የኤርትራ የወደፊት እጣ ፈንታ

በምስራቅ አፍሪካ ካሉ ሐገራት ያላት መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ ስልታዊ የሆነችው ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ የሄደችበት አቅጣጫ ብዙዎችን አሳዝኗል ። እንደ አንድ በቅትርቡ ነፃ እንደወጣ ሐገር ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ በእርጋታና በጥንታቃቄ ትጓዛለች ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ፤ በአንፃሩ የዚያች ሐገር አካሄድ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሆኖ ቆይቷል ።

ከጎረቤቶቿ ጋር በሙሉ መሳሪያን የተማዘዘችውና ከዚያም አልፋ ከሳኡዲ አረቢያ በስተቀረ ከየመንም ጭምር ጋር የተጣላችው ፣ እንዲሁም በሱማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ራሱን የአልቃኢዳ ክንፍ ነኝ ብሎ ለሚጠራው ለአልሸባብም ጭምር ድጋፍን ስታደርግ የቆየችው ይህቺው አገር ፣ ከውጪ ለሚመለከቷት ተመልካቾች ወደ መንግስት አልባነት «ፌይልድ ስቴት» ደረጃ ትወርዳለች ተብሎ አስግቷል ።

ምንም እንኳን ኤርትራ የቆዳ ስፋቷ ከኢትዮጲያ እጅግ ያነሰ ቢሆንም ፣ ያላት ከአንድ ሺ ማይል በላይ የሆነ የቀይ ባህር ጠረፍ ተፈላጊ ያደርጋታል ። በአንድ ወቅት እንደውም አሜሪካኖች ከኢትዮጲያ ይልቅ ለኤርትራ ነው የሚያደሉት ይባሉ ነበር ። ካላት እጅግ ስልታዊ ከሆነ መልከአ ምድራዊ አቀማመጧ የተነሳ ፣ የውጭ ሀይሎች በዚህችው አገር የውስጥ ጉዳይ መግባታቸው የማይቀር ነው ። ከጎረቤቷ ሱዳን ፣ መካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራትና ግብፅ ጭምር እንዲሁም እንደ አሜሪካን ያሉ ሀያላን በዚያች ሐገር የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አይሰዱም ማለት አይቻልም ።

ኤርትራ በነፃነት ትግል ወቅት ኤርትራን ነፃ ለማውጣት እንደ ጀብሀን የመሳሰሉ የነፃ አውጭ ድርጅትች የነበሩ ቢሆንም በትግል ወቅት ጀብሀ ተሸንፎ ከትግል ሜዳ በሀይል ነው የተወገደው ። ይህችው አገር ውስጣዊ አንድነት ራሱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችል ። ከአስር በላይ ብሄር ብሄረበሰቦች ያሏት ይህችው አገር የአሰብ ወደብ ባለቤት ጭምር የሆነው የአፋር ፣ የብሌን ፣ የቤጃን የመሳሰሉ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ነች ።

በአንፃሩ በስልጣን ክፍፍል እኚህ አናሳ ብሄረሰቦች ተገቢውን የስልጣን ውክልና አላገኙም ። ከዚህም በተጨማሪ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታይ ኤርትራውያንም የቆየ የስልጣን ትግልም እንዳለ በነፃነት ትግል ወቅት ጀምሮ የታወቀ ነው ። ስለዚህ በዚያች ሐገር ያለው መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ቢያቅተው ሊከተል በሚችለው የስልጣን ክፍተት አደገኛ የሆነና ለብዙ አሰርት አመታት የቆየው የተዳፈነው የስልጣን ሽኩቻ ሊቀሰቀስ ይችላል ። ካላት እጅግ ስልታዊ ከሆነ መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥም የተነሳ የውጭ ሀይሎችም በሰፊው እጃቸውን ሊሰዱ ይችላሉ ።

የዚህ ውጤትም ለአፍሪካ ቀንድ የባሳ አለመረጋጋትን ሊፈጥር ሲችል ፣ ገና በእግሯ መቆም ከጀመረችው ሶማሊያ ሌላ መንግሰት አልባ የሆነ አገር ሊፈጠር ይችላል በሚል ምእራባውያንን ክፉኛ አሳስቧል ። ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጲያ ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ገና መቋጫ ያላገኘ ከመሆኑ አንፃር ከኢትዮጲያ ጋር ያለው ሁኔታ ወዴት ሊያመራ እንደሚችልም አንዱ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው ።

Advertisements