ በአግባቡ ማስከር ችሏል ወይ ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልካም ነው ፡፡ በሃገራችን እንደሚታወቀው የፍርድ ቤት ሙግት በቀላሉ የማያልቅ ሲሆን በቀላሉ ወረዳዎች ወይንም ባስ ካለም ክፍለ ከተማዎች መፍትሄ ሊሰጡት የሚገችሉት ጉዳይ አመታትን ሰዎችን ሲያመላልስ ይስተዋላል ፡፡
አንዱ የመዋእለ ንዋይን ፍሰት ለማበረታታት ከሚመከሩት የተመቻቹ ሁኔታዎች አንዱ የንብረት ባለቤትነት (Property Right) መብትን ማስከበር ሲሆን በምእራባውያን የምጣኔ – ሐብት ባለሙያዎች እንደተጠናው ከሆነ ለአፍሪካ ኢንቨስትመንትን አግባቡና በበቂ ላለመሳቧ ዋነኛው ምክንያት የንብረት ባለቤትነት መብት በበቂ አለመከበሩ ነው ይላል ፡፡
አንድ መዋእለ ንዋይ አፍሳሽ አንድ የውጭ ሃገር ሄዶ ገንዘቡን ሲያፈስ የሚያፈሰውን ገንዘብ ሲፈልገው መልሶ ማውጣት ሚፈልግበት በማንኛውም ሰዓት ላይ ማውጣትን የሚፈልግ ሲሆን የንብረት መብት (Property Right) በአግባቡ የማይከበርባቸው ሃገራት የውጭ መዋእለ ንዋይን የማግኘት እድላቸው በጣም ጠባብ ነው የሚሆነው ፡፡ ይህም አወዛጋቢ በሚሆንበት ወቅት የሚከበር ፍርድ ቤቶች አማካይነት በተፋጠነና በተከራካሪ ወገኖች ላይ የማያስፈልግ ወጭንና ኪሳራን በማያስከትል ሁኔታ በአንዱ ኪሳራ ሌላኛው አለአግባብ በማይጠቀምበት ሁኔታ መሆን አለበት ፣ የነገሩ መንዛዛት አንደኛው ወገን በአንደኛው ኪሳራ አለአግባብ እንዲጠቀም የሚያደርግ ሲሆን ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ በሁለቱም ወገኖች ላይ ከባድ ኪሳራንና መጓተትን ያስከትላል ፡፡ ለምሳሌ በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰው ሶማልያን እናስብ ፤ አንድ የውጭ ሃገር ኢንቬስተር ሶማልያ ሄዶ መዋእለ ንዋዩን እንደማፍሰስ ብለን ብናስብ አንድ ባለሃብት እርዳታ አድርጎ ቢሰጠው ይሻለኛል ፣ ዝም ብዬ ሄጄ ገንዘቤን ከማፈስና ከምነጠቅ ብሎ ነው እሚያስበው ፣ ስለዚህ ሶማልያ መዋእለ ንዋይ የማግኘት እድሏ አናሳ መሆኑ ግልፅ ነው ፡፡
በአፍሪካ የንብረት ባቤትት መብት በአግባቡ የማይከበር ሲሆን ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ የሆነ መሬት ያለ በቂ ሰነድ የሚያዝ ሲሆን መዋእለ ንዋይን ለማፍሰስና ለማሳደግም ሆነ ለማሻሻል አስቸጋሪ አድርጎታል ብለው የውጭ ባለሙያዎች ይናገራሉ ፡፡ ከዚህ ተጨማሪ ግን ፍርድ ቤቶች ጠንካራ ሆነው የንብረት ባለቤት ህጉን ለማስከበር ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መፍታት ካልቻሉ ረጅም ግዜን መውሰዱ መዋእለ ንዋይን ከማረታታት አንፃር አሉታዊ ጎን ይኖረዋል ፡፡ ለምሳሌ አከራይና ተከራይ መሐከል ያለ ክርክር አመታትን ሊወስድ ይችላል በዚህም ምክንያት አከራዩ ፣ ክርክሩ ቤቱ ተይዞት ከሆነ የሚካሄደው ቤቱን እስከሚያስለቅቅ ድረስ የሚደርስበትን ኪሳራን ከውል ውጭ ጉዳት ደርሶብኛል በሚል ሌላ መዝግብ በመክፈት ድጋሚ ከሶ ብቻ ነው ማስከፈል የሚችለው ፡፡ ይህ ራሱ ደግሞ ከውል ውጭ ምን ያህል ነው የደረስብህ ኪሳራ የሚለው ለዳኝነት ቁልጭ ያለ ባለመሆኑ ምክንያት አሻሚ ስለሚሆን ከውል ውጭ ጉዳት ለደረሰበት ወገን አርኪ ላይሆን ይችላል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ጉዳቱ ለደረሰት ወገን የደረሰበት ጉዳት ሌላ ተጨማሪ ወጪን ፣ የጠበቃ አበልን የሚያስወጣው ሲሆን ጉዳቱ የበዛ ነው የሚሆነው ፡፡
ፍርድ ቤቶች የንብረት ባለቤትነት መብት ላይ ፈጣን ውሳኔን የማያሳልፉ መሆናቸው በንግድና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ከባድ ኪሳራንና የሚፈጥር ሲሆን ዜጎች ከፍርድ ቤት ትክክለኛውን ፍትህ በአግባቡና በግዜው አናገኝም ብለው የሚያስቡ ከሆነ በፍትህ ስርአቱ የማይተማመኑ ከሆነ አለመተማመንና የተሳለጠ የንገድ ንግድ ስርአትና አይኖርም ። እንዲሁም ትርፍ የሆኑ ንብረቶች ተከራይተው ለሌሎች ሊጠቅሙ ይችሉ የነበሩ በዚህ ምክንያት ያለስራ ታስረው እንዲቀመረጡ ያደርጋል ። ጠንካራ እና ተአማኒ የሆነ የህግ ስርአት ለአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት መሳለጥ አስፈላጊ ሲሆን በህግ ስርአቱ ዜጎች ሲተማመኑ መሸጥ ፣ መለወጥ ፣መግዛት ፣ መከራየት እና ማከራየት ወደ መሳሰለው የምጣኔ – ሐብቱን ምርታማነት (Productivity) ወደሚያሳድጉ እነርሱንም ሆነ ሌሎችን ትርፋማ ወደሚያደርጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይገባሉ ።
የኢንቨስትመንት አዋጁ እንደሚደነግገው ከዚህ ቀደም አንድ የውጭ ሃገር ዜጋ ኢትዮጲያ ውስጥ ቤት መግዛትም ሆነ መስራት የማይችል ሲሆን ነገር ግን የዚህ አዋጅ መሰረት ግን ኢንቨስተሩ ቤት ለመስራት ይፈቀድለታል ፡፡ ለምሳሌ በ2004 ዓ.ም. የወጣው የሊዝ አዋጁን ብንወስድ አዋጁ የወጣትበት ዋነኛው ምክንያት የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ማሳካት የሚል ሲሆን ፣ የግል የንብረት ባለቤትነት መብትን ይጋፋል በሚል በህግ ባለሙያዎች የተተቸ ሲሆን ነገር ግን አዋጁ የወጣበት አላማ ግን መንፈሱን መረዳት ይቻላል ፡፡
በቻይና ሃገር 2015 ዓ.ም. 1200 አካባቢ ፍርዶች የተሳሳቱ ሆነው ተገኝተዋል ፡፡
የቻይና የኮሚኒስት ፓርቲ መሪዎች ህንድ ሃገር የሚገኙትን ዳይላ ላማ ንሰሃ ላላልገባ በሚቀጥለው ግዜ ሲፈጠር ሪኢንካርኔት (Reincarinate) ሲሆን ሴት ወይንም ንብ ሆኖ ነው የሚፈጠረው ያሉ ሲሆን ፡፡
የፍትህ ስርአት የማሻሻያ ሃሳቦች
የሃገራችንን የፍትህ ስርአትን ለማሻሻል የተለያዩ ሃሳቦች በበርካታ የህግ ባለሙያዎች ቀርበዋል ፤ ነገር ግን ከግልፅነት ጋር በተያያዘነ የሚነሱ እንዲሁም ከህግጋትንና ከአዋጆች ክፍተት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ነገር ግን ሊወጡ የሚገባቸው አዋጆች አለመኖር ዋነኛ ችግሮች ናቸው ፡፡
አፈፃፀምን ማገድና ምክንያቱን አለመግለፅ እንዲሁም ምንም እንኳን ይግባኝ ማለት ለአንድ ተከራካሪ መብቱ ቢሆንም እና ያለውን የዳኝነት ስርአቱን በመከተል ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም ፣ ነገር ግን አፈፃጸሙ በሁለት መስመር ደብዳቤ ሲታገድ ለምን እንደታገደ እና ዳኛው እግዱን የሰጠው ይግባኝ በመባሉ ብቻ ነው ወይንስ ለአፈፃፀም መታገድ አሳማኝ ምክንያት አለ የሚሉ በግልፅነት የሚቀመጡ ነገሮች አለመኖር ፣ እንዲሁም የመዝገቦችም መብዛትና የዳኞች ቁጥር ማነስ ፣ የመዝገብ ቤት ሰራተኞችም እንዲሁ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ማህደሮችን የሚይዙ ሲሆን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ በበቂ አለመኖር እንደ ኮምፒውተር ያሉ በበቂ አለመኖር ፣ እንዲሁም ለዳኞች የሚከፈለው ደመወዝ አበረታች አለመሆኑ ምክንያት የህግ ባለሙያዎች ከጥቂት አመታት በኋላ ወደ ግል ወይንም ወደ የግላቸውን የህግ የጥብቅና ቢሮን መክፈት እና ደህና ደሞዝ ይከፍላሉ ወደሚባሉ ድርጅቶች መጉረፍ የመሳሰሉት ችግሮች ዋነኞች ናቸው ፡፡
አመቺ የሆኑ ቢሮዎች አለመኖር ፣ እንዲሁም ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሆኑ ቢሮዎች ዋና ዋና በሆኑ ቦታዎች ላይ አለመገኘት እንዲሁም ቢሮዎችን በየጊዜው መለዋወጥ የመሳሰሉት ዋነኛ ችግሮች ናቸው ፡፡
ከዚህም ተጨማሪ ፍርድ ቤቶች ላይ ስራን ያበዛ ነገር የአስፈፃሚው አካል ብቃት ማነስ ሲሆን አስፈፃሚው አካል በራሱ በቀላሉ ሊወስናቸውና ሊፈታቸው ይችሉ የነበሩ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶችን ሲያጣብቡ መመልከት የተለመደ ነው ፡፡ ለዚህም በአንድ በኩል ግልፅ የሆነ ህግና አዋጅ እንዲሁም መመሪያዎች አለመኖር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በየደረጃው አስተዳደር እርከን ያሉ ተቋማት አቅማቸውን አዳብረው መፍትሄን ለመስጠት የሚያስችል የተደራጀ ብቃትና አቅም ጉድለት ናቸው ፡፡
የኢትዮጲያ የፍትህ ስርአት አስተማማኝና (Dependable) ሊተማመኑበት የሚቻል (Reliable) አይደለም ። አያከራክርም ተብሎ የሚታሰበውና አልቋል ተብሎ የሚገመተው ነገር እንደገና ያከራክራል ተብሎ ለእንደገና ለክርክር ሲቀርብ እና ባለጉዳዮችን ለአመታት ሲያጉላላ ይስተዋላል ፣ አላለቀም የሚባለው ነገር ደግሞ የለም አምልቆለታል ሲባል ይስተዋላል ።
ከዘመኑ ጋር ራስን ወቅታዊ ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን ነገር ግን ለምሳሌ የፍትሐ ብሄር ህጉ ሰውነትን ለሌላ ሰው ለመስጠት መደራደር ወንጀል ነው የሚል ሲሆን ነገር ግን አሁን ባለው ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሰረት አንድ ሰው ኩላሊቱን ለመለወጥ ለምሳሌ ወደ ህንድ ፣ ታይላንድና ደቡብ አፍሪካና ወደ መሳሰሉት ሐገራት መሄድ የሚያስቀር ሲሆን ነገር ግን በሀገራችን የኩላሊት ዝውውርን ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ የሌለ ሲሆን ይህን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማዘጋጀቱ ይታወሳል ፡፡
አንድ ደግሞ በፍትሐ ብሄር ስነ – ስርአት ህግ መሰረት ከስነ ስርአት ውጭ የሆነ ነገር ከተፈፀመ ዳኛው ወይም ችሎቱ ክሱን የመሰረዝ መብት አለው ተብሏል ፡፡ ነገር ግን ይህ የዜጎችን ፍትህን የማግኘት መብትን የሚፃረር ሲሆን ህገ መንግስቱ የሚያረጋግጣቸው እንጂ የሚሰጣቸው መብቶች አለመሆናቸውን አንፃር ህገ መንግስቱ አንድ መብትን ያረጋግጣል እንጂ አይሰጥም ስለዚህ ክስን የመሰረዝ መብትን ለአንድ ችሎት ወይም ዳኛ ሲሰጥ ይህ ማለት አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ክሱ ተሰረዘበት ማለት በዚያ ጉዳይ ላይ ያለውን መብት ማጣትን እንዲሚያስከትል የታወቀ ሲሆን
ህገ መንግስት እና ፌደራሊዝም
አንድ ሚሊየን ህዝብ ቁጥር ያላቸውን ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ክልል ሲሆኑ ነገር ግን ከ1- 3 ሚሊየን ህዝብ ያላቸው እንደ ወላይታ ፣ ሃዲያና ሲዳማ ያሉት ብሄረሰቦች ግን ክልል የመሆን መብትን አላገኙም ፡፡ በአንፃሩ በህዝብ ቁጥር እጅግ ትንሽ የሆነች የሀረሪ ክልል ሲሆንና በህዝብ ቁጥር የሚያንሱ በክልሉ ምንም አይነት የፖለቲካ ስልጣንን የመያዝ መብት ሳይኖራቸው ነገር ግን የበለጠ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ግን ክልል የመሆን መብትን ተነፍገዋል ፡፡ ደቡብ ክልል ምንም እንኳን የአቅጣጫ ስያሜ ቢሆንም ነገር ግን በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙ በቁጥር ትላልቅ የሆኑ ብሄረሰቦች ግን ክልል የመሆን መብትን አላገኙም ፡፡
የአንድ ቋንቋ ተወላጅ የሆነ ወደ ሌላ ቋንቋውን ወደማይናገርበት ክልል በሚሄድበት ወቅት በአንቀፅ 32 ላይ ያለውን የመንቀሳቀስ መብትን ነው የተጣሰው ፡፡ ቤንች ማጂ ጉራ ፈረዳ ዞን ለዚህ ምሳሌ ነው የሚል ምሳሌን ያቀርባሉ ተቺዎች ፡፡ ብሄረሰቦች መሐከል ጥርጣሬን እንዲፈጥሩና እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ከማድረጉም በላይ ፡፡
በአንድ ፓርቲ አሰራር አንድን የፖለቲካ ስርአትን መፍጠር የሚቻለው በአንድ አውራ ፓርቲ ስር ሳይሆን ነገር ግን ፤ የአስፈፃሚው ስልጣንን የገነነበት እንና ህገ መንግስቱ ስልጣን አከፋፋይ ሳይሆን ነገር ግን ስልጣን አደላዳይ የሆነበት ነው ፡፡ ምንም እንኳን ህገ መንግስቱ ፌደራሊዝምን የሚከተል ነው ቢባልም ነገር ግን ከሃይለስላሴም ሆነ ከደርግ ዘመን በባሰ ሁኔታ ስልጣን በማእከል ተጠቅልሎ የገባበት ነው የሚል ትችትን ያቀርባሉ ፡፡
ሰልፍ ሩልና ሼርድ ሩል መሃከል ልዩነትም ሆነ ተመሳሳይነት አለው ፡፡ ብዙውን ግዜ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቸች አማራጭ የላቸውንም በሚል መከራከሪያን ቢያቀርብም ፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎች የፌደራል ስርአት ለኢትዮጲያ አስፈላጊነቱን ይስማማሉ ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው አንድ እርምጃ ቢሆንም ነገር ግን ፣ የብሄር ብሄረሰብ ችግር ኢትዮጲያ የዲሞክራሲ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ነው የቀረው የብሄረሰብ ጥያቄ መፍትሄን አግኝቷል ፡፡ ነገር ግን ይህ የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ እስከ መቼ ነው ይህ ጥያቄ በጥያቄነቱ የሚቀጥለው ? አንድ የፖለቲካ ጥያቄ በአንድ ወቅት ጥያቄ ወደ ምላሽ ማምራት አለበት ፡፡
ህገ መንግስት የሚተረጎመው ገለልተኛና ነፃ በሆኑ ሰዎች ሲሆን የህግ ባለሙያ በሆኑ ግለሰቦች ሲሆን ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአንድ የፖለቲካ ተቋም ህገ መንግስትን የመተርጎም ያህል ስልጣንን በተዘዋዋሪ መንገድ ለገዢው ፓርቲ መስጠት ተገቢ ነው ፡፡
የመገንጠል ጥያቄ የህልውና ጥያቄ ሲሆን ለኢትዮጲያ ይህች ካናዳ ውስጥ ኩቤክ ብትገነጠል ካናዳ ትፈርሳለች የሚል ጥያቄ ነው ፡፡ የፌደራሊዝም ዋና አላማ አንድነትን ማምጣት ነው ፣ መግቢያው ላይ ህገ መንግስቱ አንድ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ስርአትን መፍጠር ነው ነገር ግን መገንጠልን የሚፈጥረው ህገ – መንግስት ይህን እንዴት ነው ማጣጣም የሚቻለው ፡፡
ይህ ፌደራሊዚም ካፒታልና ጉልበት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ እንዳይደራ አድርጎ አንቆ ይዟል ፡፡
ዩጎዝላቪያ እነ ቲቶ ለአስርት አመታት ደፍጥጦ ሲገዛ እርሱ ሲሞት ዩጎዝላቪያ ተበታትናለች ፣ ሶቭየት ህብረትም እንዲሁ ከነሌኒንና ስካስታሊን በኋላ ከ70 አመታት በኋላ ልትበታተን በቅታለች ፡፡
ካሊፎርኒያ 32 ሚሊዮን ህዝብ ሲኖራት ቨርጂኒያ 11 ይህን ለማካካስ በሚል እኩል ወንበር እንዲኖራቸው ተደርጓል ፡፡ የቀድሞው ትውልድ ማህራዊ ፍትህን ያስቀደመ ሲሆን ነገር ግን የግለሰብን መብት ትኩረትን አልሰጠም በሚል ትችት ይቀርባል ፡፡
ህገ መንግስትን ለማሻሻል አስቸጋሪ መድረጉ ለራሱ ለኢህአዴግም ቢሆን አይጠቅምም ፤ ለምን ቢባል ራሱ ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲ በሚሆንበት ወቅት በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በጣም ጠንካራ ስለሚሆን ለተቃዋሚዎች ፈተናን ስለሚፈጥር ሲሆን ነገር ግን ፣ እንዲሁም ራሱ ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን ለማሻሻል በሚፈልግበት ወቅት አስቸጋሪ ይሆንበታል ፣ ስለሆነም በሩን ገርበብ ማድረግ ረጅም ግዜ ሊጠቅም ይችላል ፡፡ ለህግ የበላይነት ከአስፈፃሚው አካል ወይንም ስልጣን ላይ ካለው ፓርቲ ጋር ንክኪ በሌለው መልኩ ህገ መንግስቱ መተርጎሙ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው ፡፡
በሌላ አገር ክልሎች ህገ መንግስትን ለማሻሻል ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ካሳለፉ በዚህ ህገ መንግስት ግን ሁሉም ክልሎች ካላፀደቁትና በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ካልደገፉት በስተቀረ አያልፍም በሌሎች ሃገራት ሁለት ሶስተኛ ማለትም ከ9 ክልሎች 6 ከደገፉ በቂ ሲሆን ይህም ህገ መንግስቱን ለማሻሻል እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል ፡፡
የተቃዋሚዎች አንዱ ክርክር እድገትና ልማት የተለያዩ መሆናቸውንና የህንፃ ግንባታ የምናየው እድገት ነው እንጂ ልማት አይደለም ፡፡ ዋናው ልማት የሚገለፀው በሰብአዊ ልማት ሲሆን ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ድርጅት በየአመቱ በሚያወጣው ዘገባ ላይ ሲገልፅ ልማትን በፊዚካል በሆነ ኢንፍራስትራክቸር ለመግለፅ መነሳት ልማትን በአግባቡ አይገልፅም ፡፡ በዚህ ምክንያት በሐገራችን የሚታየው እድገት ነው እንጂ ዘላቂ መሆኑ አስተማማኝ የሆነ ልማት አይደለም ፡፡ የሰብአዊ ልማት ትምህርትን ፣ ጤናን ወዘተ የሚያካትት ሲሆን በዚህ መስክ ኢትዮጲያ ለውጥን ብታመጣም ነገር ግን ይህ በሰብአዊ ልማት ካልታገዘ አስተማማኝ አይሆንም የሚል መከራከሪያን ያቀርባሉ ፡፡ ኢትዮጲያ አፍሪካ ከናይጄሪያ በመቀጠል ከፍተኛ የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰት የሚታይባት ሐገር ስትሆን ይህም የተማረው የሰው ሃይል ሽሽት ሀገሪቱ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖን ማሳረፍ ከጀመረ ውሎ አድሯል ፣ በዚህ መስክ ተለይም በህክምናው ዘርፍ በጉልህ የሚታይ ነው ፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ላይ ብዙውን ግዜ ኢህአዴግ የሚያቀርበው ሃሳብ ተቃዋሚዎች «አማራጭ ሃሳብን አላቀረቡም» የሚል ሲሆን ከግዜ ወዲህ ግን ኢህአዴግ ይህን በማሻሻል «ያቀረቡት ሃሳብ ትክክል አይደለም ፣ ከዚህ በፊት ተሞክተሮ የወደቀ ነው» ወደ ማለት በማዘንበት ጭራሽ ምንም አማራጭ አላቀረቡም የሚለውን መተው «አማራጫቸው ተሞክሮ የወደቀና የማይሰራ ነው» ብሏል ። ይህም ተቃዋሚዎች «የ600 እና የ700 ገጽ አማራጭ ፖሊሲዎችን በብዙ መስኮች ዘርዝረን አቅርበናል ፣ ማኒፎስቶዎቻችንና ሰነዶቻችንን ማየት ይችላል» በሚል ለህዝብም ይፋ ሲያደርጉ ይስተዋላል ይህን መረዳትም ይመስላል ኢህአዴግ አማራጭ አላቀረቡም ከማለት ይልቅ «አማራጫቸው ተሞክር የወደቀና ፣ ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ ነው» በሚል ማሻሻል የጀመረው ።
አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የማይመስልና በእውነታው ሊሆን የማይችል ነገርን በምርጫ ክርክር ወቅት ሲናገሩ ተደምጠዋል ። ለምሳሌ «ለቤት ሰሪዎች መሬት በነጻ እንሰጣለን ፣ ለቤት መግዣ ያለወለድ ነጻ ብድር እንሰጣለን » የመሳሰሉ ክርክሮችን አቅርበዋል ። አንድ ሃገርን ሊመራ ተዘጋጅቻለሁ የሚል ፓርቲ በጣም ቀላል የሆኑ የምጣኔ – ሃብት መርሆዎችን የጣሰና የማይመስል ክርክርን ከማቅረቡ በፊት ከባለሙያዎች ጋር ምክክር ቢያደርግና ከአባላቱም ጋር ውይይትን አድርጎ ሚዲያ ላይ ቢቀርብ ይመረጣል። ነዳጅ የከበሩ የገልፍ አገራት ምናልባት ያለወለድ ወይም በነጻ ለዜጎቻቸው ቤት ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል እንደ ኢትዮጲያ ባለና የኢኮኖሚ አቅም ባልጠነከረበት አገር ላይ ይህን አደርጋለሁ ማለት አሳማኝ መሆኑ አነጋጋሪ ነው ።
በአሁኑ ወቅት የከተሞች መሬት በተጣበበትና በተመናመነበት ሁኔታ ፣ እንዲሁም የህዝብ ብዛትን እየጨመረና ከገጠር ወደ ከተሞች የሚፈልሰው በተለይም ወጣቱ ቁጥር በናረበት ሁኔታ የከተማ ቦታን በነጻ እሰጣለሁ ማለት እውነታውን ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን በተግባር ለመለወጥ አስቸጋሪ ነው ። ከዚህም በተጨማሪ ለቤቶች መስሪያ ብድር ከመንግስት ባንኮች በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚሰራ መሆኑ እየታወቀ እንዲሁም ባንኮች ከአስቀማጮቻቸው ያገኙትን ገንዘብ መልሰው እንደሚያበድሩና ከዚያም በሚያገኙት የወለድ ትርፍ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት መሆናቸው ግልጽ የሆነ ቢሆንም ያለወለድ ለቤት መስሪያና ለኮንዶሚኒየም ቤት መግዣ ወለድ ሳናስከፍል ገንዘብ እንሰጣለን ማለት በረጅም ግዜ ንኮችን የሚያከስርን ከገበያ የሚያስወጣ ነው የሚሆነው ። ይህ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ግሽበት ባለበት ሁኔታ ባንኮች ያለወለድ ገንዘብ ቢያበድሩ በአጭር ግዜ ውስጥ ትላልቅ የሚባሉ የመንግስት ባንኮች እንኳን ከገበያ ውጭ ነው የሚሆኑት ። የዚህ አይነት ተቃዋሚዎች ያለበቂ ጥናትና ውይይት ለክርክር ሲባል ብቻ የሚያቀርቧቸው ሃሳቦቻቸውን በቅጡ መመርመርና በአግባቡ ተዘጋጅቶ መቅረብ ይጠበቅባቸዋል ።
የክስ መሰረዝ
በፍ / ብ / ስ / ስ መሰረት አንድ ዳኛ የ ስነ – ስርአት ጉድለት ከተገኘ ክሱን መሰረዝ ይችላል የሚል ሲሆን ይህ ግን ከህገ መንግስቱ ጋራ ተቃርኖ ያለው ሲሆን ይህም ህገ መንግስቱ ከሚያረጋግጣቸው ‹‹የንብረት ባለቤትነት ህግ›› ፣ እንዲሁም «ፍትህን የማግኘት መብት» ፣ «እንዲሁም የባለስልጣንም ሆነ የዳኛ ትእዛዝ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ከሆነ ስራ ላይ አይውልም ይሻራል ከሚለው ጋር የሚፃረር ሲሆን ይህ የስነ ስርአት ህግ በርግጥ ከዛሬ 60 አመት አካባቢ የወጣ እንደመሆኑ መጠን ከቀድሞው ህግ ነው እንጂ ከአሁኑ ህገ መንግስት ጋር ምን ያህል የሚጣጣም ስለመሆኑ ሊስተያይ ይገባዋል ፡፡
የትውልዶች ቅብብል
በሃገራችን ላይ ከቀደመው ትውልድ ላይ የአሁኑ ምንን ይቀበላል የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ለማወቅ አይቻልም ። በሃገራችን ልማድ መሰረት የተማረ ነው ወይ ? ። ነገር ግን ይህ አልሆነም ። በዚህ ምክንያት የትውልቅ ቅብብሎሽ የሚባለው ነገር የለም ። የ1966 ቱን አብዮትን የመራውና የታገለው ትውልድ በአብዛኛው የደርግ ጥይት ሰለባ ሲሆን ነገር ግን ደርግ ያየው ከዚህ ከምሁራኑ ትውልድ በጠመንጃ የነጠቀውን ስልጣኑን በጠመንጃ ማዳኑን ነው እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ በሃገሪቱ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ውድመትና የትውልድ ክፍተትን አላሰበውም ማለት ይቻላል ።
አንድ ፖለቲካዊ ከባቢያዊ ሁኔታ ሰላማዊና የተመቻመቸ መሆን አለበት ። በኢትዮጲያ የትውልዶች መወራረስ የለም ። ለዚህ ክፍተት መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ወጣቱ ትውልድ በአባተሮቹ ቶቹና ሃገሪቱን ከፋሽስት ጣልያን ወረራ የተከላከለውና በአሸናፊነት ያስከበረው ትውልድ ምንም እንኳን የሃገሪቱን ዳር ድንበር በማስከበር በኩል ቢሳከለትም ነገር ግን በሃገር ውስጥ ለውጦችንና ማሻሻያዎችን ለማድረግ ሳይችል ቀርቷል፣በዚህምሃገሪቱ የነበረችበትን ሁኔታም ጭምር ሳይረዳው ቀርቷል ። በዚህ ምክንያት የተማረረው «ያ ትውልድ» የአባቶቹን አስተሳሰብ እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ ማርክሲዝም ጭልጥ ብሎ ሊገባ በቅቷል ።
ማንም ማርክሲዝምን ሀሁ የሚያውቅ እንደሚያውቀው ሁሉ በጣም ስር ነቀል ከሆኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ይህ አስተሳሰብ አንዱ ሲሆን ጽንፈኛ የሆነው በዚህ አስተሳሰብ የተቃኘ በመሆኑ ስራ ላይ በዋለባቸው ሃገራት ውስጥ ከባድ ውድመትን አድርሷል ። ይህ አስተሳሰብ አውሮፓውያን ራሳቸው ሶሻሊዝምን የሚከተሉ ሲሆን የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲዎች በጀርመን ፣ በፈረንሳይና የሌር ፓርቲው በእንግሊዝ ሃገር እና ሌሎችም በዋና ዋና በሆኑ ሌሎች የአውሮፓ ፓርቲዎች ውስጥ ወሳኝ ፖለቲካን የሚመሩ ቢሆንም ስር ነቀል ማርክሲዝምን ግን በየሀገሮቻቸው አልተገበሩም ።
እ.ኤ.አ በ1870 አካባቢ የፓሪስ ኮሚዩን በፈረንሳይ ሃገር ስልጣን በያዘ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሲደመስሱት ማርክሲዝም በአውሮፓ ምድር ስራ ላይ እንዳይውል ማድረግ ሲችሉ ፣ በአንጻሩ በጣም ደሃና በፊውዳሊዝም ለዘመናት የኖረችዋ በኢንዱስትሪ ያልበለጸገችዋ ሩስያ ማርክሲዝምን ወደ ስራ ስትተገብር ፣ ማርክስ «ዳዝ ካፒታልን» የጻፈላቸውና በኢንዱስትሪ የበለጸጉት እንደ ጀርመንና እንግሊዝና አሜሪካን ያሉት ሃገራት ግን ማርክሲዝምን በየሃገሮቻቸው እንኳን ሊተገብሩት ከምሁራዊ ውይይት ማካሄጃ ባለፈ ወደ ስራ ላይ አላዋሉትም ።
በአንጻሩ ግን በቅርቡ ከምእረባውያን አገዛዝ ነጻ የወጡት ታዳጊ ሃገራት በርካታ ታዳጊ ሃገራት አማላይ ሆኖ ያገኙት ፍልስፍና ማርክሲዝም ሆኖ እናገኘዋለን ። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የአውሮፓ ሃገራት ኢኮኖሚያቸውን በካፒታሊዝም ሲቃኙ ፖለቲካቸውን ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲ ስርአትን በመምረጥ አብዮትንና ግርግርን በማስወገድ ምንም እንኳን ብዙዎቹ የምእራብ አውሮፓ ሃገራት የቅኝ ግዛቶቻቸውን ቢያጡም እንደ እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመንና ኢጣሊያና ጃፓን ያሉቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከባድ ውድመት ቢደርስባቸውም በአጭር ግዜ ውስጥ የፈራረሰውን ኢኮኖሚያቸውን መልሰው መገንባት ችለዋል ።
በተለይም ጃፓንና ጀርመን በጦርነቱ እጅግ የተጎዱና የወደሙ ቢሆንም ጃፓን የአቶሚክ ቦምብ በሁለት ከተሞቿ ሲጣልባትና የተቀረውንም ከተሞቿ ቶክዮን ጨምሮ በአሜሪካ የአየር ድብደባ ቢወድሙም እና በርካታ ሲቪል ህዝቧ ለእልቂት ቢዳረግም ፣ ጀርመንም እንዲሁ ከተሞቿ በእንግሊዝና በአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች እንዳልነበረ ሆነው ሲወድሙ ከዚያ ጥፋት ለማንሰራራት በአስገራሚ ሁኔታ አስርና አስራ አምስት አመት ብቻ ነበረ የፈጀባቸው እነኚህ ሃገራት ። ኩባንያዎቻቸውን መልሰው ወደ ስራ በማስገባት ዓለም ተወዳዳሪ እና ተፈላጊ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት ፣ ምጣኔ – ሐብታቸውን መልሰው እንዲያገግም ማድረግ ሲችሉ በዚሁ አስገራሚ ስኬታቸው አግዛ በእግራቸው ያቆመቻቸውን የራሷን የአሜሪካንን የቅናት አይን ውስጥ ሁሉ እስከ መግባት ደርሰዋል ። በአሁኑ ወቅት እንዲሁ ጀርመንና ጃፓን ከአሜሪካም ጭምር የሚልቅ የበርካታ የተራቀቁ ቴክኖሎጂና የሳይንሳዊ ግኝቶች ባለቤቶች መሆናቸው ይታወቃል ።
ምእራቡ ዓለም ቅኝ ግዛቶቹን ቢያጣምና እንደ ጀርመንና ጃፓን ያሉቱ ደግሞ በጦርነት በአስከፊ ሁኔታ ቢወድሙም በካፒታሊዝም ስርአት ሲበለጽጉ አንጻሩ የቀድሞ ቅኝ ተገዢ ሃገራት ደግሞ ገና እንደ ሃገር ጅማሬ ላይ በመሆናቸው አልፎ አልፎ የድንበር ጦርነት ሲያደርጉ በአፍሪካ ተደጋጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስታትን በማድረግ ተረጋግታ ማደግና ኢኮኖሚዋን መሰረት መጣል አልቻለችም ። በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ ሳቢ ሆኖ የቀረበውና የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን ለመታገል መሳሪያ ሆኖ የታየው ማርክሲዝም በርካታ ወጣት አፍቃርያንንና ምሁራንን ሊስብ የቻለው ።
ይህ ማርክሲዝም ከቀድሞው ትውልድ ፊውዳል አስገባሪ በሆነ የመሬት ስሪት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሺህዎች አመታት እድሜ ያላት አገር ላይ ለመተግበር ሲነሳ የሚፈጠረው መመሰቃቀልና ውድመት ቀላል አይሆንም ። አዲሱ ትውልድ ግን ከአባቶቹ ያን ያህል የራቀ ስር ነቀል «Radical» የሆነ መስመርን ለምን ተከተለ? በአባቶቹ በወቅቱ ለዘመናት ማሻሻያን ለማድረግ ተነሳሽ ባለመሆናቸው ምክንያት ትእግስት በማጣት ነው ? አባቶቹ ስልጣንን ለማካፈልና እርሱ ከተማረው ከአዲሱ እውቀት በመጠቀም አገርን ለመምራት ፈቃደኞች አለመሆናቸው ነው? ወይስ በሌሎች የተለያየ ጥቅምና አላማ ባላቸው የውጭና የሃገር ውስጥ ሃይሎች ሳያውቀው ተወናብዶ ነው ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል ። እነኚህ ሁሉ የየራሳቸውን ምላሽን የሚፈልጉ ሲሆን ሰፊ ትንታኔን የሚፈልጉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው ።
የሃሳብ ሉአላዊነት
በዓለም ላይ የሃሳብን ያህል አደገኛ የሆነ ምንም ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ሃሳብ ታላላቅ ሰራዊቶች አይደፈሩም የተባሉ ኢምፓየሮች ተፈትተዋል ፣ ሰራዊቶች መሳሪያቸውን ጥለው ሸሽተዋል ፣ አገራት ተወረዋል ፣ ታላላቆቻቸውን አጥተዋል ወዘተ.…..፡፡
ሃገራችን የሃሳብን ሃያልነት ገና በቅጡ አልተረዳንም ማለት ይቻላል ። ሃሳብ አገርን ብቻ ሳይሆን ለሺህ አመታት ትክክል ነው ሲባል የነበረ የሃይማኖታዊ አስተሳሰብን ማሻሻል ብሎም መለወጥ ይችላል ። የውሃ ጠብታ ቀስ በቀስ አለትን ይበሳል እንደሚባለው ሁሉ አንድ ሃሳብም ሲደጋገም ተከታዮችን ማፍራትና ተደማጭነትን ማግኘት ይጀምራል ።
በዶክተር አበራ ጀምበሬ ፣ የኢትዮጵያ ሕግጋተ መንግሥት አጭር ታሪካዊ ቅኝት (ከ1923 – 1983)
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊኳን እውን ያደረገችበትን ሕገ መንግሥት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ማጽደቋ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ዕለት ከሕገ መንግሥት ቀንነት ወደ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በመለወጥ በየዓመቱ እያከበረች ነው፡፡
ለአገሪቱ አራተኛው ሕገ መንግሥት ከመምጣቱና ከመተግበሩ በፊት ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ሦስት ሕግጋተ መንግሥትን አስተናግዳለች፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) እስከ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን (1969-1983) ስለነበረው የሕገ መንግሥት ጉዞ ከ20 ዓመት በፊት ጥናት ያቀረቡት የሕግ ምሁሩ የዶክተር አበራ ጀምበሬ ቀጥሎ ያለውን ብለዋል፡፡

ሕገ መንግሥት በዓይነቱ የተጻፈ ወይም ያልተጻፈ እንደዚሁም በቀላሉ የሚሻሻል ወይም በቀላሉ የማይሻሻል ተብሎ ይለያል፡፡ የተጻፈ ሕገ መንግሥት የሚባለው እንደ አስፈላጊነቱ ወደ ፊት የሚሻሻል ሆኖ በአንድ ሰነድ ላይ የተካተተው መሠረታዊ ሕግ ነው፡፡ ለምሳሌ የተባበረው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት፡፡ ከዚህ አንጻር፣ “ያልተጻፈ ሕገ መንግሥት” የሚባለው ይዘቱ በአንድ ሰነድ ላይ ያልሰፈረ፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ከወጡ ልዩ ልዩ ሰነዶች ውስጥ የሚጠቀሱ ሕግ አውጪው አካል በየጊዜው በሚያውጃቸው መሠረታዊ ሕጎች የሚዳብረው የሕግ መድብል ነው፡፡ ላልተጻፈ ሕገ መንግሥት በምሳሌነት የሚጠቀሰው የብሪታኒያው ነው፡፡

በቀላሉ የሚሻሻል ሕገ መንግሥት የሚባለው በማንኛውም ርዕስ የሚወጣ ሕግ በሚሻሻልበት አኳኋን የሚሻሻለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የብሪታኒያ ሕገ መንግሥት ከዚሁ የሚፈረጅ ነው፡፡ በዚህ ተነጻጻሪነት ልዩ የማሻሻያ ሥርዓት በመከተል የሚሻሻለው ዓይነት ሕገ መንግሥት በቀላሉ የማይሻሻል ሕገ መንግሥት ይባላል፡፡ ማሻሻያ ሊደረግ የሚቻለው በለውጡ መደረግ ከሕግ አውጪው አካል ወይም ከሕዝቡ ከፍተኛው ቁጥር በድምፅ ሲደግፈው ብቻ ስለሚሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያለው መሆኑ በዚህ መንገድ ይረጋገጣልና፡፡ ለዚህም ምሳሌ የ1948 የተሻሻለውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን አንቀጽ 131 መጥቀስ ይቻላል፡፡

በማንኛውም አገር ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን የያዘ ሕገ መንግሥት በጽሑፍ ከመታወጁ በፊት፣ ያልዳበረና በሕዝብም ዘንድ በውል የማይታወቅ ቢሆንም ቅሉ፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚደነግግ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የአንድ ዓይነት የተለምዶ አሠራርና ሥርዓት እንደ የነበረ የሕግ ተንታኞች ያረጋግጣሉ፡፡

የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዚህ አጠቃላይ አመኔታ ውጭ አይደለም፡፡ የተጻፈ ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ ከመታወጁ በፊት ያልተጻፈ የተለምዶ አሠራር እንደ ነበር አይካድም፡፡ የሕግ መንግሥትን ባሕርያት አጠቃሎ የሚገኝ ባይሆንም፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ሥርዓተ ተለምዶ (ኮንቬንሽን) ይባላል፡፡ ያልተጻፈ ሕገ መንግሥት የሚባለውም ይኸው ሲወራረስ የመጣ የሕግነት ዕውቂያ የተሰጠው መንግሥታዊ አሠራር ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ሥርዓት በየዘመኑ በተነሱ ርዕሰ ብሔራን ፈቃድና ፍላጎት የተገነባ በመሆኑ፣ ታላቁ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተንትኝ ዣን ሩሶ እንደሚሉት በገዥውና በተገዥው መካከል እንደሚኖር ማኅበራዊ ውል (ሶሽያል ኮንትራት) የሚቆጠር አይደለም፡፡ ቢሆንም ለብዙ ምእት ዓመታት ሲሠራበት የቆየ ሥርዓት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ የተጻፈ ሕገ መንግሥት እንዲኖር ሐሳቡ የተጠነሰሰው በያዝነው ምእት ዓመት ውስጥ ነው፡፡ ከውጭው ዓለም ጋር የሚደረገው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመሄዱ የተነሳ፣ በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ የአውሮፓው ሥልጣኔ የጎላ ተፅዕኖ ማድረግ በጀመረበት ዘመን ፅኑ ዘመናዊ መንግሥት ለማቋቋም አስፈላጊ የሆኑትን አዳዲስ የማኅበራዊና የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ወደ ኢትዮጵየ የማስገባቱ አስፈላጊነት ግንዛቤ ስላገኘ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሙከራ ተደረገ፡፡

አንዳንድ ጸሐፍት “ሥርዓተ መንግሥት” የተባለውን የሕግ ስብስብ (ኮምፖይሌሽን) የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ብለው ቢጽፉም እንኳ ይህ የሕግ ስብስብ በተለያዩ ነገሥታት የታወጁ የፍትሐ ብሔር፣ የወንጀል የቤተ መንግሥት ሥርዓት (ፕሮቶኮል) እና የመሳሰሉትን ድንጋጌዎች የያዘ እንጂ የሕገ መንግሥት ይዘት የሌለው በመሆኑ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ “ሥርዓተ መንግሥትን” የሕገ መንግሥት ሰነድ አድርጎ አይቆጥረውም፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s